Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየአልሸባብ የጥቃት ሙከራ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውና ለምዕራቡ ዓለምም የማስጠንቀቂያ ደወል ነው

የአልሸባብ የጥቃት ሙከራ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውና ለምዕራቡ ዓለምም የማስጠንቀቂያ ደወል ነው

ቀን:

በአክሊሉ ወንድአፈረው

ሕወሓት በትግራይ ክልል ተመድቦ ያገለግል በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ (መብረቃዊ) ጥቃት ፈጽሞ ኢትዮጵያ በታሪኳ ታይቶ የማይታወቅ ውስጣዊ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ፣ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ታላቅ ሁለገብ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያን አንፃራዊ መዳከም፣ በአንፃሩም የአልሸባብን መጠናከር፣ አልፎ ተርፎም የሰሞኑን የቀጥታ ወረራ ሙከራ አስከትሏል፡፡ ይህ ሁኔታ በቀጣይ ሊያስከትል የሚችለውን አንድምታ መመርመርና አስቸኳይ የዕርምት ዕርምጃ መውሰድ አጣዳፊ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ውስጥ ቁልፍ ሚና የተጫወተችውና እየተጫወተች የምትገኘው አሜሪካ ነች፡፡ አሜሪካ የትግራይ አማፂ ኃይል ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ካካሄደ በኋላ መልሶ እንዲያንሰራራ፣ ከተቻለም ወደ ሥልጣን እንዲመለስ የሚረዳ እጅግ ብዙ ድርጊቶችን ፈጽማለች፡፡

- Advertisement -

ለምሳሌም በኢኮኖሚው መስክ አሜሪካ ብቻ ሳትሆን አጋሮቿንም አስተባብራ፣ ለኢትዮጵያ ዕርዳታ እንዳይሰጡ በማድረግ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ እንዲደቅ ተደርጓል፡፡ ከዕርዳታቸው አልፎ የንግድ ስምምነቶችን (ለምሳሌ አጎዋ) በመሰረዝ ቀና ማለት ጀምሮ የነበረውን የኢንዱስትሪ መስክ አሽመድምደውታል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ቀደም ሲልም አስከፊ የነበረውን፣ በተለይም የሴቶችንና የወጣቶችን ሥራ አጥነት እጅግ ከፍ አድርጎታል፡፡

በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ ለ13 ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት አጀንዳ ሆና እንድትወቀስ ብቻ ሳይሆን፣ ቢቻላቸው ታላቅ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ እንዲተላለፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ እያንዳንዱ ስብሰባ የተጠራውም በአሜሪካ ወይም በሸሪኮቿ ነበር፡፡ ይህ ሙከራቸው በቻይና፣ በሩሲያና የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በህንድ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ ቢሆንም ታላቅ ጉዳት አድርሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካም ጭምር ተቀባይነቷ ላይ ታላቅ ተፅዕኖ እንዲደርስባት፣ በተለይም በግብፅ ግፊት ልማቷን እንኳ እንዳትገፋበት በተለያዩ ጎረቤቶቿ ተደጋጋሚ የማስፈራራትና የሴራ ዒላማ እንድትሆን ብዙ ተሞክሯል፡፡ የሱዳንን፣ የደቡብ ሱዳንን፣ የጂቡቲን፣ የዛምቢያን፣ ወዘተ ጉዳይ ማንሳት መረጃ ይፈነጥቃል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ በይፋ የህዳሴ ግድብ በግብፅ እንዲመታ ጥሪ አድርገው እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ሕወሓትንና ሌሎች የውስጥ ኃይሎችን (ለምሳሌ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ) በወታደራዊ ኃይል ያሻቸውን በሕዝብ ላይ ለመጫን ትልቅ ወረራ እንዲፈጽሙ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ገፋፍቶ (አበረታትቶ) እነሆ ኢትዮጵያ ታላቅ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡

በትግራይ የተከሰተውና ኋላም ወደ መሀል አገር የገፋውን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ ሠራዊት ያለውን ኃይሉን ወደ ትግራይ፣ ጎንደር፣ ወሎና አፋር ስላዞረ በምሥራቅ የአገራችን ክፍል አልሸባብ ላይ የነበረው ትኩረትና ቀድሞ የማጥቃት ተግባሩ እንደ ቀደምት ዓመታት እንዳይቀጥል ሆኗል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያ የደኅንነት ክፍል ትኩረቱን ያሠጉኛል ባላቸው የውስጥ ኃይሎች ለምሳሌ በኦነግ ሸኔና በፋኖ ላይ ያደረገ በመሆኑ፣ በአልሸባብ ላይ በሚደረገው ክትትልና ሴራውን ቀድሞ ማክሸፍ ላይ ተጨማሪ ክፍተት ፈጥሯል፡፡

አልሸባብ ከላይ የተዘረዘረውንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሸረሸረ የመጣውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ድጋፍ በማየት ሁኔታ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ራሱን እጅግ አጠናክሮ ቀደም ሲል ተዋጊዎቹን አሾልኮ ለማስገባት፣ አሁን ደግሞ በግልጽ ኢትዮጵያን በሰፊው ለመውረር ሙከራ አድርጓል፡፡ ይህ ወረራ ቢቀለበስም፣ የሚያመለክተው ግን የምዕራቡ ስትራቴጂ ለአልሸባብ መጠናከር ታላቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ነው፡፡

ይህ ጉዳይ አደገኛነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላ ቀጣናው፣ ለቀሪው አፍሪካና ለምዕራቡ ዓለምም ጭምር ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ የሃይማኖት ጽንፈኞች ከአልሸባብና ከቦኮ ሀራም ጋር ተባብረወና ተናበው ከሞዛምቢክ እስከ ኮንጎ፣ ታንዛንያና ኬንያ ጭምር መስፋፋታቸውና ጥቃትም ማካሄዳቸው ይታወቃል፡፡

የሃይማኖት ጽንፈኞች በምዕራብ አፍሪካም ከናይጄሪያ እስከ ማሊ አጎራባች አገሮች እየተስፋፉ እንደሆነ፣ ከሌሎች ቦታዎች ሁሉ አፍሪካን ማዕከል አድርጎ ለመስፋፋትና ለመጠናከር እንደሚጥሩ ይታወቃል፡፡

ይህን ሁሉ በግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ የምዕራብ መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት እጅግ ጽንፍ የያዘ ተፅዕኖና ግፊት ምን እያስከተለ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን አገሮችና የራሳቸውንም ፀጥታና ጥቅም እጅግ እየጎዳ እንደሆነ ተገንዝበው፣ አስቸኳይ የዕርምት ዕርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ሁኔታውን ለመቀልበስ፣

  • በኢትዮጵያ ላይ የጣሉትን የዕርዳታ ክልከላ በአስቸኳይ ሊያነሱ ይገባል፣
  • ከንግዱ አንፃር ያስተላለፉትን የንግድ ማዕቀብ ሊያነሱ ይገባል፣
  • ቀደም ሲሉ ይሰጡ የነበረውንና ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የከለከሉትን የወታደራዊ ወይም የፀጥታ ትብብር ሊያድሱና ተገቢውን የገንዘብና ሌሎችም ድጋፍ ሊቀጥሉ ይገባል፣
  • በዲፕሎማቲክ መስኩ የሚያደርጉትን ቀጥተኛ የሆነና ቀጥተኛ ያልሆነ ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ ሊያቆሙ ይገባል፣
  • በኢትዮጵያ የውስጥ በፖለቲካ የሚያደርጉትን ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብነት ሊያስተካክሉና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ትዕዛዝ መስጠትን በአስቸኳይ ሊያቆሙ ይገባል፣
  • የኢትዮጵያ ውስጣዊ ፖለቲካ እጅግ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን ሲበዛ ውስብስብ መሆኑን በግንዛቤ ውስጥ በማስገባትም ከጣልቃ ገብነት ውጪ ቅራኔን በውይይት ለመፍታት የቴክኒክና የጥሬ ዕቃ ድጋፍ መስጠት፣ የተወሰኑ ተቃዋሚዎችን የማጠናከር ዕርምጃ መስሎ ከሚታይ አካሄድ ራስን ማቀብ አስፈላጊ ይሆናል፣
  • የአልሸባብና ሌሎችም ጽንፈኞች ጥቃትና አደጋ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ፣ የቀጣናው መንግሥታት በጋራ እንዲቆሙ ማበረታታ እንጂ ማደናቀፍ ከቶውንም አይገባም፡፡

የኢትዮጵያ መበታተን የማይገዳቸው ኃይሎች ከአልሸባብ ጋር የሚግባቡበት አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ኢትዮጵያን ቢቻል ማፍረስ፣ ባይቻል በቀውስ ውስጥ እንድትቀጥል ማድረግ ነው፡፡ የተበታተነችም ሆነች በቀውስ ውስጥ የምትቆይ ኢትዮጵያ ለሁለቱም ክፍሎች ዓላማ ስኬት ነው፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ ብትሆን ለኢትዮጵያውያን፣ ለቀጣናውም ሆነ ለምዕራቡ ዓለም ደኅንነት እጅግ አደገኛ ነው፡፡

የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት ተወካዮች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ ምስቅልቅል በአግባቡ በመረዳት፣ በማንኛውም ዕርምጃቸው ወገንተኛ እንዳልሆኑ ለማሳየት ማንኛውንም ኦፊሴላዊ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ሁሉን አቀፍ በሆነው በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ቢሆን የተመረጠ ነው፡፡ ይህ ሲሆን በምዕራብ መንግሥታት ላይ የሚታየውን ወገንተኝነትና የእምነት መሸርሸር ቀስ በቀስ ለመጠገን ይቻል ይሆናል፡፡

ከዚህ ውጪ አሁንም የምዕራቡ መንግሥታት የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብቻ የሚያሳዩትን ቅርርብ፣ በሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶችና በሕዝብም ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ዕይታ ሊያጤኑ ይገባል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት የታየው ከመስመር የወጣና ሉዓላዊነትን የሚጋፋ ግንኙነት የሚያስተላልፈው መልዕክት፣ ኢትዮጵያን አሳንሶና አጋር የሌላት አድርጎ የሚያቀርብ እጅግ አፍራሽ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ደግሞ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ብልፅግና የምዕራቡን መንግሥታት ተፅዕኖ መላላት ያላግባብ እንዳይተረጉመውና የሕዝብን መብት ለመርገጥ እንዳይጠቀምበት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የመብት ጥሰትና ረገጣውን ከቀጠለ የተፈለገውን አገራዊ መረጋጋትና የአልሸባብንም ጥቃትና መስፋፋት ማምከን እጅግ ይከብዳል፡፡

በተጨማሪም የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ የምዕራቡ መንግሥታት ፖሊስ ስላልሆነ፣ የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት ራሱን የእስካሁን ፖሊሲና ተግባሩን ገምግሞ ስህተቶቹን በተግባር አርሞ ውስብስብ ችግሮቻችንን ከሥር መሠረቱ ለመፍታት፣ በአዲስ መንፈስ ለመንቀሳቀስ (Reset) ቁርጠኛና አስቸኳይ ዕርምጃዎችን በተጨባጭ ሊወስድ ይገባል፡፡

በዚህ አኳያ ምዕራባውያኑ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል ችግርን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበት ምኅዳር እንዲዘጋጅና ተግባራዊ እንዲሆን፣ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበት ሁኔታን መነጋገርና በጋራ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ መብትን ሳያከብሩ ሰላምን ዕውን ማድረግ በአጭርም ሆነ በረዥም ጊዜ እጅግ ከባድ ነው፡፡

የአሁኑ የአልሸባብ የወረራ ሙከራ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናውም ሆነ ለምዕራቡ አገሮች ታላቅ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው፡፡ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ያሳደረው ወደር የለሽ ተፅዕኖ ከመንግሥት የተለያዩ ስህተቶችና ፖሊሲዎች ጋር ተደማምሮ እነሆ አፍራሽ ጎኑ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ በአስቸኳይ መቀልበስ ጠቀሜታው ለምዕራቡ ዓለም፣ ለቀጣናውና ለኢትዮጵያም ጭምር ነው፡፡ ሁኔታው እጅግ አጣዳፊ ትኩረትንም የሚሻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...