Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የ2014 ሒሳብ ዓመት አፈጻጸምና የገጠሙት ተግዳሮቶች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2014 የሒሳብ ዓመት ካገኙት 15.6 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ውስጥ ዘርፉን የሚመራው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 43 በመቶው የሚሆነውን የዓረቦን ገቢ ድርሻ፣ ማለትም 6.7 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ በማግኘት የገበያ ድርሻውን ጠብቆ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የ2014 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን የሚያመለክተው መረጃ እንደሚጠቁመው የዘንድሮ የዓረቦን ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ 

ድርጅቱ በ2013 የሒሳብ ዓመት ማሰባሰብ ችሎ የነበረው የዓረቦን መጠን 6.15 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የዘንድሮው የዓረቦን ገቢ በ8.7 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡ 

ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በሒሳብ ዓመቱ የተከፈለው የካሳ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡  

በመረጃው መሠረት መድን ድርጅቱ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ የካሳ ክፍያ ፈጽሟል፡፡ የዘንድሮው የካሳ ክፍያ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ የተያበት መሆኑንም የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል፡፡ ለዚህ ከፍተኛ የካሳ ክፍያ ወጪ የዳረገው ዋነኛ ምክንያት ከወቅታዊው የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ በተለይም የሞተር ኢንሹራንስ ዘርፍ የካሳ መጠን ከወትሮው በተለየ ጭማሪ በማሳየቱ እንደሆነ መረጃው ይጠቁማል፡፡ 

በአገሪቱ በተከሰተው የዋጋ ንረት ሳቢያ የተሽከርካሪ መለወወጫ ዕቃዎች ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ በመጨመሩ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ተሽከርካሪዎች ለመለዋወጫ ዕቃዎች ግዥ ያቀረቡት የካሳ ክፍያ መጠን፣ እንዲሁም ለማስጠገንና ለተያያዥ ሥራዎች ጋራዦች የሚጠይቁት ዋጋ ያልተጠበቀ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። በዚህም የተነሳ የሒሳብ ዓመቱ የጉዳት ካሳ ክፍያ መጠንን ከፍ እንዳደረገው መረጃው ያመለክታል፡፡ የካሳ ክፍያ መጠን ዕድገቱ በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የሁሉም የአገሪቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ችግር እንደሆነ ያነጋገርናቸው የኢንሹራስ ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሽከርካሪዎች የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ ባልተጠበቀ ሁኔታ መጨመር የኩባንያዎቹን የካሳ ክፍያ ማሳደጉንና አንዳንድ የመለዋወጫ ዕቃዎችም በወራት ልዩነት አራትና አምስት እጥፍ የደረሰ የዋጋ ጭማሪ እያሳዩ መዝለቃቸው ለዘርፉ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የ2014 የሒሳብ ዓመት በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢንሹራስ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከቀዳሚው ዓመት የተሻለ ዓረቦን ማሰባሰብ የቻለበት መሆኑን የዘርፉ የሥራ አፈጻጸምን የተመለከቱ ግርድፍ መረጃዎች ያሳያሉ።

በዚህ መረጃ መሠረትም ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያን ሳይጨምር 16ቱ የግል  የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በሒሳብ ዓመቱ ማሰባሰብ የቻሉት የዓረቦን መጠን ከ15.7 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህም 16ቱ የኢንሹራስ ኩባንያዎች በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገቡት የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2.49 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን፣ በመረጃው የተጠቀሱት 17ቱ ኢንሹራንሶች የዓረቦን ገቢያቸውን በተለያየ መጠን ማሳደግ ችለዋል።

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የዓረቦን መጠናቸውን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አፍሪካ ኢንሹራንስ፣ ፀሐይ ኢንሹራንስ፣ ንብ ኢንሹራንስ፣ ናይል ኢንሹራንስ፣ ኦሮሚያ ኢንሹራንስና ኅብረት ኢንሹራንስ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ 

በኢንዱስትሪው ውስጥ ከ17ቱ የግል የኢንሹንስ ኩባንያዎች ዓመታዊ የዓረቦን ገቢውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለው አዋሽ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የዓረቦን ገቢውን ከ1.75 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችሏል፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም የሚያስረደው አጭር ሪፖርት እንደሚጠቁመው፣ ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ 939 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ሲያገኝ፣ ኅብረት ኢንሹራንስ ደግሞ 930 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ በማግኘት ከአዋሽ ኢንሹራንስ ቀጥሎ ከፍተኛ የሚባለውን የዓረቦን መጠን ያሰባሰቡ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሆነዋል።

ዓመታዊ የዓረቦን ገቢያቸውን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል ደግሞ ንብ ኢንሹራንስ 710 ሚሊዮን ብር፣ ናይል ኢንሹራንስ  784 ሚሊዮን ብር፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ 584 ሚሊዮን ብር፣ ፀሐይ ኢንሹራንስ 585 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን በመሰብሰብ ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡  

በዘንድሮ የኩባንያዎቹ የሥራ አፈጻጸም ከቀደሚው ዓመት የዓረቦን አሰባሰቡ አንፃር ከፍተኛ የሚባል ዕድገት ያሳየው ዘመን ኢንሹራንስ ነው፡፡ ዘመን ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ማሰባሰብ የቻለው 77 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የዓረቦን መጠን ከሁሉም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዓረቦን ገቢ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው የዓረቦን ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ208 በመቶ ብልጫ እንዳለው መረጃው ያመለክታል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የዓረቦን መጠኑን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደገው ሌላው ቡና ኢንሹራስ ኩባንያ ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 473 ሚሊዮን ብር መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡ ቡና ኢንሹራንስ ያገኘው የዓረቦን ገቢ መጠን በ2013 የሒሳብ ዓመት ካገኘው ገቢ አንፃር ሲታይ 41.7 በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑንም መረጃው ጠቁሟል፡፡ ቡና ኢንሹራስ በ2013 የሒሳብ ዓመት 334 ሚሊዮን ብር አሰባስቦ የነበረ ሲሆን፣ የዘንድሮ ገቢ በ139 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ 

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደ ቀደመው ጊዜ ካሰባሰቡት ዓረቦን ውስጥ አብዛኛውን ያሰባሰቡት ከሞተር ወይም ከተሸከርካሪ የኢንሹራንስ ሽፋን ሲሆን፣ ይህም ከከ65 እስከ 70 በመቶ ያለውን ድርሻ እንደሚይዝ፣ በዚሁ ልክም የሞተር ዘርፍ ኢንሹራንስ ድርጅቶቹን ለከፍተኛ የካሳ ወጪ የሚዳርግ እንደሆነ ከመረጃው መረዳት ተችሏል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አንድ መንግሥታዊና 17 የግል ኢንሹራስ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች