በጭምዶ አንጫላ (ዶ/ር)
የዳሰሳው ጥናት ዋና ዓላማ
የዳሰሳው ጥናት በዋናነት ያተኮረው የኢትዮጵያ ግብርና ልማት ዘርፍ ባለፉት ሦስት ዓመታት (2010 እስከ 2013) ከየት ወዴት እንደተጓዘና በዚህ የለውጥ ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች/ስኬቶች፣ ጥንካሬዎችና ድክመቶች በአጠቃላይ በአዲሱ የፖለቲካና የአመራር ለውጥ ወቅት የግብርናው ዘርፍ እንዴት እንደነበረና አሁን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ የተደረገ ጥናት ነው፡፡ ጥናቱ የፌዴራል ግብርናና ተጠሪ ተቋሟትን፣ እንዲሁም አምስት ብሔራዊ የክልል የግብርና ቢሮዎች (ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብና ሲዳማ) ለማካተት የታቀደ ቢሆንም፣ የትግራይ ክልል በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በጥናቱ ሳይካተት ቀርቷል፡፡ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ 300 የሚሆኑ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያዎች፣ ተማራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ግብርናን በተመለከቱ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችና ሪፖርቶችም ተዳሰዋል፡፡ እንዲሁም በክልል የግብርና ቢሮዎች እየተደረጉ ላይ እንቅስቃሴዎችና መሰናዶዎች፣ በመስክ ላይ የሚታዩ ነባራዊ ሁኔታዎችና የአንዳንድ የግል ዘርፉ አስተያየቶችንም ለማካተት ተሞክሯል፡፡
የዳሰሳ ጥናቱ በ22 ዋና ዋና ርዕሶችና በ51 ቁልፍ ተግባሮች የተከፈሉ ገላጭና ግልጽ የሆኑ መጠይቆችን በማዘጋጀት በጥናቱ ላይ ለሚሳተፉ የግብርና ባለሙያዎች የተላከ ሲሆን፣ ይህም በዋናነት ባለሙያዎች ነፃና ገለልተኛ ሆነው ስማቸውን ለመጻፍ ሳይገደዱ (Anonymous) ባለፉት ሦስት ዓመታት የግብርና ልማት ዘርፍ እንቅስቃሴን በተመለከተ የታዘቡትን፣ ያስተዋሉትንና በአጠቃላይ ያላቸውን ሙያዊ አስተያየቶቻቸውን ከለውጡ በፊትና ከለውጡ በኋላ ካሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማነፃፀር እንዲሰጡን ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ የተገኘውን መረጃ በማሰባሰብና ለመተንተን ቀላልና ገላጭ የሆኑ የስታቲስቲክስ ሥሌቶች፣ የትንተና የማነፃፀሪያ ዘዴዎችን ለመጠቀም ተሞክሯል፡፡
የጥናቱ ውስንነቶች
ይህ ጥናት ሦስት ዋና ዋና ውስንነቶች አሉት፡፡ አንደኛ ሁሉንም ክልሎች አያካትትም፡፡ ሁለተኛ እንዲሁም ዞኖችና ወረዳዎች አልተካተቱም፡፡ ሦስተኛ የኢንተርኔት ግንኙነት በመቆራረጡ የተነሳ መጠይቆችን መሙላት የጀመሩ 47 ባለሙያዎች መጠይቁን ሙሉ በሙሉ አጠናቀው በወቅቱ ለመላክ አልቻሉም፡፡
የጥናቱ አጠቃላይ ውጤት
በአጠቃላይ የዳሰሳው ጥናቱ ውጤት እንደሚያመላክተው ከሆነ ባለፉት ሦስት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ከአዝጋሚ ጉዞ (Evolution) ወደ ፈጣንና አስተማማኝ የዕድገት ጉዞ መሸጋገሩን (Transition to transformation) እና ለዚህም ወሳኝ የሆኑ የሪፎርም፣ የመዋቅርና ስትራቴጂካዊ የሆኑ ቁልፍ ተግባራት (Basic Reforms, Strategic and Foundation Works) ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ለአብነትም ቀደም ሲል በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ መሠረታዊ ችግሮችና ክፍተቶች (የአመራር፣ የአደረጃጀት፣ የአሠራር፣ የቴክኒክ፣ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ፣ የሕግ፣ የአቅም፣ የቅንጅትና የትስስር የመሳሳሉት) በሒደት እየተቀረፉ መምጣታቸውን ከዳሳሳው ጥናቱ የተገኘው ውጤት ያመላክታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፉት ሦስት ዓመታት በግብርናው ዘርፉ የተደረጉ ማሻሻዎችንና ከዚህ የተነሳ የመጡትን ለውጦች በተጨባጭ ለማወቅ ያስችል ዘንድ፣ ወደ 51 የሚሆኑና ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ቁልፍ ተግባራትና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ናቸው የተባሉት በጥንቃቄ ተለይተው እነዚህ ከለውጡ በኋላ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ በተደረገው የዳሳሳ ጥናት መሠረት 29 (57 በመቶ) የሚሆኑ ቁልፍ ተግባራትና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ከበፊቱ ሁኔታቸው ጋር ሲነፃፀሩ ከፍተኛ መሻሻል የታየባቸው 13 (25.5 በመቶ) ደግሞ በመጠኑ የተሻሻሉ፣ ዘጠኝ (17.6 በመቶ) ምንም መሻሻል ያላሳዩ፣ እንዲያውም ከበፊቱ ከነበራቸው ነባራዊ ሁኔታቸው የመቀነሰ አዝማሚያ ያሳዩ መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል፡፡
ለዚህ ተስፋ ሰጪ ጉዞና መሻሻሎች ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው ተብሎ መጠይቁን በሞሉት በአብዛኛው የግብርና ባለሙያዎች ከተጠቀሱት ውስጥ፣ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ተቋሙን ከፍ ወዳለ ተቋም ደረጃ ለማሸጋገር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የመንግሥትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩና መንግሥት ቃል እንደገባው የግብርናው ዘርፍ ለማሳደግ ከፍተኛ ዕገዛና የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን፣ በጥናቱ ላይ በተሳተፉ በአብዛኛው ባለሙያዎች እንደ ምክንያት ተጠቅሰዋል፡፡ ለማሳያነትም ከተጠቀሱት መንግሥት ግብርናን የሚመጥን መሪ ከመመደቡ የተነሳ በግብናው ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ንቅናቄና መነሳሳት (Mobilization and New Initiation) ተፈጥሯል፡፡ ይህ ደግም በግብርና ባለሙያዎችም ሆነ በአመራሩ ዘንድ ጥሩ ተስፋን ፈጥሯል፡፡ የዕይታ ለውጥም (Paradigm Shift) አምጥቷል፡፡ እንዲሁም መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ለግብርና ዘርፉ አንፃራዊ የሆነ በጀት መመደቡ፣ እስካሁን ለመጣውና ለወደፊትም ይመጣሉ ተብለው ለሚታሰቡ ለውጦች ትልቅ ምክንያት ነው ተብሎ በጥናቱ የተሳታፉ ባለሙያዎች ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ለምሳሌ የ2015 ዓ.ም. በጀት ብቻ እንኳን ብናይ ከጠቅላለው ለአገሪቱ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ከተመደበው 786.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል በጀት ውስጥ፣ ለግብርናው ዘርፍ 34 በመቶ የሚሆን በጀት ተመድቧል፡፡ ይህ ደግም ከለውጡ በፊት ከአሥር በመቶ ያልበለጠ በጀት ጋር ስነፃፀር ታሪካዊና በዓይነቱ የመጀመርያ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በፌዴራል ደረጃ የግብርናውን ዘርፍ የሚመሩ አስፈጻሚ አካላት ለመጀመርያ ጊዜ የትምህርት ደረጃን፣ ሙያንና ልምድን መሠረት ባደረገ መልኩ መመደቡና በዚህም የተነሳ በከፍተኛው አመራር ዘንድ አንፃራዊ የሆነ የአመለካከት ለውጥና ስትራቴጂካዊ ፕሮግራሞችን የማስፈጸም አቅም ማደጉ (Relative Paradigm Shift and Improved Implementation Capacity)፣ መንግሥት ከዚህ በፊት ከውጭ የሚገቡ የግብርና መገልገያ መሣሪያዎችና ማሽነሪዎች ላይ የጣለውን