Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየውድቅት ታሪክን ላለመድገም ስለሚያስፈልጉ የትውስታና የሽረት ስንቆች

የውድቅት ታሪክን ላለመድገም ስለሚያስፈልጉ የትውስታና የሽረት ስንቆች

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

የ50 ዓመት ያህል የፖለቲካ ትግል ልምድን አበራይቶ፣ ገመናንና ጥንካሬን ለይቶ ትምህርት የመሰነቁን ነገር ለአገራዊ ምክክሩ ሒደት እንተወውና ከቅርብ ጊዜ የደፋ ቀና ልምዳችን ያተረፍነውን አይረሴ ትምህርት በማንጠር ላይ እንወሰን፡፡ የቅርብ ጓረቤት አጥር ለመጎድፈር እስኪደፍር ያጋለጠ የአገር ልጅ ጠላት ከአገር ጓዳችን ውስጥ እንደምን ሊበቅል ቻለ? ብሔርተኛ የሠፈር ጉዳዮችን ዓላማዬ ያሉ ብጥስጣሽ ዕይታዎች ህሊናችንና አገራዊ ማንነታችን በሳስተው እርስ በርስ ሊያናችፉን ስለቻሉ፣ ጠባብ (ሠፈር ገብ) ዓላማዎች ከአገራዊ ማንነታችን ጋር ተጣልተው የተወሰነ ማኅበረሰብን ጠላቴ ብሎ እስከ መጥላት/እስከ ማጥቃት፣ ከዚህም ሁሉ በላይ አገር ብተናን ከነፃነት ጋር አምታተው፣ እኛው ለእኛው ጠላት እንድንሆን ስላደረሱን ነው፡፡ ይህንን መቼውንም ልንዘነጋው አይገባም፡፡ የፈለገውን ያህል ዕይታችንና ዓላማችን ቢጎነዳደሽስ፣ በየትም አገር ታይቶ በማይታወቅ እኳኋን አንድ ከጫካ ትግል የመጣ ቡድን የውስጥ አገር ወራሪ ለሆነበት ፍዳ እንደምን ተጋለጥን? ቅድመ 1983 ዓ.ም. የፖለቲካ ትግል ውድቀታችን፣ አርቆ የሚያይ የተባበረ የፖለቲካ አስኳል ስላሳጣን፣ ወደንና ሳንወድ ከጫካ የመጣ ጎጠኛ/ብሔርተኛ ቡድን በውጭ ኃይል ምርቃት የኢትዮጵያ ሥልጣን ላይ እንዲወጣ ስለፈቀድንና ይኼው ቡድን ዓይኑን በጨው አጥቦ የአገሪቱን ነባር የፀጥታ አውታራት አፈራርሶ በራሱ ሠራዊት ያዋቀረበት ትልቅ ስብራት በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ውስጥ ስለደረሰ ነበር፡፡ ይህንንም መቼም አንረሳውም፡፡ አንረሳውም ማለት ተግባራዊ ትርጉም የሚኖረው መቼውንም ህሊናችንና ሕዝባችን የብጥስጣሽ ብሔርተኝነት መጫወቻ እንዳይሆን፣ ዳግመኛ አገራችን ለፖለቲካና ለምሁራዊ ድህነት እንዳትጋለጥ፣ እናም ዳግመኛ አገረ መንግሥታችን የአንድ ቡድን ንብረት እንዳይሆን አድርገን ቤታችንን ለማደራጀት እስከ ቆረጥንና እስከተጋን ድረስ ነው፡፡

ከፋም ለማም በዚህ መንገድ ውስጥ ከ2010 ዓ.ም. መጋቢት ወደዚህ ገብተናል፡፡ በለውጡ አፍላ ጊዜ የመላ ሕዝቦቻችን ምልዓታዊ የለውጥ ደጋፊነት ከአዲሱ መንግሥት ጋር በነበረበት ጊዜ መንግሥትንና የለውጥ ቡድኖችን ከመላ ኅብረተሰባችን ጋር ያያያዘ የተባበረ ፖለቲካ ፈጥረን፣ በ27 ዓመታት ውስጥ የደረሰው የአተያይ/የአዕምሮና የአገረ መንግሥት ሙሽት ብልሽት፣ አገርን የሚያመሳቅል ወታደራዊ ቀውስ እንዳይወልድ አድርገን ለማቃለል ባንችልም፣ ቀውሱ እየተብላላ ሲከር ቆይቶ ከፈነዳ በኋላ አገራዊ ህልውናችንን ለማትረፍ መንግሥትና አገሬን ያሉ ፖለቲከኞችና የኢትዮጵያ መላ ኅብረተሰብ አንድ ላይ በተመሙበት አኳኋን ከባዱን የህልውና አደጋ አስወግደናል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከውስጥና ከውጭ ያለው አደጋ ገና ጥርሱን እንዳገጠጠ ቢሆንም፣ የጦርነት ፍላጎት የሌለን መሆኑን አሳውቀን ህልውናችንን ለማስተማመን ጉልበት የሚሆኑ ባለብዙ ግንባርና ፈርጀ-ብዙ ውጊያዎችን እያካሄድን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቶችንና የምግብ ዋስትና ችግራችንን የሚያቃልሉ ለውጦች በማካሄድ ትግል ውስጥ ተጠምደናል፡፡ ከውጭና ከውስጥ ተቀናብረው ሊመጡ የሚችሉ ወታደራዊ ጦርነቶችን ነቅተን እየጠበቅን የመከላከልና የማሸነፍ አቅማችንን በሁሉም ፈርጅ እያሳደግን ነው፡፡ አቅም ከማሳደግም ጋር በአገራችን ላይ የሚመጡ የሳይበር ጥቃቶችን እየተዋጋን ነው፡፡ ከጦር ሜዳ በተወሰነ ደረጃ መለስ ያሉት የሕወሓት ጦረኞችና አፍራሾች፣ በየአካባቢው ያሉ ከአፍንጫ አይርቄዎችን እየጋለቡ የብሔርና የሃይማኖት መተላለቅ ለማስነሳት የሚያደርጉትን ዱለታና ትንኮሳ እንዋጋለን፡፡ እየተዋጋንም የግፍ ኃይሎችን እውነተኛ ማንነት ለሕዝባችንና ለዓለም ከማጋለጥ ጋር የኃይል ቅጥልጥላቸውን እየበጣጠስንና ኅብረተሰባችንን የማመስ አቅም እንዳይኖራቸው እያደረግን ነው፡፡ ስርሰራና ጥናት በማካሄድ ከ2014 ዓ.ም. ግንቦት አጋማሽ ወደዚህ የተወሰደው ከገጠር እስከ ከተማ፣ ፀጥታ የማስከበርና አደብ የማስያዝ ዕርምጃ የዚሁ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የሕዝብ ደኅንነትና ፀጥታ የማስከበር ዕርምጃ ብጥስጣሽ ብሔርተኛነትን በማመናመን ረገድ፣ በተለይም በአማራና በኦሮሞ ዘንድ ያለውን ትምህርት ቀመስ አመጣሽ ጥርጣሬን በማዳከም ረገድ፣ በጥቅሉም የሕዝብ ለሕዝብም ሆነ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነቶችን ለማጠንከር፣ ብሎም ቀሪ የውስጥና የውጭ አደጋዎችን ለማምከን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ትርጉም ሰጪነቱ የሚቆየው ግን የሕዝብ ደኅንነትና ሰላም አገኘሁ ባይነቱ እስከ ዘለቀ ድረስ ነው፡፡ ይህ እንዲሟላ አምስት ነገሮች አስፈላጊዎች ናቸው፡፡

