Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየዘር ማጥፋት ምክንያቶችና መፍትሔያቸው (ክፍል አራት)

የዘር ማጥፋት ምክንያቶችና መፍትሔያቸው (ክፍል አራት)

ቀን:

በያሬድ ኃይለ መስቀል

በክፍል ሦስት የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም አቀፋዊ ወንጀል ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መፅደቁን፣ ማንም በዘር ማጥፋት ወንጀል የተጠረጠረ ሰው ወይም የመንግሥት ባለሥልጣን ሆኖ የዘር ማጥፋትን ያላስቆመ ሰው በተገኘበት አገር ሁሉ ሊከሰስ እንደሚችል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕግና የምዕራባዊያን አገሮች እንደ ምሳሌ ተጠቅሰዋል።

በዚህ ጽሑፍ ደግሞ በዘር ማጥፋት ላይ ጥናት ያደረጉና የዘር ማጥፋት ምክንያቶችን ዘርዝረው የጻፉትን በመገምገም፣ ከእኛ አገር ጋር እያዛመድኩ እጠቅሳለሁ። የዘር ማጥፋት ጥናቶችን አቀነባብረው ከጻፉ መካከል፣ ‹‹ለምን ሁሉንም አንገድላቸውም፣ የዘር ማጥፋት ምክንያቶችና መከላከያው›› በሚል ዳንኤል ቻሪኦትና ክላርክ ማካውሊ እየጠቀስኩ አቀርባለሁ (Why not kill them all? The logic and prevention of mass political murder፣ Daniel Chirot and Clark McCauley)።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዘር ማጥፋት በጣም ጨካኝ በሆኑ ማኅበረሰቦች ባህል፣ ሃይማኖት፣ ፈሪኃ እግዚአብሔር ባልፈጠረባቸው ሰዎች የሚፈጸም ይመስለናል። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። እንደኛው ጤነኛና ጨርቃቸውን ያልጣሉ እሑድ፣ እሑድ ቤተ ክርስቲያን ተንበርክከው የሚጸልዩ፣ ወይም ዓርብ፣ ዓርብ መስጊድ ሄደው የሚሰግዱ፣ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነው ስለማኅበራዊ ደኅንነት የሚደሰኩሩ፣ የተማሩና የፈረንጅ ቋንቋን አቀላጥፈው የሚናገሩ፣ በአደባባይም ሱፍና ከረባት የሚያስሩ ይበዙበታል። ገበሬው ጨርቅ ለባሽ በግጦሽና በምንጭ ይጣላ እንደሆን እንጂ፣ በዓለም ላይ ተከሰቱ በተባሉት የዘር ማጥፋት ታሪኮች ውስጥ አይጠቀስም።

ለምሳሌ ከሩዋንዳ የዘር ማጥፋት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ገዳዮችም ሟቾችም በአንድ ቤተ አምልኮ ውስጥ ተሰብስበው የክርስቶስን መነሳት እየዘመሩ ነበር ያከበሩት። ሁቱዎችም (Hutu) ቱሲዎችም (Tutsi) በእኛ አገር የተዛባ አመለካከት የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብና ወይም ሕዝብም ተብለው አይመደቡም። ሁለት ማኅበረሰቦች የተባሉት አንድ ቋንቋ የሚናገሩ፣ ሁለቱም የካቶሊክ እምነት ተከታዮችና በዓለም አቀፋዊ አንትሮፖሎጂ ትንታኔ አንድ ማኅበረሰብ ተብለው የሚመደቡና ልዩነታቸው መደባዊ ተብለው የሚመደቡ ናቸው (Status Community)። ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት የኦሮሞ ባላባትና የኦሮሞ ጭሰኛ እንደ ማለት ነው። ወደ ቁምነገሩ ስንመለስ። የካናዳው የሰላም አስከባሪ ጄኔራል ሮሚዮ ዳላኤሬ (General Roméo Dallaire) በሔሊኮፕተር ሆነው የፋሲካ ዕለት ይዘዋወሩና ወደታች ሲመለከቱ የታዘቡትን፣ ‹‹ከሰይጣን ጋር መጨባበጥ›› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ አስፍረውታል።

‹‹On April 3, Easter Sunday, .….. We had a magnificent fifty-minute flight at very low altitude over the rounded mountaintops of central Rwanda. Below me that morning it looked like all the villagers in the country were dressed in their finest, walking in near-procession toward their places of worship. Here is what my experience in Rwanda has done: I am unable to remember the serenity, order and beauty of that scene without it being overlaid with vivid scenes of horror. Extremists, moderates, simple villagers and fervent worshippers were all in church that day, singing the message of Christ’s resurrection. One week later, the same devout Christians would become murderers and victims, and the churches the site’s of calculated hutchery.››

‹‹የፋሲካ እሑድ በሔሊኮፕተሬ ለ55 ደቂቃ ዝቅ ብዬ በረርኩ። ከታች ሁሉም የሩዋንዳ መንደሮች የክት ልብሳቸውን ለብሰው፣ ሁሉም ወደሚቀርባቸው ቤተ አምልኮ ሲሄዱ ይታዩኛል። የሩዋንዳን ፀጥታ ማማርና ሥነ ሥርዓት ተመለከትኩ። የሚገርመው ጽንፈኞቹና አማኞች በአንድ ቤተ አምልኮ በአንድ ቦታ ሆነው የክርስቶስን መነሳት ይዘምሩ ነበር። ከአንድ ሳምንት በኋላ ግን እነዚህ አማኞች ግማሾቹ ገዳይ፣ ግማሾቹ ተገዳይ ሆኑ፣ ቤተ አምልኮዎቹም የማረጃ ቄራ ሆኑ፤›› ብለው ትውስታቸውን ጽፈዋል።

ይህንን መጽሐፍ ለመጥቀስ የፈለግኩት በእኛ አገርም ይህ ከመሆን የሚያግደው ነገር እንደሌለና ‹‹ጄኖሳይድ›› የሚፈጽሙባቸው አገሮች አንደኛው ሃይማኖትም ሥነ ምግባርም ባላቸው ሰዎች ነው። ወለጋ ለምሳሌ በጣም በስፋትና በጥልቀት መጽሐፍ ቅዱስ ተሰብኮበታል የሚባል ክፍለ አገር ነው። ይሁንና ሕፃናት ሲታረዱ ‹‹ኧረ ተው ኃጢያት ነው›› የሚል ክርስቲያን ወይም ፓስተር እስከ ዛሬ አልታየም።

የቀዮቹን ህንዶች ያጠፏት የደቡብ አሜሪካ ክርስቲያን ሰባኪዎችና አማኞች ነን ነበር የሚሉት። ወደ አሜሪካ ያሰደዳቸውም የእነሱ ክርስትና ተጨቁኖብናል ብለው ነበር። በብዛት ወደ አሜሪካ የተሰደዱት ፒዩሪታንስ (Puritans) እና ክዌከርስ (Quakers) በፕሮቴስታንት የሚመደቡት የእንግሊዝ አንገሊካን ቸርች ከካቶሊክ ቢገነጠልና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ቢሆንም፣ ከካቶሊክ የወረሳቸውን የቅዳሴ ሥርዓቶች አራግፎ አልጣለም። እኛ ከዚህ ኮተት ፅድት ያልን ነን። ‹‹Pure›› ከሚለው ቃል የተወለደ ‹‹Puritans›› ንፁሆቹ እንባላለን ብለው ከሥርዓቱ ጋር በመጋጨታቸው ነበር።

የናሚቢያን ሄሬሮ የጨፈጨፉት ጀርመኖችም መጀመርያ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው የመጡና በመጨረሻ ቅኝ የያዙት ናቸው። የጀርመን የዓለም ፕሮቴስታንት እምነት መሥራችና ሰባኪ አገር ነበረች። ጀርመን የክርስቲያን፣ የሠለጠኑ፣ የብዙ ቴክኖሎጂና የፍልስፍና ማዕከል አገር የነበረች፣ ይሁንና ይሁዳውያን እየተለቀሙ ሲቃጠሉ ጀርመኖች ድምፅ አላሰሙም። ታድያ በእኛ አገር አይሆንም የሚል ጥራዝ ነጠቅ የምሁራን ክርክር አይሠራም።

ሩዋንዳዎች የሚያምር ባለብዙ ቀለም ቀሚሳቸውን ለብሰው፣ ወንዱም ሴቱም በአንድ ሆነው የክርስቶስን መነሳት አብረው ዘምረው በሳምንቱ የመሪያቸው አውሮፕላን መከስከስ ሲሰሙ፣ ጎረቤቶቻቸውን ሊያርዱ ገጀራ ይዘው ነው የወጡት። በእርግጥ ሁሉም አይደሉም የተሳተፉት። ትንሽ ግን የተደራጁና የመንግሥት ደጋፍ ያላቸው ስለሆኑ ነው። እነዚህ የታጠቁ ወጣቶች በፈጸሙት ጭፍጨፋ ሁቱዎች አልተጠቀሙም። ዛሬ በሩዋንዳ ‹‹እኔ ሁቱ ነኝ››፣ ‹‹እኔ ቱሲ ነኝ›› ማለት በሕግ ቢከለከልም በስደትና በውጭ የሚኖሩ ሁቱዎች ግን ዛሬ ‹ሁቱ ነኝ› አይሉም። ምክንያቱም ‹ሁቱ› ማለት አረመኔ የሚል ስሜት ስለሚፈጥር። ጽንፈኞች እናጠፋዋለን ብለው ከሚያስቡት ቡድን በላይ የራሳቸውን ብሔረሰብ ስያሜ እንደሚያጠፉ ከሁቱዎች መረዳት ይቻላል።

የዘር ማጥፋት ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በተሰበከው የጥላቻ ሰበካና ‹‹የእኛ›› እና ‹‹የእነሱ›› ትርክት ምክንያት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰት ይችላል ብዬ እሠጋለሁ። ከዘር ማጥፋት የሚቀድመው ‹‹ራዲካላይዜሽን›› (የጽንፍ ሐሳብን) ማስተው ነው። ይህ በብዙ በጀትና ብዙ ካድሬ የሚዲያ ሰዓት ተሰጥቶት ተሠርቶበታል።

ይህ ባይሆን ኖሮ ለምሳሌ ጃዋር ተከበብኩ ሲል፣ ሃጫሉ ተገደለ የተባለ ቀን ካራውን ይዞ ጎረቤቱን ለመግደል የሚነሳ ወጣት ባላየን ነበር። ይህ እንደ ሩዋንዳ ያለ የአውሮፕላን መከስከስ ቢፈጠር የሩዋንዳ ዓይነት ተግባር አይፈጠርም ማለት ትልቅ የዋህነት ነው። ይልቁንም ችግሩ ሊከተል እንደሚችል ገምቶ ችግሩ እንዳይፈጠር መወያየትና መፍትሔ መፈለግ ያሻል።

ስለዚህ እኛ ከሩዋንዳዎቹ፣ ከጀርመኖቹና ከአሜሪካኖቹ የተለየን ፍጡር ነን ብለን ካሰብን የዋሆች ነን። ምናልባትም የእኛ ትምህርት፣ ፍልስፍና እምነትና ሥነ ልቦና የተቀረፀው ከዚያው ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ነውና። ስለዚህ ለ30 ዓመታት የተሠራውን የአዕምሮ አጠባ በምክንያታዊነትና በመረጃ መሞገት እንጂ፣ እንደ ሰጎኗ ራሳችንን በአሸዋ ውስጥ መቅበር አይጠቅምም። አሁን የምናየው ግን በርካታ ‹‹ምሁራን›› ውይይቱ እንኳን ሲነሳ ይረበሻሉ። መንግሥትን የሚያስቀይሙና የሚያስቆጡ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ ዳርዳሩን ሲሉና አጀንዳውን ሲዘጋጉ ይውላሉ።

ወደ መጽሐፋችን ስንመለስ ዳንኤል የ‹‹ጄኖሳይድ›› መንስዔዎችን በአራት ይከፍሉታል። አንደኛውይል አለመመጣጠን፣ ሁለተኛው የዘርና የይማኖትን ብከላ መፍራት ሦስተኛው ፍር፣ አራተኛው በቀል ነው።

በእኛ የፍርኃት ‹‹ጄኖሳይድ›› እና የሃይማኖትና መበከል ችግር ያለ አይመስለኝም። እያቆጠቆጠ ያለው የብሔር መበከል ሥጋት የሚመስል ሥነ ልቦና ይታያል። ንፁህ ኦሮሞ ትግሬ አለመሆን እንደ መጥፎ በሽታ ሲጠቀስ በአደባባይ ዓይተናል። የኦሮሞ አክራሪዎች አንዳንድ መሪዎችን እሱ ‹‹ዲቃላ ነው›› እያሉ መፈክር ሲያሰሙ በአደባባይ ዓይተናል። ዲቃላ መባል እንደ መበከል እንዲቆጠርና ከበርካታ ‹‹ብሔር›› መወለድ ከንፁህነት መውረድና መበከል ተደርጎ፣ በአደባባይም በየማኅበራዊ ሚዲያው የሚሰበክ የማይማን ፍልስፍና ይታያል። እንዲያውም በፈረንጆቹ ከተሜነት (Cosmopolitan) እንደ ሥልጣኔ ቁኝጮነት፣ ‹‹having wide international sophistication: worldly Greater cultural diversity) .., cosmopolitan attitude among younger generations. 2 : composed of persons, constituents, or elements from all or many parts of the world a city with a cosmopolitan population…›› እያሉ የሚያንቆለጳጵሱትን የባላገር ካድሬዎች የራሳቸውን ድክመት ለመሸፈን፣ እነሱ ንፁህ አይደሉም ዲቃላዎች ናቸው እያሉ ሲቀሰቅሱና የበታችነት ስሜታቸውን በዘረኝነት ስሜትና ጥላቻ ሲሸፋፍኑ እያየን ነው። ስለዚህ መሠልጠን ከተሜነት፣ ተቻችሎና ተዋዶ ተቀላቅሎ መኖር እንዲቆምና መጥፎ ለማስመሰል ሲሞከር ዓይተናል። በካምቦዲያ ፖል ፖት በሚባል ቀውስ የተመራው አብዮት በዚህ ልክፍት ይወሰድና ለሁለት ሚሊዮን ካምቦዲያውያን ሞት ምክንያት ነውና አይሆንም ማለት ይከብዳል።

በእርግጥ እንደ ይሁዳውያን ወይም እንደ 15ኛው ክፍለ ዘመን የፕሮቴስታንትና የካቶሊኮች ጦርነት የከረረ የማፅዳት እንቅስቃሴ ላይ የደረሰ አይደለም፡፡ ይሁንና ፀረ አዲስ አበቤነትና ከተሜነት ቅስቀሳ (ራዲካላይዜሽን) እናያለን። ይህ መኖሩና አለመኖሩ የሚታወቀው ከድርጊቱ በኋላ ነው። አሁን እስከ ሰባት ዘር ቁጠር መባል ያልተበረዘ፣ ያልተደለዘ፣ ያልተራከሰ የንፁህ ዝርያ መገለጫ እየሆነ እየመጣ መሆኑን ግን እየታዘብን ነው።

ይህ ገኖ የሚወጣው ቀጥሎ በሚነሳው የሥልጣን ሽኩቻ ነው። ሥልጣንና ኃይል የሚገኝ ከሆነ ‹ይህ ዲቃላ› ነው የሚለው ሐሳብ አድጎ የተቀናቃኞች ማስወገጃ ሆኖ ብቅ ይላል።

የበቀል ዘር ማጥፋትም በኢትዮጵያ ይካሄዳል ብዬ አልሠጋም። በናሚቢያ የተጨረሱትን ሄሬሮዎች በምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የተወሰኑ ሄሬሮዎች የቅኝ ገዥዎቻቸውን የጀርመን ወታደሮችና ወንዶች ገደሉ። በዚህ ምክንያት የጀርመን ወታደራዊ ጄኔራል ትሮታ (Trotha)፣ ‘Any Herero found inside the German frontier, with or without a gun or cattle, will be executed. I shall spare neither women nor children” ‹‹በናሚቢያ ግዛት ወስጥ የተገኘ ሄሬሮ ከብት የያዘም የታጠቀም፣ ሴትም ሆነ ልጅ እንዳትምሩ፤›› ብሎ አውጆ እንዲረሸኑ አደረገ። የጄኔራል የግራዚያኒም ተግባር በዚህ ነው የሚመደበው። አብረሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ቦምብ ወርውረው አቆሰሉት፡፡ በዚህ ምክንያት ለሦስት ቀናት የጭፍጨፋና የማቃጠል ዘመቻ አውጆ ቤት ለቤት እየሄደ ከሰላሳ ሺሕ በላይ ወጣትና አዛውንት ጨረሰ።

ሦስተኛው ፍርኃት የሚባለው ከተሸነፍን ያጠፉናል ስለዚህ ቀድመን አናጥፋቸው የሚለው ዕሳቤ ነው። የሩዋንዳው ዘር ማጥፋት በዚህ ሊመደብ ይችላል። ጠንክሮ የካጋሜን ጦር ተዋግቶ ከመመለስ ይልቅ ጎረቤቱን ወደ ማረድ ተለወጠ።

እኛ አገር ሊፈጠር የሚችለው የዘር ማጥፋት እንደ ቀይ ህንዶቹ ወይም እንደ አበርጂኒሶቹ የኃይል ያለ መመጣጠን ነው። የአሜሪካ ነጮች የአትላንታን መሬት ለጥጥ እርሻ ሲፈልጉት፣ ህንዶቹን ከዚያ አንስተው ኦክሎሁማ ወደ የሚባል ግዛት ይዛወሩ አሉ። እ.ኤ.አ. በ1830 እንደ ዛሬ መኪናም ሆነ አውሮፕላን አልነበረም። ስለዚህ ቸሪኬ የሚባሉት ቀይ ህንዶች 8,000 ኪሎ ሜትር በእግራቸው ሲነዷቸው አለቁ። በዚህ ጉዞ በየመንገዱ አስከሬናቸውን እየጣሉ ነው የተጓዙት። ይህ ተጠያቂነት የለብንም ወይም አፀፋውን አይመልሱም ተብሎ ሲታሰብ የሚፈጸም የዘር ማጥፋት ነው።

ይህንንና የአውስትራሊያ የቀይ ህንዶች መጥፋት ምክንያት የአቅም አለመመጣጠን ነው። አናሳ የሆኑ ማኅበረሰቦች ትልቅ ጠላት ብሎ በፈረጃቸው ማኅበረሰብ ውስጥ ሲኖሩ፣ ጉልበት አለኝ የሚለው ኃይል የምፈልገውን ባደርግ የሚጠይቀኝ የለም ብሎ ስለሚያስብ ዘር ማጥፋትንም እንደ አማራጭ ይቆጥሩታል።

የዘር ማጥፋት ሙከራን ማስቆሚያው

ለዚህ ዓይነቱ የዘር ማጥፋት ማርከሻው ዘር ማጥፋት ዋጋ እንዲያስከፍል ሲደረግ ብቻ ነው። ለምሳሌ ለጥቃት የተጋለጠ ማኅበረሰብ ራሱን የመከላከል አቅም ከገነባ የዘር ማጥፋት ይሞከር እንደሆን እንጂ ማጥፋት አይቻልም። አሁን እንደምናየው ሰዎች ተሠልፈው አይረሸኑም፣ ወይም አይታረዱም። ዋጋ ሲያስከፍል በጽንፈኛ ቡድንም ውስጥ የተቀበሩ ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች አቅም ያገኛሉ፣ ወደ ምክንያታዊነት እንሂድ ይላሉ።

በአንደኛና በሁለተኛው ክፍል እንደተጠቀሰው ጽንፈኝነት ማለት ከምክንያታዊነት መፅዳት ነው። ጽንፈኛ በራሱ ዓለም ስለሚኖር ምንም ሺሕ አጀንዳ ቢደረድር ወይም ተማፅኖ ቢቀርብ፣ በምንም ዓይነት መንገድ ሐሳቡን አይቀይርም። ለምሳሌ ዛሬ አውሮፕላን መጥለፊያ መሣሪያ ቢፈቀድ ዛሬም አውሮፕላን ጠልፈው ከፎቅ የሚያጋጩ ጽንፈኞች ተመልሰው ይመጣሉ። የአውሮፕላን ጠለፋን ማስቆም የተቻለው የጽንፈኞችን የመጥለፊያ አቅም በማሳጣት ብቻ ነው።

ዛሬ እንደ እኔ ተራ ሰው ይሁን ወይም የተከበሩ ሚኒስትር ሁለታችንም ቀበቷችንን ፈተን፣ ጫማችንን አውልቀን፣ ድንገት ፈንጂ ውጠን ይሆናል ተብሎ ውስጥ በሚያሳይ ጨረር ተፈትሸን ነው አውሮፕላን ውስጥ የምንገባው። ወደ ፓይለቱ መግቢያ ያለው በርና ግድግዳ ጥይት በማይበሳው ኬቭላና አልትራ ሃይ ሞሎኪዩላር ዌይት ፕላስቲክ ነው የሚሠራው። ወደ ፓይለቱም ለመግባት ከውስጥ ካልተፈቀደ ማንም ሽጉጥ ቢያወናጭፍ ፓይለቱን የሚያስገድድበት ዕድል ወደ ዜሮ ስለወረደ ነው።

በኢትዮጵያም የጽንፈኝነትንና የዘር ማጥፋት ሙከራ ማስቆም የሚቻለው፣ ሰዎች ተሠልፈው የማይታረዱበትን ሁኔታ በመፍጠር ብቻ እንጂ ሌላ አማራጭ የለውም። ይህ ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ነበር። ይህንን ያለማድረግ ብቻ ሳይሆን ቸልተኝነትም በዓለም አቀፋዊ ፍርድ ቤት ያስከስሳል። ሰዎቹ ከማንም ወንጀለኛ ራሳቸውን የሚከላከሉበትን ሥልጠናና ትጥቅ መስጠት ብቻ ነው የሚያስቆመው። ከዚያ በተረፈ ሻማ ማብራትና የዓዞ ዕንባ መርጨት ከአስመሳይነት አያልፍም።

የዓለም አቀፋዊውን ሕግ ላላነበቡ አንደኛ ዘር ማጥፋት ዓለም አቀፋዊ ወንጀል መሆኑን ግንዛቤ መውሰድ። ይህ ማለት አንድ ሰው በሥልጣን ላይ ሆነም ከሥልጣን ወርዶ በውጭ አገር ከተገኘ ማንኛውም አገር ማሰርና ለፍርድ ማቅረብ ግዴታው ነው። ሁለተኛ ዘር ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ባለሥልጣን ሆኖ የዘር ማጥፋትን ያላስቆመ፣ እንደ ዘር አጥፊው እንደሚከሰስ ያለመረዳት ያለ መሰለኝ። እንደ ማንኛውም የደረቅ ወንጀል ተሳታፊ መሆን ብቻ ከተጠያቂነት አያድንም።

ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን በቸልተኝነት ተከሳሽ ይሆናል ‹‹Complicity in Genocide››። ለምሳሌ የዩጎዝላቪያው ሚሎሶቪች በራሱ የዘር ማጥፋት ወንጀል አልተከሰሰም። ምክንያቱም እሱ የሚያዛቸው ወታደሮች የዘር ማጥፋት አልፈጸሙም። ይሁንና እሱ መንግሥት ሆኖ ሳለ፣ የሰርብ ሚሊሻዎች የዘር ማጥፋት ሲሞክሩ አላስቆመም በማለት ነው። የሱዳኑም አል በሽር የሱዳንን ጦር አዝምተው አይደለም የዳርፉር ሰዎችን የጨፈጨፉት። በዚህ አልተከሰሱም። ይልቁንም የጃንዊድ የዓረብ ሚሊሻዎች ሄደው ሲጨፈጭፋ ለማስቆም አልሞከሩም በሚለው ‹‹Complicity in Genocide›› ነው። የአማርኛው ትርጉም ትክክል ይሁን አይሁን ባላውቅም ‹‹Complicity in Genocide›› ማለት ‹‹ቸልተኝነት›› ይመስለኛል።

የእኛ አገር የሕግ አዋቂዎች ጉግል አድርገው የሚመረምሩዋቸው በርካታ የሕግ ጆርናሎች አሉ። ስለዚህ እኛ አገር ወደ ስህተት እያመራ ያለው መጀመርያ ማጎብደድ፣ ከዚያ ደግሞ ገድዬህ እጄን እሰጣለሁ የሚለው ጽንፈኝነት ነው። ‹‹የወደቀ ምሳር ይበዛበታል›› የሚለው መቆም ያለበት ከንቱ ግብዝነት ነው። ይልቁንም ስህተት እንዳይረሳ ሕግን መተርጎምና ሙያዊ ትንተና መስጠት ለአገርም ለማንኛውም ሥርዓትም ጠቃሚ ነው።

ይህንንም ማድረግ ደግሞ የሚሞቱትን ማዳን ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ተስፋ ያላቸው ገዳዮችን ማዳን ነው። በዓለም ላይ ተዟዙረው፣ ሠርተውና ተፎካክረው መኖር እንዳይችሉ እንደ አቤል ደም የሕፃናት ደም እያሳደዳቸው፣ እንደ ቃየል በገነባው ግንብ ተንዶበት እስከሚያርፍ ጊዜ ድረስ መቅበዝበዝ ይሆናል። ለምን ቃየል ወንድሙን በገደለበት ድንጋይ ሞተ የሚለው የንፁኃን ደም እንደሚወራረድ ለማስተማር መሰለኝ።

ሃይማኖተኛ ነን፣ የእግዚአብሔር ስልክ ቁጥር አለን ብለው የሚመፃደቁ የከተማ መናኞች የአቤል ድምፅ ከተሰማ በኋላ ፈጣሪ ማድመጥ ያቆመ የሚመስላቸው ብዙ ናቸው። ቀን የማንም ደም ሲፈስ የተደሰቱ ማታ ተንበርክከው ከፈጣሪ ጋር ኩኩሉ መጫወት ይፈልጋሉ። እነሱም ስላልገደሉ እንደ ጲላጦስ እጃቸውን የሚታጠቡ ይመስላቸዋል።

በብሔርም ደረጃ ካሰብነው ከተገደለው ብሔር በላይ በስሙ የሚገሉለት ብሔር ሲጠፋ ነው ያየነው። በማንም፣ በምንም ስም ወንጀል ይሠራ ለሚቀጥሉት ዓመታት ሁቱ ነኝ ማለት በዓለም ላይ የሚያሸማቅቅ ይሆናልና። ለዚህ ነው ወንጀሉ ማዘዝ ለማይችሉ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን በዝምታ ለሚያልፉትም ነው። የአሜሪካው ጥቁር ዘር እኩልነት ታጋይ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ “The greatest tragedy is not the brutality of the evil people, but rather the silence of the good people” ‹‹ትልቁ አሳዛኝ ነገር የአረመኔዎች ጭካኔ ሳይሆን የመልካም ሰዎች ዝምታ ነው፤›› ብለው ስሜታቸውን ገልጸው ነበር።

ሁሉም ወደ ምክንያታዊነት እንዲመለስ መጣር አለበት። ምክያቱም ዘር ማጥፋትን በ20ኛው ክፍለ ዘመን ናዚዎች እንኳን አልቻሉም። ጀርመኖች ለማጥፋት ሄደው ጦርነቱ ሲያልቅ ከተሞቻቸው ፈርሰው ከሁለትና አምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎቻቸውን አጥተው ነው የተጠናቀቀው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያልታጠቁ ሴቶችንና ሕፃናትን እንደ መግደል ያለ ዘር ማጥፋት በተግባር መተርጎም አይቻልምና።

ለዚህ ነው ሕፃናትና ሴቶች እንደ ፖለቲካ ትግል መታየት የሌለባቸው። የረዥም እጅ ጽንፈኞችን የሚመሩና የሚቀሰቅሱም ከዚህ ወንጀል ነፃ መሆን እንደማይችሉ ይህንን ጽሑፍ ካነበቡ በኋላ ጉግል ያደርጉ፡፡ በሺሕ የሚቆጠሩ የሕግ ጆርናሎች ማየት ይቻላል፡፡ ዕብደቱን ትተን ወደ ህሊናችን እንመለስ። ሴቶችንና ሕፃናትን መግደል የሚያሳፍር እንጂ የፖለቲካ ትግል አይሆንምና።

አሜሪካኖቹ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ቀይ ህንዶች ቢንፈራገጡ ኖሮ ስምንት ሺሕ ኪሎ ሜትር እንነዳቸዋለን ብለው አያቅዱም ነበር። ይሁንና አንድ ነገር ዋጋው ዜሮ ከሆነ መሞከሩ አይቀርም። በብዙ አገሮች ውስጥ የሚፈራው ትልቁ ሃይማኖትና ትልቁ ማኅበረሰብ ትንሹን ማኅበረሰብ እንዳይጨቁነው እንዳያጠፋው ነው። ይህንን ‹‹The Tyranny of Majority›› ይሉታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የሥነ ልቦና ተገላቢጦች ሆኖ አናሳው ቡድን ነው ሁሌም ትልቁን ሃይማኖት ትልልቆቹን ብሔረሰቦች ሲገድል፣ ሲያፈናቅልና ሲጨቁን የሚታየው። ለምሳሌ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ወደ 45 በመቶ ይሆናሉ። ይህ ማለት ወደ 60 ሚሊዮን ሕዝብ ይገመታል፡፡ ይሁንና በበርካታ ቦታ እየተቃጠለ ያለው ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን በአመዛኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ነው። ይህ ማለት እነ ዳንኤል፣ አና ክላርክ በጻፊት መጽሐፍ ውስጥ እንደታየው አንድ ማኅበረሰብ ራሱን የመከላከል አቅም ካልገነባና ካልተፍጨረጨረ እንደ ቀይ ህንዶች ከመጥፋት ራሱን አያድንም። ምክያቱም ባርነት የቀጠለው በባሪያ አሳዳሪዎች ጥንካሬ ሳይሆን በ‹‹አርዓያ›› ሥላሴ የተፈጠሩ ሰዎች ባርያ ማድረግ ትክክል አይደለም ብለው የሚያምኑ፣ ግን ዝምታን የመረጡት ነበሩ ወንጀለኞቹ። ሰው መሞት የለበትም ብሎ የሚያምን፣ ግን ቃል መተንፈስ የሚፈራው ከራሱም ጋር ከፈጣሪውም ጋር ኩኩሉ የሚጫወት ነው።

ስለዚህ የዘር ማጥፋትን ሙከራ ሊያከሽፍ የሚችለው ራስን የመከላከል አቅም መገንባት እንጂ፣ በአቦ በሥላሴ ወይም በአላህ ብሎ መለመን አይደለም። ይህንን ነው ‹‹ጄኖሳይድ››ን ያጠኑት፣ የጻፉት የሚሉት። በዚህ አራተኛ ክፍል የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚለውን አጀንዳ እዘጋለሁ። በሌላ አጀንዳ ለመገናኘት ያብቃን።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዋይኤችኤም የማማከርና የኮሙዩኒኬሽን ኤጀንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...