Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ምሬት ቦታ አይመርጥም!

ሰላም! ሰላም! ኧረ ብርዱ እንዴት ነው? አልቻልነውም እኮ፡፡ እስኪ አስቡት በዚህ የሰቀቀን ኑሮ ላይ ሌላ አሰቃቂ ነገር ተጨምሮበት። አንችለው የለም ይኼው ኑሮንም ብርዱንም ችለን ሰንብተን ተገናኝተናል። እንዲያው አብዛኛውን ሰው ወክዬ የሰሞኑን አጥንት ቆርጣሚ ብርድ ማንሳቴ እንጂ፣ እኔስ እውነት ለመናገር ዕድሜ ለማንጠግቦሽ ሙቀቱን ነው ያልቻልኩት። ሃ…ሃ…ሃ… ይብላኝ ፍቅርና አብሮነት መሀል ፖለቲካና ነገር እየቆሰቆሱ ለተኳረፉ። እንዲያው እናንተ፣ ምነው ሰው ግን እንዲህ የፍቅርና የአንድነት ጠላት ሆነሳ? ‹‹ፍቅርና አብሮነት የሚገኘው በመተሳሰብ ውስጥ እንጂ ለብቻ በሚከማች ገንዘብ አይደለም…›› ብዬ ለአዛውንቱ ባሻዬ ብሶቴን ባሰማ፣ ‹‹ልፋ ቢልህ እንጂ የአሁን ዘመን ሰው መካሪ የሚያሻው ነው? አውቆ አጥፊ ሁሉ…›› ነበር መልሳቸው። እውነት ነው እኮ፣ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት መቼ ይሰማል? የመስማት ነገር ከተነሳማ መንግሥትስ መቼ ነው ሕዝብን የሚሰማው? ሕዝብስ የማይሰማውን መንግሥት እንዴት አድርጎ ነው የሚሰማው? አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር፣ በመጨረሻው ዘመን ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሳል የተባለው እኮ ለቀልድ አይደለም፡፡ አንዱ ሌላውን በቅጡ ካልሰማው የሚከተለው መጠፋፋት እንደሆነ እኮ ነው መልዕክቱ…›› የሚሉኝን ሳስታውስ እፈራለሁ፡፡ ወድጄ አይደለም!

 እንዳልኳችሁ ሰው በሚያገኘው ቀዳዳ ሁሉ ሥራው ጎራ መለየት ሆኗል። ለሌላው አለማሰብና ለራስ ብቻ መኖር ገኗል። በቀደም ምን ሆነ መሰላችሁ? አንድ የሚከራይ ቪላ ቤት ነበርና የሚከራየው ሰው ለማግኘት ላይ ታች ስል ውዬ በመጨረሻ ተሳክቶልኝ ቤቱን የሚከራየው ሰው አገኘሁ። ሰውዬው ብቻውን ነው። ልጅም ሚስትም የለውም። ‹‹እንዴት ነው ቤተሰቦችህ በአገር የሉም?›› አልኩት ጎልማሳነቱንና መልከ መልካምነቱን መላልሼ እያየሁ። ‹‹የለም፣ ቤተሰብ ምን ይሠራል?›› ቢለኝ ክው አልኩላችሁ። ይህችን ይወዳል አንበርብር ምንተስኖት? ምነው ተዘጋጅ እንኳ ቢለኝ እያልኩ፣ ‹‹እንዴ ምን ለማለት ነው?›› አልኩት በደረቀ ድምፅ። ‹‹በዚህ ጊዜ ቤተሰብ? ያምሃል እንዴ? ሚስት ከመፈለግ ነዳጅ ብፈልግ ብቻዬን ይሳካልኛል እኮ…›› አይለኝ መሰላችሁ። ሰው አምርሯል ማለት እኮ ይኼ ነው። ቀላል አምርሯል? ወዲያው ከምሬቱ ጀርባ ምን እውነት ቢኖር ይሆን ብዬ መመራመር ጀመርኩ። እንዲህ ዓይነት ሰው ጠፍቶ እኮ ነው ምሬታችን ገደቡን ያለፈው፡፡ መልሱን ታዲያ አንድ ወዳጄ ድሮና ዘንድሮ በሚለው ጨዋታው ውስጥ ያገኘሁት መስሎኝ ከእሱ ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜ ያወጋኝን አሰላስል ጀመር። ትዝታ ማለት ይህ ነው!

ጨዋታን በጨዋታ አይደል ደንቡ? ድሮና ዘንድሮ በሚል የቤቱን ድባብ ወዳጄ ያጫወተኝ እንዲህ ብሎ ነበር። ‹‹ድሮ ትዳር ለመያዝ ገና ማቀድህ ሲሰማ ደግሶ ከመዳር አልፎ፣ በርታ እስከምትል ድረስ ቀለብ ሸመታ ሳይቀር ዘመድ ወዳጅ ያግዝሃል። ‹አይዞህ› የሚልህ፣ የሚጠይቅህ አገር ምድሩ ነው። አንተ አመል ይኑርህ እንጂ ሚስትህም ታዛዥ፣ ግንባርህን ዓይታ የምታስበው የሚገባት፣ ከመብቷ በፊት ትዳሯና ቤቷ የሚበልጥባት ነበረች…›› አለና ጥቂት ራሱን በአሉታ አወዛወዘ። ‹‹አሁንስ?›› እለዋለሁ ወሬው ግላዊ አመለካከትና አስተያየት የሠፈነበት እንደሆነ እየተገነዘብኩ፣ ‹‹አሁንማ ብቸኝነት ቢፀናብህ ከሰልህን ገዝተህ፣ በቆሎህን እየጠበስክ ቲቪህን ስታይ ታድራታለህ እንጂ ከሌለህ ማን ሊጠጋህ? ቲቪ ከሌለህ ደግሞ ዩቲዩብ አለልህ የተጋነኑና የለዘዙ ዜናዎችንና ትንተናዎችን ሲያራግፍብህ ያድራል። እዚህ ላይ ብናበቃስ…›› አለኝ እጁን ወደ ላይ እየዘረጋ። እኔም፣ ‹‹አይ አንተ፣ የእኛንስ የፀባይ ለውጥ መቼ አየኸውና?›› ብዬ ክፉ ሳልናገር ተሳስቄ ዝም። ሰው አመለካከቱንና እምነቱን ሲነኩበት ተርብ ሆኗላ ጎበዝ፡፡ ታዲያ ቪላ ቤቱን የተከራየው ደንበኛዬም ይኼን አስተሳሰብ የደገመው ስለመሰለኝ ለማጣራት ደግሜ ብጠይቀው፣ ‹‹ወንድሜ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ሰው ራስ ተኮር ሆኗል። ዕድሜ ግራ ገብቶት ግራ ለሚያጋባን መንግሥታችን። ትዳር ለመመሥረት ፍቅር ሳይሆን ገንዘብና ንብረት አለው/አላት በሚባልበት በዚህ ዘመን፣ ቤተሰብ ሳይቀር ሠርተው ያገኛሉ ሳይሆን ምን አለው/አላት እያለ በሚደልልበት በዚህ ጊዜ፣ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ተሠርቶ ስለሚገኝ ሀብት ሳይሆን ተሰርቆ ስለሚከበርበት አቋራጭ በሚጨነቅበት ወቅት ምን አስጨነቀኝ…›› አለኝ። እንዳልክ ብዬ ኮሚሽኔን ተቀበልኩና ተሰናበትኩት። መቼስ ዘመናችን ምን ያህል እንደ ከበደ ለመረዳት ነጋሪ አያሻንም። የጥቂቶች አዋዋልና አዳር ለብዙዎች መገለጫና ስም ሲሆን ግን ያሳዝናል። በጣም ያሳዝናል!

እናላችሁ ሰሞኑን ብርዱ ሲፀናብኝ ነገር ዓለሙ እያስጠላኝ ቤቴ ተጠቅልዬ ከማንጠግቦሽ ጋር ሳወጋ፣ ከዚያም ከዚህም የለቃቀምኩትን ወግ እያነሳሁ ሳጫውታት እውላለሁ። (‹ሺሕ ዓመት አይኖር› እያሉ ሥራ መፍታት ካለማመዱን እንግዲህ ምን ይደረግ?) ድንገት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር ሳላስበው ከአፌ ካመለጠ፣ ‹‹ኧረ አንተ ሰውዬ ተወኝ ስለፈጠረህ? ምንድነው እንደ አገራችን ፖለቲከኞች የሚምታታ ነገር መዘባረቅ? ቀጥ ያለ ነገር አውራ፡፡ ተምታቶ ማምታታት እንኳን ለአንተ ለገዥው ፓርቲም አልጠቀመ፡፡ ተመልከት እስኪ ያኮረፉ የገዥው ፓርቲ ሰዎች ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ኩርፊያቸውን እየገለጹ ነው፡፡ ይልቅስ ለምን አኮረፉና አደባባይ ወጥተው መናገር ጀመሩ ብለህ ተመራመርና ራስህን ለመጪው ፈታኝ ጊዜ አዘጋጅ…›› ስትለኝ፣ ውዴ ማንጠግቦሽ እኔ ሳላውቅ ከታዋቂ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ መቼ ነው የማስተርስ ዲግሪዋን የያዘችው ብዬ አሰላስል ጀመር። እውነቴን ነው እኮ። የትኛው ምሁር ነው እንዲህ ፖለቲካችንን እየፈተፈተ የሚያጎርሰን፡፡

‹‹በቀደመው ሥርዓት ‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!› ከተባለ በኋላ፣ የዘመኑ ተገዳዳሪ ፖለቲከኞች አገሪቱን በደም እያጠቡ ከመርሁ ጋር እየተጋጩ በርካታ ሺዎች በነጭና በቀይ ሽብር ታጨዱ። በእነሱ እግር የተተካው ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ› ብሎ ዴሞክራሲ አለ ብለን ያሻንን ስንናገር ፀረ ልማት፣ አክራሪና ጽንፈኛ ብሎ ፈርጆ ስንቱን ፈጀው፣ ስንቱን እያሰቃየ አሰረው፣ ስንቱን አሰደደው። በቃ ስሙ ተቀይሮ ‹ልማት› ተባለ እንጂ አብዮት ውስጥ ነን ስንል ሐሳብን በነፃነት ስለመግለጽ፣ ስለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፣ ስለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሰበካው ቢበዛም ውጤቱ አፈና ነበር። ዛሬ ደግሞ ለውጥ ብለን ጀምረን አንድ ላይ ሆ ብለን ብንነሳም፣ ለውጡ በብልጦች ተጠልፎ ምን እየሆንን እንደሆነ ታውቀዋለህ፣ ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ስለዚህ አንተንም ተምታቶ የሚያምታታ ነገር አያጥቃህ የምልህ ለዚህ ነው…›› ስትለኝ እውነት ማንጠግቦሽ አልመስልህ ብላኝ ፈዝዤ አየኋት፡፡ ‹‹በይ እኔ እንደሰማሁሽ ሌላ ሰው እንዳይሰማሽ አደራ…›› ብያት ልወጣ ስል፣ ‹‹አንበርብር ልብ ብለህ ስማኝ፡፡ ከዘመኑ ሰው ውስጥ እኮ የማይረባ ስትለው ቁም ነገረኛ፣ ባለጌ ስትለው ጨዋ፣ አፍራሽ ሲባል ገንቢ ሆኖ የሚገኝ ብዙ አለ። ስለዚህ ሁሉንም በአንድ ፈርጀህ አትፍራ…›› ብላ ስትጨምርልኝ ከጓዳ ሕይወቷና ሥራዋ ባሻገርም ምንም የምታውቀው የማትመስለኝ ውዷ ማንጠግቦሽ በሳል የፖለቲካ ተንታኝ ሆና አረፈች። ጉድ እኮ ነው! 

