Monday, September 25, 2023

በባሌ ዞን ከ8,000 በላይ ዜጎች በድንበር ግጭት ሳቢያ መፈናቀላቸውን ተናገሩ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

  • በዞኑ የተፈናቃዮች ቁጥር ብዛት 53 ሺሕ ደርሷል
  • 400 ሺሕ ዜጎች በድርቅ ተመተዋል

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት 8,759 ዜጎች መፈናቀላቸው ተገለጸ፡፡ ዜጎቹ በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ ጉራ ዳሞሌ ቀበሌ ነዋሪ እነደነበሩ፣ ከአንድ ወር በፊት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ በኮሌ ጎልባ ቀበሌ መጠለያ መስፈራቸው ታውቋል፡፡

ግጭቱ ሁለቱ ክልሎች ከሚያዋስናቸው ስድስት ወረዳዎች አንዱ በሆነው በጉራ ዳሞሌ ቀበሌ የተከሰተ ሲሆን የመሬት ሽሚያ፣ ወሰን አልፎ ማረስና በኢንቨስትመንት ምክንያት መሬት ለመያዝና ግዛት ማስፋፋት የመፈናቀሉ ዋና መንስዔ መሆናቸውን የኦሮሚያ የአደጋ መከላከል ዝግጁነት ቢሮ ዞን (ቡሳ ጎኖፋ) ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ከበደ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ወንድማገኝ ገለጻ፣ ከ2009 ዓ.ም. ወዲህ በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ቀበሌዎች ተደጋጋሚ ግጭቶች እየተለመዱ መምጣታቸውን ጠቅሰው፣ በስድስት ወረዳዎች 53 ሺሕ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡

በስድስት ወረዳዎች የሚዋሰኑ ሁለቱ ክልሎች በባሌ ዞን ሥር ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል መደወላቦ ወረዳ ከሦስት ዓመት በፊት በተፈጠረ የድንበር ግጭት ምክንያት፣ 18,600 አባወራዎች በደሎ መና ወረዳ፣ በራቅ በሚባል ቀበሌ አሥር ሺሕ ተፈናቃዮች፣ እንዲሁም በሌላኛው የደሎ መና በከሌ ጎልባ ቀበሌ ከወራት በፊት የተፈናቀሉ 8,759 ዜጎች መኖራቸውን አቶ ወንድማገኝ አስረድተዋል፡፡

በሌላኛው ጉራ ዳሞሌ ቀበሌ በሦስት ጣቢያዎች የሠፈሩ ከ15,000 በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን፣ በደሎ መና ወረዳ ሆከልቱ ቀበሌ ከአሥር ሺሕ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ መሐመድ አደም ሮባ ከወር በፊት ከመኖሪያ ቀዬአቸው ከተፈናቀሉ አባወራዎች አንደኛው ሲሆኑ፣ ለሦስት ወራት ከበባ ተደርጎባቸው የምግብ ዕርዳታ እንዳይደርሳቸው በታጠቀ ኃይል ቁጥጥር ሥር መክረማቸውን ገልጸው፣ በድንበር አዋሳኙ ላይ የተኩስ ልውውጥ በመኖሩ የሰው ሕይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ መሐመድ አስተያየት ከሆነ፣ በርካታዎቹ ተፈናቃዮች አርብቶ አደር በመሆናቸው ከብቶቻቸውን ጥለው ሕይወታቸውን ለማዳን ሸሽተዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ግጭት እየተከሰተ፣ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚገልጹት አቶ ወንድማገኝ፣ ሕዝቡ አብሮ እንደመኖሩ ዕርቅ ወርዶ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በተለያዩ መድረኮች ውይይት ቢደረግም መፈናቀሉ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚያም ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት ዕርቅ ቢወርድም፣ ዳግም ግጭቱ እያንሰራራ በመሆኑና ዘላቂ መፍትሔ በመጥፋቱ፣ የፌዴራል መንግሥት ለጉዳዩ ዕልባት መስጠት አለበት ብለዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች ግጭት ምክንያት ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በዞኑ አምስት ቀበሌዎች ላይ የሠፈሩ ሲሆን፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መሠረታዊ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መቆየት መቻላቸው ታውቋል፡፡

ከወር በፊት በባሌ ዞን በደሎ መና ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ183 ሺሕ ዩሮ በላይ ከአውሮፓ ኅብረትና ከአይሪሽ ኤድ በተገኘ ድጋፍ፣ በዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ድርጅት (International Rescue Committee) አማካይነት መሠረታዊ የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በዚህም 1,040 አባዎራዎች ለመጠለያ የሚረዳ ሸራ፣ 17 ዓይነት የቤት ቁሳቁሶች፣ እንዲሁም የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ በቀዳሚነት ማድረስ መቻሉንና ሆኖም የጤና፣ የውኃና የተጨማሪ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮቹ አሳስበዋል፡፡

የሁለቱ ክልሎች የድንበር ግጭት እያሰለሰ ከ30 ዓመታት በላይ የዘለቀ መሆኑን ተፈናቃዮች ለሪፖርተር የገለጹ ሲሆን፣ በ1997 ዓ.ም. የሁለቱን ክልሎች የድንበር ግጭት ለመፍታት ሕዝቡ የሚፈልግበት ክልል ለመኖር ሕዝበ ውሳኔ ቢያደርግም፣ መንግሥት ችግሩን መፍታት ባለመቻሉ ግጭቱ መቀጠሉን አቶ ወንድማገኝ ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል በባሌ ዞን በቆላና በደጋማ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት በመከሰቱ፣  ዘንድሮ 400 ሺሕ ሕዝብ ለረሃብ መጋለጡ ተገልጿል፡፡ ድርቁ የተከሰተው በዞኑ ሰባት ወረዳዎች ሲሆን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እጅ ዕርዳታ እያቀረቡ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

በዚህም ከኦሮሚያ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ (ቡሳ ጎኖፋ) በተገኘ 25 ሺሕ ኮንታል ሰንዴ መከፋፈሉን የጠቀሱት አቶ ወንድማገኝ፣ የነፍስ አድን ሥራ ላይ የተሰማሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ድርቁ ካለፉት ሦስት ዓመት ወዲህ እየከፋ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በከብት ዕርባታ  የሚተዳደረው አርብቶ አደሩ እንስሳቶቹን እያጣ፣ እንዲሁም አርሶ አደሩ ለዘር የሚሆን እህል እጁ ላይ ባለመኖሩ አሥጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው የችግሩን አሳሳቢነት አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -