Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ባለፈው ሰሞን በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ በሌብነት ምክንያት በመሰረዙ፣ ከሚገባው በላይ ከተበሳጩ ተመዝጋቢዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ እኔ ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት ጀምሮ እስካሁን በትጋት እየቆጠብኩ የምጠባበቀው፣ ወገብ ከሚያጎብጠው የቤት ኪራይ ለመገላገል ነው፡፡ ነገር ግን በሌቦች ምክንያት ዕድሌ ቢከሽፍም አሁንም በጉጉት እየተጠባበቅኩ ነው፡፡ በዚህ ንዴት ውስጥ ሆኜ ግን ከ40/60 የመኖሪያ ቤት ምዝገባ ጋር ገጠመኝ አለኝ፡፡ ያኔ ምዝገባ ለማድረግ ከተጣበበው ሰዓቴ ላይ ተውሼ ምሣ ሰዓት አካባቢ የምሠራበት መርካቶ አካባቢ ከሚገኝ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ስደርስ ዝናብ መዝነብ ጀመረ፡፡ ፍተሻውን አልፌ ወደ ውስጥ ስዘልቅ ለምዝገባ የሄዱ ሰዎች ቅርንጫፉን ሞልተውታል፡፡ ቀለል እስኪል በማለት ዣንጥላዬን ዘርግቼ አካባቢው የሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ጎራ አልኩ፡፡ ምግብ ቤቱ ከአፍ እስከገደፉ ሞልቷል፡፡ ሦስት ወጣት ሴቶች ከበው የተቀመጡበት ጠረጴዛ አንድ ትርፍ ወንበር ስለነበረው ጠጋ ብዬ ሰው እንዳለው ጠየቅኳቸው፡፡ ሦስቱም በፈገግታ ተቀመጥ ብለውኝ አረፍ አልኩ፡፡ እነሱም እንደ እኔ ምሣ ለመብላት መጥተው ያዘዙትን ምግብ እየጠበቁ ነበር፡፡ እኔ ከተቀመጥኩ በኋላ የጀመሩትን ወሬ ቀጠሉ፡፡ የወሬያቸው ርዕስ ደግሞ ያው የ40/60 የቤት ፕሮግራም ነበር፡፡

በስንት መከራ በምልክት ተጣርቼ ያገኘሁትን አስተናጋጅ ጥብስ እንዲያመጣልኝ አዝዤ የሴቶቹን ወሬ መስማት ጀመርኩ፡፡ አንደኛዋ ሴት፣ ‹‹ይኼ ቤት በቶሎ ይድረሰኝ እንጂ የማደርገውን እኔ ነኝ የማውቀው…›› አለች፡፡ ሁለቱ ጓደኞቿ ሳቅ በሳቅ ሆኑ፡፡ እኔ ደግሞ ምንድነው የሚያስቃቸው ይኼን ያህል በማለት ጣልቃ ገብቼ፣ ‹‹ምን ታደርጊ ነበር?›› በማለት ድንገተኛ ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹ሠንጋ ተራ ከደረሰኝ ጆሮውን ብዬ ለቡ ወይም ፉሪ ኮንዶሚኒየም እገዛና አሪፍ መኪና ገዝቼ እሸልላለሁ፡፡ አንተም ተመዝጋቢ ነህ?›› አለችኝ፡፡ ስላልገባኝ፣ ‹‹ቤቱ ይኼን ያህል ዋጋ ያወጣል እንዴ?›› ስላት፣ ‹‹ሰው አቅም አጥቶ እዚህ ላይ አልተረባረበም እንጂ ቆይ ታያለህ በሚሊዮኖች ቤት ነው ዋጋው…›› ስትለኝ ገረመኝ፡፡ ሰው አርቆ እያሰበ የእኔ ዓይነቱ ደግሞ የዕለት ተዕለቱ እንኳ አልተሳካለትም፡፡

ምሳችንን አንድ ላይ ቀላቅለን እየበላን ስናወራ ሴቶቹ የያዙት ዕቅድ አስገረመኝ፡፡ ጓደኞቻቸው በጎተራ፣ በባልደራስ፣ በገርጂና በመሳሰሉት ኮንዶሚኒየሞች በተጋነነ ዋጋ ቤቶችን እየተከራዩ የተጧጧፈ ቢዝነስ ውስጥ መሆናቸውን ሲያወሩኝ እንግዳ ሳልሆን ጓደኛቸው እመስል ነበር፡፡ ጎተራ ኮንዶሚኒየም ለሁለት ክፍል ኮንደሚኒየም ሰባት ሺሕ ብር የምትከፍለው ሺሻና ጫት የምትነግደው ጓደኛቸው የቀን ትርፍ በአማካይ ከሁለት ሺሕ ብር በላይ ነው አሉ፡፡ እዚያው ጎተራ ጫት፣ መጠጥ፣ ሺሻና የተለያዩ ንግዶችን ያለ ንግድ ፈቃድ ታክስ ሳይከፍሉ የሚያጧጥፉ ጓደኞቻቸው ዛሬ ባለቪትስና ባለያሪስ ናቸው ሲሉኝ ገረመኝ፡፡ በተለያዩ ኮንዶሚኒየሞች በአልቤርጎና በተለያዩ ሕገወጥ ድርጊቶች ውስጥ የተሰማሩትም እንዲሁ ሀብት እየዘነበላቸው መሆኑን ተነተኑልኝ፡፡

ምሣችንን ጨርሰን ወደ ቅርንጫፉ ተመልሰን በወረፋችን መሠረት ጉዳያችንን ፈጽመን ስንለያይ አንዷን ተጠግቼ፣ ‹‹ይኼ ሁሉ የምትነግሩኝ ጉዳይ እውነት ነው? ወይስ የስሚ ስሚ ታሪክ ነው?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ልጅቷ ፈርጠም ብላ፣ ‹‹ለምን ስልኬን ሰጥቼህ ሲመችህ ጎተራ ወስጄ አላስጎበኝህም?›› ብላኝ ስልክ ተለዋውጠን ተለያየን፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ ምሽት ደውዬላት ለእሑድ ጎተራ ቀጠሮ ያዝን፡፡ በሕይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ የጎተራ ኮንደሚኒየምን በዓይኔ ሳየው ተደነቅኩ፡፡ ራሱን የቻለ ቀበሌ ይወጣዋል፡፡ ፀጉር ቤቶች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ የሸቀጥ መደብሮች፣ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች፣ ወዘተ በብዛት ይታያሉ፡፡ ልጅቷ ስትደርስ ደውላልኝ ተገናኘን፡፡ ይዛኝ ቁጥሩን የማላስታውሰው ብሎክ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ያለው የጓደኛዋ ቤት ደረስን፡፡ በሩ ተከፍቶ በፐርሺያ ምንጣፍ ከዳር እስከ ዳር የተዋበው ቤት ውስጥ ስገባ ጎተራ ሳይሆን ኢራን ያለሁ መሰለኝ፡፡

ወደ ውስጥ ስንዘልቅ በአንድ በኩል የተመቻቸው የሚመስሉ ሰዎች ጥጋቸውን ይዘው ካርታ እየተጫወቱ ይቅማሉ፡፡ በሌላው ጥግ ዓረብ የሚመስሉ ሰዎች እንዲሁ፡፡ እኔና ልጅቷ አንድ ጥግ ይዘን ስንቀመጥ ውኃና ለስላሳ መጠጥ ቀረበልን፡፡ ወዲያው በልጅቷ ትዕዛዝ ምርጥ የተባለው ጫት መጣ፡፡ ቀስ በቀስ በምቾት ውስጥ ያሉ የሚመስሉ ወንዶችና ሴቶች ሰፊውን ክፍል ሞሉት፡፡ በሌሎቹ ክፍሎችም ሰው እንዳያያቸው የሚፈልጉ ቅምጥል ሰዎች መኖራቸውን አወቅኩ፡፡ ነጋዴ፣ ባለሥልጣን፣ ምሁር፣ ሴት፣ ወንድ፣ አዛውንት፣ ወዘተ በየዓይነቱ እንደሚመጡ ሰማሁ፡፡ እንክብካቤው ደስ ስለሚያሰኝ ውጡ ውጡ አይልም፡፡ መሸትሸት ሲል የጫት ሥርዓቱ አልቆ ቢራና የአልኮል መጠጦች (ጎርደን ጂን፣ ውስኪ፣ ቮድካ፣ ወዘተ) መቅረብ ጀመሩ፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ገንዘብ ያለ ምንም ስስትና ሰቀቀን ይረጫል፡፡ እኔና ልጅቷም ተጉመጥምጠን ወደ መጠጡ ዞርን፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት ከዚያ ስንወጣ የሁለታችን ወጪ 1,500 ብር ደርሶ ነበር (የዛሬውን አያድርገውና)፡፡ ቤቱ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ቁጥር በዚህ ብናባዛው እዚያ ቤት ውስጥ ሺሕ ብሮች በቀላሉ ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ በእርግጥም በቀን ሁለት ሺሕ ብር ትርፍ ቢገኝ አይደንቅም፡፡ እውነቴን ነው በዚህ የዋጋ ግሽበት ቢሆን ኖሮ ይህ ትርፍ ከአሥር እጥፍ በላይ ነበር፡፡

የጎተራውን ገጠመኜን የነገርኩት አንድ ጓደኛዬ ለካ ከዚህ በፊት ይህንን ዓይነቱን ወሬ ሰምቶ ስለነበር ብዙም አልገረመውም፡፡ ነገር ግን በቤት ኪራይ እጦት የሚሳቀቅ ስለነበር፣ ‹‹አንተ ንግዱ ይገርምሃል? አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ተብሎ የተሠራው የኮንዶሚኒየም መኖሪያ እኮ የሀብታሞች መጨፈሪያና መዳሪያ ከሆነ ቆይቷል፡፡ እኔን የሚቆጨኝ ግን…›› ብሎ ተወው፡፡ ‹‹ምን ይቆጭሃል?›› ስለው ምርር ባለስሜት፣ ‹‹ወይ ገንዘቡ የለን? ወይ ቤቱ የለን? የማንም ዘራፊ ታሪክና ጀብዱ አዳማጭ ሆነን መቅረታችን ነው…›› ሲለኝ ውስጤ ድረስ ዘልቆ ተሰማኝ፡፡ መጥኔ ለመጨረሻችን ከማለት ሌላ ምን ይባላል? አሁንስ ቢሆን ዘጠኝ ዓመት ሙሉ መንግሥትን ተማምነን ቤት ለማግኘት መከራ ስናይ፣ በጎን እንደ አይጠ መጎጥ የሚቦጠቡጡ ሌቦች ዕድላችንን እያመከኑ ይጫወቱብናል፡፡ ለመሆኑ ከንቲባዋ በገቡት ቃል መሠረት ዕጣው በቅርቡ ይወጣል ወይስ አፋችንን ከፍተን ስንጠባበቅ የሌባ ሠራዊት መጫወቻ ሆነን እንቀራለን?

(ዘውዱ ከበደ፣ ከአዲስ ከተማ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...