የባንኩ 112 ቅርንጫፎች አሁንም ከአገልግሎት ውጪ ናቸው
ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ የትርፍ ምጣኔው ቀንሶ የነበረው ወጋገን ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከነበረበት ዝቅተኛ አፈጻጸም ወጥቶ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን ገለጸ፡፡
ወጋገን ባንክ ይህንን ውጤት ያስመዘገበው የባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ባለአክሲዮኖች ማኔጅመንትና ሠራተኞች ባንኩን ወደ ትርፋማነት ለመመለስ ባከናወኑት የተቀናጀ ጥረትና ርብርብ መሆኑን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ውበት አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና ባለአክሲዮኖች በየጊዜው እየተገናኙ በቅርበት በመሥራት የባንኩን እውነተኛ ገጽታ ደንበኞችና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ እንዲገነዘቡት ማድረጋቸው ለውጤቱ መሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፡፡ ቀደም ሲል ባንኩ ላይ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመርኩዞ የደረሰበት የስም ማጥፋት ወደ ቀደመ መልካም ስሙ እንዲመለስ እንዲሁም ደንበኞች ያላቸው መተማመን ተመልሶ ከባንኩ ጋር እንዲሠሩ በማስቻሉ ባንኩ የተሻለ አፈጻጸም እንዲያስመዘግብ አስተዋጽኦ ማድረጉንም የባንኩ በተጠናቀቀው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት ወጋገን ባንክ ያስመዘገበው ትርፍ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በትግራይ ክልል አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት 112 ቅርንጫፎቹ አሁንም ድረስ ተዘግተው ባሉበት ሁኔታ የተገኘ መሆኑንም ባንኩ ጠቁሟል። ባንኩ ይህንን ውጤት ያመጣው በቀሪዎቹ 288 ቅርንጫፎቹ ብቻ አገልግሎት እየሰጠ ከመሆኑ አንፃር ትልቅ እመርታ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት አትርፎ የነበረው 193 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ወደ 43.6 ቢሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ ዓመና በተመሳሳይ ወቅት 40 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 3.4 ቢሊዮን ብድር የደረሰ ሲሆን፣ የተፈረመ ካፒታልን ጨምሮ አጠቃላይ የባንኩ ካፒታል ደግሞ 6.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ባንኩ የሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብም በ2013 የሒሳብ ዓመት ከተገኘው 31.5 ቢሊዮን ብር ወደ 33.9 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ባለፈው የሒሳብ ዓመት 27.4 ቢሊዮን ብር የነበረው ለተለያዩ ዘርፎች የሰጠው ብድር በ2014 መጨረሻ ላይ 30.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመልክቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ወጋገን ባንክ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት መጋቢት ወር ላይ ተግባራዊ ካደረገው አዲስ የደመወዝ ስኬል በተጨማሪ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለሠራተኞቹ ከአንድ እስከ አራት ዕርከን የደመወዝ ጭማሪ ያደረገ ሲሆን የአንድ ወር የማትጊያ ክፍያ መስጠቱንም ገልጿል፡፡
ወጋገን ባንክ ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም. በ16 ባለአክሲዮኖች 60 ሚሊዮን ብር የተፈረመ መነሻ ካፒታልና 30 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ ባንክ በመላው አገሪቱ 400 ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በአሁኑ ወቅት የባለ አክሲዮኖቹ ቁጥር 5,888 የደረሰ ደርሷል፡፡ ከ5,000 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ ወጋገን ባንክ ባለፈው ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት በደመቀ ሁኔታ ማክበሩ ይታወሳል፡፡