በከተማዋ ውስጥ ያሉ የግል ሕንፃዎች በታለመለት መንገድ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ በተለይም የመኪና ማቆሚያ ወለል ለሌላ አገልግሎት አውለዋል ያላቸው 23 ሕንፃዎች የንግድ ፈቃድ እንዲታገድ መጠየቁን አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በከተማዋ ውስጥ ያሉ የግል ሕንፃዎች ለታለመላቸው አገልግሎት መዋል አለመዋላቸውን በተመለከተ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ 1,360 ሕንፃዎች የመኪና ማቆሚያ ቦታ አጠቃቀም ኦዲት መደረጉን ያስታወቁት አቶ አረጋዊ፣ ይህም በአማካይ በአንድ ክፍለ ከተማ 100 የሚደርሱ ሕንፃዎች ላይ ምልከታ (ኦዲት) መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከከፍላተ ከተሞች ባሻገር በማዕከል ደረጃ 260 በሚደርሱ ሕንፃዎች ላይ ምልከታ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ በምልከታውም የ58 ሕንፃዎች የመኪና ማቆሚያ ወለል ለታለመለት ዓላማ ሳይውል መቅረቱን እንዳረጋገጠ ታውቋል፡፡
ድርጅቶቹ የተገኘባቸውን ክፍተትና የመመርያ መተላለፍ እንዲያስተካክሉ በወቅቱ እንደተገለጸላቸው ያስታወሱት አቶ አረጋዊ፣ ከዚያ ውስጥ 35 ባለሕንፃዎች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. አስተካክለው ፈቃዳቸው ወደ ነበረበት መመለሱን ገልጸው፣ 23 ባለሕንፃዎች የተገለጸላቸውን ባለማሟላታቸው ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ለሚመለከታቸው አካላት መረጃ መላኩን ተናግረዋል፡፡
ሕንፃውን ከታለመለት ዓላማ ውጭ አገልግሎት እንዲሰጥ ያደረጉ ባለሕንፃዎች ላይ ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች አንደኛው የደንብ ማስከበር ዕርምጃ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ሕንፃዎቹ እንዲታሸጉ ከማድረግ አንስቶ የንግድ ሕንፃዎች ከሆኑ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ የማድረግና በሕንፃው ላይ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ የማድረግ ዕርምጃን የሚያጠቃልል ነው ተብሏል፡፡ ይህንንም የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮና የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን እንደሚያስፈጽሙት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ምልከታው የተደረገባቸውና ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የተጠየቀባቸው ሕንፃዎች፣ በአብዛኛው በከተማው ከፍተኛ የሕንፃ ብዛት በሚገኝባቸው ቦሌ፣ አራዳ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ እንዲሁም አዲስ ከተማ ክፍላተ ከተሞች መሆናቸውን አቶ አረጋዊ አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን በ11 ክፍላተ ከተሞች ምልከታው ተደርጎ ችግሩ በተለያየ መጠን እንደሚገኝ መታወቁ ተገልጿል፡፡
የንግድ ፈቃዳቸው እንዲታገድ ጥያቄ የቀረበባቸው ሕንፃዎች ለመኪና ማቆሚያ የተዘጋጀውን ቦታ ወደ ነበረበት ቦታ የሚመልሱ ከሆነ፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዳግም ቅኝት አድርጎ ድርጅቶቹ አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ የማድረግ ዕድል እንደሚኖር ታውቋል፡፡
አቶ አረጋዊ እንዳስታወቁት፣ የከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው መመርያ መሠረት አንዳንዱ ባለሕንፃ የራሱ የሆነ በቂ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ሊኖረው እንደሚገባ በሕግ ይገደዳል፡፡ ይህም ሲባል ሁለት አማራጮችን ያስቀመጠ ነው፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ በቂ የሆነ ከሕንፃው ውጭ የመኪና ማቆሚያ ለተገልጋዮች ማቅረብ ሲሆን፣ ነገር ግን ከሕንፃው ውጭ በቂ የሆነ የመኪና ማቆሚያ ከሌለው በተለምዶ ቤዝመንት ተብሎ የሚጠራውን የምድር ክፍል ለመኪና ማቆሚያ እንዲጠቀም ይጠበቅበታል፡፡
አንድ ሕንፃ በውጭ በቂ የሆነ ማቆሚያ ካለው የምድር ክፍሎችን ለመኪና ማቆሚያ የግዴታ ያውል ተብሎ አይገደድም ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው፣ ነገር ግን በቂ የውጭ መኪና ማቆሚያ በሌለበት ሁኔታ የምድር ክፍሉንም ለመኪና ማቆሚያ ሥፍራነት ወይም ለታለመለት ዓላማ ካልዋለ አንድ ሕንፃ የመኪና መቆሚያ ሥፍራ የለውም ተብሎ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
በቂ የሆነ የመኪና ማቆሚያ ሳይኖር ሕንፃዎችን መገንባት ለተጨማሪ የትራፊክ አደጋ መጨናነቅና ሌሎች አደጋዎች እንዲከሰቱ ከማድረጉ ውጪ ባለጉዳዮች በአግባቡ እንዳይስተናገዱ እንቅፋት ይፈጥራል ያሉት አቶ አረጋዊ፣ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሕንፃዎች ለታለመላቸው ዓላማ ውለዋል ወይስ አልዋሉም የሚለውን ጉዳይ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገበት እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በ2015 የበጀት ዓመት አንዳንዱ ክፍለ ከተማ በትንሹ 200 የሚደርሱ ሕንፃዎችን ኦዲት እንደሚያደርግ የታወቀ ሲሆን፣ በጠቅላላው በበጀት ዓመቱ በማዕከልና በክፍለ ከተማ ከ2,600 በላይ ሕንፃዎች ላይ የሕንፃ ውስጥ የመኪና ማቆሚያ ቦታ አጠቃቀም ኦዲት ይደረጋል ተብሏል፡፡