Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ንባብ ለሕይወት›› የመጻሕፍትና የምርምር ተቋማት ዓውደ ርዕይ ዳግም ሊጀመር ነው

‹‹ንባብ ለሕይወት›› የመጻሕፍትና የምርምር ተቋማት ዓውደ ርዕይ ዳግም ሊጀመር ነው

ቀን:

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ዓመታዊ ‹‹ንባብ ለሕይወት›› የመጻሕፍትና የምርምር ተቋማት ዓውደ ርዕይ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ዓውደ ርዕዩ ከሐምሌ 28 እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሄድ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲና ንባብ ለሕይወት ፕሮጀክት በጋራ ያሰናዱት ነው፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጻሕፍት አሳታሚዎች፣ ደራሲያንና የምርምር ማዕከላት የሚሳተፉ ሲሆን፣ ከ50 በላይ መጻሕፍት እንደሚመረቁ የንባብ ለሕይወት ፕሮጀክት መሥራች አቶ ቢንያም ከበደ ወልዴ ገልጸዋል፡፡

አዳዲስ መጻሕፍት በቅናሽ የሚገኝበት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢ-ቡክ በነፃ የተዘጋጀበት መሆኑን፣ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚደረገው የንባብ ለሕይወት ዓውደ ርዕይ፣ የልጆች መማሪያዎችና የተረት ተረት መጻሕፍት በብዛት የሚገኝበት ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ከንባብ ለሕይወት ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የሚሰናዳው ዓውደ ርዕይ፣ በርካታ የግልና የመንግሥት ተቋማት የሚሳተፉበት መሆኑንም አክለዋል፡፡

የንባብ ለሕይወት ፕሮጀክት መሥራች አቶ ቢንያም እንዳሉት፣ በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት ከ2011 ዓ.ም. በኋላ ንባብ ለሕይወት ተቋርጦ ነበር፡፡

ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው ንባብ ለሕይወት ዓውደ ርዕይ አዳዲስ ከ50 ያላነሱ የታሪክ፣ ትምህርታዊ፣ የሃይማኖት፣ የልጆችና የልብ ወለድ መጻሕፍት ይቀርባሉ፡፡

የዘንድሮው ‹‹ንባብ ለሕይወት›› ዓውደ ርዕይ በይዘትና በአቀራረብ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ለማድረግ መሠራቱን የገለጹት አቶ ቢንያም፣ በኢ-ቡክ አማካይነት ለልጆች፣ ለሁለተኛ ደረጃና ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሁለት ሚሊዮን ያላነሱ መጻሕፍት በነፃ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሜ የኅትመት፣ ጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ፣ ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት የተቀመጡ ነባር መጻሕፍት በዓውደ ርዕዩ የሚቀርቡ ይሆናል፡፡

መጻሕፍት በማንበብ ልዩ ክህሎት ያላቸውን ሕፃናትና ታዳጊዎች፣ ካነበቡት የሚያካፍሉበት መድረክ መዘጋጀቱን መሥራቹ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 13 ዓመት ባሉ ታዳጊዎች የተጻፉ መጻሕፍት፣ ስለሥራዎቻቸውና ልምዶቻቸው የሚያካፍሉበትም ነው፡፡

በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱም ላይ በየዓመቱ ሲደረግ እንደቆየው የ‹‹ወርቅ ብዕር›› ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በነበረው ደራሲ አዳም ረታና የመጻሕፍት አርታኢ አማረ ማሞ መሸለማቸውን አስታውሰዋል፡፡

የዚህ ሽልማት ዋነኛ ዓላማ በሥነ ጽሑፍ ታሪክ ለውጥ ያመጡና ለረዥም ዓመታት የቆዩት ደራሲያን የሚሸለሙበትና የሚዘከሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ ሌላኛው ገጽታ የሆሔ የሥነ ጽሑፍ ሽልማትን ያካተተ ሲሆን፣ በሥነ ጽሑፍ ብልጫ ላሳዩ የመጻሕፍት ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ የንባብ ለሕይወት ዓውደ ርዕይ አዳዲስና ነባር የመጻሕፍት ደራሲያንን የሚያበረታታ ሲሆን፣ በቅናሽ ዋጋ መጻሕፍትን ለማግኘት ለሚፈልጉም ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም የዕድሜ ክልል ላይ ለሚገኙ ዜጎች የሚሆኑ የታሪክ፣ ትምህርታዊ፣ ልብወለድ፣ የሃይማኖት መጻሕፍት የሚገኙበት መሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...