በቅርቡ በአዋጅ ፀድቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ከሚጠበቀው የንብረት (ፕሮፐርቲ) ታክስ፣ ክልሎች ከሚሰበስቡት ገቢ 25 በመቶው ለፌዴራል መንግሥት እንዲሆን የገንዘብ ሚኒስቴር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ አቀረበ፡፡
ከንብረት ታክስ ከሚገኘው ገቢ በምን ያህል መጠን ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት ይከፋፈላል የሚለውን የሚወስነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ይሁንና ከዚህ አስቀድሞ የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ከንብረት ታክስ የሚገኘው ገቢ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሊካፈሉት የሚገባ የጋራ ገቢ ስለመሆኑና አለመሆኑ ውሳኔ ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በተጀመረው በጀት ዓመት ከታክስ የሚገኘውን ገቢ ለማስፋት ማሻሻያ ይደረግባቸዋል ብሎ ከሚጠብቃቸው የታክስ ሕጎች ውስጥ አንዱ፣ የንብረት ታክስ (Property Tax) ሕግ ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ሕጉ ፀድቆ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የታክስ መሠረቱን እንደሚያሰፋና በዚህም የታክስ ገቢ ይጨምራል የሚል እምነት አለው፡፡
ሪፖርተር የተመለከተው የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፣ የፌዴራል መንግሥት ከንብረት ታክስ ገቢ ለማግኘት ያቀደው፣ ሕጉ ተግባራዊ ሲሆን በክልሎች ሥር ካሉ ንብረቶች የሚሰበሰብ የንብረት ታክስ ውስጥ 25 በመቶው ገቢ ወደሱ እንዲመጣ ለማድረግ ነው፡፡ ክልሎች ደግሞ 75 በመቶውን የንብረት ታክስ ገቢ እንደሚወስዱ ታስቧል፡፡
ገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን የገቢ ክፍፍል የያዘውን የውሳኔ ሐሳብ ለፌዴሬሽንና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች አቅርቦ ውሳኔ እየተጠባበቀ እንደሆነ፣ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌደሬሽን ምክር ቤት የፊስካል ጉዳዮችና የክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት ጥናት ዳይሬክተር ዋቅቶሌ ዳዲ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ የውሳኔ ሐሳቡ መቅረቡን አረጋግጠው፣ እስካሁን ውይይት እንዳልተካሄደበት ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ሚኒስቴሩ ያቀረበው የገቢ ክፍፍል ድርሻ ሐሳብ ላይ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ሁለቱ ምክር ቤቶች ከንብረት ታክስ የሚገኝ ገቢ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የጋራ ገቢ ወይም የክልሎች ብቻ ገቢ የመሆኑ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ አለባቸው፡፡
‹‹እነሱ በራሳቸው ይሁን ያሉትን ፕሮሲጀር ልከዋል፡፡ ግን ተግባራዊ የሚሆነው የመጨረሻው ውሳኔ የሚወሰነው አንደኛ የጋራ ገቢ ይሆናል? ወይስ እንደ ማንኛውም ታክስ ይሆናል? የሚለው ከተለየ በኋላ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 95 የፋይናንስ ገቢን በተመለከተ፣ የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የሚዋቀረውን የፌዴራል አደረጃጀት የተከተለ የገቢ ክፍፍል እንደሚያደርጉ አስቀምጧል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በቀጣዮቹ ሦስት አንቀፆች የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የትኞቹን የታክስና የግብር ዓይነቶች ለብቻቸው የመሰብሰብ ሥልጣን እንዳላቸው፣ የትኞቹ ላይ ደግሞ ለጋራ እንደሚሰበስቡ ዘርዝሯል፡፡
ተከታዩ አንቀጽ 99 ደግሞ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ተለይተው ያልተሰጡ የታክስና የግብር ሥልጣኖችን በተመለከተ፣ የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ አድርገው ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ደንግጓል፡፡ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ስለ የጋራ የታክስና ግብር ገቢው ውሳኔ የሚተላለፈው በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ሲወሰን እንደሆነ አንቀጹ አስቀምጧል፡፡
ዋቅቶሌ (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደተናገሩት፣ ከንብረት ታክስ የሚገኘው ገቢ ጉዳይ በቀጥታ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥራ የሚያስፈልገው ሁለቱ ምክር ቤቶች ከንብረት ታክስ የሚገኘው ገቢ የሁለቱ መንግሥታት የጋራ ገቢ ነው የሚል ውሳኔ ካሳለፉ ነው፡፡
‹‹ከዚህ በኋላ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለጋራ ክፍፍሉ ምን ዓይነት ቀመር ላዘጋጅ ይላል፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ምክር ቤቱ በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረበውን የ75/25 ገቢ ክፍፍል ሊጠቀምበት ወይም በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የራሱን ቀመር ሊያዘጋጅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር ሲዘረዝር ንዑስ አንቀፅ ሰባት ላይ የምክር ቤቱ ለፌዴራልና ክልል መንግሥታት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች የሚከፋፈሉበትን ቀመር እንደሚወስን ተደንግጓል፡፡