  1. ለዴሞክራሲ ነፃነትና ለሕግ መታመን፣ እንኳን ለዴሞክራሲ እንግዳ ለሆንነው ይቅርና ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ በዴሞክራሲ ተጉዘናል በሚሉት አገሮች እንኳ ከባድ መሆኑን በማጤን መንግሥት፣ የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝብ በተማመኑበት ሁኔታ ከጠባብ ወደ ስፋት በሚጓዝ እርጋታና ጥንቃቄ የዴሞክራሲ ልምምዳችንን መግራት፣ በዴሞክራሲያዊ አገረ መንግሥትና ባህል ግንባታ ዓውድ ውስጥ ፀጥታና ሰላምን የማዝለቅ ተግባርን አጥብቀን መያዝ ግድ ነው፡፡
  2. ጦርነት በዋናነት ጥይት መተኮስን ስላቋረጠ የሌለ (አደጋ የተወገደ) ያህል ቆጥሮ የተለመደ ንቁሪያ ውስጥ መግባት አሳፋሪ ጮርቃነት ነው፡፡ የህልውና አደጋችን አሁንም ጦርነት በመደገስ መልክ አለ፡፡ ከጦርነት መልክ ባሻገር ኢትዮጵያን ኮንፌዴራላዊ አድርጎ የመበተን ዱለታ የሰላምና የድርድር ካባ ለብሶ ላይ ታች ይላል፡፡ አሁንም ኅብረታችንን እናጥብቅ፡፡
  3. በአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤትና በሴኔቱ ውስጥ ለኢትዮጵያ የተረቀቁባት የስቀዛ ሕጎች ላንቃቸውን ከፍተው ሰበቦች እየተጠባበቁ ነው፡፡ እነዚህን ለማምከን መንግሥትና የለውጥ ፖለቲካ ቡድኖች አንድ ላይ ሕዝብን ይዘው በብልኃት መሥራት የወቅቱ ተግባራቸው ነው፡፡ ይህንን ተግባር የማሳካት ጉዳይ ደግሞ የግፍ፣ የበቀልና የጥላቻ ኃይሎችን ከኢትዮጵያ ሕዝቦችና ከዓለም ድጋፍ አራቁቶ፣ የውስጥም የውጭም ጉልህ ድጋፍ ባለበት አኳኋን፣ በአገራዊ ምክክራችን የፖለቲካ ቡድኖች ምሁራንና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሰፊው የተገናኙበት መግባባትና መፍትሔ ማበጀት ነው፡፡ ለዚህ ሒደት እስከታመንን ድረስ በሒደቱ ውስጥም ሆነ ከሒደቱ በኋላ የሚከሰት የጦርነት ስንዘራን አይቀጡ ቅጣት የመቅጣት ሞራላዊ ተገቢነት ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡
  4. ጦርነት በተከሰተበትም መልክ ይሁን ሳይከሰት ያንዣበቡ አደጋዎችን ከመከትን በኋላም ቢሆን፣ ‹‹ቤታችን ውስጥ እርስ በርስ ብንጣላም የጋራ ጠላት ሲመጣ አንድ ላይ ሆኖ ማሸነፍ እናውቅበታለን›› ከሚል አሮጌ አመለካከት መውጣት አለብን፡፡ አገራዊ ዕይታና ዓላማ ይዞ አገርን አንድ ላይ ማንሳት የሁላችንም ተልዕኮ ሆኖ፣ በየሠፈራ ሠፈር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የዚሁ ትልቅ ዕይታ ገባር፣ አገራዊ ተልዕኳችንም ሁሉንም ሠፈር በፍትሐዊነት የሚያነሳ ማድረግ መቻል አለብን፡፡ የሐሳብ ልዩነቶቻችን/ክርክሮቻችን ሁሉ ከጠመንጃ ጋር ሳይገናኙ፣ በዚሁ የጋራ ህልውናና ግስጋሴ ዓውድ ውስጥ የሚደረጉ መሆን አለባቸው፣ ማለትም የሥልጣኔ ወይም የአዲስ ባህል ግንባታችን ይህንን በመሰለ የግንኙነት አውታር ላይ መዋቀር ይኖርበታል፡፡
  5. ያፈጠጡ አደጋዎችን ካመከንን፣ ብጥስጣሽ አስተሳሰቦችና አፈንጋጭ ዓላማዎች ያልቅላቸዋል ማለት አይደለም፡፡ እንደገና ሙቀትና ነዳጅ አግኝተው ለመንሰራራት መጣራቸው አይቀርም፡፡ የሆነ በረሃና ጫካ ውስጥ መሽገው ጠመንጃ ለመተኮስም ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የቡድንና የግል መብቶች ከፌዴራላዊ አገረ መንግሥት ግንባታችን ጋር ተዋድደው፣ ፍትሕና ፍትሐዊነት፣ እንዲሁም እኩልነትና ነፃነት አለኝ ባይነት እስኪፋፉ ድረስ (በኢኮኖሚ፣ በባህልና በሰብዕና ልማት ሁሉን ያዳረሰ አስገራሚ ግስጋሴ እስከ አሳየን ድረስ) ብጥስጣሽ አስተሳሰቦች ከእነ ጠመንጃቸው ድራሻቸው ይጠፋል፡፡ እዚህ የማያዳግም ድል ላይ ለመድረስ ቆርጠን መሥራት አለብን፡፡

እነዚህ ዓብይ ነጥቦች የሚከተሉትን ሁለት ነጥቦች በውስጠ ታዋቂነት አዕምሮ ውስጥ የሚሰነቅሩ ይመስለኛል፡፡ በዚህ በጡንቸኞች ዓለም ውስጥ ደሃ ሆኖና አቅመ ቢስ ሆኖ በክብር መኖር አይቻልም፡፡ የሉዓላዊነት መከበርና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚሠራው ለፈርጣሞች ቀዳዳ የማያስገባ የውስጥ ሰላም ላጎለበቱ አገሮች ብቻ ነው፣ ይህ እውነት ለኢትዮጵያ እንግዳ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ በውጭ አፈናና ጣልቃ ገብነት/ወረራ የተሞላ ነው፡፡ የትናንትናም ሆነ የዛሬ ጣልቃ ገብነቶች/ወረራዎችና አፈናዎች ዓላማቸው በመሠረቱ ያው ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥቅም ማሳና ሎሌ ማድረግ ነው፡፡ በቀድሞ ጊዜ ጣልቃ ለመግባት ይቅርና፣ መውጫና መግቢያ በርን ለመያዝም ሆነ አገርን ወሮ ለመጋጥ ሰበብ መደርደር አስፈላጊ አልነበረም፡፡ የቅኝ ዘመን አልፎ የአገሮችን ሉዓላዊነት ‹‹የማክበርና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት›› ወግ ከመጣ ወዲህ ግን መግቢያ ሰበቦቹ ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹የጋራ ደኅንነት ቃል ኪዳን አለን››፣ ‹‹ሕጋዊው መንግሥት ዕርዳታ ጠየቀኝ››፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊው መንግሥት በሕገወጥ መንገድ ተገለበጠ›› እና ‹‹የዜጎቼ ደኅንነት አሳስቦኛል›› ባይነት ቀላሎቹ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ላቅ ያሉና በሩኅሩኅነት የተሞሉ የሚመስሉ ሰበቦች አሉ፣ ‹‹የአካባቢና የዓለም ሰላም/የሰው ልጅ ደኅንነትና መብት አሳስቦናል›› የሚሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ‹‹በሰው ልጆች ላይ መፈጸም የማይገባው ግፍ ተፈጸመ፣ ረሃብ የፖለቲካ መሣሪያ ሆነ፣ ንፁኃን የጦርነት ጋሻ ተደረጉ፣ የዘር ጭፍጨፋ ተካሄደ፣ ዘር የማፅዳት ወንጀል ተፈጸመ፣ የእርስ በርስ ፍጅት ተካሄደ፣ የጦር ወንጀሎች ተፈጸሙ››፣ ባይ ኡኡታዎች ዝነኞቹ መነገጃዎች ናቸው፡፡

መነገጃዎች ያልኳቸው ብዙ ጊዜ ስለሚነገድባቸው ነው፡፡ ሠለጠንን/ርኅራኄ አለን የሚሉት አገሮች ቀውስ ደርሶባቸው ሕዝብ እርስ በርስ ሲፋጅ፣ ሥርዓትና ሕግ ጠፍቶ ሕዝብ የወሮበሎች መጫወቻ ሲሆን፣ ዝም ብለው የተመለከቱባቸውን ጊዜያት ዓይተናል፡፡ ለሕዝብ ነፃነት መብት ተቆረቆርን ብለው፣ አገሮች ውስጥ ቀጥተኛና የእጅ አዙር ጦርነት ከፍተውና መንግሥትን ንደው ከነፃነትና ከመብት ይልቅ የሥርዓተ አልባነት፣ የግፍና የሰቆቃ ቀፍቃፊ የሆኑባቸውን ክስተቶች በተደጋጋሚ ዓይተናል፡፡ ነገር ፈልገው አገሮችን ጦርነት ውስጥ በማስገባትና ሕዝብ ፍዳ እንዲቆጥር ማድረግ ሌላው ፈርጃቸው ነው፡፡ ለእነሱ የጥቅም አጋር/ሎሌ የሆነ አገረ መንግሥት በገዛ አገሩ ውስጥ ግፈኛ ዕርምጃዎች ሲወሰድ፣ ከዚያም አልፎ በጎረቤት አገር ላይ በሰበብ ጦርነት ከፍቶ ሕዝብን በጦርነት፣ በረሃብና በስደት ሲዖል ሲቀጣ ቡፍ እንኳ ማለት ተስኗቸው ተመልካች ሲሆኑ፣ ከግፍ ዋዩ ሸሪካቸው ጋር ከመዋብም አልፈው መሣሪያ በመሸጥ ከግፍ ሲያተርፉም አስተውለናል፣ እያስተዋልንም ነው፡፡

ይኼው የተቆርቋሪነት ንግዳቸው በእኛ አገር ሥራ ላይ ውሏል፡፡ የሕወሓት ጦረኞች ያካሄዱትን ከክህደትም ክህደት የሆነ አገር የማፍረስ ወረራ የመቀልበስ አፀፋ በተካሄደበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥትን እንደ ወራሪና ግፍ ፈፃሚ አድርገው የጦረኞቹን ቆርጦ ቅጠላ ሲያጫፍሩ አስተውለናል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ከወጣ በኋላ የሕወሓት ጦረኞች ክረምቱን ተገን አድርገው በአማራና በአፋር ላይ የውድመት፣ የዘረፋና ሲቪሎች ላይ ሰቆቃ የሚያካሂድ ወረራ ሲያካሂዱ፣ ለሰው ልጆች አሳቢዎቹ አገሮች የአማራና የአፋር ሕዝብን ዋይታና ቃስታ ጆሯቸው አልሰማም፣ አንደበታቸው አላስተጋባም፡፡ እንዲያውም የአበጋዞቹን ግፈኛ ዘመቻ በፕሮፓጋንዳ ከማጀገንም ባሻገር በሳተላይት የመረጃ ጥበብ አማካይነት የተቃራኒ ወገንን ሥምሪት እየቃኙና እያሳወቁ መንገድ በመምራት የጦርነቱ ሥውር ተሳታፊ የነበሩም ነበሩ፡፡ ይህንን መጥፎ ልምድ አንረሳውም፡፡

ትናንትና ከወዳጅነት ወደ ጠላትነት ሚና ሲዞሩ ያየናቸው ‹‹ሥልጡኖች›› እንደገና ዛሬ ደግሞ ወደ ወዳጅነት ሲመለሱ ወዳጅነታቸውን አንገፋም፡፡ ክብራችንን ሳንሸጥ ከወዳጅነታቸው ልናገኝ የምንችለውን ንግድ ነክም ሆነ ሌላ ጥቅም ራሳችንን አጠንክሮ ለመውጣት ስንቅ ለማድረግ ንቁ መሆን ግዴታችን ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባይኖርበትም ከመጣመድ ወዳጅነት ይሻላል፡፡ ጠንክሮ የመውጣት ዒላማችን ለጎረቤት ያጋጣሚ ጥቀመኞችም ሆነ ኃያላን ነን ለሚሉ ዳግም ቀዳዳ ባለመስጠት ግቦች ላይ እስካነጣጠረ ድረስም የውስጥ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሰላማችንን የአገራችንን ሕዝቦች ሕይወት በለወጠ ልማትና የኢኮኖሚ ግስጋሴ ላይ ማነፅ የእንቅስቃሴያችን ሁሉ ማዕከል መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህንን ማዕከላችንን ማጠንከር ከቻልን ጠንካራ ወታደራዊ አቅምም አብሮ ይመጣል፡፡ ከጎረቤቶቻችንም ጋር የሚኖረን ሁለገብ የጋራ ጥቅም ትስስርም ፅናትና አክብሮት ያገኛል፡፡ የጉዳት ጥብሳትን ሳይረሱ ዳግም ላለመጎዳት መማሪያ ማድረግ እንዲህ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ አቅጣጫ አልማ፣ ሠርታ፣ በቀጣናዋ ውስጥ የልማትና የጥንካሬ ማሾ መሆን ከቻለች፣ የአፍሪካ ቀንድ መሰባሰቢያ ዕንብርት የመሆን ነገር፣ ደጅ ጠኚና ተጠኚ የማይኖርበት ለሸርም የማይበገር የሚሆን ይመስለኛል፡፡

እዚህ አስጎምዥ ውጤት ላይ ለመድረስ የምናደርገው ትግል ‹እየፈጩ ጥሬ› የማይሆነው ግን መልሰው ራሳችን ላይ (አስተሳሰባችንና ተግባራችን ላይ) እየተጠመጠሙ ሲያወላክፉንና ለጥቃት ሲያጋልጡን የቆዩ ጅላጅል (ቡትለካ ተብዬ) ልፍላፎዎችን ማራገፍ እስከቻልን ነው፡፡ ከልምድ የተማረ ትውስታ ለመፍጠር እንድንችል ልጠቃቅሳቸው፡፡

  • ጨፍጫፊ ቡድኖች አጋጣሚ ጠብቀውና አድብተው ሰቅጣጭ ጭፍጭፋ በእመጫት እናቶች፣ ጨቅላዎች ላይ ሳይቀር የሚያካሂዱት፣ አገራዊ ስብስባችንና የለውጥ ጥረታችን ውልቅልቁ እንዲወጣ መሆኑን የምንጠራጠር አይመስለኝም፡፡ የእነሱ ፍላጎት ይህ መሆኑ እየገባን እነሱ እንድንሆን የሚፈልጉትን ስለምን እንሆናለን ታዲያ? ከጭካኔም ጭካኔ እየመረጡ ሲያሳዩን እርር፣ ቅጥል እያልን አንደኛችንን ‹‹አስጠቂ›› ሌላችንን የተጠቂ ‹‹ተቆርቆሪ›› አድርገን እርስ በርሳችን በተሸነቋቆጥን ቁጥር አገራዊ ኅብረታችንን (ራሳችንን) እየጎዳን ጠላቶቻችንን ነው የምንጠቅመው፣ አንጀታቸውን ቅቤ የማጠጣት ሥራ ነው የምንሠራው፡፡ ከዚህ በላይ ምን ጅልነት አለ! በእኛ ፈንታ እነሱን አንጨርጭረን፣ ተስፋ አስቆርጠን ለማመናመን የምንችልበት ዕድል በእጃችን አለ፡፡ በግፍ ለወደቁ ወገኖቻችን አንድ ላይ እህህ! ብለን (አክብሮት ሰጥተን) የእነሱን ደምና ዕንባ ባልተከፋፈለ ልብና እልህ ግፈኞችን የሚያራውጥ ዕቅድ መደገሻ ማድረግ፡፡
  • ክፍልፋይ ብሔርተኝነትን ነጋ ጠባ ‹‹ይከፋፈላል፣ ያናጫል፣ ሄዶ ሄዶም ይበትናል›› እያልን በምላስ ስለነዘነዝነው አይጠፋም፡፡ በዚህ በዚያ ብለን ክፍልፋይ ብሔርተኝነትን ያስወግዳሉ ያልናቸውን አንቀጾች ሕገ መንግሥት ላይ ስላሠፈርንም ብሔርተኛነት ገደል አይገባም፣ ልክ የሕገ መንግሥት ሰነድ ውስጥ የዴሞክራሲ መብቶችንና የግንኙነት ሥልቶችን ስለደረደርን የኅብረተሰባችን ሕይወት ዴሞክራሲ በዴሞክራሲ እንደማይሆን ሁሉ፡፡ ዋናው ሥራ ያለው አመለካከትንና ፖለቲካን ማቃናት ላይ ነው፡፡ በተቀዳሚ ክፍልፋይ ብሔርተኝነት የሚነግድባቸውን ብሦቶችንና ተዛነፎችን አጢኖ መፍትሔ ለመስጠት የፈቀደ፣ ማኅበረሰባዊ ዥንጉርጉርነትና መተሳሰብ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ዕድገት፣ መከባበርና ሌሎች መብቶች የተግባቡበት ሥርዓት መገንባትን የህልውና ጉዳይ ያደረገ አተያይ መያዝ ነው፡፡ በዚያ ዕይታ ውስጥ ሆኖ፣ ይህንኑ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ዝግጅት ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ‹‹ብሔርተኛነት ከፋፋይ ነው…›› እያሉ ቁንጥርጣሪ ቡድኖች ውስጥ ተወሻሽቆ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ ስብስብ ለመፍጠር የረባ ጥረት ሳያደርጉ መኖር ፋይዳ ቢስ መሆን ነው፡፡ ለኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ መሰባሰብና አተያይ የረባ አስተዋጽኦ ሳያደርጉ በብልፅግና ፓርቲ በኩል የታየውን ኅብረ ብሔራዊ (ውህድ የመሆን) ጉዞ፣ ‹‹የተቀየረ ነገር የለም፣ አሁንም በየክልሉ ያሉት ብሔርተኛ ፓርቲዎች ናቸው!›› እያሉ ማዋደቅ ብሔርተኝነትን ማጥቃት ሳይሆን፣ ኅብረ ብሔራዊ የውህድነት ጥረትን መኮርኮም ነው፡፡ ጥቃቱ ከኩርኮማም ያልፋል፡፡ በአሁኑ ደረጃ የኢትዮጵያ መያያዣ አንድ ለእናቱ የሆነውን ብልፅግና ፓርቲ በዚህ፣ በዚያም እየተከተኩ እርር፣ ቅጥል እያለ ወደ ብሔርተኝነት እንዲሰባበር መልፋት ኢትዮጵያንም የመሰባበር ጥቃት ነው (ብሔርተኛነትን ከሃይማኖታዊ ፖለቲካ ጋር አያይዤ በስተ መጨረሻ እመለስበታለሁ)፡፡
  • በአሁኑ ሰዓት ብልፅግና ፓርቲ የሚመራውን መንግሥት ‹‹ሌላ የተረኝነት መንግሥት›› እያሉ የማብጠልጠል ቡትለካ በጅልነቱ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ አንደኛ፣ አገራችን ህልውናዋን ከሚፃረሩ ኃይሎች ጋር ትንቅንቅ ላይ ባለችበትና የዴሞክራሲ ለውጥ ገና በጅምርማሪ ደረጃ ባለበት ሁኔታ፣ የዚህ ዓይነት ንዝነዛ ውስጥ መግባት፣ ለጠላቶች በዚህ ነገር ህልውናችንንም ለውጣችንንም ሰርስራችሁ እንዳይሆን ማድረግ ትችላላችሁ የሚል ምክር ከመስጠት አይሻልም፡፡ ችግሩ የእውነት ኖሮ ቢሆን እንኳ፣ በዚህ የፈተና ወቅት ይህንን ማንጎላጨት ከመቄል የሚቆጠር ነው፡፡ ሁለተኛ፣ ‹‹የተረኝነት›› ሐሜቱ ‹‹በሥልጣን የመጠቀም ተራ የኦሮሞች ሆነ›› የሚል እንደመሆኑና የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ በቁጥር ተቀዳሚ እንደመሆኑ (እስካሁን ባለ ግንዛቤ)፣ የቁጥር ብዛቱን የሚያንፀባርቅ የሥልጣን ድርሻ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዓይቶ እንዳለማወቁም፣ ለዚህች ያህል የብርቅ ጊዜ የምትሆን ትዕግሥት ማጣት፣ ለመግባባትም ‹‹የተረኝነትን›› ችግር ሥር እንዳይዝ ለሚያደርግ ተግባርም አንዳችም አዎንታዊ አስተዋጽኦ የለውም፡፡ ሦስተኛ፣ የ‹‹ተረኝነት›› ነዝናዦች ‹‹ኦሮሞ የወርድና የቁመቱን ያህል ሥልጣንና ተጠቃሚነት አላገኘም›› እያሉ ኦሮሞን ለመነጠል (ኢትዮጵያን ለመበተን) የሚሠሩ ፅንፈኞችን በፖለቲካ የማንኮታኮት ትልም እንደሌላቸውም ራሳቸውን፣ በራሳቸው እያጋለጡ ነው፡፡ ኖሯቸው ቢሆን ኖሮ፣ ‹‹ተረኝነት››ን ያየ ዓይናቸው ተረኝነትን የሚቀናቀኑ የዴሞክራሲ ነክ ጅምርማሪዎችንም ማየት በቻለ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ከሁሉም ነገር በላይ ኢትዮጵያን ለማስቀጠልም ሆነ ዴሞክራሲን ለመገንባት ካስማ የሆነውን፣ በግለሰብም በፓርቲም አምልኮ ያልተጠፈረ ለኢትዮጵያና ለሙያቸው የሚታመኑ የመከላከያና የፀጥታ አውታራትን የብልፅግና መንግሥት ማደራጃቱ ግዙፍ ስንቅ ነው፡፡ ከዚህ ዋና ስንቅ ጋር፣ የገዥ ፓርቲ አሻንጉሊት ያልሆኑት የምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና እየተደረጉ ያሉ የሕግ ማሻሻያዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ፖለቲከኞቹም እነዚህን የመሳሰሉ ማሻሻያዎች አቅፈውና በኦሮሞዎችም ሆነ በሌሎች ማኅበረሰቦች የአገረ መንግሥቱን መዥጎርጎር እሰይ ብለው፣ አይዞህ አይዞን እየተባባሉ፣ ተረኝነትን የሚቃረኑ የዴሞክራሲ ሰበዞችን የማዳበርና ሁሉንም የአገሪቱን አካባቢዎች የሚያዳረስ የልማት ተዓምር የሚያመጣ የርብርብ ኃይል መሆን በቻሉ ነበር፡፡ ይህንን ተግባር ማሳካት ከቻልን የጥፋት ኃይሎች ብትንትናቸው ከመውጣቱ ባሻገር፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት የትኛውንም ዓይነት ሙስናና ዝባት ለማጋለጥ፣ ለመመርመር፣ ለመጠየቅና በሕግ ፊት ለማቆም በሚያስችል ሥርዓቱና ከሕዝብ ፈቃድ ጋር በሚገናዘብ የሥልጣን አያያዝና የአቆያየት ሥልቱ ጤናማነቱን ይጠብቃል፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥትና የሙያ አውታራት ውስጥ የማኅበረሰቦችን ስብጥር የመተሳሰቢያ ጊዜ ባይሆንም፣ መጪዋ ኢትዮጵያ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ማኅበራዊ ዥንጉርጉርነቷን በአግባቡ ማሠረጫጨቷ አይቀርም፡፡ ዛሬ ያሉት በፆታም ሆነ በእምነት ሠፈር የተደለደሉ የሚመስሉ ዝባቶች ሁሉ የመዥጎርጎር ለውጥ ያገኛቸዋል፣ ሒደቱም ተጀምሯል፡፡ አገረ መንግሥት ግንባታችን፣ የሙያተኞች፣ የልሂቃን ልማታችንና የሥራዎች ሥምሪታችን የኢትዮጵያን ዥንጉርጉርነት ያንፀባርቅ ሲባል ‹‹ኮታ፣ የብሔር ተዋፅዖ›› እየታሰባችሁ የሚጎፈንናችሁ ትኖራላችሁ፡፡ አመለካከታችሁን ለመግራት ቢያንስ በአጠቃላይ የፀጥታ ኃይሎች ውስጥ የነበረና በተለይም ሰሜን ዕዝ ውስጥ እንዳይነካካ ተደርጎ የቆየ በአንድ ብሔርተኛነት/ጎጠኝነት የተዋጠ የዕዝ ሰንሰለት ምን ጉዳት እንዳደረሰ አይዘንጋችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ (ብሔረሰባዊ ሃይማኖታዊ) ሰላም ከእንግዲህ ፍትሐዊ በሆነ ጥልቀትና ስፋት ዥንጉርጉርነታችንን ለኢትዮጵያ ግስጋሴ ከማንቀሳቀስ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ የስብጥር ምጣኔና የሙያ ብቃት ባላንጦች አይደሉም፡፡ የስብጥር ምጣኔን ነጋ ጠባ ላሥላ ማለትም የየማኅበረሰብም ሆነ የአገር ጥቅም አይደለም፡፡ ስብጥር/‹‹ተዋጽዖ›› ይጠበቅ ማለት፣ የሙያ ብቃት ለስብጥር ምጣኔ ሲባል ይጎዳ ማለት አይደለም፡፡ ጥያቄው በክህሎትና በሙያ የማብቃትና የማብሰል ሥርዓታችን ሁሉንም የሕዝብ ጥንቅራችንን በአግባቡ የሚነካ (ዥንጉርጉር ባለብቃቶችን የሚያፈላና የሚያተባ) ይሁን ነው፡፡ በብቃት ማነስ ምክንያት ስብጥርን የምንጎዳበትን አማራጭ ማጣት እናስወግደው ነው፡፡

የስብጥር ምጣኔን ከሞላ ጎደል ለመጠበቅ መሞከርና በሕወሓት/ኢሕአዴግ ጊዜ እንደታየው የሹመት ሥፍራዎችን ከዚህ ከዚያ ብሔር ለሚመጣ ሰው ብሎ መመደብ መምታታት የለባቸውም፡፡ እንዲህ ያለ ምደባ ኢዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ከሶማሌ የተገኘ ሰው በአገር አቀፍ ፓርቲው ውስጥም ሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገኖ ቢወጣና በኢትዮጵያ ሕዝብ ሰፊ ተመራጭነት ቢያገኝ ‹‹ፍትሐዊ አይደለም›› የሚል ቅሬታ መነሳት የለበትም፣ ቢነሳ እንኳ መሳቂያ ከመሆን አያመልጥም፡፡ የመላ ሕዝብን ምርጫ ለመቀየር መሞከር ፍትሐዊም ዴሞክራሲያዊም ስለማይሆን፡፡ በአማራና በኦሮሞ ማኅበረሰቦች ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትር መመረጥ የነበረበት ከእኛ ውስጥ ነበር የሚል ጉምጉም ቢነሳም የመንግሥት መሪነት የእኛ ርስት ነው (ዴሞክራሲ ደህና ሰንብች) ከማለት የተለየ አይደለም፡፡ እነሱ የየበኩል የቁጥር ግዙፍነታቸውን ለአገር መሪነት መከራከሪያ ቢያደርጉ ከአማራና ከኦሮሞ ውጪ ያሉ ሕዝቦች አንድ ላይ ቁጥራቸውን ደምረው ‹‹እህሳ!›› ማለት አይሳናቸውም፡፡ በአጭሩ የስብጥር ምጣኔን መጠበቅ ማለት የተወሰኑ ሹመቶችን ርስት ማድረግ ማለት አይደለም፡፡

በዚህና በዚያ ክልል የእኔ ማኅበረሰብ በአግባቡ አልተወከለም የሚል ጥያቄን ከዛሬና ከነገ ጋር እያገናዘብን ትንሽ ነጥቦችን እናክል፡፡ ጥያቄው ዞሮ ዞሮ በምርጫም በሹመትም አወካከላችን ማኅበራዊ ጥንቅርን ያንፀባርቅ ባይ ነው፣ ተገቢም ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ ባለው የእኝኝ ፖለቲካና ተፎካካሪ የለሽ አንድ ፓርቲ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ተጨባጭነቱም ከአንድ ፓርቲ ፍላጎት ጋር ከመቆራኘት አያመልጥም፡፡ ተቆራኝቶም፣ ፕሮግራሜን ለማስኬድ አስተማማኝ ሰው አገኛለሁ ወይስ ለሰርጎ-ገብ እጋለጣለሁ? ለምርጫ ዕጩ ባደርግም ሆነ ብሾም ምን ያህል ተቀባይነት ያገኝልኛል? የሚሉ ሥጋቶች ተጨባጭነቱን ይወስናሉ፡፡ መናጨት መጠቂያችን መሆኑ ገብቶን፣ ከላይ የተጠቃቀሱትን ጅል እኝኞች ማራገፍ ከቻልንና ፉክክርን ከአገራዊ ኅብረት (ሶሊዳሪቲ) ጋር ማፋቀር ከቻልን በአገራዊ ምክክር መግባባትና ሰላምና ዴሞክራሲን መገንባት ብዙም አያሰቃየንም፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ በአግባቡ ሕይወት ባገኙበት (ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተሟሉበት) የነገ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ፣ ብዙ የሕዝብ ድጋፍና ድምፅ የማግኘት ፉክክሩ በራሱ የውክልናን መስተካከል ጉዳይ በጣም ቀላል ያደርገዋል፡፡

ዩክሬይን ለውድመት አደጋ የተጋለጠችው ዛሬ አይደለም፡፡ ክሬሜያን ከማስቦጨቋ በፊት ገና የህልውና እውነታዋ ከአውሮፓም ከሩሲያም ጋር የተጣጣመ ግንኙነትን እንደሚፈልግ በሳተች ጊዜ ነው፡፡ ከሩሲያ ጋር ያላትን ዝምድና ባበለሻሸ ኪሳራ የአውሮፓ ወዳጅነቷን የማጥበቅ ሙከራዋ የአገር አንድነቷን እስከማናጋት ድረስ ቀውሰኛ መሆኑን ያሳዩ ፍንጮችም ቀደም ብለው ታይተው ነበር፡፡ የዩክሬን ፖለቲካ ከፍንጮቹም ከፖለቲካ ውጣ ውረዶቹም ሳይማር እንደታመመ ውሎ አደረ፡፡ ይባስ ብሎ ኮሜዲያን የአገር መሪ ሆነና ይኸው የዩክሬን ሕይወት ሳቅ የሚኮመኩም ሳይሆን በትራጀዲ የሚያነባ ሆነ፡፡ የዩክሬንን አበሳ ያነሳሁት ለአንድ ዓብይ መልዕክት ስል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት የዛሬ ፈታኝ እውነታ የሚሻው ከእኝኝ ይልቅ ተባብሮና ተመካክሮ መሥራትን ነው፣ ፖለቲከኞቻችን ልብ ግዙ!!!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በ2014 ዓ.ም. የፓርላማ የዓመቱ መገባደጃ (በጀት ማፅደቅንና ወቅታዊ ሁኔታዎችን የተመለከተ) ስብሰባ ላይ፣ በየቀኑ ስንት ዓይነት የጥቃት ደባዎች ለመሹለክለክ እንደሚሞክሩና ስንቶቹን የማክሸፍ ሥራ እየተሠራ እንዳለ የተናገሩትን ቃል ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪካዊና የአሁን ሁኔታ ማገናዘብ እየቻለ፣ ዛሬ በአራቱም ማዕዘን ብዙ ጉድጓድ እንደሚቆፈርልንና ብዙ ነገር እንደሚቃጣብን ማሰብ የሚቸግረው ካለ፣ የማስተዋል አቅሙ ላይ የተኛ መሆን አለበት፡፡ እነ አልሸባብና አልቃይዳም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያችንን ማንደድ የሚሹ የውጭ ጠላቶች ሰርገውም ሆነ በውስጥ ተቀጢላዎች ፈንጂ እያፈነዱ ከተሞችን/መሠረተ ልማቶችን ያላደባዩት ፈንጂ ቸግሯቸው እንዳልሆነ፣ በብዙ የአገራችን ሥፍራዎች የተረጋጋ ሕይወት ኖሮን የእኔ ዓይነቶች አፋችንን ለማሾልና አቃቂር ለማውጣት የበቃነው፣ የፀጥታ አውታሮቻችን የዕለት በዕለት የነቃ ሥራ እየሠሩና እየተዋደቁ በመሆኑ እንደሆነ ማጤን የሚቸግረን ካለንም፣ ችግራችን የምሥጋና ስስታምነት እንዳይሆን እሠጋለሁ፡፡

ለማንኛውም የፀጥታ ኃይሎቻችንን ደከመኝ የማይባልበት ከባድ ሥራ ማመሥገን አለብንና አመሠግናለሁ፡፡ ግፈኞች እያደቡ በወገኖቻችን ላይ የሚያደርሱት ጭፍጨፋ ልፋታቸውን እጀ-ሰባራ የማድረግ ጊዜያዊ ጭጋግ ቢፈጥርም ጭጋጉ እንደሚበን የወገኖቻችን አሰቃቂ መስዋዕትነት ለመንግሥት መሪዎችና ለፀጥታ ኃይሎቻችን የወኔና የስኬት ነዲድ እንደሚሆናቸው እተማመናለሁ፡፡

የብሔር ፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ፖለቲካ የሚጋሩት ባህርይ አላቸው፡፡ ሁለቱም ከሌሎች ዝምድናዎች ይበልጥ አንድ ዝምድናን አብልጠው ፖለቲካቸው ያደርጋሉ (አንደኛው የብሔር ማንነትን አብልጦ ፖለቲካው ያደርጋል፣ ሌላው ደግሞ ዓይነተኛ የሃይማኖት ማንነትን)፡፡ ሁለቱም ያበለጧቸው (ፖለቲካቸው የደረጓቸው) ማንነቶች የሚገኙባቸውን ዋነኛ ማኅበራዊ ሥፍራዎች የራሴ ይላሉ፡፡ ‹‹የእኔ ማንነት ለዚያ ሥፍራ ባለቤት ነው›› ሲሉም ገዥ መሆን አለበት ማለታቸው ነው፡፡ የእኔ ማንነት አባላት ከሁሉም በላይ ለቦተለከው ማንነታቸው መወገን (ማድላት) አለባቸው የሚል አስተሳሰብም አላቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ከሌላው ይበልጥ ቅድሚያ ዕድልና ጥቅም ለእኔ የማንነት ማኅበረሰብ አባላት ይላሉ፡፡ ዋና የዝምድና መለኪያ ሆኖ ከቦተለከው ማንነት ውጪ ያሉ የብሔር/የሃይማኖት ማንነቶች ይንጓለላሉ፣ እንደ ባይተዋር ይቆጠራሉ፣ መብታቸው ያንሳል፡፡ በአጭሩ ሁለቱም ፖለቲካዎች አግላይና አድልኦኛ ናቸው፡፡

የብሔር ፖለቲካም፣ የሃይማኖት ፓርቲም ይህን በመሰለ አስተሳሰብ ላይ ነው የሚገነቡት፡፡ ይህ ማለት ከፓርቲ በፊት አስተሳሰቦቹ ይቀድማሉ፣ አስተሳሰቦቹ በይፋ ፓርቲነት ሳይደራጁ ሊኖሩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ የብሔር ፓርቲ/ግንባር፣ ወዘተ የሚል ቅርፅ ከመያዙ በፊት በዕድርና በማኅበርነት ሲጀመር ታይቷል፡፡ በግብፅ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ ባህርይ ይዞ በመሐመድ ሙርሲ አማካይነት ወደ ሥልጣን የወጣው እስላማዊ ወንድማማችነት የፓርቲ ባህርይ ከመያዝ የቀደመ ሕይወት ነበረው፡፡ ይህ ምን ያሳየናል? ሃይማኖታዊም ሆነ የብሔር ፖለቲካ የፓርቲ ቅርፅ ሳይዝ ሊኖር እንደሚችልና የሃይማኖት ወይም የብሔር ፖለቲካን የማስወገድ ጉዳይ የክልከላ ሕግ የማውጣት ጉዳይ እንዳልሆነ ነው፡፡ የብሔር ፓርቲነትንም ሆነ የሃይማኖት ፓርቲነትን ህልውና የማሳጣት/የማሸነፍ ነገር ‹‹ብሔርንም ሆነ ሃይማኖትን የፖለቲካ ቡድን ማደራጃ ማድረግ አይቻልም›› በሚል የሕግ አንቀፅ የሚሟላ አይደለም፡፡ ዋናው የማሸነፍ ሥራ መካሄድ ያለበት የመደራጀት ዕገዳ ላይ ሳይሆን፣ ለፖለቲካ ድርጅት መብቀያ የሚሆኑት አስተሳሰቦች ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ወቅት ብልጭ ያለው የሃይማኖት ፖለቲካ ቡድን የከሰመው በሕግ አንቀፅ ሳይሆን አስተሳሰቡ በሕዝቦች ፖለቲካዊ ንቃት ዘንድ ተሸናፊ ስለሆነ ነበር፡፡ የብሔር ፖለቲካ (አስተሳሰቡ) በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ልቦና ውስጥ ከተሸነፈም ከከልካይ የሕግ አንቀጽ በፊት የብሔር ፓርቲዎች ድጋፋቸውንና አባልነታቸውን እየተራቆቱ (በሕግ ሳይፈርሱ እየፈረሱ) የኅብረ ብሔር ፓርቲዎች ስብስብ እየደረጀና ፖለቲካውን እየቃኘ የሚሄድበት ዝንባሌ እየጎለመሰ ይመጣል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፓርቲን ለማሸነፍ ከፈለግን ማትኮር ያለብን ይህንን ሒደት በማሳካት ተግባር ላይ ነው፡፡

በፓርቲ ደረጃም ሆነ ከዚያ በመለስ የሚካሄድን ክፍልፋይ ብሔርተኝነትን የመታገል ሐሳብ እኔን ከመሰሉ ሰዎች የመጣ አይደለም፡፡ ከራሱ ከብሔርተኛነት ልምድ የመጣ መራር መልዕክት ነው፡፡ እስካሁን ያለን ልምድ በመከራ እየቀጣ የሚነግረን ሌሎች ዝምድናዎችን ደፈጣጦ አንድ የዝምድና ዘንግ ላይ የሚገደገድ አንጓላይ ወገንተኝነት እያናቆረ የሚያቀያይም፣ ጥላቻና ግጭት የሚያመርት፣ ከዚያም ሲብስ ወደ መጠፋፋት እብደት የሚወስድ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ የመጨረሻ የዕብደት ደረጃውም ይኼው እየታመስንና እየተቀጣን እንገኛለን፡፡ አንድ የዝምድና ዘንግ ላይ የተገደገደ አድሏዊ ወገንተኛነት ምን ያህል እንደሚያጨፋጭፍ በማሳየት ረገድ ደግሞ የሃይማኖት አክራሪ ወገንተኛነት ጥሩ አብነት ነው፡፡ አትርሱ! እምነት (አምልኮ-ፈጣሪና ፊሪሃ-ፈጣሪ)፣ ጥሩ መሥራትና ፅድቅ ፍለጋ ያለበት ሕይወት ነው፣ እንዲህም ሆኖ የሃይማኖት ፖለቲካ፣ ከፅድቅና ከፈጣሪ መንገድ ወጥቶ በፍጥነትና በስፋት ከደሙ ንፁህ የሆኑ ሰዎችን ወደ መጨፍጨፍ ኃጢያት የሚያንሸራትት ነው፡፡ ለዚህ ነው አደገኛና አስፈሪ የሚሆነው፡፡ በዚህ በኩል አደጋውን በትንሹ ያየንባቸው የጎንደርና የወራቤ ልምዶች የየራሳቸው አስተማሪነት አላቸው፡፡ ጎንደር ውስጥም ሆነ ወራቤ ውስጥ የተደረገው ነገር ‹‹የክርን ፍትሕ›› (ዋይልድ ጀስቲስ) የሚባለውን በራስ ጉልበት ‹‹ያጠፋን›› የመቅጣት ተግባርን እንኳን አያሟላም፡፡ ጎንደር ውስጥ ምን እንደተደረገ? ማን እንዳደረገው? ሳያጣሩና ሳይለዩ፣ የጉርብትና ዝምድናን፣ የጎንደሬነት ዝምድናን፣ የአማራነት ዝምድናን ሁሉ ረጋግጠው በቢጤ ሃይማኖት ረድፍ የያዘ ግጥሚያ ውስጥ ገቡ ‹‹ለሃይማኖታቸው ብለው››፡፡ ግለሰቦች የሠሩትን ስህተትና ጥፋት በጭፍን አጡዘው፣ የግለሰቦችን ጥፋትም በጭፍኑ ላፈጠጡበት እምነት ሰጥተው፣ በጥይት ተኩስ፣ በድንጋይ ውርውርያ፣ በንብረት ውድመት ጉዳት ደረሰ፡፡ የቁጥር ብልጫ ምናምን ውስጥ ሳንገባ በሁለቱም በኩል እምነት ያለ ጥፋቱ ተቀጪ ተደረገ (ማለትም፣ አጥፊዎቹ ግለሰቦች የሚከተሉትን እምነት መከተላቸው ወንጀል ሆኖባቸው፣ ያላጠፉ ሰዎች በጭፍኑ ተቀጡ፡፡ እንደ ሰዎቹ ቤተ እምነቶችም ተቀጡ)፡፡ እዚህ ውስጥ ፈጣሪን ማክበር፣ እምነትን ማክበርና ለፅድቅ መሥራት የለበትም፡፡ የተሠራው ሳፊ ወንጀል፣ ሳፊ ኃጢያት ነው፡፡

ወራቤ ውስጥ የተደረገው ደግሞ፣ ጎንደር ተፈጸመ የተባለውን ወሬ በመያዝ ጎንደር ለተፈጸመ ወንጀል ወራቤ ያሉ ንፁኃንና ቤተ እምነቶች በበቀል መቅጣት ነው፡፡ አንደኛቸውም እምነቶች ለአማኞቻቸው ‹ራሳችሁ በራሳችሁ የቅፅበት ሕግ—ፍርድ ቤት—ፈራጅ ሆናችሁ ንፁኃንን ቅጡ› አይሉም፡፡ የዚህ ዓይነት ወንጀል ያፀድቃል አይሉም፡፡ ጎንደርም ውስጥ ወራቤ ውስጥ ወደ ጥቃት የገቡ ሰዎች ለሃይማኖታቸውም ሆነ ለሃይማኖት አባሎቻቸው አልቆሙም፣ አልተቆረቆሩም፡፡ ይህንን የተናገርኩት እኔ ሳልሆን ዳፈኛ ተግባራቸው ነው፡፡ የጎንደሩ የጥፋት ሥራ ጀማሪዎች እዚያውና በሌሎች ሥፍራዎች ያሉ የእምነት ወገኖቻቸውንና የእምነት ሥፍራዎች ለአደጋ አሳልፈው ነው የሰጡት፡፡ በወራቤ የሆነው የዚያ በቀለኛ መልዕክት ጭፍን የመልስ ምት ነው፡፡ ወራቤ ውስጥ ያንን ጭፍን ጥቃት የፈጸሙ፣ ያስፈጸሙና የማከላከል ኃላፊነታቸውን እንኳ ሳይወጡ ቆመው ያዩ ዜጎችና የፀጥታ የሰዎችም ለተጠቂው እምነት ሰዎች ግብዣ ነበር ያቀረቡት፣ (እኛ እንዳደረግነው በሌላ ቦታ የእኛን የእምነት ሰዎችና የማኅበረሰብ አባላት መግደል/ቤተ እምነታቸውን ማውደም ትችላላችሁ የሚል ግብዣ)፡፡ በዚህ ዓይነቱ በቀል የመገባበዝ ምልልስ ውስጥ፣ ለእምነትም ለፈጣሪም ሆነ ለቢጤ አማኒያን የመቆም ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ ከሁሉቱም በኩል የተደረጉትን የእንፋጅ ግብዣዎች ገፍ በገፍ የሚቀበል ሕዝብ ቢኖር ኖሮ፣ ተያይዞ ከማለቅ ማን ይተርፋል!? የሚደንቀው ደግሞ የቁጣና የበቀል ፍላት ከበረደ በኋላ እንኳ፣ የተሠራው ሥራ ለእምነትም ለእምነት ወገኖችም የመቆም ይዘት የሌለው (ወንጀል) እንደሆነ፣ ከሕግ የሸሸጓቸው ሰዎች እምነታቸውንና የእምነት ወገኖቻቸውን ለሰፊ የጅምላ ጥቃት ያጋለጡ የወንጀል ተሳታፊዎች እንደሆኑ ያልተረዱ ሰዎች መገኘታቸው ነው፡፡

ያወሳናቸው የሃይማኖት ግጭት ልምዶች ጭፍን ግጭትና በቀል ውስጥ መንከባለል የፈጣሪ መንገድ አለመሆኑን፣ ለእምነትም ለእምነት ባልንጀሮችም መቆም አለመሆኑን በማሳየት መልክ መፍትሔውንም በውስጠ ታዋቂ ጠቁመውናል፡፡ ላስቀምጣቸው፡፡ ለእምነታችንና ለእምነት ባልንጀሮቻችን መብት፣ እኩልነትና ደኅንነት ተቆርቋሪነታችን በተግባር የሚረጋገጠው፣ እንደተረጋገጠም እንዲዘልቅ ማድረግ የምንችለው፣ ለየትኛውም እምነትና የእምነት ሰዎች መብት መከበር እኩልነትና ደኅንነት ስንቆም፣ በየትኛውም እምነትና የእምነት ተከታዮች ላይ የሚፈጸም መንጓለልንና ጥቃትን ተቃውመን ስንቆም፣ በራሳችን የእምነት ሰዎችና እምነት ላይ የጥቃት ትንኮሳ ቢከሰት እንኳ፣ በስሜት ከመወሰድ ተቆጥበን ሕግና ፍትሕ ሥራው እንዲሠራ (የጥፋት ተጠርጣሪዎች ለሕግ እንዲቀርቡ) ስንታገል ነው፡፡ ለእምነታችንና ለእምነት ወገኖቻችን በፅናት መቆርቆር የምንችለው (የእምነት መብቶችንና የአማኞችን ደኅንነት መንከባከብ የምንችለው) በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ይህንን በልቦናችን ያሳድርልን!! ይህንን የህሊና ንቃት ይዘን፣ እንኳን ድብድብና ግድያ መሞከር፣ በቀልድ አስመስሎ ሃይማኖትን፣ ብሔርንና ፆታንም ሆነ አካላዊ ጉዳትን የሚነካ ትንኮሳን ነውር አድርገንና በተግባራዊ ሕግ እየቀጣን ተከባብሮ ለመኖር ያብቃን፡፡ (በፈረንጆቹ አገርማ፣ የተመሳሳይ ፆታ ተራክቦ ያላቸውን ሰዎች በጥዩፍ ዓይን ከፍ ዝቅ ማድረግ እንኳ ሊያስከስስ ይችላል)፡፡

የብሔር ጥቃት ወደ ሃይማኖት ነክ ጥቃት ሊንቦራቀቅ፣ በእምነት የመጣ ጥቃትም ወደ ብሔር ሊዞር ይችላልና ለሁለቱም ዓይነት ጥቃቶች ላለመጋለጥ የሚቻለው ደግሞ፣ ሁሉንም መልካም የማንነት ክሮቻችንን አክብረን ስንይዝ፣ የትኞቹንም ደፈጣጠን አንዱን ማንነት የሁሉ ነገር መመልከቻ መነጽራችን (የረድፍ መሰባሰቢያችን) ከማድረግ መንገድ ራሳችንን ነፃ ስናወጣ ነው፡፡ ከብሔርም ሆነ ከሃይማኖት አንጓላይነትና የፅንፍ ሸርተቴ መውጣት ማለት ይኼው ነው፡፡ በእነዚህ ነፃነቶችና የመብቶች አያያዝ ላይ መንግሥት፣ ፖለቲከኞች፣ የእምነቶች መሪዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ሲቪል ማኅበራት ገና ብዙ ብዙ የማንቃት ሥራ አለብን፡፡ የንቃት ሥራው ፍሬያማነት ደግሞ ዞሮ ዞሮ በሕግ ማስከበርና በፍትሕ ተቋማት ሕይወት (አመለካከትና ተግባር) መታደስ መታገዝን የሚሻ ይመስለኛል፡፡ የተቋማቱ መታደስ ደግሞ ከጥንቅራቸው ኅብረ ብሔራዊ ሆኖ መዥጎርጎር ጋር ይያያዛል፡፡ የፌዴራል ፖሊስና የፌዴራሉ ፍርድ ቤት አውታራት በአግባቡ ተሟልተው በእነሱ የኃላፊነት ጥላ ሥር የሚወድቁ የመብት ጥሰቶችንና የሰብዕና ጉዳቶችን የመከታተልና ተጠያቂ የማድረግ ተግባር መጎልመስ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁን ባለው የአወቃቀር ደረጃ ልዩ ወረዳ/ልዩ ዞን በሚባሉ ሥፍራዎች ያሉ አካባቢያዊ የፀጥታና የፍርድ ቤት ጥንቅሮች በክልል ደረጃ ባለ የዥንጉርጉርነት ደም ግባት መታነፅ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡ በክልልና በልዩ ወረዳ/ዞን መሀል ያለ መናቆር የዚህ ዓይነት ተሃድሶና የመዋቅር ማሻሻያ ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል ውስጥ በኦሮሞ ልዩ ዞንና በክልሉ አስተዳደሮች ዘንድ በጋራ ህልውናና መለማማት ተማምኖ መሥራት የሚቻለው በዚህ ጎዳና ውስጥ መሄድና ማሰብ ከተቻለ ነው፡፡

እስካሁን ያወሳነው ነገር በሕገ መንግሥት መጽሐፍ ውስጥ በአንቀጾች ከታዘሉ ዕሳቤዎች ይበልጥ፣ አንቀጾቹ ያዘሏቸው ዕሳቤዎች ተፍታተው የኅብረተሰብ ንቃት መሆን መቻላቸው ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን እንደሚቀድምና እንደሚበልጥ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይህ ግንዛቤ ደግሞ ከፊታችን ላለው አገራዊ የመግባባት ተግባርና እሱን ተከትለው ለሚመጡ ሕግ ነክ ሥራዎች መሠረታዊ ይመስለኛል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...