መቼም ሮጬ ሄጄ የማወራው ለእሱ ስለሆነ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ አግኝቼ የማንጠግቦሽን ታሪክ ብነግረው፣ ‹‹እውነቷን እኮ ነው!›› ብሎኝ የሚሉት ሌላ የሚሠሩት ሌላ ስለሆነባቸው የዘመኑ ምሁራኖቻችን በሰፊው ተጨዋወትን። በኋላም ‹‹ኔጋቲቭ›› እና ‹‹ፖቨቲቭ›› የሚሉ ቃላትን በስሙ ስላስቀየራቸው ንጉሥ የባሻዬ ልጅ የሚያስቅ ነገር አጫወተኝ፡፡ እኔም ‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ›› እያልኩ ሰማሁት፡፡ ሆሊውድ አምባገነኖች ምን ያህል ራስ ወዳድና ህሊና ቢስ ገዥዎች እንዳሉ ለማሳየት ፈልጎ ከሠራው ፊልም ያየው መሆኑን ጠቅሶ የባሻዬ ልጅ ጨዋታውን ቀጥሏል (የእኛ አገር ፊልሞች እንደሆኑ ‹ካሳቁ ይበቃል› የተባሉ ይመስል ጠንከር ያለ መልዕክት ሲያስተላልፉ ለማየት አልታደል ብለናል)፡፡ ‹‹የንጉሡ ስም አላዲን ይባላል። ሁሉም ነገር በእሱ ስም እንዲቀየር ከማዘዙ የተነሳ ‘ኔጌቲቭ’ እና ‘ፖዘቲቭ’ በስሙ ተዛውረዋል። ታዲያ የኤችአይቪ ምርመራ ውጤት ያደረገ ሰው ውጤቱ የሚነገረው ‘ኤችአይቪ አላዲን’ ወይም ‘ፖዘቲቭ አላዲን’ ተብሎ ነው። ይታይህ እንግዲህ…›› አለኝ ፈገግ ብሎ። ጨዋታችን በምድራችን ላይ የተነሱ አምባገነንና ጨካኝ መሪዎችን አስታወሰኝ። ከማናለብኝ ስሜታቸው የተነሳ የሰው መብት የደፈሩ ስማቸው በታሪክ መዝገብ ላይ ጎድፎ ተጽፎ ትውልድ ሲሳለቅባቸው የሚኖሩ በአዕምሮዬ ተዘረዘሩ። ብልህ መሪና መንግሥት ግን በታሪክ ተወቃሽ መሆንን ስለማይሻ ከልብ ለሕዝብ መሥራትና መቆርቆር መገለጫ ባህሪው ነው፡፡ የሚሰማ ካለ! 

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ብርዱ ሲጠናብን እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን አመራን። ግሮሰሪያችን ከወትሮ የተለየ ድባብ አይታይባትም። ሳቅ ጨዋታ ብሽሽቁ እንደተለመደው አለ። እንደ ወትሮው ያልነበረው የባሻዬ ልጅ ነው፣ ድንገት ተለውጧል። ‹‹ምነው? ምን ሆነሃል?›› አልኩት ከፍቶት እያየሁት። ‹‹እ… እንዲያው ዝም ብዬ ነው እባክህ፣ ብቻዬን የምፈጥረው ነገር ያለ ይመስል…›› አለኝ። ‹‹በእርግጥ መፍጠር የፈጣሪ ተግባር ነው። ልዩነት ማምጣት ግን መቻሉን አትርሳ…›› አልኩት ትከሻውን ቸብ እያደረግኩ። አሁንም ዝምታው ቀጠለ። ‹‹ኤጭ ትነግረኝ እንደሆነ ንገረኝ። ለጨዋታ እንጂ የሚያስቆዝምማ መቼ ጠፋ?›› ስለው ደንገጥ ብሎ፣ ‹‹አንዳንዴ ለራሴም ጭምር ስለሚገርመኝ እኮ ነው…›› አለኝ በተጨነቀ ድምፅ። ‹‹ምኑ?›› ጠየቅኩት መልሼ። ‹‹የዚህች አገር እንቆቅልሽ ነዋ፡፡ ሌላ ምን አለብን አንበርብር?›› ብሎ መልሶ ጠየቀኝ። ‹‹ምነው የሰማኸው አዲስ ነገር አለ እንዴ?›› ስለው፣ ‹‹አዲስ ነገር ባንሰማስ ያልፈታነው ችግር ተጠራቅሞ አለ አይደል እንዴ?›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹ዝም ብዬ ስታዘብ ወዴት ይሆን እየተጓዝን ያለነው? ስል መሽቶ ይነጋል። ተመልከት እስኪ አብዛኛው ተማሪ ዕውቀት ከመቅሰም ይልቅ በአቋራጭ እንዴት ሀብት እንደሚገኝ ይማራል፣ ስግብግብ ነጋዴ ከዚህም ከዚያም እያምታታ የአገሩን ሕዝብ ይዘርፋል፣ ፅንፈኛው አማኝ ‘ከእኔ ሌላ የለም’ የሚል አክራሪነት አጥቅቶታል። በዚህ በኩል ሌብነቱ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦቱን ታየዋለህ። ሁሉም ለራሱ ጎርሶ ለራሱ ሊድን ብቻ እየሮጠ የአገር ችግር የሚፈታ ጠፋ። እውነት ማን ነው ከራሱ አስቀድሞ የዚህችን አገር ጥቅም እያስቀደመ ያለው? እንጃ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ይመስለኛል…›› ብሎኝ ካስቀዳው ተጎነጨ። ነገሩ ያስጠጣል!

‹‹አንተስ ታዲያ ምን ይሁን ትላለህ?›› አለው ፊት ለፊታችን ተቀምጦ የምናወራውን ሲሰማ የነበረ ጎልማሳ። የባሻዬ ልጅ ከአንገቱ ቀና ብሎ ድምፁን ጎርነን አድርጎ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም!›› ብሎ ሲመልስ የግሮሰሪዋ ታዳሚዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ቀና ብለው አዩት። ጠያቂው ብርጭቆውን ወደ ላይ አንስቶ፣ ‹‹ከራስ ጥቅም በፊት ለአገር!›› አለው ፈገግ ብሎ። ድራማ የማይ እስኪመስለኝ ድረስ የምሰማውንም ሆነ የምመለከተውን ማመን አልቻልኩም። ሁሉም የሚጎነጨውን አንስቶ በአንድ ድምፅ መፈክር ያወርዳል፡፡ ከራስ ወዳድነት እስከ ጽንፈኝነት የመረረው ሁሉ ወደኋላው እያየ ነገን የናፈቀ ይመስላል፡፡ ራስ ወዳድነትና ቡድንተኝነት ፋሽን በሆነበት በዚህ ዘመን ጠያቂና መርማሪ ትውልድ ካልተፈጠረ ነገም ያስፈራል፡፡ ለዚህም ይመስላል ከራስ በፊት ለአገር የሚለው የግሮሰሪዋን ሰዎች ‹‹ቺርስ›› የሚያስብለው፡፡ ከራስ ወዳድነት እስከ ፅንፈኝነት ድረስ ያሉት በሽታዎች ይወገዱ ዘንድ ስንቴ ቺርስ እንደተባለ አላስታውስም፡፡ ነገር ግን የእኛ ሰው በአገሩ ላይ የሚያሴሩ ሰዎች ድርጊት የመረረው ይመስላል፡፡ ምሬት ሲበዛ ደግሞ ቦታ አይመርጥም፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት