Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ባንኮች በየዓመቱ ይህንን ያህል ትርፍ እያገኘን ነው እያሉ ከሚከፋፈሉ ካፒታል ማሳደግ ላይ በሚገባ መሥራት አለባቸው›› አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ የፋይናንስ ተቋማት የትርፍ ምጣኔ እያደገ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የውስጥና የውጭ ችግሮች አሉ በሚባልባቸው ጊዜያት ሁሉ የዚህ ዘርፍ ዕድገት ሳይቋረጥ ቀጥሏል፡፡ በተለይ ባንኮች እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም ዕድገታቸውን አስቀጥለዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 16 የግል ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 40 ቢሊዮን ብር አትርፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ 27.5 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል፡፡ ይህ ዕድገት በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት 6.6 በመቶ አካባቢ ይደርሳል ተብሎ ነው ታቅዶ የነበረው፡፡ ነገር ግን ወደ ዘጠኝ በመቶ አካባቢ ደርሷል እየተባለ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከዕቅድ በታች ሲሆን፣ የፋይናንስ ተቋማት ዕድገት ግን ቀጥሏል፡፡ ይህ በብዙዎች ዘንድ ብዥታን ሲፈጥር ይታያል፡፡ ከዚህ ምልከታ በመነሳት ባንኮች በችግር ውስጥም ሆነው የማትረፋቸው ሚስጥር ምንድነው? የሚለውን መንደርደሪያ በመያዝ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገቱ እንዴት ይተነተናል የሚለውን ጥያቄ በማስከተል በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በተለይ በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉምቱ ከሚባሉት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ከሆኑት ከአቶ ተክለወልድ አጥናፉ ጋር  አጭር ቆይታ ተደርጓል፡፡ አቶ ተክለወልድ በይበልጥ የሚታወቁት ከ14 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው ማገልገላቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን እያገለገሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድና የሌሎች ተቋማትም የቦርድ አባል ናቸው፡፡ ዳዊት ታዬ ከአቶ ተክለወልድ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ከሌሎች ዘርፎች በተለየ አትራፊ ሆነው ተጥለዋል፡፡ እርስዎ በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ዘንድሮ 27.5 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ሆኖ የባንኮች ትርፍ ማደጉ ምንን ያሳያል? የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገትስ ከዚህ ትርፍ ምጣኔ ጋር ያለው ትስስር ምን ያህል ነው? የባንኮች የትርፍ መጠን ዕድገትስ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?

አቶ ተክለወልድ፡- በዋናነት መታየት ያለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢኮኖሚው አልወደቀም፣ እንዲያውም አድጓል፡፡ በዚህ ወቅት ከስድስት በመቶ በላይ ዕድገት ማስመዝገብ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህ ዕድገት እስካለ ድረስ የፋይናንስ ተቋማቱም ያድጋሉ፡፡ የዕድገት ዓይነቱ ሁለት ነው፡፡ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የፋይናንስ ዘርፉ ዕድገት አድርጓል፡፡ ለፋይናንስ ዘርፉ ውጤት ማማር ደግሞ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህ ማለት ግን የፋይናንስ ዘርፉ ብቻ ስላደገ የመጣ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉ ባለፉት አራት ዓመታት ብዙ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም ዕድገቱ ተንገራግጮ አልቆመም፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በአማካይ ወደ 6.6 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ይህ ዕድገት ተገኘ ማለት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሚገባ አለ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ስታይ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የያዘው የአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ ባንኮችንም ይጨምራል፡፡ ንግዱንና ተያያዥ ዘርፎችን ይጨምራል፡፡ ከዚህ ቀደም ዘጠኝና አሥር በመቶ የሚባለው አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የወረደው በኮቪድ አይደለም፡፡ እንደ ሌላው አገር ኮቪድ ገባ ተብሎ ሥራ ይቁም የተባለበት መስክ የለም፡፡ ሥራው ቀጥሏል፡፡ ኮቪድ በእኛ አገር ላይ ያስከተለው ነገር የተወሰነ ነው፡፡ እንደ ሌላው አገር ሥራ ሙሉ ለሙሉ አላስቆመም፡፡ ስለዚህ ከቱሪዝም ዘርፉ በቀር ሥራው ቀጥሏል ማለት ነው፡፡ ሌላውም ሥራ እንደተጠበቀ ነው፡፡ በመሆኑም የኢኮኖሚው ዕድገት ቀጥሏል ማለት ነው፡፡

ይህ ጉዳይ በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ከኢንቨስትመንት አንፃር ሲታይም ዕድገት እየታየበት ነው የቀጠለው፡፡ ኤክስፖርቱንም ካየኸው ከብዙ ዓመታት በኋላ ባለፉት ሦስት ዓመታት ነው እያደገ የመጣው፡፡ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ሳይበልጥ ሲዳክር የነበረው የአገሪቱ የወጪ ንግድ ዓምና 3.6 ቢሊዮን ዶላር፣ ዘንድሮ ደግሞ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ኤክስፖርት አደገ ሲባል ምንጩ ምንድነው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለኤክስፖርት ዕድገቱ የባንኮች ሚና አለበት፡፡ ከባንኮች ብድር ተገኝቶ የተሠራ ነው ማለት ነው፡፡ አንድን ምርት ለውጭ ገበያ እስኪቀርብ ድረስ በሰንሰለቱ የሚያልፉ ተዋንያን ሳይቀሩ ከባንክ ተበድረው ነው የሠሩት፡፡ ያው እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ በራሱ ገንዘብ የሚሠራ የለም፣ ተበድሮ ነው፡፡ በመሆኑም ኤክስፖርቱ ባደገ ቁጥር የባንኮች የብድር መጠንም ከፍ ይላል፡፡ ከታች ጀምሮ እስከ ኤክስፖርተሩ ድረስ አትራፊ ከሆኑ ደግሞ መጨረሻ ላይ ባንኮችም ትርፍ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ የኤክስፖርት ገቢ መጠኑ ከፍ አለ ማለት ደግሞ የውጭ ምንዛሪው ገቢ ባንኮች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ባንኮች አትራፊ ሆነው እንዲቀጥሉ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የሬሚታንስ ገቢ ዕድገትም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው፣ ጨምሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የዘንድሮ የሐዋላ (ሬሚታንስ) ገቢ ምን ያህል ዕድገት አሳይቷል? ይህ ገቢ የባንኮችን ገቢና ትርፍ ከማሳደግ አኳያ ምን ያህል ጠቀሜታ ሰጥቷል?

አቶ ተክለወልድ፡- ዘንድሮ የሬሚታንስ ገቢው ወደ 6.8 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ነው፡፡ የሐዋላ ገቢ ደግሞ ብዙ ነገር ይዞ ይመጣል፡፡ ባንኩ በሁለት በኩል ይጠቀምበታል፡፡ ኮሚሽን ያገኛል፣ ለኢምፖርተሮች የሚሰጡት የውጭ ምንዛሪ ያገኛሉ፡፡ ኢምፖርተሮቹ ደግሞ በተሰጣቸው ገንዘብ ዕቃ ያመጣሉ፡፡ ለጅምላ ነጋዴው ይሰጣል፣ ይህንን ሲያደርግ የጅምላ ነጋዴውም እንደገና ይበደራል፡፡ ቸርቻሪም ይበደራል፡፡ ስለዚህ የባንኮችን ትርፍ እንዲያድግና የትርፍ ቻናል እንዲሰፋ በማድረግ ለባንኮቹ የገቢ ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ኢኮኖሚው ስላደገ እኮ ነው ዘንድሮ ኢምፖርት ያደገው፡፡ አምና በ20 በመቶ፣ ዘንድሮ በ25 በመቶ አድጓል፡፡ ይህ ዕድገት ከሌለና ፍላጎቱ ከሌለ ኢምፖርት ማድረግ አትችልም፡፡ ኢምፖርት በአንድ በኩል ብዙ የውጭ ምንዛሪ ይወስድብሃል እንጂ የዕድገት ምልክት ነው፡፡ የምታመጣው የሚበላና ሸቀጣ ሸቀጥ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ኢኮኖሚውን ከፍ የሚያደርጉ የካፒታልና ጥሬ ዕቃዎች ይገባሉ፡፡ ሌሎች ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚጠቅሙ ብዙ ነገሮች ናቸው የምታመጣው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ዓይነቶች ከ5,900 በላይ ናቸው፡፡ እኛ ግን ኤክስፖርት የምናደርገው እንጀራና ሌሎች በጥቃቅን ደረጃ የሚላኩ ምርቶችን ጨምሮ ከ900 አይበልጡም፡፡ ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ገቢ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ የምንልከውም ምርት ቁጥር አነስተኛ ነው የሚባለው፡፡

ነገር ግን እንዲህ ያሉ የወጪና የገቢ ንግድ ምርቶች በሙሉ ገንዘብ እንዲዘዋወር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁሉ ኢኮኖሚ ውስጥ ይፈሳል፡፡ ሁልጊዜ በቁጠባና በኢንቨስትመንት መካከል ያለው ከፍተኛው ከአሥር በመቶ በላይ ነው፡፡ አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ከጂዲፒ 30 በመቶ ከሆነ የእኛ አጠቃላይ  ቁጠባ (አግሪጌት ሴቪንግ) ከጂዲፒው 20 በመቶ አካባቢ ነው፡፡ አጠቃላይ ኢንቨስትመንት ደግሞ ወደ 31 በመቶ አካባቢ ነው፡፡ 11 በመቶ ጂዲፒ አለ፡፡ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና ቁጠባ ክፍተቱ 11 በመቶ አካባቢ ሲሆን ይህም በጣም ትልቅ ነው፡፡ ይህም እኛ ከምናመርተው በላይ ዕድገትን ለማምጣት 11 በመቶ ያህል የጂዲፒውን ከውጭ እናመጣለን ማለት ነው፡፡ እዚህ ካመረትከው ምርት 80 በመቶ ያህሉን ስለምንበላ ለቁጠባ የምትውለው 20 በመቶ ነች፡፡ ይህች ለኢንቨስትመንት ትውላለች፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት ስድስትና ሰባት በመቶ ለማድረስ የጂዲፒውን 30 በመቶ ኢንቨስት እንድታደርግ ይፈለጋል፡፡ ይህንን ልዩነት የተለያዩ የጥሬ ዕቃዎችና ሌሎች ምርቶች ከውጭ ማምጣት የግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ኢምፖርቱ ከወደቀ ነው ዕድገት የለም ወይ የሚባለው፡፡

ስለዚህ ኢምፖርቱ ለዕድገቱ አንድ ነፀብራቅ ነው፡፡ ይህን ያህል ኢምፖርት ካደረግህ በኋላ የሚወጣው ብረትና የካፒታል ዕቃዎች ለኢኮኖሚ ዕድገት ነው የሚውሉት፡፡ የሚወጣው ጥሬ ዕቃ ሁሉ ለማኑፋክቸሪንግ ነው የሚውለው፡፡ ይህ ማለት ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከምግብ ግብዓት ውጪ ማለት ነው፡፡ በምግብ ረገድም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን 25 በመቶ ምግብ ከውጭ ነው የሚያስገባው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚችለው 75 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ለ25 በመቶ የምግብ ፍላጎት ማሟያ ደግሞ ሁልጊዜ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል፡፡ አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ያንሳል፡፡ ስለዚህ ይህንን ፍላጎቱን ለማሟላት ከውጭ ነው የምታወጣው፡፡ ይህ የምግብ ፍጆታችን ዕድገት ላይ አይታይም፡፡ ሌላው የሚገባው ሁሉ ከዕድገት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ባንኮችን በመንካት የሚሠራ በመሆኑ ባንኮች በብዙ ሁኔታ ትርፍ እያገኙ ይሄዳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ከባንኮች ህልውና ጋር የተያያዘ ከሆነ፣ ባንኮች እያተረፉ መሄዳቸው ኢኮኖሚው ዕድገት እየታየበት በመሆኑ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ተክለወልድ፡- ኢኮኖሚው ከወደቀ ከሁሉም በፊት የሚወድቀው ባንክ ነው፡፡ ምክንያቱም ባንክ ከወደቀ የሚቆጥብ ሰው የለም፡፡ የቆጠበውን ለመውሰድ ይሠለፋል እንጂ አይቆጥብም ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ የተበደረ ሰው መክፈል አይችልም፡፡ የሰጠኸው ብድር ሁሉ የተበላሸ ብድር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የትም አገር መጀመርያ ኢኮኖሚው በማንኛውም ምክንያት መውደቅ ከጀመረ ቀውስ የሚመጣው በባንኮች ላይ ነው፡፡ አንድ ባንክ መውደቅ ከጀመረ ሁሉንም ባንክ ያዳርሳል፡፡ ባንክ ከወደቀ ኢኮኖሚው ወደቀ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ባንኮችን የግል የመንግሥት ሳይባሉ መንግሥት በማዕከላዊ ወይም በብሔራዊ ባንክ በኩል የሚቆጣጠራቸው፡፡ ለዚህ ነው ባንኮች ለራስህ ስትል ጣፍጥ የሚባሉት፡፡ ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግና ለመሳሰሉት ለዕድገት ወሳኝ ለሆኑ ዘርፎች ብድር በመስጠት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲመጣ ካላደረጉ አስቀድመው የሚወድቁት እነሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ባንኮች የሚሠሩትና ብድር የሚሰጡት ለራሳቸውም ህልውና ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚው ቢወድቅ አስቀድመው የሚወድቁት እነሱ ናቸው፡፡ ባንኮች ለንግድና ለመሳሰሉት አብላጫውን ብድር ይሰጣሉ፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል ባንኮች 80 እና 90 በመቶ የሚሆነውን ትርፍ ለሚያስገኝላቸው የአጭር ጊዜ ብድር ላይ ያተኩራሉ፡፡ ከዚህ በቢሊዮን አተረፍን ይባላል፡፡ የራሳቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ሲሉ ግን ኢኮኖሚውን የበለጠ የሚያሳድግ ብድር ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኮቪድ፣ ጦርነትና የመሳሰሉት ችግሮች ውስጥም ሆና ኢኮኖሚው 6.6 በመቶ አድጓል መባሉ ትክክል አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህንን ምልከታ እርስዎ እንዴት ያዩታል? ቀውስ በሚታይበትና ችግር በበረታበት ወቅት ይህንን ያህል ዕድገት እንዴት ተገኘ የሚለው ብዙዎችን ሲያነጋግር ይሰማል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ ተክለወልድ፡- ዋናው ነገር ጦርነቱ አይደለም፡፡ የበለጠ ችግር የሚሆነው በመሀል የአገሪቱ አካባቢ የታዩት ችግሮች ከቀጠሉ ነው፡፡ ጦርነቱ ዳር ላይ ያለ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን አንተ የምትለው ነገር ሊመጣ የሚችለው አገሪቱ ሙሉ ጦርነት ላይ ነች የሚል ዕሳቤ ከመጣ ነው፡፡ ነገር ግን በሁሉም አቅጣጫ ሥራው ቀጥሏል፡፡ ሰሜን ሸዋ እስኪደርሱ ድረስ እኮ ደሴ ላይ ሳይቀር ሥራ ነበር፡፡ ወልድያ ተይዞ ደሴ ላይ የሞቀ ሥራ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሜን ሸዋ ተይዞ ጎጃም ላይ እኮ ሥራው ይሠራ ነበር፡፡ ስለዚህ ጦርነቱ አጠቃላይ ኢትዮጵያን ይዞ ያካለለና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የገታ አይደለም፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ ገንዘብ በልቷል፡፡ የውጭ ምንዛሪ በልቷል፣ የመንግሥትን በጀት በልቷል፣ ሰው ተጎድቷል፡፡ ከሥራ የቆመ አካል ግን አልነበረም፡፡ ለዚህ ነው ባንኮቹ ካቻምናም፣ አምናም፣ ዘንድሮም የሰበሰቡት ቁጠባ የማይገመት ሆኖ የተገኘው፡፡ አሁንም እኮ ችግር ውስጥ እያለን ነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ በዚህ ዓመት ከ155 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ቁጠባ ገንዘብ የሰበሰብነው፡፡ ከሰጠው ብድር ውስጥ ደግሞ ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቧል፡፡ በድምሩ ወደ 280 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል ማለት ነው፡፡ ዓምና ጦርነቱ እያለም 110 ቢሊዮን ብር አካባቢ ቁጠባ ሰብስቧል፡፡ ወደ 80 ቢሊዮን ብር የሚሆን ብድር ሰብስቧል፡፡ ጦርነት ግን ነበር፡፡ ይኼ የሚያሳየን ጦርነቱ በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ላይ ያስከተለው ጉዳት አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ ጉዳት ግን አላስከተለም ማለት አይደለም፡፡ ከሰዎች ጉዳት ባሻገር ያስከተላቸው ቀውሶች አሉ፡፡ በዋናነት ደግሞ የመንግሥትን በጀት ጎድቷል፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ከአጠቃላይ አገራዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አንፃር ተፅዕኖው የጎላ አይደለም የሚባልበት ሌላው ምክንያት፣ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ አነስተኛ መሆን ነው፡፡

የሰሜኑ የአገራችን ጫፍ ለግብርና ያለው አስተዋጽኦ ሁለት በመቶ አይደርስም፡፡ በአጠቃላይ ለአገሪቱ ጂዲፒ ክልሉ ያለው አስተዋጽኦ ወደ 4.5 አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውንም ነገር ስታስብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በሚያመዝንበት አካባቢ ሥራው እየተሠራ ስለነበር የኢኮኖሚ ዕድገቱ እንዲታይ አድርጓል፡፡ ስለዚህ የሰሜኑ አካባቢ አገራዊ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ተለጥጦ ሰባት በመቶ ነው እንኳን ቢባል 93 በመቶው አልተነካም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት እጅግ ብልጫ ባለው ክፍል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስላለ የታሰበውን ያህል ባይሆንም የኢኮኖሚ ዕድገቱ እንዲታይ አድርጓል፡፡ ዋናው ነገር ኢኮኖሚው እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው መገለጫ ባንኮቹ ቁጠባ እየሰበሰቡ ነው፡፡ የሰጡትን ብድር እያስመለሱ ነው፡፡ ብድር እየሰጡ ነው፡፡ ትርፍ እያገኙ ነው፡፡ ይህ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ትልቅ አመላካች ነው፡፡ በኮቪድ ሥራ አልቆመም፡፡ ገበሬው ሥራ አልተወም፡፡ መርካቶ ሥራ አልቆመም፡፡ በኮቪድም ቢሆን ጉዳቱ ኢምንት ነው፡፡ እኛ ሞቅ እናደርጋለን እንጂ እንደ ሌላው አገር አልተጎዳንበትም፡፡ እርግጥ ነው ጦርነቱ ብዙ ነገር በልቷል፣ ሥነ ልቦና ላይም የፈጠረው ነገር አለ፡፡ ዘጠኝ በመቶ እናድጋለን ተብሎ ወደ 6.6 በመቶ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ እንዲህ ያለው ውጤት አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ወጣ እንበልና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር ነቀል ሪፎርም ለማድረግ በመወሰን ሰፊ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይም ባንኩን የበለጠ ለማዘመንና ከፍ ለማድረግ የተጀመረው ሪፎርም ምን ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ተክለወልድ፡- ሪፎርሙ በሁለት መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡ አንዱ ባንኩን ከነበረበት አደጋ ማዳን ነው፡፡ ሊወድቅ ጫፍ ላይ ነበር፡፡ ይህ እንዳይሆን በቦርዱና በማኔጅመንቱ ርብርብ እንዲገታ አድርገናል፡፡ የመጀመርያው ዕርምጃችን ባንኩ ወደ ነበረበት መስመር ገብቶ ሥራውን እንዲቀጥል ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እኛ ዕርምጃ በወሰድንበት ጊዜ አሥርና አሥራ አምስት በመቶ ተቀማጭ ያለው አካል ገንዘቡን እወስዳለሁ ቢል እንኳን ባንኩ ገንዘብ አልነበረውም፡፡ ብዙ ካሽ አልነበረውም፡፡ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ገንዘብ ለመስጠትም አቅም አልነበረውም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትና ኤክስፖርተሮችንም ለማበረታታት፣ እንዲሁም ብድር ለመስጠት አቅም አልነበረም፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም የወሰዱትን ብድር ሊመልሱ ስላልቻሉ ባንኩ የገንዘብ ችግር ነበረበት፡፡ በጥቅሉ ሲታይ እኛ በተረከብንበት አካባቢ ባንኩ ጫፍ ላይ ነበር፡፡ ስለዚህ ከገባበት ችግር ለማውጣት የመጀመርያው ሥራ ባንኩን ወደነበረበት አሠራር መመለስ ነው፡፡ የመጀመርያው ዙር ሪፎርማችንም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ማድረግ ችለናል፡፡ ይህን ማስተካከያ ካደረገና የተገኘውን ውጤት ይዘን ነው ወደ ዋናው የሪፎርም ሥራ የገባነው፡፡ የውጭ ባንኮች ቢመጡም ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲጠብቅ፣ ከዚያም ባሻገር ወደ ውጭ ሄዶ እንዲሠራ ጭምር የሚያስችል ትራንስፎርም የሚያደርግ ጥናት አስጠናን፡፡ ከዚያ በኋላ ዓለም አቀፉን አሠራር መሠረት በማድረግ ያስጠናነውን ጥናት ባለፈው ታኅሳስ በሙሉ ተረክበን በጥናቱ ላይ በመንግሥት ደረጃ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተደረገ፡፡ የቀረበውን ጥናት ለአምስት ዓመት እንዲያገለግል ተደርጎ ወደ ዝርዝር ዕቅድ ቀይረናል፡፡ በሁለት ዓመት የምናደርስበትን የሚያሳይ፣ በአምስት ዓመትስ ባንኩ የት ይደርሳል የሚለው ሁሉ ተቀምጧል፡፡ በሀብቱ፣ በተቀማጭ ገንዘብ መጠኑና በሁሉም ዘርፍ  የሚደርስበትን በአጠቃላይ በሦስት ዓመት የት እንደርሳለን የሚለው በሙሉ ዶክመንት ተደርጓል፡፡ ዝርዝር ዕቅዱና ግቡ በመንግሥት ፀድቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ሪፎርም ባንኩን ምን ያህል ይለጥጠዋል? ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱንስ እንዴት ማስኬድ ያስችለዋል? የሰው ኃይል በማፍራቱ ረገድስ ሪፎርሙ የሚያሳየው ነገር ምንድነው?

አቶ ተክለወልድ፡- በዚህ ሪፎርም መሠረት እየተተገበረ ያለው አዲስ አሠራርና ትግበራ በየዓመቱ ይቀጥላል፡፡ ይህም ከየትኛውም ዓለም የውጭ ባንክ ቢመጣ ብቁ ተወዳዳሪ ያደርገዋል፡፡ አሁን እየተሠራ ያለውም ይህ ነው፡፡ ባስቀመጥነው ዕቅድ መሠረት እየሠራን ወደ ምንፈልገው ግብ ከደረስን፣ መንግሥት ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እጁን እንዲያወጣና ለመንግሥት ኢንተርፕራይዝ ብድር መቆም አለበት የሚለውም ፕሮፖዛል ቀርቧል፡፡ ንፁህ የባንክ ቢዝነስ እንዲሠራና ተተኪዎችን ማፍራት ነው፡፡ አሁን የምናስበው ከመቶ በላይ አቶ አቤን [ፕሬዚዳንቱን] የሚተኩ ሰዎች መኖር አለባቸው በማለት ነው በዕቅድ ያስቀመጥነው፡፡ ከ400 በላይ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ማፍራት አለብን ብለን እየሠራን ነው፡፡ እንዲህ እያልን ወደ ታች ጭምር ነው የምንሄደው፡፡ እከሌ ከሄደ ባንኩ እንዲህ ይሆናል የሚባል ነገር የለም፡፡ ዘንድሮ አንዱ ፕሬዚዳንት ሲመጣ የእሱን ሰዎች የሚሰበስብበት ሌላውም ሲመጣ እንደዚያ የሚያደርግ ሁኔታ የለም፡፡

አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ የሚባል ነገር የለም፡፡ በዚህ ባንክ ውስጥ ከአሥር ሺሕ በላይ ማስተርስ ዲግሪ ያላቸው አሉ፡፡ ከ20 ሺሕ በላይ ባለዲግሪዎች አሉ፡፡ አሁን ደግሞ በየዓመቱ ስድስትና ሰባት ሺሕ እየቀጠርን እንሄዳለን ብለን አቅደናል፡፡ ስለዚህ በውስጥ ያለውን በየደረጃው በማሠልጠን ተተኪ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ አዲስ የሚገባውንም እያመቻቸን በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሰው ኃይል፣ በዲጂታል ባንኪንግ፣ በሌላውም የዘመነ ባንክ እናደርገዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሪፎርሙ የባንኩን ካፒታልም ማሳደግ የሚያጠቃልል እንደሆነ ይታወቃልና በዚህ ዕቅድ የባንኩን ካፒታል ምን ያህል ለማድረስ ታስቧል? አሁንስ ምን ያህል ካፒታል አለው?

አቶ ተክለወልድ፡- አሁን ወደ 59 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነው፡፡ በአራት ዓመት ውስጥ ተጨማሪ ወደ 100 ቢሊዮን ብር ለማከል ነው በጥናታችን ያስቀመጥነው፡፡ መንግሥት በአራት ዓመት ውስጥ በየዓመቱ 25 ቢሊዮን ብር እየጨመረ በመሄድ ካፒታሉን ወደ 150 እና 160 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ነው፡፡ ይኼ ለመንግሥት የቀረበ ስለሆነ አዎንታዊ ምላሽ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ በመንግሥት ካልተቻለ ባንኩ የሚያተርፈውን ካፒታል ለማሳደግ እንዲውል የሚቻልበት አሠራር ይተገበራል ተብሎ ታስቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ባንኮችን ይገባሉ ተብሏልና ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዝግጅት ምን ይመስላል? ሌሎች የአገራችን ባንኮችስ ምን ዓይነት ዝግጅት ማድረግ አለባቸው?

አቶ ተክለወልድ፡- የውጭ ባንክ እዚህ መጣም አልመጣም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ወጥቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራ ተቋም ይሆናል፡፡ ከአራትና ከአምስት ዓመታት በኋላ ኬንያ ገብተን እንወዳደራለን፡፡ ሱዳን ገብተን እንሠራለን፡፡ አሁን በደቡብ ሱዳንና በጂቡቲ እየሞከርን ነው፡፡ ከዚያ ልምድ ወስደን ወደ ሱዳንም ገብተን ነበር፡፡ ሱዳን ብጥብጥ ስለተነሳ እንጂ እዚያም ተወዳዳሪ ባንክ ሆነን እንገባ ነበር፡፡ ስለዚህ ውጪ ወጥተን ተወዳዳሪ ሆነን ለመሥራት ቁርጠኛ ሆነን እየሠራን ነው፡፡ እዚህ ከመጡም እነሱ ሊሠሩ የሚችሉትን ሥራ አስቀድመን በመሥራት ተወዳዳሪ ለመሆን ዝግጁ ነን፡፡ ካፒታሉን እናሳድጋለን፡፡ አሁን ያለን ካፒታል ወደ ዶላር ሲቀየር ትንሽ ስለሆነ ይህን ማሳደግ አለብን፡፡ ለዚህም ዝግጁ ነን፡፡ ሌሎች ባንኮችን በተመለከተ የእኔ ምልከታ የኢትዮጵያ ባንኮች በየዓመቱ ይህንን ያህል ትርፍ እያገኘን ነው ብለው ከሚከፋፈሉ ካፒታል ማሳደግ ላይ በሚገባ መሥራት አለባቸው፡፡ ዕውቀት ላይ መሥራት አለባቸው፡፡ በዋናነት ግን የብሔረሰብ፣ የሃይማኖት የሚለውን ነገራቸውን ትተው አራት አምስቱ ተሰባስበው አንድ ባንክ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ይህንን ማድረጋቸው ለካፒታል ዕድገት ብቻ አይደለም፡፡ ይብዛም ይነስም ሁሉም ዘንድ ልምድ ያለው ሰው አለ፡፡ ይኼ ተሰባስቦ ቢሠራ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...