በሴካፋ የሚሳተፈው የንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን ተጋጣሚዎች ታወቀ
በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በኮትዲቯር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፣ ቀሪ የምድብ ጨዋታዎች እንዲራዘሙ መደረጉን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታወቀ፡፡ በማጣሪያው ምድብ አራት የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም. ከጊኒ አቻው ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ፣ ወደ መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. እንዲሸጋገር ተደርጓል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሎ ቆይቷል፡፡ በችግሩ ምክንያት ስፖርቱን ጨምሮ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ፕሮግራሞች በተያዘላቸው ጊዜ ሳይከናወኑ እንዲሰረዙ፣ አልያም ደግሞ አንዲራሙ መደረጉ አይዘነጋም፡፡
በአሁኑ ወቅት ኮቪድ-19 ዓለም ላይ እያስከተለው ያለው ተፅዕኖና ሥጋት እንደ ጅምሩ ባይሆን፣ ነገሮችን ወደ ቀድሞ መልካቸው ለመመለስ ግን እንቅንስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በየሁለት ዓመቱ አንድ ጊዜ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫን ጨምሮ የስፖርቱ ዘርፍ ይጠቀሳል፡፡
በዚሁ መሠረት አኅጉራዊ የእግር ኳስ ተቋም (ካፍ) ባለፈው የውድድር ዓመት በካሜሩን አስተናጋጅነት የተከናወነው 22ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፣ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ 33ኛውን የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ በኮትዲቯር አስተናጋጅነት እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 20 እስከ 28/2023 ድረስ ለማከናወን ዕቅድ ይዞ የምድብ ማጣሪያዎችን መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ካፍ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳስታወቀው፣ ቀደም ሲል ይዞት የነበረውን የአፍሪካ ዋንጫ ፕሮግራም ከመጋቢት ወደ ሰኔ ወር አሸጋግሮታል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ቀሪ የምድብ ጨዋታዎችም የፕሮጋራም ለውጥ ተደርጎባቸዋል፡፡
በማጣሪያው ምድብ አራት ከግብፅ፣ ከጊኒና ማላዊ ጋር ተደልድሎ ሁለት ጨዋታዎችን ማለትም በሜዳው (በስታዲየም ችግር) ከሜዳው ውጪ ለመጫወት የተገደደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ በማላዊ 2 ለ1 ተሸንፎ፣ የግብፅ አቻውን ደግሞ በአልተጠበቀ የጨዋታ እንቅስቃሴ 2 ለ 0 ማሸነፉን ተከትሎ ምድቡን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡
ካፍ ቀደም ሲል ይፋ ባደረገው የጨዋታ ፕሮግራም መሠረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሦስተኛውን የምድብ ማጣሪያ በሜዳው (በስታዲየም ዕገዳ ምክንያት) ከሜዳው ውጪ የጊኒ አቻውን በመስከረም ወር ሊያከናውን የነበረው ጨዋታ ወደ መጋቢት ወር 2015 እንዲሸጋገር ተደርገዋል፡፡
ጨዋታው የፕሮግራም ለውጥ ማድረጉ ምናልባትም በስታዲየም ዕጦት ምክንያት በጎረቤት አገር ስታዲየም እንዲጫወት የተፈረደበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ በዚህ የጊዜ ሽግሽግ የማሻሻያ ግንባታ እየተደረገለት የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም፣ ካፍ ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቃበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል በመግለጽ፣ አጋጣሚውን ልንጠቀምበት እንደሚገባ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡
ካፍ በአዲስ መልክ ይፋ ባደረገው የጨዋታ ፕሮግራም መሠረት፣ የምድብ ሦስትና ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምድብ አራት አገሮች እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 11 እስከ 19 ቀን 2015 ድረስ የየምድባቸውን አራተኛ የማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
አምስተኛው የምድብ ማጣሪያ ደግሞ እ.ኤ.አ. ከሰኔ 5 እስከ 13 ቀን 2015 ድረስ ባሉት ቀኖች ይደረጋል፡፡ በኮትዲቯር ስተናጋጅነት እ.ኤ.አ. ከሰኔ 12 እስከ 20 ቀን 2015 ድረስ ይካሄዳል፡፡ 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተፋላሚ አገሮች የሚለዩበት የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ደግሞ እ.ኤ.አ. ከነሐሴ 29 እስከ መስከረም 1 ቀን 2015 ስለመሆኑ ጭምር ካፍ በማኅራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በታንዛኒያ አስተናጋጅነት የ2022 ቀን 23 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ በሚደረገው የምሥራቅ መካከለኛና አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ተጋጣሚዎች ታወቁ፡፡
በምድብ ‹ሀ› ከዛንዚባር ዋሪየስ፣ ከቡርንዲው ፎፊላና ከሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ ጋር እንደሚጫወት ታውቋል፡፡ በዚሁ መሠረት ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከዛንዚባሩ ዋሪየስ ጋር ከተጫወተ በኋላ፣ ሁለተኛውን ጨዋታ ደግሞ ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቡርንዲ ፎፊላ ጋር፣ እንዲሁም ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ እንደሚጫወት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