Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሶማሌ ክልል በቀድሞ አስተዳደር የደረሱ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን የሚመረምር ኮሚሽን አቋቋመ

የሶማሌ ክልል በቀድሞ አስተዳደር የደረሱ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን የሚመረምር ኮሚሽን አቋቋመ

ቀን:

ከለውጡ በፊት በኢሕአዴግና በ(አብዲ ኢሌ) አስተዳደር ዘመን በሶማሌ ክልል የተፈጸሙ ኢሰብዓዊ ጥቃቶችን የሚመረምር ኮሚሽን እንዲቋቋም ተወሰነ፡፡ የክልሉ ምክር ቤት በፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ ኡመር የቀረበውን ሐሳብ ሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ያፀደቀ ሲሆን፣ የመርማሪ ኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅም ፀድቋል፡፡ ኮሚሽኑ ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን፣ በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ ፈጽሟል፡፡

ውሳኔው በአብላጫ ድምፅ ከመፅደቁ በፊት ግን የተቃውሞ ክርክሮች የቀረቡ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ከፍ ያለ የምክር ቤት አባላት ድምፀ ተዓቅቦና ባለመደገፍ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

መርማሪ ኮሚሽኑ በዋናነት የሚያተኩረው በኦብነግና የሶማሌ ልዩ ኃይል መካከል በነበሩት ግጭቶች ሰለባ የሆኑ ንፁኃንና ተጎጂ ቤተሰቦችን ለመካስ፣ በፈጻሚዎቹ ላይ ፍትሕን ለማስፈንና ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ነው ተብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው ቀደም ብሎና ለተወሰነ ጊዜ በቀጠለው ግጭት፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ ኢሌ የሚመራው ልዩ ኃይል በእሱ በሚደገፉት ሄጎ የሚባል ኢመደበኛ አደረጃጀትና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) መካከል በነበሩት ከፍተኛና ተከታታይ ግጭቶች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ቤት ንብረታቸው ወድሞ ለስደት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

ከሕወሓት ትዕዛዝ ይቀበሉ ነበር የሚባሉት የቀድሞ ፕሬዚዳንት አብዲ ኦሌ፣ ኦብነግን ለማጥፋት እንዲሁም የሌላ ክልል ተወላጆች ኢሰብዓዊ ጥቃቶች እንዲፈጽሙ አዘዋል የተባለ ሲሆን፣ ከአጎራባች ክልሎች ኦሮሚያና አፋርም ንፁኃንን ሰለባ አድርገዋል፡፡

‹‹በወቅቱ የኦብነግም ሆኑ የአብዲ ኢሌ ኃይሎችም በሕዝቡ ውስጥ የየራሳቸው ደጋፊዎች ነበራቸው፤›› ያሉት አንድ የክልሉ ባለሥልጣን፣ ሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በነበረው ድምፅ አሰጣጥ ላይ የኮሚሽኑን መቋቋም ያልደገፉ፡፡ ከለውጡ በኋላ ኦብነግ ወደ ሰላማዊ ትግል ገብቶ ከክልሉ መንግሥት ጋር እየሠራ ሲሆን፣ አብዲ ኢሌም በፌዴራል መንግሥቱ በ2010 ዓ.ም. ሐምሌ ወር በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመርማሪ ኮሚሽኑን መቋቋም የማይደግፉት የምክር ቤቱ አባላት ጊዜው መዘግየቱንና በዚህ ሰዓት የክልሉ መንግሥት ሌሎች አጣዳፊ ጉዳዮች እንዳሉበት አውስተዋል፡፡

‹‹ያኔውኑ ኮሚሽኑ ቢቋቋም ጥሩ ነበር፡፡ እስከ ዛሬ ዕርቅ ያላወረዱም ያልተካሱ ሰለባዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት ሊታይ ይችላል፤›› ይላሉ ባለሥልጣኑ፡፡

በተለይ የአልሸባብ ጥቃት ክልሉን በከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት ላይ በጣለበት ሰዓት የክልሉን ሕዝብና ኃይል በመከፋፈል ጉዳይ መወጠር እንደሌለበት አንስተው የሚከራከሩ ያሉ ሲሆን፣ ቢዘገይም ፍትሕ መሰጠት እንዳለበት የሚያነሱ የክልሉ ባለሥልጣናትም አሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ሰዓት የኦብነግ ኃይሎች ከክልሉ ልዩ ኃይልና መከላከያ ጋር ሆነው አልሸባብን እየተዋጉ ነው፡፡ መርማሪ ኮሚሽኑ ሥራ ሲጀምር በክልሉ ውስጥ መከፋፈል እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል፡፡ አልሸባብ ለአሁኑ ቢሸነፍም ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት ነው፡፡ ያለን የድንበር ወሰን ረዥም መሆንና አንዳንድ በክልሉ አስተዳደር ደስተኛ ያልሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለሽብርተኛ ቡድኑ መደላድል መሆን ትልቅ ትኩረት የሚፈልግ ሥራ ነው፡፡ በክልሉ ለተፈጠረው የድርቅ አደጋ በቂ ምላሽ ባለመሰጠቱ አልሸባብ ደግሞ ገንዘብ ስላለው የተወሰኑ ኅብረተሰብ ክፍሎችና የድርቅ ተጎጂዎችን ልብ እያሸፈተ ነው፤›› ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የክልሉ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ በተለይ በኦጋዴን እስር ቤት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ አንደነበር የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ አብዲ ኢሌ ግን ለተፈጸሙት ጥሰቶች ተጠያቂው የኢሕአዴግ ደኅንነት ኃላፊው የጌታቸው አሰፋ ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡

‹‹በሕዝቡ ውስጥ መተማመንና ፍቅርን እንዲሁም የመንግሥት ግልፀኝነትን ለማስፈን ለተፈጠሩት ነገሮች ሁሉ ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ ያለፈውን ማንሳት የለብንም የሚሉ አሉ፣ ግን የተጎዳ ኅብረተሰብ ደግሞ አለ፡፡ የአንድ አገር ወገን ሆነን በአዲስ መንፈስ አገር ለመገንባት ሁሉንም እያጠራን መሄድ አለብን፡፡ ዴሞክራሲን መለማመድ አለብን፡፡ በጦርነት ሕይወት ከመቅጠፍ በፊት የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አለብን፤›› ያሉት የክልሉ መንግሥት አማካሪ አቶ አብዲሰላም እስማኤል፣ ኮሚሽኑን ማቋቋም ጊዜ የወሰደው መንግሥት በሌሎች አጣዳፊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ስለነበረ ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ የትኞቹን ጉዳዮችና ከመቼ እስከ መቼ የተፈጸሙትን ሰብዓዊ ጥሰቶች መመርመር እንዳለበት ኮሚሽኑ ራሱ መወሰን እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በጊዜ ሊወሰንም ይችላል ወይም ከሥር መሠረቱ ጀምሮ ላጥና ሊልም ይችላል፤›› ብለዋል አቶ አብዲሰላም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...