በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ሰባ ቦሩ ወረዳ በተከሰተው ረሃብ ምክንያት አሥራ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የቡሳ ጎኖፋ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቡሳ ጎኖፋ ቢሮ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ብቻ በረሃብ ምክንያት የአሥራ ሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ለሪፖርተር ገልጿል፡፡፡
በጉጂ ዞን የሰባ ቦሩ ወረዳ የቡሳ ጎኖፋ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሞኮና ሆጤሳ እንደተናገሩት፣ በወረዳው 35,442 ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡
እነዚህ ዜጎች ድሬሳ በንሳ፣ ደጋላልቻ፣ ሰባሎሌማሞ፣ ኡቱሉ፣ ኦዴ፣ ሀራጌሳ ቀበሌዎች ከፍተኛ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡
ለወረዳው አልፎ አልፎ የምግብ ዕርዳታ እንደሚመጣ፣ ነገር ግን ምግብ ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በወረዳዎች በረሃብ ምክንያት የሟቾች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን አቶ ሞኮና ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የምግብና መሰል ዕርዳታዎች መቋረጣቸውንና ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጡን ገልጸዋል፡፡
በወረዳው አስቸኳይ የምግብ እጥረት ቢኖርም ትኩረት ሰጥተው የሚዘግቡ የመገናኛ ብዙኃን አለመኖሩን የገለጹት አቶ ሞኮና፣ ረሃቡ ሥር የሰደደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የጉጂ ዞን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ኦልኮ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የጉጂ ዞን ቆላማ አካባቢዎች ማለትም አምስት ወረዳዎች ውስጥ ድርቅ ተከስቷል፡፡
እነዚህ ወረዳዎች ከሶማሌ ክልልና ከቦረና ዞን ጋር የሚዋሰኑ ቦታዎች መሆናቸውን በመግለጽ፣ ከፍተኛ የዝናብ እጥረት በመኖሩ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ዜጎች ብዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በረሃብ ምክንያት ሞቱ ስለተባሉ ዜጎች መረጃ እንደሌላቸው፣ ነገር ግን አካባቢው የፀጥታ ችግር ያለበት መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
አምስቱ ወረዳዎች ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ውስጥ አንዱ በቆሎ መሆኑን፣ በተያዘው ዓመት የተዘራው አዝዕርት እንዳልበቀለ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
በሰባ ቦሩ ወረዳ የተፈጠረው ችግሩ ሊኖር እንደሚችል የገለጹት አቶ ዮሐንስ፣ ስለሞቱ ዜጎች ምናልባት በፀጥታ ችግር ምክንያት ሊሆንም ይችላል ብለዋል፡፡
ጉሜ ኤልደሎ፣ ሊበን፣ ጎሮ ዶላ፣ ዋደራ፣ ግርጃ፣ ሰባቦሩ ወረዳዎችና አዶላ ሬዴ ቆላማ ሰባት ቀበሌዎች ላይ ድርቅ መከሰቱን ገልጸዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ እንዳስረዱት፣ በረሃብ ሞቱ የተባለው የወረዳው ከፊል ቀበሌዎች ላይ በኦነግ ሸኔ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ናቸው፡፡
በወረዳው መንግሥት አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ማቅረብ እንደማይችል፣ ለገበያ የወጡትን ዜጎች ኦነግ ሸኔ 200 ብር ግብር እንደሚያስከፍላቸው መረጃ እንደደረሳቸው ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ በፀጥታ ችግር ምክንያት በአካባቢው የምግብ ዕርዳታ ማቅረብ አለመቻሉንም አስረድተዋል፡፡
የዞኑን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ከሰጡን መረጃ በተጨማሪ የዞኑን የቡሳ ጎኖፉ ኃላፊ ለመጠየቅ በተደጋጋሚ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