ኮቪድ-19 እንደ ዓለም አቀፍ በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያደረሰ ይገኛል፡፡ አሁንም ወረርሽኙ የማኅበረሰቡ ዋነኛ የጤና ሥጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የኮቪድ-19 በሽታ እንደ አገር ከተከሰተ በኋላ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለከፋ ሕመምና ሞት ዳርጓል፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡ ኮቪድ-19 ጠፍቷል በሚል እንዳይዘናጋ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስኪያጅ መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከጥር ወር 2014 ዓ.ም. የኮቪድ-19 ማዕበል በኋላ፣ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ጋር ተያይዞ ማኅበረሰቡ ከመዘናጋትም በላይ ቫይረሱ እንደጠፋ አድርጎ እያየ እንደሆነ የሚያመላክቱ አዘናጊ ድርጊቶችና አስተሳሰቦች እየተስተዋሉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታም ቫይረሱ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሠራጨ ይገኛል፡፡
ከሰኔ 5 እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ አምስት ሺሕ ሦስት ሰዎች የኮቪድ 19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህ ከግንቦት 6 እስከ ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ከነበረው በንፅፅር ሲታይ 9.7 በመቶ ወደ 5.7 በመቶ የመያዝ ምጣኔ ቀንሷል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት 38 ሰዎች በፅኑ ሕሙማን የሕክምና ክፍል ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙ ሲሆን፣ ከሰኔ 17 እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ውስጥ 40 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ በአገራችን 491,917 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፣ 7,568 የሚሆኑ ወገኖች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ እነዚህ የሕሙማንና የሞት አኃዞች የሚያመለክቱት ማኅበረሰቡ ውስጥ አሁንም መዘናጋትና የመከላከለያ ዕርምጃዎችን በተገቢው ያለመተግበር ሁኔታዎች እንዳሉ፣ በዚህም የዜጎች ሕይወት እየተቀጠፈ እንደሆነና አሁንም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዋነኛ የማኅበረሰባችን የጤና ሥጋት ሆኖ መቀጠሉን ነው ብለዋል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ ሁሌም ቢሆን ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዳውን ማስክ ማድረግ፣ ርቀትንና የእጅ ንጽሕናን መጠበቅ እንደዚሁም በኮሮና ቫይረስ ተለዋዋጭ ባህሪ ምክንያት ከሚመጣ የጤና ችግር ለመጠበቅና በሽታ የመከላከል አቅምን ለማጎልበት ዕድሜያቸው 12 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው የኮቪድ መከላከያ ክትባት ያልተከተቡ፣ አንድ ጊዜ ወስደው ሁለተኛውን ዙር ያልተከተቡ እንዲሁም ሁለተኛውን ዙር ተከትበው 6 ወር የሞላቸው ደግሞ ቡስተር ዶዝ ክትባትን በጤና ተቋማት በመኘት በነፃ እንዲከተቡ መክረዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ 43,082,517 የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኮቪድ መከላከያ እንደተከተቡ ጠቁመዋል፡፡