Friday, September 29, 2023

የትምህርት ዘርፍ በግጭት ሳቢያ ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም 2.2 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በስድስት ክልሎች ውስጥ በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የትምህርት ዘርፍ ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም 2.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው የግጭት ተፅዕኖ ዳሰሳና የማገገሚያ ዕቅድ ሰነድ አመላከተ፡፡

ይህ የገንዘብ መጠን በአምስት ዓመታት ውስጥ አጠቃላይ ዘርፉ እንዲያገግም ለሚሠራው ሥራ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 464.8 ሚሊዮን ዶላር በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሚሠራው ሥራ እንደሚያስፈልግ ሪፖርተር ሚኒስቴሩ ካዘጋጀው ሰነድ ላይ ተመልክቷል፡፡ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ 1.02 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በማገገሚያ ዕቅዱ ላይ ተቀምጧል፡፡

ሚኒስቴሩ በዚህ ሰነድ፣ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን በተከሰቱ ግጭቶች በትምህርት ዘርፉ ላይ የደረሰውን ጉዳት ዳሷል፡፡ በእነዚህ ክልሎች ውስጥ በተከሰቱት ግጭቶች ሳቢያ 2681 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለመሉ ሲወድሙ፣ 4158 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ሰነዱ ሲዘጋጅ ማግኘት በተቻለው መረጃ መሠረት 38 የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት እንዲሁም ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ‹‹ከፍተኛ መጠን ያለው›› ጉዳት እንዳስተናገዱ ጥናቱ አሳይቷል፡፡

በዚህም ምክንያት 4.2 ሚሊዮን ተማሪዎች እንዲሁም 200 ሺሕ ገደማ መምህራንና ሠራተኞች ተጎድተዋል፡፡ ይኼ ጉዳት ሞት፣ የአካል ጉዳትና መፈናቀልን ጨምሮ በተለይ በተማሪዎች ላይ የደረሰን የትምህርት ዘመን መዛባትን ያካትታል፡፡

በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ለማወቅ በሚያስችል ሁኔታ መረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ የሚጠቅሰው ሰነዱ፣ በተገኘው መረጃ መሠረት ግን በዘርፉ ላይ የደረሰው ጉዳት 1.9 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚገመት ተቀምጧል፡፡

የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መገንባትን ጨምሮ ዘርፉ በአጠቃላይ ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም የሚያስፈልገው የኢንቨስትመንት መጠን 2.2 ቢሊዮን ዶላር ድረስ እንደሚሄድ የሚኒስቴሩ የማገገሚያ ዕቅድ አሳይቷል፡፡

ሰነዱ እንደሚያመላክተው ከስድስቱ ክልሎች ውስጥ በትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው በትግራይ ክልል ነው፡፡ በክልሉ ከ1,300 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ሲወድሙ፣ 678 ያህሉ በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በቀጣይ የተቀመጠው የአማራ ክልል ከአንድ ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ወድመውበት፣ ከሦስት ሺሕ በላይ የሚሆኑት በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህም በክልሉ ካሉት ትምህርት ቤቶች 42 በመቶው ተጎድተዋል እንደማለት ነው፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ደቡብ ክልል በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል፡፡

በእነዚህ ክልሎች በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመመለስ 1.36 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ይህም በአጠቃላይ ዘርፉ እንዲያገግም ከሚያስፈልገው 2.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 62.2 በመቶው የሚፈሰው በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ መሆኑን ያሳያል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ በሰነዱ ላይ የተካተቱት በአማራ ክልል የሚገኙት ወሎ፣ ወልዲያና መቅደላ አንባ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲ የደረሰበት ጉዳት 243.3 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ በሰነዱ ላይ ተቀምጧል፡፡

በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት በመረጃ ማጣት ምክንያት እንዳልተካተተ ሰነዱ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ሰነዱ በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን እንዳላከተተ ተጠቅሷል፡፡

የማገገሚያ ዕቅዱ እንደሚያሳየው ዘርፉ እንዲያገግም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ ሥራዎችን ለመሥራት ታስቧል፡፡ ትምህርት በአስቸኳይ ለማስጀመር ጊዜያዊ ማስተማሪያ ስፍራ ማዘጋጀት፣ የወደሙና የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ መገንባት፣ ለተማሪዎችና መምህራን ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ድጋፍ ማድረግና ለትምህርት ቤቶች የገንዘብ ድጋፍ ማዘጋጀት ከሚሠሩት ሥራዎች መካከል ናቸው፡፡

በግጭቶቹ የተነሳ ወላጆች የኢኮኖሚ ድቀት ስለሚያጋጥማቸው ከዚህ ቀደም የትምህርት ቤት ምገባ ባልነበረባቸው አከባቢዎች ላይም ፕሮግራሙን ለማስጀመር ታቅዷል፡፡ የመልሶ ግንባታው ሲጀመር ለስድስት ወር ያህል በግጭት ከተጎዱት ተማሪዎች መካከል 20 በመቶውን፣ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ደግሞ አሥር በመቶውን ለመመገብ እንደታቀደ ሰነዱ ያሳያል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የግጭት ምክንያት ትምህርት የተቋረጠባቸውን ቀናትና ተማሪዎች በጊዜ ርዝመት የረሷቸውን ትምህርቶች ለማካካስ የካሪኩለም ክለሳ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ዕቅዱ ጠቁሟል፡፡

ለትምህርት ዘርፉ ማገገሚያ የተዘጋጀው ዕቅድ አምስት ዓመት የሚፈጅና በሦስት ምዕራፎች የተከፈለ ነው፡፡ የመጀመሪያ ምዕራፍ እስከ ስድስት ወር ሲቆይ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ይዘልቃል፡፡ የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ ከሦስተኛ እስከ አምስትኛ ዓመት ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው፡፡

ከወራት በፊት የፌዴራል መንግሥት በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚደረግለት የ19 ቢሊዮን ብር የብሔራዊ መልሶ ግንባታና ነዋሪዎችን ማቋቋም ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ለአምስት ዓመት የሚቆየው ይኼ ፕሮጀክት በጦርነትና ግጭቶች የተጎዱትን የትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን የሚያካትት ነው፡፡

የዓለም ባንክም ለፕሮጀክቱ 15.6 ቢሊዮን ብር ወይም 300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ይኼ የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት በትግራይ ክልል የሚከናወነው በሦስተኛ ወገን ሲሆን የፌዴራል መንግሥት ለዚህ ሥራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎቶች ጽሕፈት ቤትን መወከሉ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -