አዋሽ ባንክ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ለተለያዩ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት 5.5 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።
ባንኩ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት (ለአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት) ለማበደር ካቀደው በጀት ውስጥ 1.5 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ብድር ተጠቃሚ ከሚሆኑ ዘጠኝ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፈራርሟል፡፡
ባንኩ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ለማክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ ለመስጠት ያቀደውን ብድር በተለዋዋጭ ውሎችና ሁኔታዎች፣ ማለትም በዝቅተኛ የወለድ ተመኖች፣ ጥብቅ ባልሆነ የመልሶ ክፍያ ውልና ተለዋዋጭ የዋስትና አማራጮችን፣ ማለትም እንደ ንፁህ ብድር (መያዣ የሌለው) በመጠቀም እንደሚያቀርብ ገልጿል።
ይህ ባንኩ በኢትዮጵያ ውስጥ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችንና ጥቃቅንና አነስተኛ ንግዶችን ለማገልገል የያዘው ዕቅድ አካል ሲሆን፣ ይህም ከ110,000 በላይ ጥቃቅንና አነስተኛ ንግዶችን ተጠቃሚ የሚያደርግና በዚህም ለ220,000 የሚጠጉ የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ስምምንቱን በማስመልከት የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው እንደገለጹት እነዚህ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ያላቸውን የመያዣ ችግር ከግምት በማስገባትና ብድሩን ለጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት በተመጣጣኝ ወለድ ለማቅረብ እንዲያስችላቸው በማሰብ የተመቻቸ ነው፡፡
ከአዋሽ ባንክ ይህንን ብድር ለማግኘት ስምምነት የፈጸሙት ዘጠኙ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቪዥን ፈንድ ማክሮ ፋይናንስ፣ ንስር ማክሮ ፋይናንስ፣ ቀንዲል ማክሮ ፋይናንስ፣ ተማመን ማክሮ ፋይናንስ፣ መክሊት ማክሮ ፋይናንስ፣ ዋሳስ ማክሮ ፋይናንስ፣ ሐርቡ ማክሮ ፋይናንስና ፒስ ማክሮ ፋይናንስ ናቸው፡፡
ባንኩ የተጠቀሰውን ብድር ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ ለማቅረብ እንዲችል መቀመጫውን ካናዳ ያደረገው ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ አድርጎለታል።
በዚህም መሠረት ባንኩ ለዘጠኙ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚያቀርበው 1.5 ቢሊዮን ብር ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የወጣቶች ሥራ ፈጠራን ለማበረታታት በቀየሰው ፕሮጀክት አማካኝነት የተመቻቸ ሲሆን፣ አፈጻጸሙን ደግሞ አገር በቀል አማካሪ ድርጅት የሆነው ‹‹ፈርስት ኮንሰልት›› እንደሚያስተባብር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የተገኘው መረጃ ያመልከታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ ‹‹ታታሪዎቹ›› የተሰኘ የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ውድድር በቅርቡ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህ ውድድር አሸናፊ ለሚሆኑ ተወዳዳሪዎች የገንዘብና ከዋስትና ነፃ የብድር አገልግሎት ለመስጠት ባሰናዳው ውድድር እስካሁን ከ8,000 በላይ ተወዳዳሪዎች ማመልከታቸውን ባንኩ አስታውቋል፡፡