Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ ኩባንያዎች ከመዳረሻቸው የመረካከቢያ ሰነድ ካላመጡ ነዳጅ እንዳይጭኑ ትዕዛዝ ተላለፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የነዳጅ ኩባንያዎች፣ ነዳጅ አመላላሽ ቦቴ ተሽከርካሪዎቻቸው ከጂቡቲ ነዳጅ ሲቀዱ፣ ከዚህ በፊት የጫኑት ነዳጅ መዳረሻው ደርሶ ስለመራገፉ የርክክብ ሰነድ እንዲያመጡ፣ ካልሆነ ግን ከነገ ከሐሙስ ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ነዳጅ መጫን እንዳይፈቀድላቸው የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ከዚህ በተጨማሪም ቦቴዎቹ ነዳጅ ቀድተው ሲወጡ ስለመዳረሻቸው ሙሉ መረጃ ለጥፈው መውጣት እንዳለባቸው፣ በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሃረላ አብዱላሂ፣ ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፈርሞ የወጣውና ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተጻፈ ደብዳቤ ያሳያል።

የኩባንያዎቹ ቦቴዎች የርክክብ ሰነድ የሚያገኙት በየማደያው አካባቢ ካሉ የወረዳ ንግድ ቢሮዎች ሲሆን፣ ይህም የሚሆነው የንግድ ቢሮዎች ባለሙያዎች ቦቴዎቹ ነዳጁን ለማደያዎች ሲያስረክቡ እዚያው ማረጋገጫቸውን በመስጠት ነው። ስለቀጣይ መዳረሻዎቻቸውም ሙሉ መረጃ በመስጠትና በመለጠፍ ይቀዳሉ ተብሏል።

የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በመመርያው ይህን እንዲያስቀድም የታዘዘ ሲሆን፣ የነዳጅ ኩባንያዎቹም ይህን አውቀው የማይታዘዙ ከሆነ መጫን እንደማይችሉ ማወቅ እንዳለባቸው የባለሥልጣኑ የነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት ዳይሬክተር አቶ ደረሳ ቆቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል። ‹‹ለኩባንያዎቹ በደብዳቤም አሳውቀናል፡፡ ይህን ካላደረጉ ዳግም ነዳጅ ለመጫንና ሥምሪት ለማድረግ አይችሉም፤›› ሲሉም አክለዋል።

የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ተግባራዊ እንዲያደርግ ያዘዘው ደብዳቤ ዓላማ፣ ባለፈው ወር የወጣውን የነዳጅ ውጤቶች የሥርጭት፣ ርክክብና ሽያጭ አፈጻጻም መመርያ ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ ሲሆን፣ በዚህም ከጂቡቲ እስከ ማደያ ድረስ ይፈጸማል የሚባለውን የኮትሮባንድ ንግድ ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንደሚኖረው ታምኗል፡፡

ከማደያ የሚወጣ የነዳጅ ኮንትሮባንድን ቁጥጥርን በተመለከተም አቶ ደረሳ እንደገለጹት፣ ነዳጅ ከተጠቃሚዎች ባሻገር ለማንም አይሸጥም፡፡

የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም የእዚህን ትዕዛዝ ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚነት ጥያቄ ውስጥ ያስገቡ ሲሆን፣ ለተግባራዊነቱም የባለሥልጣኑ ክትትል ማነስ እንደ ችግር ሊገለጽ እንደሚችል አሳስበዋል። ለዚህም እንደ ማሳያ ያነሱት ለመመርያው ከሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ምንም ትኩረት አለመደረጉን በመጥቀስ ነው።

‹‹እስካሁንም ላወጡት መመርያ ተግባራዊነት ክትትል ማድረግ ነበረባቸው፡፡ እነሱ ካልሠሩ ኩባንያዎቹ ለእኛ አይታዘዙም፤›› ሲሉ አቶ ታደሰ ለሪፖርተር ገልጸዋል። ባለሥልጣኑ በሚወጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ድንገተኛ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት፣ የመዳረሻ መረጃ ያላሟሉትን በመቅጣት ችግሩን መቅረፍ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጂቡቲ በሚገኘው ነዳጅ መቅጃ ይህን አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን ከለጠፈ መቆየቱን፣ የቦቴ ተሽከርካሪዎች ትዕዛዙን አለማክበራቸው እንዳስቸገረው አቶ ታደሰ ገልጸዋል። ‹‹ካላሟላችሁ ነዳጅ አንቀዳም የማለት ችግር የለብንም፡፡ ነገር ግን የቦቴዎቹ ባለቤቶች ጉዳያቸውም አይደለም፣ እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ትርምስ፣ እጥረት እንዲከሰትና ሠልፍ እንዲሆን ምክንያት ስለሚሆን ይፈልጉታል፤›› ሲሉ ውሳኔው የሚያስከትለውን ችግርም ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ገና ጂቡቲ ሳይደርሱ ከአዳማ ወይም ከአዲስ አበባ ሳይርቁ መረጃ እያሟሉ እንዲሄዱ ቢያደርጉና ቢቀጧቸው፣ እርስ በእርስ እየተነጋገሩ መረጃቸውን እንደሚያሟሉና ይህም ችግር እንደማይፈጠር አቶ ታደሰ መፍትሔ ብለው ያሰቡትን ተናግረዋል። ‹‹አሁንም ቢሆን እኛ እንለጥፋለን፣ ግን አንጭንም ካሉን ጂቡቲ ያለውም መኪና ይቆማል፣ መንገድ ላይ ያለውም አይመጣም፤›› ብለዋል።

ለአቶ ታደሰ የንግድ ቢሮዎች ሰነድ አሰጣጥም ሌላው ጥያቄ የሚያስነሳ ችግር ጉዳይ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ሳይደርሱ ደረሱ እያሉ ሰነድ የሚሰጡ መገኘታቸውን ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች