Saturday, December 2, 2023

የአልሸባብ ጥቃትና የኢትዮጵያ ምላሽ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓምና በጥር ወር አጋማሽ በባሌ ዞን ደሎመና ወረዳ ቀርሳ በሚባል አካባቢ ‹‹ኢስላማዊ መንግሥት››፣ ‹‹ኢስላሚክ ስቴት ሴንተር›› ብሎ ራሱን የሚጠራ ቡድን ለሽብር ሲደራጅ ተደረሰበት የሚል ዜና በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መነገሩ ይታወሳል፡፡ የተያዙት የቡድኑ አባላትም በዚህ ዜና ከአይኤስና ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሲነገር ተደምጧል፡፡ በሎጂስቲክስና በሥልጠና ራሱን ሲያደራጅ የነበረው ቡድኑ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት እንዳለው፣ የአካባቢው የፀጥታ ባለሥልጣናት ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል፡፡ የውጭ ዜጎች ጭምር የዚህ ቡድን ደጋፊና አባል ሆነው መያዛቸውንም ነው የፀጥታ ባለሥልጣናቱ ያስታወቁት፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ ለባሌ ዞን አዋሳኝ በሆነው የሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ኤልከሬ ወረዳ፣ የሶማሊያው አሸባሪ ቡድን አልሸባብ ጥቃት ለማድረስ ሞከረ የሚል ዜና ተሰምቷል፡፡ የሶማሌ ክልል ፀጥታ ኃይሎች ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በቅንጅት በከፈቱት ዘመቻ፣ የአልሸባብ ህዋስ መደምሰሱ ቢነገርም፣ ቡድኑ የሶማሊያን ድንበር አልፎ የሶማሌ ክልልን ተሻግሮ ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመዝለቅ ተደጋጋሚ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተገምቷል፡፡

የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ መሐመድ ኡመር ሐሙስ ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የቡድኑን የጥቃት ዓላማ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አልሸባብ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ አለባቸው ተብሎ የሚገመቱ የሶማሌ ክልል አካባቢዎችን ከመቆጣጠር ባለፈ፣ በአፍዴር ዞን በኩል ወደ መሀል አገር የመግባት ፍላጎት ነበረው፡፡ ሆኖም በመከላከያና በፀጥታ ኃይላችን ጥረት ሙከራው በአጭሩ ተቀጭቷል፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

አልሸባብ በሰሞኑ የጥቃት ሙከራውና በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ ድንበር ህዋሱን ለመዘርጋት ባደረገው ጥረት፣ ድንበር ተሻጋሪ አደጋ መሆኑን እያሳየ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሶማሊያ ተሻግሮ በኬንያና በኡጋንዳ ጭምር ጥቃት ቢያደርስም ወደ ኢትዮጵያ ግን ብዙም ድፍረቱን ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ አሁን ወደ ኢትዮጵያ ለመዝለቅ ያደረገው ጥረት ባይሰምር እንኳ፣ ቡድኑ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ለማሳየት መቻሉን ብዙዎች ይገምታሉ፡፡ አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ፍላጎቱና አቅሙን ያገኘው ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ለሽብር ቡድን መደራጀት አመቺ አጋጣሚ አለ ብሎ በማመኑ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

መቀመጫውን በጂግጅጋ ያደረገው ጋዜጠኛ አህመድ አብዲ፣ አልሸባብ ድንበር ተሻግሮ በኢትዮጵያ ጥቃት ለመሰንዘር መዘጋጀት ከጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነው ይናገራል፡፡ ‹‹ከዓምና ግንቦት ወር ጀምሮ የአልሸባብ ታጣቂዎች ከእነ መሣሪያቸው እንደተያዙ ሲነገር ቆይቷል፡፡ የአልሸባብ ኃይል ድንበር ዘልቆ የመለመላቸው ታጣቂዎችና ቆፍሮ የቀበራቸው መሣሪያዎች መያዛቸውን የሶማሌ ክልል ይፋ አድርጎ ነበር፤›› ሲል ጋዜጠኛው ያብራራል፡፡

Ethiopian Forces (Ethiopia Politics News)

