Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ትራኒያ ኮ ኮይሣኒ›› ዳኛው

‹‹ትራኒያ ኮ ኮይሣኒ›› ዳኛው

ቀን:

ለቋንቋና ባህል ዕድገት ሙዚቃ፣ መጽሐፍ፣ ቲአትርና ፊልም ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ ከብዙ አገሮች ቋንቋና ባህል ዕድገት በስተጀርባ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ዓለምን እንዲገናኝ እንደሚያደርገው ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ምስክር ናቸው፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዝኛ ቋንቋን ብንመለከት በርካታ የዓለም ሕዝቦችን አንድ ያደረገና ያግባባ ለመሆኑ ማሳያ ይሆናል፡፡ በቋንቋ ፊልም፣ ሙዚቃ፣ መጽሐፍና መሰል ነገሮች የሚከናወንበት በመሆኑ በብዙ እንዲነገር አድርጎታል፡፡

በደቡብ ኦሞ ከሚገኙና በቱሪስት መስህብ ከሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ሙርሲዎች ይገኙበታል፡፡ በሙርሲ ዘንድ ብዙ የተለያዩ፣ ያልታዩና ያልተነገሩ ባህልና እሴትን የሚያንፀባርቁ ሀብቶች አሉ፡፡

ውብ ተፈጥሮ የታደለውን ማጎ ፓርክ ተያይዘው ወንዙ ዳር የሰፈሩትን ሙርሲዎች ለመመልከት ጎብኚዎች በየዓመቱ ይጎርፋሉ።

 የተለያዩና ያማሩ የፀጉር አጊያጌጦችንም በተለይም በወንዶቹ ላይ መመልከትም የተለመደ ነው።  ሰውነታቸውን በመተልተል ሸክላ በማስገባት የሚያጌጡትም ከበፊቱ የባርያ ንግድ ለማምለጥ በዘየዱት ሥርዓት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡

ይህ ሥርዓት ግን ከጊዜ በኋላ የባህላቸው አንድ አካል በመሆኑ፣ ሴቶች ከአሥራ አምስት ዓመታቸው ጀምሮ ከንፈራቸውን በመተልተል ክብ ሸክላ ያስገባሉ። ይህም እንደ ውበት መገለጫ የሚታይ ሲሆን የሸክላው መጠንም ለቤተሰቦቿ እንደሚሰጠው ከብት ሊጨምር ይችላል። እየቀነሰ ወይም እየቀረ ቢመስልም አሁንም ይከናወናል። ሰውነታቸው ላይ የምንመለከታቸውም የተለያዩ ጠባሳዎች ራሳቸውን ለማስዋብና ለማጌጥ የከፈሉት መስዋትነት ነው።

የሙርሲ ወንዶች ከማግባታቸው በፊት ወንድነታቸውን ለማስመስከር ማከናወን ያለባቸው የዶንጋ ሥርዓት አለ። ይኼም ሥርዓት የጀግንነት ምልክታቸውና የሚፈልጓትን ኮረዳ ተጋጣሚውን በያዘው ዱላ ተፋልሞ ማሸነፍ ሲችል ነው።

ሙርሲዎች በአብዛኛው አርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደሮች ሲሆኑ፣ በዋናነትም በቆሎና ማሽላ ያመርታሉ። በቱሪስቶች ከመጎብኘት በተጨማሪ በራሳቸው ታሪካቸውን፣ ፖለቲካዊ ዕይታቸውን፣ ባህልና ትውፊታቸውን ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡

የሳውዝ ኦሞ ቴአትር ካምፓኒ ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ስኩል ኦፍ ኦሬንታልና አፍሪካን ስተዲስ፣ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጋር በመተባበር በሙርሲዎች የተሠራ ቴአትር እሑድ ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ለዕይታ አቅርቧል፡፡

ቴአትሩም በሙርሲዎችና በሙርሲ ቋንቋ የተሠራ ሲሆን፣ ‹‹ትራኒያ ኮ ኮይሣኒ›› የአማርኛ ፍቺው ‹‹ዳኛው›› የተሰኘ ርዕስ ይዟል፡፡

ቴአትሩም የመልቲ ሚዲያ ይዘት ያለውና በኢትዮጵያ እምብዛም ባልተለመደ መልኩ የቀረበ ሲሆን፣ አጫጭር ዶክመንተሪ፣ ትረካ፣ አጫጭር ፊልም፣ ትራዴሽናል ቴአትር፣ ኮሙኒቲ ቴአትር ሙዚቃና ሌሎች ተካተውበት የተሠራ ነው፡፡

እነዚህን ሁሉ ያካተተውን ቴአትር ሁለት ሰዓት ያህል ርዝመት ያለው ሲሆን፣ የቴአትርን ቅርፅ ጠብቆ የተሠራ እንደሆነ የቴአትሩ አዘጋጆች ገልጸዋል፡፡

የሙርሲ ብሔር 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሞቃታማ በሆነው በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኝ ሲሆን፣ ባህል፣ አመጋገብ፣ ማኅበራዊ አኗኗር፣ የጋብቻ ሥርዓት፣ ለቅሶና ሌሎችን ይዘው በመምጣት ቴአትሩ ላይ ማቅረብ ችለዋል፡፡

በተለይም የሙርሲ ሰዎች ልማትን እንደሚፈልጉ ነገር ግን መንግሥት የሙርሲን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም የሚያደርጋቸው አካሄዶች ማኅበረሰቡን ታሳቢ ያደረገ አለመሆኑን የቴአትሩ ይዘት ያሳያል፡፡

የሙርሲ ማኅበረሰብ በቆሎና ማሽላ ላይ በይበልጥ በመሥራት የመስኖ ልማትን እንደሚያስበልጡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ይህንን ሥራ ሲሠሩ ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ እንደሚገቡም ያሳያል፡፡

በሙርሲ ማኅበረሰብ ውስጥ ከሚታወቁ ነገሮች መካከል ዶንጋና ኦምባር የሚባሉ መጠሪያ ያላቸው ግጥሚያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

‹‹ዶንጋ›› የወንዶች ፍልሚያ ሲሆን፣ ‹‹ኦምባር›› ደግሞ ሴት ልጆች የሚያደርጉት ግጥሚያ እንደሆነ ቴአትሩ የሚያሳይ ነው፡፡

‹‹ዶንጋ›› በሙርሲ ማኅበረሰቦች ዘንድ የረዥም ጊዜ ታሪክ ከሆነ የቆየ ግጥሚያ ሲሆን፣ ሕፃናት ልጆች ሳይቀር ከአፍላ ዕድሜያቸው ጀምሮ ግጥሚያውን ለማድረግ ዝግጅት የሚያደርጉበት ነው፡፡ ‹‹ዶጋን›› ወንድ ልጅ የሚፈልጋትን ‹‹ሴት›› የጀግንነት ምልክቱን ለማሳየት ከተቃራኒ ጎራ ጋር የሚፋለም መሆኑን ይናገራል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚፈልጋትን ወይም የመረጣትን ሴት ልጅ ለማግባት ፍልሚያው አማራጭ ይሆንለታል፡፡

በሙርሲ ማኅበረሰብ ዘንድ አንድ ወንድ ልጅ የመረጣትን ሴት ልጅ ለማግባት 40 ከብቶችን ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡ አንድ ወንድ ልጅ የዶጋን ፍልሚያ ለመፋለም መጀመርያ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለፍልሚያው የሚሆነውን ዱላ ሄዶ የሚመርጥ መሆኑ በቴአትሩ ተመልክቷል፡፡

‹‹ቱላ›› ወይም ‹‹አምባር›› ደግሞ የሙርሲ ሴት ልጆች የሚያደርጉት ፍልሚያ ሲሆን፣ ይኼም የሚያደርጉት ፍልሚያ የጀግንነት ምልክታቸውን የሚያሳይ ይሆናል፡፡

‹‹አምባር›› ወይም ደግሞ ሴቶቹ የሚያደርጉት ፍልሚያ ከወንዶቹ የተለየ አለመሆኑን፣ የጀግንነት ይዘትን የሚያንፀባርቅና በወንዶቹ ዘንድ የመወደድ መንፈስ የሚሰጥ እንደሆነ ያወሳል፡፡

የሙርሲ ሴት ልጆች በተፈጥሮ የታደሉትን ቅንድባቸውን በመንቀል የሚታወቁ እንደሆነ፣ ውበታቸውንም የሚያዩበት መንገድ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ እንደሚለይ ይነገራል፡፡ ከንፈራቸውን፣ ሰውነታቸውን በመተልተል፣ ቅንድባቸውን ደግሞ በመላጨት ውበታቸውን እንደሚገልጹ ቴአትሩ ያሳያል፡፡

የሙርሲ ሰዎች ፀብ ወይም ያልተፈለገ ነገር ውስጥ ሲገቡ ሽማግሌዎች መሀል በመግባት ፀብን የሚያቆሙበት መንገድ እንዳለ ቴአትሩ ያሳያል፡፡

የሙርሲ ሴት ልጆች በወንዶች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆኑና በየጊዜው ውብታቸው እንዲጨምር ሰውነታቸውን በምላጭ እንደሚተለተሉ ያሳያሉ፡፡ በተለይም ከንፈራቸውን በመተልተልና ሸክላ በማስቀመጥ ውበታቸውን የሚጠብቁ ሲሆን፣ በየጊዜው ውበታቸውን በሚጠብቁ ጊዜ የሸክላው መጠን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ሙርሲዎች ከአጠገባቸው ወንድ ልጅ ካለ ሸክላውን ማድረግ የግድ እንደሆነ ይህ ባህል መሆኑንም ቴአትሩ ያሳያል፡፡

በቴአትሩ ላይም መንግሥትን፣ ራሱ የሙርሲ የማኅበረሰብ ክፍልን የሚወቀስ ሲሆን፣ በተለይም ደግሞ መንግሥት ሲተች የሚታይ እንደሆነ የቴአትሩ ፕሮዲውሰር አስተዋይ መለስ ይናገራል፡፡

26 የሚሆኑ ተዋናዮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ሰባቱ ደግሞ በቴአትሩ ላይ መሪ ተዋናይ ሆነው እንደሚሠሩ ፕሮዲውሰሩ ገልጿል፡፡

አብዛኛውን የሙርሲ ማኅበረሰብ ክፍሎች ከአካባቢያቸው እርቀው እንደሚሄዱና ለቴአትሩም ተዋናይ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማግኘት ችግር ሆኖባቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ተዋናዮችን ወደ ትወናው ለማምጣት አምስት ወራት ያህል ሥልጠና እንደተሰጣቸው የተናገሩት ፕሮዲውሰሩ፣ ቴአትሩም የሙርሲ ባህል፣ የእርቅና የሠርግ ሥርዓትና ሌሎችን የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

መሪ ተዋናይ የሆኑ ባለሙያዎች የመረጡበት አካሄድ የሙርሲን አኗኗር የሚያውቁና ቋንቋውን መናገር ከሚችሉ የሙርሲ ሰዎች ጋር በመሆን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሙርሲ ባህል፣ የአመጋገብ ሥርዓት ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የተለየና በአብዛኛውም የአካባቢው ተወላጆች ከአካባቢያቸው ወጥተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

በወንዶች ዘንድ የሚደረገው ‹‹ዶንጋ›› የተሰኘው ግጥሚያ የራሱ የሆነ ባህልና የሚደረግበት ጊዜ እንዳለው የሚናገሩት አቶ አስተዋይ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ለቱሪስቶች ብቻ እየተባለ ያለ ሥርዓቱ ፕሮግራሙ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በባህላቸው ላይ ትልቅ ችግር እንደገጠማቸው፣ ከዚሁ ጎን ለጎን መንግሥት የኦሞ ማጎ ናሽናል ፓርክ መሬታቸውን 70 በመቶ እንደወሰደባቸው ገልጸዋል፡፡

የሙርሲ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውና መብቶቻቸው እየተጠበቀ አለመሆኑን የገለጹት ፕሮዲውሰሩ፣ ማንነታቸውን በመጠበቅ መንግሥት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉም የሚገኘው የቱሪዝም ቢሮ ምንም ዓይነት ሥራ እየሠራ እንዳልሆነ ገልጸው፣ መስህቡን ለማሳደግና የሙርሲን ባህል ለማስጠበቅ መሥራት እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

በሙርሲዎችና በሙርሲ ቋንቋ የተሠራው ቴአትርም የመጀመርያ ዕይታ የቀረበው በዚያው አካባቢ ሲሆን፣ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ቴአትሩ እሑድ ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ለዕይታ ቀርቧል፡፡

ቴአትሩም እሑድ ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በብሔራዊ ቴአትር ለዕይታ የሚቀርብ ሲሆን፣ የሙርሲ ባህልንም ለማሳየት በቀጣይ በለንደን ለማሳየት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም በወቅቱ ተገልጿል፡፡

የሙርሲ ባህልን ያንፀባረቀው ቴአትርም ለዕይታ ከቀረበ በኋላ በቴአትሩ ላይ የተሳተፉት የሙርሲ ተወላጆች ‹‹አቻሌ›› ‹‹አቻሌ›› ‹‹አቻሌ›› ‹‹ሰላም›› ‹‹ሰላም›› ‹‹ሰላም›› በማለት አክብሮታቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...