የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን መሆን ለአኅጉሪቱ ዕድገት አንድ የማዕዘን ድንጋይ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ አፍሪካውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ከኃያላን አገሮች ተፅዕኖ የሚላቀቁበት ሌላው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኃይል ነው፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ በአካባቢውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖራት የሚገባትን ትልቅ ሥፍራ የሚያቆናጥጥ ነው፡፡ ግድቡ እኛ ኢትዮጵያውያን ተባብረን ከሠራን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ የሚያስገኝልን መሣሪያ እንደሆነም መታወቅ አለበት፡፡ በዓባይ ተፋሰስም ሆነ ከተፋሰሱ ውጪ ካሉ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ስንቀናጅ ደግሞ፣ አፍሪካን የዳቦ ቅርጫት ለማድረግ የሚያስችል ዕምቅ ኃይል እንዳለን ማሳያም መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟን በበጎ ተስፋ እያስነሳ ያለው የኩታ ገጠም ስንዴ ልማትና ሌሎች ሥራዎች ሲታከሉ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ሰላማቸውን በአስተማማኝ መንገድ ማስቀጠል ሲችሉ መጪው ጊዜ የመትረፍረፍ እንደሚሆን ጥርጣሬ አይኖርም፡፡
ይሁንና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት መከናወኑ፣ ወይም በኩታ ገጠም እርሻ ስንዴ ማብቀልና ሌሎች ተስፋ ሰጪ ልማቶችን ማቀድ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን ለአገራችን ዘለቄታዊ ህልውና ስንል ሥርዓት መያዝ አለብን፡፡ ይህ ሥርዓት አገርን ከሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ጀምሮ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ በየደረጃው ያሉ ሹማምንት፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ የእምነት መሪዎችና ምዕመናን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሙያና የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮችና በዙሪያቸው ያሉ፣ እንዲሁም በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በሙሉ ይመለከታቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትለማውና የምታድገው በሕግና በሥርዓት ማስተዳደርና መተዳደር ሲቻል ነው፡፡ ሥርዓተ አልበኝነትና ሕገወጥነት የሚሰፍኑት የሕግ የበላይነት ሲገረሰስ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከላይ እስከ ታች ልዩነቶቻቸውን ይዘው ለአገራቸው በአንድነት መቆም ሲችሉ፣ ድህነትን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ማድረግ ይቻላል፡፡ በተፈጥሮ የበለፀገች ዕድለኛ አገር ይዞ ምንም ሳይሠሩ ድህነት ውስጥ ተወዝፎ መነታረክና መጋጨት አስነዋሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በቀጥታም ሆነ በውክልና ለጥቃት የሚነሱት፣ ኢትዮጵያውያን ለኩርፊያ በማይበቁ ሰበቦች እርስ በርስ ሲባሉ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡
በቅርቡ አልሸባብ አድርጎት የማያውቀውን የኢትዮጵያ ድንበር ድረስ መጥቶ ጥቃት መፈጸሙ፣ ከበስተጀርባው ያለውን ጂኦ ፖለቲካዊ ፍላጎት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ከውስጥና ከውጭ ወጥሮ መፈናፈኛ የማሳጣት ፍላጎት ያለው የውጭ ኃይል፣ የሦስተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ለማሰናከል የአልሸባብን ጥቃት እንደሚያቀነባብር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አልሸባብ ከባድ ምት ደርሶበትና አመራሮቹን ሰውቶ ለጊዜው ቢሸሽም፣ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ የማይዋጥላቸው ሌላ ሴራ እንደሚሸርቡም የታወቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ ስትዳከም የሚጎዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ኃይሎች በሙሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ፡፡ ግባችሁን ሥልጣንና የሚያስገኘው ጥቅም ላይ ያደረጋችሁ የመንግሥት ሹማምንትም ሆናችሁ፣ ለሥልጣን የምትፎካከሩ በሙሉ ከራሳችሁ በፊት የአገርን ጥቅም አስቀድሙ፡፡ በሕዝብ ደምና ላብ የምታላግጡም ከድርጊታችሁ ተቆጠቡ፡፡ ኢትዮጵያ የምትለማውና የምታድገው በሸርና በክፋት ሳይሆን በተባበረ መንፈስ ነው፡፡ ለብሔራዊ ጉዳይ ለመተባበር ደግሞ የብሔርና የእምነት አጥር አያስፈልግም፡፡
ኢትዮጵያ በሚያኮራ ሁኔታና በሚገባ በተጠና መንገድ ሦስተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት በማከናወን በዓለም ፊት ግርማ ሞገስ ስታገኝ፣ መንደርተኝነት አስተሳሰብ ውስጥ መዘፈቅ እንደሚያስንቅ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭ ኃይል መሆን የምትችለው፣ ለስሟና ለክብሯ ከማይመጥኑ ከንቱ ነገሮች በመራቅ ነው፡፡ ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚያጠቁት ለኢትዮጵያ ደረጃ የማይመጥን ድርጊት ውስጥ ስንርመጠመጥ ነው፡፡ የግድቡን ሦስተኛ ዙር ውኃ ሙሌት የታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች (ሱዳንና ግብፅ) ጉዳት ሳይደርስባቸው በስኬት ሲጠናቀቅ፣ የኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ ምን ያህል ታማኝና ቃሉን ጠባቂ እንደሆነ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶ እንዲወጣ ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግብፅ አሁንም ይህንን እውነታ እየካደች ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ለውንጀላ ስትሄድ፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እግር በእግር እየተከታተሉ የማጋለጥ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ማሸርገድ ወንጀል ብቻ ሳይሆን፣ በታሪክና በትውልድ ኃፍረት የሚያከናንብ ቅሌት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ አንገቷን ቀና አድርጋ በኩራት መረማመድ እንድትችል ለማድረግ፣ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ በመንግሥት በኩል ተቋማትን በማጠናከር የግለሰቦችን ፈላጭ ቆራጭነት ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ከተቋማት በላይ ግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭ ሲሆኑ በሥልጣን መባለግ፣ ዘረፋ፣ በጥቅም መደራጀት፣ አገልግሎት መንፈግ፣ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን መፈጸምና ሥርዓተ አልበኝነትን ማንሰራፋት ይከተላል፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በየዕለቱ ምሬት የሚፈጥሩ ድርጊቶች ሲባባሱ፣ በሕዝብና በመንግሥት መሀል ሊኖር የሚገባው ጤናማ ግንኙነት ይበላሻል፡፡ በዚህም ምክንያት ተቃርኖው እየሰፋ አንድነት ይጠፋል፡፡ አንድነት ሲጠፋ ደግሞ ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥና ከውጭ በወኪሎቻቸው አማካይነት ጥቃት ይከፍታሉ፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የመንግሥት ሥልጣን በያዙ ግለሰቦችና ተከታዮቻቸው አማካይነት በሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ የክፋት ድርጊቶች መብዛታቸው፣ ሊኖር የሚገባውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ለመበተን እንደሆነ አለመገንዘብ ዋጋ ያስከፍላል፡፡
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከላይ እስከ ታች መዋቅሩን አጥርቶ አገር መምራት የሚቸገረው፣ ውስጡ በተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች በተወጠሩ ግለሰቦች በመወረሩ እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡ ከመሀል እስከ ዳር ባሉ በርካታ ሥፍራዎች ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት እየታደኑ የሚጨፈጨፉት፣ የሚፈናቀሉት፣ የሚሳደዱትና የሚዘረፉት ኢትዮጵያ አንገቷን እንድትደፋ በሚፈልጉ ኃይሎችና ተላላኪዎቻቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቀና ስትል ተደማጭነታቸው የሚጠፋባቸው ኃይሎችና ውሉ በማይታወቅ የታሪክ ድሪቶ ሰበብ ሊያፈራርሷት የሚሞክሩ ሲነሱ፣ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንደ ጀግኖቹ አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው አደብ የማስገዛት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ የአኮኖሚ የበላይነት ለማግኘት የሚደረጉ ሕገወጥ ጥረቶችን በማክሸፍ፣ በኢትዮጵያ ምድር ማኅበራዊ ፍትሕ የማስፈን ተቀዳሚ ኃላፊነት አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ የጋራ ቤት እንጂ፣ አንዱ ባለቤት ሌላው መጤ ተብሎ የሚለይባት መሆን የለባትም፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየው፣ በታላቅ መስዋዕትነት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለኢትዮጵያ ልማት፣ ዕድገትና ህልውና አሁንም የጋራ ግንዛቤ ይኑር፡፡ የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!