እንደ ዋቅቶሌ (ረዳት ፕሮፌሰር) ገለጻ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ከቀረበ በኋላ ለውሳኔ እንዲረዳ በሚል በሌሎች አገሮች የንብረት ታክስ ዙሪያ ስላለው ልምድ በባለሙያ ሥልጠና እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ከውሳኔው በፊት እንዲህ ዓይነት ውይይቶች እንደሚቀጥሉም አክለዋል፡፡
ከውይይቶች በኋላ ሁለቱ ምክር ቤቶች በጋራ ተሰብስበው የውሳኔ ሐሳብ የሚያሳልፉት ሁለቱ ምክር ቤቶች፣ የአዲሱ በጀት ዓመት ሥራቸውን በቀጣዩ ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ከጀመሩ በኋላ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የታክስ ሕግ ባለሙያ፣ ሁለቱ ምክር ቤቶች በንብረት ታክስ ገቢ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያደርጉት ውይይት፣ ጠንካራ ሕገ መንግሥታዊ ሙግት የሚደረግበት እንደሚሆን ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የንብረት ታክስ ገቢ የጋራ ነው ወይስ የክልሎች ብቻ ነው ለሚለው ለሁለቱ ሙግት ከሕገ መንግሥቱ አንቀፆችን ጠቅሶ መከራከሪያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
የንብረት ታክስ የሚሰበሰበው ከሕንፃዎችና ከመሬት መሆኑና ሕገ መንግሥቱ ደግሞ ከእነዚህ የሚገኝ ገቢ የክልሎች እንደሆነ መደንገጉ አንድኛው መከራከሪያ ነው፡፡ የክልል መንግሥታት የታክስና የግብር ሥልጣንን የሚዘረዝረው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 97 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ክልሎች የመሬት መጠቀሚያ ክፍያ ወስነው እንደሚሰበስቡ ደንግጓል፡፡ ከዚህ በላይ የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ስድስት በክልሎች ውስጥ በግል ባለቤትነት ሥር ባሉ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች በሚገኝ ገቢ ላይ ግብር የመጣልና የመሰብሰብ ሥልጣን የክልል መንግሥታት እንደሆነ አስቀምጧል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 96፣ 97 እና 98 የፌዴራልና የክልል መንግሥታት እንዲሁም የሁለቱ የጋራ የሆኑ የግብር ዓይነቶችን ሲዘረዝር፣ የንብረት ታክስ የሚል ጠቅሶ በየትኛው ሥር እንደሆነ አላስቀመጠም፡፡ በዚህ ምክንያት የንብረት ታክስ ጉዳይ በአንቀጽ 99 መሠረት ተለይተው ባልተሰጡ የታክስና የግብር ሥልጣናት እንደ አንዱ ታይቶ የተናጠል ወይስ የጋራ ለሚለው ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ ይቻላል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር የውሳኔ ሐሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የላከው በንብረት ታክስ ተለይቶ ያልተጠቀሰ በመሆኑ፣ አንቀጽ 99 ላይ ተመሥርቶ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ አስረድተዋል፡፡
ይሁንና የሕግ ባለሙያው ክልሎች በሥራቸው ካሉ የግል ንብረቶች የሚበስቡትን የንብረት ታክስ የፌዴራል መንግሥት ሊጋራ የሚችልበት ጠንካራ የሕግ መሠረት አለው የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ቢፀድቅም ወደፊት ጭቅጭቅ የሚያስነሳ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉም ሥጋታቸውን አጋርተዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ክልሎች የየራሳቸውን የንብረት ግብር ሕግን ሲተገብሩ ወጥነት እንዲኖር አዋጅ ማውጣት፣ እንዲሁም ቴክኒካዊ ድጋፍ ማድረግ ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የብዙ ፌዴራሊዝም ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው ከንብረት የሚሰበሰብ ግብር የከተሞች ገቢ እንጂ የፌዴራል፣ የክልልም ሆነ የጋራ ገቢ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ የታክስና ግብር ገቢን በተመለከተ የሚጠቅሰው የፌዴራልና የክልል መንግሥታትን በመሆኑ የንብረት ግብር ገቢን የከተሞች ገቢ ብሎ መበየን አይቻልም፡፡
የፌዴራል መንግሥትም የንብረት ግብር ህግን የሚያወጣው ከተሞች ቢያንስ 70 በመቶ የሚሆነውን ወጪያቸውን በራሳቸው መሸፈን አለባቸው በሚል ዕሳቤ እንደሆነ፣ ረቂቅ ሕጉን አዘጋጅቶ ለገንዘብ ሚኒስቴር የላከው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒቴር አስታውቆ ነበር፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ብዙ መሠረት ልማቶቻቸውን ከፌዴራል መንግሥትና ድጎማ ለዓለም አቀፍ መንግሥታት ዕርዳታ በሚያገኙት ገንዘብ የሚዘረጉት ከተሞች ገቢያቸውን እንዲያሻሽሉ፣ በሥሩ የከተሞች ገቢ ሪፎርም ጽሕፈት ቤት አቋቁሞ ሲሠራ ቆይቷል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዚነት ኢብራሂም፣ የከተሞችን የማዘጋጃ ቤት ገቢ ለመጨመር በማሰብ ስድስት የገቢ ዓይነቶች እንደተለዩና ከዚህ ውስጥ ቀዳሚው የንብረት ግብር መሆኑን ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በሙከራ ደረጃ እስካሁን የድሬዳዋና የባህር ዳር ከተሞችን ጠቅላላ የሀብት ግመታ አጠናቆ ለከተሞቹ ማዘጋጃ ቤቶች አስረክቧል፡፡ የሀብት ግመታው በመቀሌ ከተማም ተጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት አዳማ ከተማ ተተክታለች፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተም የንብረት አዋጅ ከፀደቀ በኋላ ለመተግበር የእያንዳንዱ ቤትና መሬት ሀብት መገመት እንደሚኖርበት፣ ለዚህም ካዳስተር እየተሠራ መሆኑን ከሁለት ሳምንት በፊት ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር፡፡