የፀጥታ ባለሙያው አቶ ሐሰን አደን ግን አልሸባብ የዘረጋው የሽብር መረብ መበጣጠሱን ነው የሚናገረው፡፡ ‹‹በቅርቡ ከመቶ በላይ የአልሸባብ ህዋስ አባላትና ደጋፊዎቻቸውን ከተደበቀ የጦር መሣሪያቸው ጋር በቁጥጥር ሥር አውለናል፤›› ሲልም ይናገራል፡፡ አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ ለመግባት ለረዥም ጊዜ ሲዘጋጅ እንደነበር የሚጠቅሰው ሐሰን፣ እንቅስቃሴው ቀድሞ ስለተደረሰበት አደጋው መክሸፉን ያስረዳል፡፡

ሁለቱ አስተያየት ሰጪዎች አልሸባብ ወደ ደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል ለመሻገር ዕቅድ እንዳለው ይስማማሉ፡፡ ቡድኑ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሰፊው ከሚንቀሳቀሰው ከኦነግ ሸኔ ኃይል ጋር ቅንጅት ለመፍጠር መፈለጉንም ነው የሚናገሩት፡፡

ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በሶማሊያ በኮል ግዛት በኩል በ15 ተሽከርካሪዎች ተጭኖ የመጣ ከ250 በላይ የሚገመት የአልሸባብ ኃይል በኢትዮጵያ ሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኙት የድና አቶ የሚባሉ መንደሮች ላይ ጥቃት አደረሰ፡፡ የሽብር ቡድኑ አባላት ሁለቱን መንደሮች ማውደም ሳይሆን፣ ድንበር ተሻግረው በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ የመንቀሳቀሻ ቀጣና ለመፍጠር ነበር ፍላጎታቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከሶማሌ ክልል የልዩ ኃይል በኩል ጠንካራ ምት ስለገጠማቸው ዓላማቸው መሰናከሉ ተነግሯል፡፡

ጋዜጠኛ አህመድ፣ ‹‹በየድና አቶ በኩል የመጣ የአልሸባብ ኃይል ከ500 በላይ ነበር፡፡ ኃይሉ ጠንካራ ውጊያ ቢያደርግም ነገር ግን ብዙው ተደምስሷል፡፡ ከታንዛኒያና ከሌሎች አገሮች የመጡ ታጣቂዎች በጥቃቱ ተሠልፈዋል ቢባልም እኔ ይህን ማረጋገጥ አልቻልኩም፤›› በማለት ነው ስለዚህ የጥቃት ሙከራ ያስረዳው፡፡

የፀጥታ ባለሙያው አቶ ሐሰን ግን የውጭ ዜጎች የሉበትም የሚለውን ሐሳብ አይስማማበትም፡፡ በቀናት ልዩነት በአፍዴር ዞን ኤልከሬ አካባቢ ከ200 በላይ የአልሸባብ አባላት ጥቃት መሞከራቸውንና ብዙዎቹ ተደምስሰው ስድስቱ መማረካቸውን አስታውሶ፣ በአጠቃላይ በዘመቻዎቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የጥቂቶቹን ቃል መቀበሉን ይናገራል፡፡ ‹‹የታንዛኒያ ሰው ከመሀላቸው አግኝቻለሁ፡፡ ብዙዎቹ በኦሮሚኛ ተናጋሪ ሲሆኑ ሶማሌዎችም አሉበት፤›› በማለት ነው የአሸባሪዎቹን ማንነት ያመለከተው፡፡

የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት ከሰሞኑ በሁለት አቅጣጫ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሞከረ ከ500 የማያንስ የአልሸባብ ኃይል መደምሰሱን ተናግረዋል፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት የክልሉ ልዩ ኃይል በወሰደው ዕርምጃ የአልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ምኞት በአጭሩ መቋጨቱንም ገልጸዋል፡፡ አልሸባብ ኢትዮጵያን መድፈሩ ዋጋ የሚያስከፍል ጥፋት መሆኑን በሚገባው ቋንቋ አስተምረነዋል ሲሉም የክልሉ ባለሥልጣናት ይደመጣሉ፡፡

የአሜሪካ ድምፅ እንግሊዝኛ በሁልሁል በኩል በ13 ተሽከርካሪዎች ተጭኖ የመጣ የአልሸባብ ኃይል በሦስት ቀናት ዘመቻ በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መደምሰሱን ዘግቦታል፡፡ አልሸባብ ለምን በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት መክፈት ፈለገ (Why Did Al-Shabab Attack inside Ethiopia) የሚል በሌላ የቪኦኤ እንግሊዝኛ ዘገባ ደግሞ፣ የቀድሞ የቡድኑ አባል የኦማር መሐመድ አቡ አያንን ምላሽ አስነብቧል፡፡

ነዋሪነቱን በስዊድን ያደረገው ይህ የቀድሞ የአልሸባብ መሪ፣ ‹‹በኢትዮጵያ መሬት ላይ አልሸባብ ባንዲራውን መትከሉና እንደሚንቀሳቀስ ማሳየቱ ለቡድኑ ትልቅ የፕሮፓጋንዳ ስኬት ነው፤›› በማለት መናገሩንም ቪኦኤ አስነብቧል፡፡ አልሸባብ ከአፈጣጠሩና ከባህሪው በመነሳት መናገር እንደሚቻለው ከሆነ ግን ቡድኑ ሶማሊያም፣ ኬንያም ሆነ ኢትዮጵያ በረገጠበት ሁሉ ደም መፋሰስ፣ ግጭትና ውድመት የሚያስረዳ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህን በመረዳት ይመስላል ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት መሞከሩ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አለመሆኑን ሲገልጹ የተሰሙት፡፡ የአሜሪካ የአፍሪካ ኮማንድ ተሰናባች አዛዥ ስቴፈን ታውንሰንድን (ጄኔራል) ዋቢ በማድረግ ቪኦኤ እንግሊዝኛ ባወጣው ሌላ ዘገባ፣ የአልሸባብ ሰሞነኛ የጥቃት ሙከራ በቀላሉ የሚታይ  አለመሆኑን ያትታል፡፡ ‹‹የአልቃይዳ ክንፍ ነኝ የሚለው የአልሸባብ ሰሞነኛ ጥቃት እንደ ቀላል አይታይም፤›› ሲሉ የተናገሩት ጄኔራሉ፣ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱ መምከኑን መግለጻቸው በዘገባው ተወስቷል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ በሰጡት መግለጫ ጉዳዩ ቀሎ መታየት እንደሌለበት ነው ያሰመሩበት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የማንም አሸባሪና ወንጀል ቡድን መፈንጫ አትሆንም፤›› ሲሉ የገለጹት ሙስጠፌ፣ ክልሉ ከሶማሊያ ጋር በሚዋሰነው ሰፊ ድንበር ጥብቅ ጥበቃ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

የዓለም ሽብር ሪፖርት (Global Terrorism Report 2022) እንደሚያትተው፣ የአልሸባብ ሽብር ጥቃት ቢቀንስ እንጂ አሁንም ድረስ አልተገታም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 አልሸባብ የ571 ሰዎችን ሕይወት የነጠቀ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ የቡድኑ የሽብር ግድያ ከ2020 ጋር ሲነፃፀር 17 በመቶ መቀነሱ ቢመለከትም፣ በሶማሊያና በኬንያ ዋና የደኅንነት ሥጋት ሆኖ መዝለቁ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

ከአልሸባብ ሰለባዎች ውስጥ 93 በመቶ ሶማሊያውያን ሲሆኑ፣ ስድስት በመቶ ደግሞ ኬንያዊያን ናቸው፡፡ የሽብር ቡድኑ በ2020 ብቻ ወደ 303 የሽብር ጥቃቶች ያደረሰ ሲሆን፣ በ2021 ግን ይህ ቀንሶ 56 ጥቃት ነው ያደረሰው፡፡ ይህ ጉልህ የመጠን ቅናሽ ግን ቡድኑ በሚገድላቸው ሰዎች አኃዝ ላይ 17 በመቶ ቅናሽ ብቻ ነው ያመለከተው፡፡ ከዚህ በመነሳት አልሸባብ ጥቃቱን ቢቀንስም ውጤታማ ገዳይነቱን ግን አልቀነሰም ማለት ይቻላል፡፡

ከ7,000 እስከ 9,000 ታጣቂዎች አሉት ተብሎ በዓለም የሽብር መዝገብ ላይ ስሙ የሰፈረው አልሸባብ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ዋናው የደም መፋሰስና የሞት ምንጭ ቡድን መሆኑ ተቀምጧል፡፡ አልሸባብ ለቀጣናው ብቻም ሳይሆን ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ዋና ሥጋት ከሚባሉ ሽብር ቡድኖች አንዱ መሆኑን ነው የተለያዩ ሪፖርቶችና ተንታኞች የሚያስረዱት፡፡

በካውንስል ኦን ፎሬይን ሪሌሽንስ (CFR) ገጽ ላይ የኋላ ታሪኩ እንደተዘገበው ከሆነ፣ አልሸባብ የአል ኢትሃድ የአል ኢስላሚያና የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ውጤት መሆኑ ተከትቧል፡፡ አልሸባብ ወይም ወጣቶቹ ተብሎ የተመሠረተው ከአልኢትሃድና ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት በወጡ ሰዎች የሚመራው የሽብር ቡድኑ እ.ኤ.አ. ከ2004 ዓመት ጀምሮ መጠንሰሱን፣ እስላማዊ መንግሥትን በሶማሊያ መፍጠር ዋና ግቡ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ቡድን መሆኑን ታሪኩ ያስረዳል፡፡ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶችን ማሰባሰብ የቻለው ቡድኑ፣ በአክራሪ የሃይማኖት ርዕዮተ ዓለም እያጠመቀ በሶማሊያና በዙሪያዋ ባሉ አገሮች ጥቃትና ደም መፋሰሶችን ሲፈጥር መቆየቱን ይኼው ዘገባ ያትታል፡፡

ይህን የሽብር ቡድን ለመደምሰስ በርካታ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ እስካሁንም ጠንካራ መንግሥት መፍጠር የተሳናት ሶማሊያን በመደገፍ የአፍሪካ ኅብረት ጦር አዝምቷል፡፡ ከኅብረቱ የአሚሶም ጦር ጎን ደግሞ ኢትዮጵያ በተናጠል ጦር በማዝመት ጭምር፣ የሶማሊያ ፀጥታን አስተማማኝ ለማድረግ ብዙ መልፋቷ ይታወቃል፡፡

አልሸባብን በሽብር መዝገቧ ለመጻፍ እ.ኤ.አ. እስከ ፌብሩዋሪ 2008 ስታመነታ የቆየችው አሜሪካ፣ ከአልቃይዳ ጋር በይፋ ትስስር መፍጠሩን የሚናገረውን አልሸባብ ለመዋጋት የኋላ ኋላ ብዙ ጥረት ማድረጓ ይነገራል፡፡ ‹‹ደናብ›› ተብለው የሚጠሩ ልዩ ወታደሮችን ለሶማሊያ በማሠልጠንና በማስታጠቅ ስትረዳ የቆየችው አሜሪካ፣ በአየር (ድሮን) ጥቃትም በርካታ የቡድኑ አመራሮችን በማደን በቀጥታ ተሳትፋለች፡፡ የትራምፕ አስተዳደር ይህን የአሜሪካ ተሳትፎ እንዲቆም በማዘዝ በሶማሊያ የሚገኘውን የአሜሪካ ጦር እንዲወጣ አዞ የነበረ ቢሆንም፣ ትራምፕን የተኩት ጆ ባይደን እንዲመለስ ማዘዛቸው ይነገራል፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ያልተደመሰሰው አልሸባብ ዛሬም የሶማሊያን ሩብ ያህል መሬት መቆጣጠሩ ነው የሚነገረው፡፡ በአንዳንድ የመረጃ ምንጮች እንደሚነገረው ቡድኑ 180 ሚሊዮን ዶላር በጀት በየዓመቱ ይመድባል፡፡ የሃይማኖት ፅንፈኛ ርዕዮተ ዓለሙን የሚደግፉ የውጭ ኃይሎች ከሚሰፍሩለት ዕርዳታ በተጨማሪ፣ አልሸባብ በግድም በውድም በሶማሊያ ግብር እንደሚሰበስብ ይታወቃል፡፡

የአልሸባብ ታጣቂ ቁጥር አሜሪካ ቡድኑን እንዲዋጉ ካሠለጠነቻቸው ልዩ ኃይሎች ጋር ሲነፃፀር ስድስት ለአንድ እንደሚደርስ ቢነገርም የአልሸባብ ኃይል ከአሚሶም፣ ከኢትዮጵያ፣ ከሶማሊያና ከሌሎች አገሮች ኃይል ቁጥር ጋር ተነፃፃሪ ኃይል አለው ለማለት ግን አይቻልም፡፡ በተነፃፃሪነት በሶማሊያ ካሉ የፀጥታ ኃይሎች ያነሰ ታጣቂ ያለው ይህ ኃይል ዛሬም ሶማሊያን ማሸበሩ፣ ድንበር ተሻግሮ የፀጥታ ሥጋት መሆኑ ብዙ ያነጋግራል፡፡

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ከአልሸባብ ጋር የሚደረገው ውጊያ ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹አይዲዮሎጂያዊ፣ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ›› መልክ ያለው ነው ብለውታል፡፡ ሼክ ሀሰን ለዚህ ይመስላል ወደ ሥልጣን ሲመጡ ‹‹በቀልና ግጭት ቆሞ ውይይት ያስፈልገናል›› በማለት አልሸባብን ጨምሮ ከሁሉም የፖለቲካ ኃይል ጋር ለመነጋገር ያላቸውን ዝግጁነት ይፋ ያደረጉት፡፡ የቴክኒክና የሙያ መምህሩ የቀድሞ የዩኒሴፍ ሠራተኛ፣ በሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር አባል መሆናቸውን ግለ ታሪካቸው ይናገራል፡፡

ሰውየው ለዘብተኛ አማኝ እንጂ ፅንፈኛ ሃይማኖተኛ ሆነው አያውቁም ይባላል፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች አባልና ደጋፊ ናቸው ቢባልም እንደ አልሸባብ ካሉ ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመመሥረት የሚታሙ እንዳልሆኑም ይነገራል፡፡ ሼክ ሀሰን በምርጫ ካሸነፏቸው ከቀድሞው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ ጋር ሲነፃፀር የላላ የደኅንነት ፖሊሲ እንደሚኖራቸው ተገምቷል፡፡ ይሁን እንጂ በቀደመ የፕሬዚዳንትነት ቆይታቸው ወቅት የግድያ ሙከራ ካደረገባቸው ከአልሸባብ ጋር ይሻረካሉ የሚል ግምት ብዙም የለም ቢባልም፣ ውሎ አድሮ ማየት ይሻላል የሚሉም አሉ፡፡

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲው የሕግ ምሁርና አክቲቪስት ሙክታር ኡስማን (ሙክታሮቪች ኡስማኖቫ) ግን፣ ‹‹የሰውየው በፎርማጆ እግር መተካት ነው አልሸባብን ያጠነከረውና ኢትዮጵያን እንዲያጠቃ ያደረገው፤›› በማለት ይናገራል፡፡

‹‹ፎርማጆ ከሙስጠፌና ከዓብይ ጋር ተናቦ ነበር የሚሠራው›› ሲል የሚናገረው ሙክታር፣ የሶማሊያ መሪዎች መቀያየር ብቻ ሳይሆን የእነ አሜሪካ ፖሊሲም መቀየር አሁን አልሸባብን ችግር እንዲፈጥር እንዳገዘው ይናገራል፡፡ ‹‹በሶማሊያ በኩል አልሸባብን በማስረግ ኢትዮጵያን የማስጨነቅ ፖሊሲ የኢትዮጵያ ጠላቶች ይከተላሉ፤›› በማለትም ያክላል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ኢትዮጵያ ቤቷን ካስተካከለች አልሸባብም ሆነ ሌላ የውጭ ኃይል አይደፍራትም፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቀውስ እኮ ለአልሸባብ ሲሳይ ነው፡፡ በሰሜን ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና በሁሉም አቅጣጫ የውጭ ጠላት አገሪቱን የሚፈትናት፣ ቤቷን ያፀዳችና ከሕዝቦቿ ጋር ሰላም መፍጠር የቻለች ኢትዮጵያን መፍጠር ባለመቻሉ ነው፤›› ሲሉም መረራ (ፕሮፌሰር) ያስረዳሉ፡፡

የአልሸባብ ጥቃት ከትናንት በስቲያ ዓርብ መቀጠሉ ተነግሯል፡፡ የሶማሌ ክልል ምንጮች ልዩ ኃይል መከላከያ ተቆርጦ የቀረ የአልሸባብ ኃይልን የመልቀም ሥራ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመከላከያ ሚኒስቴርም ይህን ያረጋገጠ ሲሆን የስምሪት ኃላፊና ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ተስፋዬ አያሌው (ሜጀር ጄኔራል) ተቆርጦ የቀረ የአልሸባብ ኃይልን የማፅዳት ዕርምጃ ተወስዷል የሚል መግለጫ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -