የፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ በአዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀፅ 38(2) መሠረት ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 ድረስ ለሁለት ወራት ዝግ እንደሚሆንና ዳኞችም ዕረፍት እንደሆኑ ተደንግጎ የሚገኝ ቢሆንም፣ ዳኞች ግን አንደኛውን ወር ማለትም ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ለመሥራት መስማማታቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማክሰኞ ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡
አዋጁ የዳኞች የዕረፍት ጊዜ ብሎ በደነገጋቸው ወራት ውስጥ አስቸኳይ የሆኑ ጉዳዮችን ብቻ ሊያስተናግዱ እንደሚገባም ደንግጓል፡፡ በድንጋጌው መሠረት ምንም እንኳን ዳኞች ዓመቱን ሙሉ እጅግ አድካሚ የሆነ የዳኝነት አግልግሎት ሲሰጡና ሲሠሩ ቢቆዩም፣ ጊዜ የማይሰጡ የሕፃናት ቀለብን ጨምሮ አስቸኳይ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸውን ጉዳዮች በተመደቡ ችሎቶች አገልግሎቶችን ይሰጣሉ፡፡
እንደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መግለጫም ቀደም ብሎ በተሠሩ ሥራዎችም አዎንታዊ የሆኑ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ ይህን ሥራ ይበልጥ ለማስቀጠል፣ ወደ 2015 ዓ.ም. የሚያልፉ መዝገቦችን ቁጥር ለመቀነስ፣ የበሰሉ መዝገቦችን ዕልባት ለመስጠት፣ እስረኛ ያለባቸውን መዝገቦች ቅድሚያ ሰጥቶ ለመሥራት እንዲያስችል በዳኞች ፈቃደኝነት ላይ በመመሥረት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የነሐሴን ወር መደበኛውን የዳኝነት አገልግሎት መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞች ያላቸውን የዕረፍት ጊዜ መስዋዕት በማድረግ መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆናቸው አመሥግኖ፣ ተገልጋዮችም ሙሉ የነሐሴን ወር የፍርድ ቤቶቹን አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማለትም የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በ2014 ዓ.ም. በሕገ መንግሥትና በሕግ የተጣለባቸውን የዳኝነት አገልግሎቶችን ሲሰጡ መቆየታቸውንና በዚህም በ2014 ዓ.ም. በ12 ወራት ውስጥ 209,317 የሚሆኑ መዛግብት በሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቀርበው፣ 176,797 ለሚሆኑ ጉዳዮች ዕልባት ማግኘታቸውን አስታወቋል፡፡
ከሰኔ ወደ ሐምሌ 2014 ዓ.ም. የተላለፉ 32,520 መዛግብትም በመታየት ላይ እንደሚገኙና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አማካይ የማጥራት አቅም 103.7፣ የመጨናነቅ ሁኔታ 1.18፣ እንዲሁም የክምችት ምጣኔ 0.18 ማድረስ መቻሉን አክሏል፡፡ ይህም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በ2014 ዓ.ም የ12 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ከዓለም አቀፍ የፍርድ ቤቶች ውጤታማነት መለኪያ መሥፈርቶች አንፃር ሲታይ፣ የውጤታማነት ደረጃው ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያመለክት ገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ 300 የሚሆኑ መዝገቦች በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርዓት ዕልባት በማግኘታቸው ባለጉዳዮች በአጭር ጊዜና ሰላማዊ ግንኙነታቸውን አስጠብቀው አለመግባባታቸውን እንዲፈቱ ከማድረግ ባሻገር፣ የመደበኛ ችሎቶች የመዝገብ ጫና እንዲቀንስ መደረጉንም አክሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመርያን መነሻ በማድረግ፣ ጉዳዮች እንደየተናጠል ባህሪያቸውና የጊዜ ገደባቸው ዕልባት እንዲሰጣቸው ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህም በሦስቱም ፍርድ ቤቶች በአማካይ 90 ከመቶ የሚሆኑ ጉዳዮች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ዕልባት እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንና የወንጀል ጉዳዮችን በተመለከተ እስረኛ ያለባቸው መዛግብት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ዕልባት እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑንም አብራርቷል፡፡