Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕፃናትን ከኩፍኝ ወረርሽኝ የመታደግ ሥራ

ሕፃናትን ከኩፍኝ ወረርሽኝ የመታደግ ሥራ

ቀን:

ኩፍኝ በአብዛኛው በሕፃናት ላይ የሚከሰት ሞት፣ ዘላቂ የአካል ጉዳት (እንደ ዓይነ ሥውርነት) እና ከፍተኛ ሕመም ሊያመጣ የሚችል በሽታ ነው፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ፣ በተጨማሪም ወረርሽኝን ለማስከተል የሚችል አደገኛ በሽታ መሆኑና በክትባት መከላከልና መቆጣጠር እንደሚቻል ይታወቃል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ይህንን በሽታ ለመከላከል ለረዥም ዓመታት የኩፍኝ ክትባትን ሕፃናት በተወለዱ በዘጠኝ ወራቸው እንዲከተቡ ተደርጓል፡፡ የክትባቱም ሥራ የተከናወነው በዘመቻ መልክና በጤና ተቋማት ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በዘጠኝ ወራት ከሚሰጠው ክትባት በተጨማሪ ሕፃናት አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ሲሞላቸው ሁለተኛ ዶዝ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት በተጨማሪ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ በአገር አቀፍ ደረጃ በመከናወን ላይ ነው፡፡

በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የኩፍኝ ክትባት ሽፋን በመደበኛው የክትባት መርሐ ግብርና ቀድሞ የመከላከል የክትባት ዘመቻዎችን በማካሄድ ሊከሰቱ የሚችሉ የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝን መከላከል እንደተቻለ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ግን በመላ አገሪቱ በተከሰቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ የኩፍኝ የክትባት ሽፋን ዝቅተኛ በሆኑባቸው ውስን አካባቢዎች የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ እንደተከሰተ፣ በዚህም የተነሳ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልል ጤና ቢሮዎችና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ፈጣን ምላሽ የመስጠት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

የኩፍኝ ወረርሽኙ በተለያዩ ጊዜያት በአምስት ክልሎች ማለትም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ በ45 ወረዳዎች ላይ ተከስቷል፡፡ አብኛዎቹን መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በ11 ወረዳዎች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየተሠራ ይገኛል፡፡ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ ዋነኛውና አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት የክትባት ዘመቻዎችን ማካሄድ ሲሆን፣ በእነዚህ ዘመቻዎች 827,053 ሕፃናትን መከተብ ተችሏል ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ከአማራ፣ ከአፋር፣ ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮዎችና አጋር አካላት ጋር በመተባበር በጦርነት ምክንያት ለረዥም ጊዜ የክትባት መርሐ ግብር በተቋረጠባቸውና ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ ሕፃናት የኩፍኝ ክትባት በዘመቻ መልክ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

በእነዚህም ዕድሜቸው ከስድስት ወራት እስከ 23 ወራት የሞላቸውን 1,204,926 ሕፃናት መከተብና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች የመደበኛውን የክትባት ሥራውን ለማጠናከር የበጀት ድጋፍ በማድረግ ያልተከተቡ ሕፃናትን በመለየት የመከተብ ሥራዎች መከናወናቸውንና በእነዚህም ከ88 ሺሕ በላይ ሕፃናት የኩፍኝ መከላከያ ክትባት እንዳገኙ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴርና አጋር አካት (UNICEF እና WHO) ጋር በተባባርም በትግራይ ክልል የኩፍኝ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ዕድሜያቸው ከስድስት ወራት እስከ 59 ወራት ለሞላቸው 731,474 ሕፃናት የኩፍኝ ክትባት በዘመቻ መልክ መስጠት እንደተቻለ አክለዋል፡፡

የኩፍኝ በሽታን ለመከላከል በየትኛውም አካባቢ የሚኖር ወላጅ ልጆቹን እንዲያስከትብ፣ ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሚዲያዎች የኅብረተሰብ ንቅናቄ በማድረግ ሕፃናት እንዲከተቡ ጥረት እንዲያደርጉና ሌሎችም ባለድርሻ አጋር አካላት የመከላከል ሥራው ላይ እንዲረባረብ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ እስካሁን በአገራችን በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ታማሚ ያልተመዘገበ ሲሆን፣ የበሽታውን ቅኝት ሥራ ለማጠናከርና ወረርሽኙን ለመከላከል ይቻል ዘንድ ከውጭ አገር ተመላሾች ለጥንቃቄ ሲባል የቆዳና ሌሎች የሕመም ምልክቶች ሲገኝባቸው ከግለሰቦች ላይ ናሙና እየተወሰደ የምርመራና የክትትል ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ደረጀ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡  

የላቦራቶሪ አቅምን በማጠናከርና በአገር ውስጥ ምርመራ መሥራት የተቻለ ሲሆን፣ የተለያዩ  የቅኝትና ምላሽ እንዲሁም የላቦራቶሪ መመርያዎች ተዘጋጅተው ለክልሎች ተሠራጭተዋል፡፡ የመግቢያና የመውጫ ኬላዎች ላይ የልየታ እንዲሁም  የቅኝት ሥራዎች በሁሉም ቦታዎች ላይ ተጠናክረው እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...