በሐምሌ ወር የታየው ከመደበኛው ወቅት የተለየ ከባድ ዝናብ በወርኃ ነሐሴ አይሎ ስለሚከሰት በተዳፋት፣ በወንዞች፣ እንዲሁም በከተማ ውስጥ በትንንሽ ወንዞች አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩቱ አሳሰበ፡፡
በመደበኛ ሁኔታ በሐምሌና በነሐሴ ወር ከፍተኛ የዝናብ መጠን የሚመዘገብባቸው ወራት ቢሆኑም፣ በዘንድሮ ክረምት በተለይም በሰሜናዊና በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩቱ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ጫሊ ደበሌ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በሰኔና በሐምሌ ወራት የነበረው ዝናብ በተለይም በሰሜናዊና በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የተመዘገበ ነበር፡፡
በነሐሴ ወር የዝናቡ ሁኔታ በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ የሚዘንበው ዝናብ የአፈር እርጥበትን ከማግኘቱ የተነሳ ሲሆን፣ ዝናቡ ወደ ውስጥ ከመስረግ ይልቅ ወደ ጎርፍነት የመቀየር ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ የጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በነሐሴ ወር በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ለተከታታይ ሰዓታትና ቀናት የሚዘንብበት አጋጣሚ ስለሚኖር፣ የወንዞች ሙላትና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
የዘንድሮ ክረምት በናሚና ክፍተት ሥር ይገኛል ያሉት ወ/ሮ ጫሊ፣ ይህም ማለት በትሮፒክስ አካባቢ ያለው የፓስፊክ ውቅያኖስ የመካከለኛና ምስራቃዊ ክፍሉ የላይኛው የውኃ አካል ከመደበኛው በታች በመቀዝቀዙ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡ ቅዝቃዜው በበጋም ሆነ በበልግ ወቅት የነበረና ቀጣይነት ያለው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ለክረምቱ ዝናብ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በነሐሴ ወር ከኦሮሚያ ክልል የምዕራብ፣ የምሥራቅና የሆሩ ጉዱሩ ወለጋ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ጂማና አዲስ አበባ ዙሪያ፣ አዲስ አበባ ሁሉም የአማራ ክልልና የትግራይ ዞኖች፣ እንዲሁም የአፋር ክልል ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ላይም ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።
በተጨማሪም የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በረባዳማ፣ ውኃ ገብና በወንዝ ዳርቻ ባሉ ማሳዎች ላይ በሰብሎች፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል በተጠቀሱት አካባቢዎች ተገቢው የመከላከል ዕርምጃ ቢወሰድ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ የሚቻል መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
ከሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ጎርፍ፣ የወንዞች ሙላትና የመሬት መንሸራተት ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል የተባለ ሲሆን፣ በመሆኑም በየአካባቢው ኅብረተሰብና የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ኢንስቲትዩቱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
በከተሞች ግንባታ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የውኃ መሄጃ ቱቦዎቹ በትክክል ያልተሠሩ በመሆናቸው፣ እንዲሁም በከተማ ውስጥ የሚፈሱ ወንዞች ያሉበት ሁኔታ አሥጊ ከመሆኑ አኳያ ኅብረተሰቡ ቀንም ሆነ ሌሊት ሕይወቱንና ንብረቱን ከአደጋ ለመጠበቅ ክትትል ከማድረግ ባሻገር ትንበያዎችን መከታተል አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተዳፋት፣ በወንዞች፣ እንዲሁም በከተማ ውስጥ በትንንሽ ወንዞች አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ወቅት ክትትል ማድረግ ይገባቸዋል ያሉት ወ/ሮ ጫሊ፣ በተለይም ለጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸውን የተረዱ ግለሰቦችም ሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በተጎዳኝ የጎርፍ ቱቦዎችን በደንብ መጥረግ፣ የወንዝ ዳርቻዎችን መከታተልና ወንዝ የሚሞላ ከሆነ ከአካባቢው መራቅ አስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በአዲስ አበባ የክረምት ወራት ከገባበት ወቅት አንስቶ ባጋጠመ የጎርፍ አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ያጋጠመው ጉዳት በኮሚሽኑ የተረጋገጠውን ብቻ የሚያካትት መሆኑን ያሳወቁት አቶ ንጋቱ፣ በሌሎች ተቋማት የተመዘገበ ሌላ ተጨማሪ መረጃ ሊኖር እንደሚችል ተናግረው፣ ከሕይወት በተጨማሪ በሰዎችና በንብረት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡
አቶ ንጋቱ እንደገለጹት፣ የመጀመሪያው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ላዛሪስት ትምህርት ቤት በአንድ ሕፃን ልጅ የደረሰው ጉዳት ሲሆን፣ ሁለተኛው በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አማኑኤል ሆስፒታል አካባቢ ከባድ ዝናብ በመጣሉ ሳቢያ ጎርፍ የመጋዘን ግንብ በመደርመሱ ያጋጠመ የአንድ ወጣት ሕልፈት ነው፡፡
የነሐሴ ወር ዝናቡ የሚበረታበት መሆኑን የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው፣ የዝናብ መጠኑ በዚህ የሚቀጥል ከሆነም የሚደርሰው ጉዳት ከዚህ ሊበልጥ የሚችል መሆኑን ገልጸው፣ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት የአሥር ሰዎች ሕይወት ከጎርፍ አደጋ ጋር በተያያዘ ማጋጠሙን አስታውሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዓምና የደረሰው ጉዳት ዳግም እንዳይፈጠር የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽኑን ጨምሮ ሰባት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በትብብር እየሠሩ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በዚህ ጥምረት ውስጥ የተሰጠው ሚና የተጋላጭ ጥናት ማድረግና የጥናቱን ውጤት መፍትሔ ለሚሰጡ ተቋማት ማቅረብ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የመፍትሔ ሰጪ ተቋማት የድጋፍ ግንብ መሥራት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን ማስተካከል፣ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከቦታ ማዘዋወርና ሌሎችንም የተጋላጭ ጥናት ውጤትን መሠረት አድርገው የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ፈጣን ዕርምጃ እንደሚወስዱ ተገልጿል፡፡
የተጋላጭነት መጠኑ ካልተለያየ በስተቀር በሁሉም ክፍላተ ከተሞች የጎርፍ አደጋ እንደሚያጋጥም ያስታወቁት አቶ ንጋቱ፣ ነገር ግን በተያዘው ክረምት ያጋጠሙ አደጋዎች ሲታዩ አቃቂ ቃሊቲ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራንዮ፣ አዲስ ከተማ፣ ቦሌና ለሚ ኩራ በተደጋጋሚ አደጋ ማጋጠሙን አስረድተዋል፡፡