ከፍተኛ የቀረጥ ዕገዳ እንዲነሳ ማድረጉ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ለግብርና ሚኒስቴር ራሱን የቻለ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንዲቋቋምለት ማድረጉ፣ አንዲሁም መንግሥት ለግብርናው ዕድገት መሠረት የሆኑት ለምሳሌ ለአረንጓዴ ልማት/አሻራ፣ ለአፈር ለአካባቢና አየር ጥበቃ ‹‹አትዮጵያን እናድናት››፣ ‹‹አትዮጵያን አረንጓዴ እናልብሳት›› በሚል መርሐ ግብሮች ኅብረተሰቡን በማነሳሳት (Mobilizing the Entire Populations) ይህ ሪፖርት አስከተጠናቀቀ ድረስ ወደ 16 ቢሊዮን የሚደርሱ ልዩ ልዩ ችግኞችን በመተከሉ፣ በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹‹ምግባችን ከደጃፋችን›› በሚል መርሐ ግብር ኅብረተሰቡ የከተማ ግብርናን እንዲያስፋፉ በወሰዱት ተነሳሸነት መንግሥት በገጠርም ሆነ በከተማ ግብናውን ለማሳደግ ከፍተኛ ሥራ እንደሠራ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
ከዚህም በላይ መንግሥት ለኩታ ገጠምና ለመስኖ እርሻ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱ፣ ትልልቅ የግብርና ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞችን (Flagship Projects and Programs) እንደ መደበኛ ሥራው በመከታተልና በመስክ ላይ ያላሰለሰ ድጋፍ ማድረጉ ለመጡት ለውጦችና ለተገኙት አንፃራዊ ውጤቶች ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን በጥናቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም መንግሥት ለግብርናው ዘርፉ ዕድገት ምን ያህል ቁርጠኛና ከልብ የመነጨ ተነሳሽነት እንዳለው በቂ ማሳያዎች መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡
እንዲሁም ከለውጡ ጋር ተያይዞ በርካታ ተቋማዊና መዋቅራዊ የሆኑ የሪፎርምና የማሻሻና ሥራዎች (Institutional and Structural Reforms and Rebuilding the Organizations) በፌዴራል ግብርና ሚኒስትርና በአንዳንድ የክልል የግብርና ቢሮዎች በመከናወኑ የተነሳ ቀደም ሲል በሰብል፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት መካካል የነበረው የእኩል ዕይታና ሚዛን ያለ መጠበቅ ችግሮች እንዲቀረፉ ተደርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ እያንዳንዱ ንዑስ ዘርፍ ለመጀመርያ ጊዜ በሚባል መልኩ በሚኒስቴር ደረጃ የአስፈጻሚ ባለሥልጣን እንደተመደበላቸው፣ ይህም ለዘመናት በግብርናው ንዑስ ዘርፎች መካካል የነበሩ አላሰፈላጊ ልዩነቶችና በዚህም የተነሳ በባለሙያዎች መካካል የሚስተዋሉ አላስፈላጊ መነቋቆርና ያለ መደጋገፍ ችግሮችን የፈታ መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡
ከለውጡ በፊት የነበሩ የአመራር፣ የአደረጃጀት፣ የአሠራር፣ የቴክኒክ፣ የአቅምና የቅንጅት ክፍተቶች በዕውቀትና በጥንቃቄ ከተለዩ በኋላ በእነዚህ ላይ ከለውጡ ወዲህ በተሠሩ የሪፎርም፣ አደረጃጀትና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ችግሮቹ በሒደት እየተቀረፉ መምጣታቸውን ጭምር ጥናቱ የሳያል፡፡ ለአብነትም ቀደም ሲል በግብርናና በተጠሪ መሥሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም በክልል የግብርና ቢሮዎችና መካካል የነበሩ ሰፊ የቅንጅትና የተግባቦት ክፍተቶች ከለውጡ በኋላ እንዲቀረፉ ተደርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ ለመጀመርያ ጊዜ በሚባል ሁኔታ ግብርና ላይ የሚሠሩ የግብርና ተጠሪ ተቋሟትን በአንድ የጋራ ዓላማና ራዕይ በግብርና ሚኒስቴር ሥር የሚያስተሳስር መዋቅር/አደረጃጃት ተፈጥሯል፡፡ ይህም በተቋሟቱ መካከል መልካም የሆነ የሥራ ትብብርና የመተጋዘዝ ስሜትን በመፍጠሩ ከለውጡ በኋላ የግብርናው ዘርፍ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ ፕሮግራሞችና የፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል እንዳሳዩ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ለማሳያነትም ቀደም ሲል ከ50 እስከ 60 በመቶ ያልበለጠው የፕሮጀክቶችና የፕሮግራሞች አፈጻጸም፣ ከለውጡ በኋላ የውስጥ አቅምን ከማሻሻል ጎን ለጎን ዴሊቨሪ የሚባል የኤክስፖርት ቡድን በመጠቀም ከ80 እስከ 85 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉ በጥናቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ሲል በነበረው አደረጃጀት በፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር አላስፈላጊ የዳይሬክተሮችና የባለሙያዎች ክምችት በመኖሩ፣ አላስፈላጊ የሥራ መደራረብ መብዛትና ባለሙያዎችን በአግባቡ ካለመጠቀም የተነሳ አላስፈላጊ የተማረ የሰው ኃይል እንደባከነ የነበሩ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ በተደረገው ሪፎርም ሥራ ግን እነዚህ ሁኔታዎች እንዲሻሻል በመደረጉ፣ ለምሳሌ ከለውጡ በፊት በፌዴራል ደረጃ ወደ 49 የሚጠጉ የዳይሬክተሮች ቁጥር ከሪፎርረሙ በኋላ ወደ 15 ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ የሥራ መደራረብና የሰው ኃይል ብክነትን ለመቀነስ እንደሚያስችል ይገመታል፡፡
እንዲሁም ከሃያ ዓመታት በላይ ያገለገለው የገጠር ግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ ምንም እንኳን ባለፉት ዓመታት ለግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመር የበኩሉን አሰተዋጽኦ ያደረገ ቢሆንም፣ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያልዋጀና መንግሥት ከሚፈልገው የግብርና ልማትና ስትራቴጂ አንፃር በርካታ ጉድለቶችና ውስንነቶች ያሉበት በመሆኑ ከለውጡ ወዲህ ፖሊሲው እንዲከለስ ወይም እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞም ቀደም ሲል የነበሩ የፖሊሲ ክፍተቶችና ጉድለቶች እንዲታረሙ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ በተሻሻለው የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ ውስጥ የግብርና መሬት አያያዝና የውኃ አጠቃቀም፣ የኮንትራት እርሻ፣ የብዙኃን የግብርና ኤክስቴሽንና የምክር አገልግሎት፣ ሥርዓተ ምግብ፣ የግሉ ሴክተሩ በግብርና ልማት ዘርፍ ላይ የሚሳተፍበትንና የሚበረታታበትን አስቻይ ሁኔታዎች፣ አነስተኛ አርሶ/አርብቶ አደሮች ምርትና ምርታማነታቸው ለመጨምር የሚያስችሉ ማበረታቻዎች፣ የቴክኖሎጂ ብዜትና የግብዓት አቅርቦት፣ የግብርና ኢንሹራንስ፣ የገጠር መሠረተ ልማትና የፋይናንስ ተደራሽነት ለማስፋፋት፣ የግብርና ባንክ ለማቋቋም፣ ወዘተ የመሳሳሉት በፖሊሲው ውስጥ በተጨማሪ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ የፖሊሲ፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ ደንቦችና መመርያዎች በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ከተሻሻለው የገጠርና ግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ መረዳት ይቻላል፡፡
በተመሳሳይ ቀደም ሲል የፌዴራልም ሆነ የክልል ቢሮዎች ብዙውን ጊዜ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን፣ እንዲሁም በጀታቸውን በአብዛኛው የሚያጠፉት በጥቃቅንና በደራሽ ሥራዎች (Campaign and Routine Types of Works) ላይ እንጂ፣ በትላልቅ ፕሮግራሞችና ለግብርናው ልማት ሥር ሰደድ የሆኑ ማነቆዎችና ችግሮች (Systemic Issues and Deep-Rooted Bottlenecks) መፍታት ላይ እንዳልሆነ ቀደም ሲል የተጠኑ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ጥናት መረዳት እንደተቻለው ግን፣ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ የፌዴራል ግብርናም ሆነ የክልል ቢሮዎች ዋና ትኩረት በአንፃራዊነት ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት መሠረታዊ የሆኑ ሥርዓታዊ ችግሮችና ሥር ሰደድ ማነቆዎች ላይ በመሆኑ፣ ግብርናው የዕይታ ለውጥ (Paradigm Shift) ብቻ ሳይሆን የትግበራና የአፈጻጸም ለውጥም እንዳደረገና በትክክለኛው ጎዳና ላይ መጓዝ እንደጀመረ ጥናቱ ያሳያል፡፡
እንዲሁም ሙሉ በሙሉ በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነውን ግብርናችን በመስኖ የታገዘ እንዲሆንና አርሶ/አርብቶ አደሩ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያመርት ታስቦ፣ ከለውጡ ወዲህ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችና በቀጣይም እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች አጅግ የሚያበረታቱ መሆኑን ጥናቱ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጋር በታያያዘም በተለይም የበጋ ስንዴን በመስኖ የማልማት ባህል መጀመሩና ከዚህ ጋር ተያይዞም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘው ውጤት አጅግ አበረታች መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ለማሳያነትም ይህ ጥናት ማጠናቀቂያ አካባቢ ማለትም የ2014 ዓ.ም. የበጋና የበልግ ወቅት ብቻ ወደ 25 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት በመስኖ እንደተመረተ የ2014 ዓ.ም. የግብርና ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ይህን ያህል መጠን ያለው ምርት በመስኖ ባይመረት ኖሮ በኮቨድ-19 እና በአገራችንና በዓለም ደረጃ በተፈጠሩት የተለያዩ ሰውና ተፈጥሮ ሠራሽ ቀውሶች ይህንን ያህል ምርት ከውጭ ማሰገባት ምን ያህል ከባድ ፈተናና አስቸጋሪ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ ከበጋው ስንዴ ልማት ጎን ለጎን በቅርብ ጊዜ የተጀመሩ የቡና፣ የአቮካዶና የአኩሪ አተር የመሳሳሉት ትላልቅ ልማቶች በተመሳሳይ ብሩህ ተስፋን ከጫሩት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ/አርብቶ አደሮች በቴክኖሎጂ በማዘመንና የግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎት በማሳለጥ ወደ ኮሜርሻላይዜሽን ለማሸጋገር ያስችል ዘንድ፣ ቀደም ሲል በአራት ክልሎችና በ300 ወረዳዎች በፓይለት መልክ የተጀመረው የኩታ ገጠም እርሻ ከለውጡ በኋላም በተለያዩ ወረዳዎች በመስፋፋቱና ይህም የመንግሥትን ትኩረት በመሳቡ የተነሳ፣ ከፍተኛ ወጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የ2013 ዓ.ም. ግብርና ሚኒስቴር ሪፖርትና የመስክ ምልከታዎች ያስረዳሉ፡፡
ግብርናውን በዘላቂነት ለማዘመንና አገራችን በምግብ ሰብል ራሷን አንድትችል ለመጀመሪያ ጊዜ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች (Home Grown Professionals) የተዘጋጀው የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በ2023 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ከምግብ ተመፅዋችነት ነፃ ለማድረግና በኢንዱስትሪ ምርት ራሷን የምትችል ታላቅ አገር ለመፍጠር ታስቦ ከመዘጋጀቱም በላይ፣ ለዚህ ማስፈጸሚያ የሚሆን ‹‹10 in 10›› የሚል በዓይነቱ የመጀመርያ ሆኖ ፈጠራ የታከለበትና ጥንቃቄ የተሞላበት መርሐ ግብር በግብርና ሚኒስቴር ተዘጋጅቷል፡፡ የዚህ መርሐ ግብር ዋና ዓላማው በአሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ መፈጸሚያ ወቅት በሌሎች ላይ የሚደረጉ ልዩ ልዩ የልማቶች ሥራዎች ተጠናቅረው መቀጠላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን በአሥር ዋና ዋና የምግብና የኢንዱስትሪ ሰብሎች (Commodities) ላይ ያተኮረ ሥራ በማናወን የምግብ ፍላጎትንና ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ የጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርቶች ከማሟላት ጎን ለጎን፣ የምግብ ዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የውጭ ምንዛሪ አቅም ለማሳደግ ታስቦ እየተሠራ ያለ አገራዊ ፕሮግራም ነው፡፡ ይህን ዓላማ ለማሳካት የሚረዱና የሚያሳልጡ ልዩ ልዩ ፍኖተ ካርታዎች ለምሳሌ የዲጂታል የግብርና ኤክስቴሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ፣ የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ፍኖተ ካርታ፣ የኢትዮጵያ የብዙኃን የኤክስቴሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ እና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች መከናወናቸው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ግብርናውን ለማሳደግ ምን ያህል ጠቃሚ የመሠረት ድንጋዮች እንደተጣሉና ግብርና ወደ ፈጣን የዕድገትና የለውጥ ጉዞ (Transformation) መሸጋገሩን አመላካቾች ናቸው፡፡
የግብርና ቢሮ የጽሕፈት ቤት ሥራዎች፣ እንዲሁም የመልካም የአስተዳደር አገልግሎት በአንፃራዊነት በየደረጃው መሻሻሉ፣ የተሻለ የሕዝብ ግንኙነትና ተግባቦት መፈጠር መቻሉ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ ብዙኃን መገናኛዎችን መጠቀም መጀመሩ፣ የዕቅድ ክንውን አፈጻጸምና የሪፖርት አቀራረብ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻሉ፣ ግብርና ላይ በተለያዩ ጊዜያት የሚስተዋሉ ሥጋቶች (ለምሳሌ የበረሃ ተምች፣ የስንዴ ዋግና መጤ ተባዮች፣ ወዘተ) የመቆጣጠር አቅም መጨመሩ፣ እንዲሁም በለሙያዎችን፣ አጋር የልማት አካላትንና ደንበኞችን የማስተናገድና የመልካም አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ሁኔታዎች መታየታቸውን መጠይቁን በሞሉ ተሳታፊዎች በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል አሳይተዋል ተብለው ከተጠቀሱት ምልከታዎች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በመጨረሻም ባለፉት ሦስት ዓመታት ግብርናውን ለማሳዳግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ተብሎ በጥናቱ ላይ በተሳታፉት ባለሙያዎች ከተመረጡት ተቋሟት መካካል የፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ የቡናና ሻይ ልማት በለሥልጣን፣ የክልል የግብርና ቢሮዎችና የፌዴራል የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበር ይገኙበታል፡፡
በጥናቱ የተለዩ ውስንነቶች
የግብርናውን ዘርፍ ዕድገት የሚፈታተኑ በርካታ አስተዳደራዊ፣ ቴክኒካዊና የአሠራር ውስንነቶችና ማነቆዎች አሁንም ቢሆን እንዳሉ ጥናቱ በግልጽ ይጠቁማል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተሠራው መዋቅራዊ ለውጥ በክልል ደረጃ ወደ መሬት በታሰበው መንገድ በፍጥነት ያለመውረድ/ያለመተግበር፣ የተደረጉ ለውጦችና ሪፎረሞች ላይ በየደረጃው ላሉት ሠራተኞች ያለማስተዋወቅና በእኩል ደረጃ ግንዛቤ ፈጥሮ በእኩል ያለመራመድ ችግር ይጠቀሳሉ፡፡
ቀደም ሲል ለግብርናው ዘላቂ ዕድገት አንዱ ማነቆ ሆኖ የቆየው የከፍተኛው አመራር፣ በተለይም የግብርና ሚኒስቴርና የክልል ቢሮ ኃላፊዎች በተደጋጋሚና ለውጥ መናወጥ የተነሳ ሥራቸውን ተረጋግቶ መሥራት አለመቻል ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፉት 50 ዓመታት የግብርና ሚኒስትሮች ከ35 ጊዜ በላይ እንደተቀያየሩ ጥናቶች የሳያሉ፡፡ ይህም ደግሞ አንድ ሚኒስትር በሥራው ላይ በአማካይ የሚቆየው አንድ ዓመት ተኩል ብቻ ነው፡፡ ይህ ችግር ደግሞ በዞንና በወረዳ እጅግ የከፋ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት መደምደም የሚቻለው ግብርና በአመራር ተደጋጋሚ ለውጥ የተነሳ መታወኩን ነው፡፡ ምንም እንኳን ካለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ከዚህ ጥናት መረዳት የተቻለ ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን የከፍተኛው አመራር በየጊዜው መቀያየር/መለዋወጥ (Instability of the Top-Level Leadership) በተለይ በወረዳ ደረጃ ሥጋቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዳለ በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች አልሸሸጉም፡፡
በየደረጃው ያሉ አብዛኛው የግብርና ባለሙያዎች የግብርናን ፖሊስና ስትራቴጂ ላይ የማስፈጸም አቅም ዝቅተኛ መሆን፣ በተለይም የተግባርና የክህሎት ሙያ በከፍተኛ ደረጃ መኖር፣ ሥራን ቆጥሮ መስጠትና ሰፍሮ የመቀበል ባህል መዳበር፣ አንዳንድ የከፍተኛና የመካከለኛ አመራሮችና በለሙያዎች አሁንም ቢሆን በደራሽና በትንንሽ ሥራዎች መጠመድ፣ የወረቀት ሥራና የስብሰባ መብዛት፣ ለብዙኃን መገናኛ መረጃዎችን ያለመስጠት ያለመተባባር ይስተዋላል፡፡
የፌዴራል የግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለውጥ እያሳዩ ቢሆንም፣ በክልሎችና በአዲስ አበባ ግን ያን ያህል መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ችግሮች አሁንም ቢሆን በበቂ ሁኔታ ያለመፈታት ችግር፣ ለግሉ ሴክተር የሚደረገው ድጋፍና ማበረታቻ በተግባር አለመደገፍ፣ የግብዓት ሥርጭትና ተደራሽነት ውስን መሆን፣ የሎጂስቲክስ አቅርቦትና ድጋፍ በተለይም በወረዳ ደረጃ እጅግ በጣም አናሳ ከመሆኑ የተነሳ የግብርና ወረዳዎች በመልካም አስተዳዳር ዕጦትና አስፈላጊ በሆኑ ቁሳቁሶች በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዱ መሆናቸው፣ የምርት ሥርጭትና ግብይት አስቸጋሪ ሰንሰለት አሁንም ቢሆን ለአምራቹ ሥጋት ሆኖ መቀጠሉና የግብርና ውጤቶች የዋጋ ንረት፣ የግብርናና የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ላይ የነበረው ችግር በተሻሻለው የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲሻሻል ቢደረግም በተግባር ግን የዘገየ መሆኑ፣ የኤክስቴሽን አገልግሎቱ አሁንም ቢሆን ራቅ ያሉ ቦታዎች በተለይም ለአርብቶ አደሩ የተደራሽነት ክፍተት መኖሩና አገልግሎቱ ብዙም ከዘልማድ ያልተሻገረና ፕሮፌሽናል ለማድረግም በርካታ ውስንነቶች መኖራቸው፣ ከዚህ በተጨማሪም የአፈር ጤንነትነና ለምነት አያያዝ ላይ የተሰጠው የኤክስቴሽን አገልግሎት ከችግሮቹ አንፃር ሲታይ በጣም ደካማ መሆን፣ ግብርና ዘርፍ ላይ የወጣቶችና የሴቶች ተሳትፎ እንደታሰበው ያለመሆን፣ አሁንም ቢሆን ውኃን በአግባቡ ለመስኖ ሥራ ለመጠቀም የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በብዛት ያለመኖርና ከዚህ ጋር ተያይዞም የመስኖ መሣሪያዎችና የወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች እጥረት መኖርና ለግብርና ባለሙያዎች የሚደረጉ ማበረታቻዎችና ጥቅማ ጥቅሞች እጅግ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ግብርናን ለቆ መሄድ፣ ወዘተ መሆናቸው መጠይቁን በሙሉ ምላሽ ሰጪዎች ዋና ዋና ችግሮች ተብለው የተለዩ መሆናቸውን የዳሰሳ ጥናቱ ያሳያል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ከዳሰሳው የጥናት ውጤት በመነሳት መደምደም የሚቻለው ባለፉት ሦስት ዓመታት የግብርና ዘርፉን ለማዘመን በርካታ የመሠረተ ልማትና የሪፎረም ሥራዎች (Reform and Basic Foundations) እንደተሠሩ፣ በዚህም ግብርናው ከአዝጋሚ ጉዞ ወደ ፈጣንና አስተማማኝ ጉዞ መሸጋገሩን የጥናቱ ውጤት ያስረዳል፡፡ እነዚህ ጀምሮች አሁን ባለው ግለት ከቀጠሉና ሌሎች በዚህ የዳሰሳ ጥናት እንደ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው ተብለው የተነሱት ችግሮች በቂ ትኩረት አግኝተው ከተቀረፉ፣ በግብርናው ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣንና አስተማማኝ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም አገራችን ለግብርናው ዘርፍ ዘላቂ ልማትና ፈጣን ዕድገት ለማምጣት አሁንም አያሌ ያልተነኩ ዕምቅ የተፈጥሮና የሰው ሀብት ያላት አገር እንደ መሆኗ መጠን፣ ፈጣንና አስተማማኝ ለውጥ ለማምጣት የሁሉንም ርብርብና ትጋት ይፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የውጭ ዕርዳታን ተረት አድርጎ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ አገራችን ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም የምትተርፍ መሆኗ የማይቀር ነው፡፡ ለማሳያነትም ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ስትወደደር በአንፃራዊነት እየተሻለች የመጣች መሆኑን የተለዩ ሪፖርቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ተጠናክሮ ከቀጠለ ኢትዮጵያ አገራችን የገጠማት ስብራቷ ተጠግኖላት አንገቷን ቀና አድርጋ በዓለም ፊት ጎላ ብላ እንደትታይ ከማድረጉም በላይ፣ ሁል ጊዜ የምንመኘውና የምንናፍቀው የበለፀገችና ለልጆቻችን የምትመች አገር ለመፍጠር ሁሉም ከደረቅ ፖለቲካና አላስፈላጊ ክርክር፣ እንዲሁም ከዘረኝነትና ከጥላቻ መንፈስ ወጥቶ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ጥናት አድራጊው ምክረ ሐሳቡን ይሰጣል፡፡
በመጨረሻም በጥናቱ ላይ በተለያየ ደረጃ ለተሳታፉ ባለሙያዎችና ላገዙኝ ግለሰቦች ክፍ ያለ ምሥጋናዬን እያቀረብኩ፣ የዳሰሳው ጥናት ዝርዝር ሪፖርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በቅርብ ጊዜ ታትሞ ስለሚቀርብ ሙሉ ጽሑፉን ማግኘት እንደሚቻል ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ አመሠግናለሁ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ከፍተኛ የግብርና ተመራማሪና የግብርና ኤክስቴሽን ባለሙያ፣ የኢትዮጵያ የገጠር ልማትና የግብርና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበሩና በአሁኑ ወቅት የሙያ ማኅበሩ የክብር አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