Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየአልቃይዳ የጀርባ አጥንት አይመን አል ዘዋህሪ ሞት

የአልቃይዳ የጀርባ አጥንት አይመን አል ዘዋህሪ ሞት

ቀን:

የአሜሪካና የታሊባን ወይም የዶሃ ስምምነት ይሉታል፡፡ ይህ አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2001 በአፍጋኒስታን የጀመረችውን ሽብርተኞችን የማጥፋት ጦርነት እንድታቆም በ2021 በኳታር ዶሃ የተደረገ ስምምነት ነው፡፡

ከስምምነቱ አንዱ አፍጋኒታንን ከዓምና ጀምሮ የተቆጣጠረው ታሊባን ማናቸውም የሽብር ቡድኖች በአፍጋኒስታን እንዳይጠለሉ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት የሚያደርግ ነው፡፡ አሜሪካ ደግሞ በአፍጋኒስታን ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን እንድታቆም ያስገድዳል፡፡

 ታሊባን አፍጋኒስታንን ማስተዳደር ከጀመረ ማግሥት ጀምሮ በኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አቅሟ በተንኮታኮተችው አፍጋኒታን የአሜሪካ መከላከያ እንደ ቀድሞው በአካል ባይገኝበትም፣ አገሪቷ ከዕይታ መረብ አልራቀችም፡፡ ለዚህም ደግሞ አንዱ ምክንያት በአሜሪካ የሽብርተኞች ዝርዝር ቀዳሚውን የሚይዘው የአልቃይዳ መሪ በዚያው ቀጣና መገኘቱ ነው፡፡

ይህ ሰው የአልቃይዳ የጀርባ አጥንት፣ ስትራቴጂስትና ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ለተገደለው የአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን አማካሪ የነበረው የ71 ዓመቱ አይመን አል ዘዋህሪ ነው፡፡

ዛሬ አል ዘዋህሪ የለም፡፡ ያ በግብፅ ለአንዋር ሳዳት ግድያ በመጠርጠር የታሰረው፣ በኢትዮጵያ ለግብፁ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ግድያ ሙከራ እጁ አለበት የተባለው፣ በአሜሪካ የ9/11 ጥቃትን በማቀነባበር ከኋላ አለ የተባለው አል ዘዋህሪ በአሜሪካ የድሮን ጥቃት መገደሉን አሜሪካ አስታውቃለች፡፡

በአፍጋኒስታን ካቡል ውስጥ በአሜሪካ የድሮን ጥቃት በዚህ ሳምንት መጀመርያ ተገድሏል የተባለው አልዘዋህሪ፣ ኦሳማ ቢን ላደን በአሜሪካ ከተገደለ ከ2011 በኋላ አልቃይዳን እየመራ የነበረ የቡድኑ የጀርባ አጥንት ነው፡፡

በአሜሪካ የድሮን ጥቃት መገደሉን አስመልክቶ ‹‹ይህ የሽብር መሪ ከዚህ በኋላ የለም›› ሲሉ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና የአሜሪካ ባለሥልጣናት፣ ከ2001ዱ የአሜሪካ የሽብር ጥቃት 9/11 ጀርባ ግብፃዊው አል ዘዋህሪን ይወነጅላሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ተገድሏል ሲባል የነበረው ዘዋህሪ፣ በአፍጋኒስታንና ፓኪስታን ድንበሮች ይኖራል ተብሎ ሲጠረጠር የነበረ ቢሆንም፣ አሜሪካ እንደገደለችው ያስታወቀችው እሑድ ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ከሚኖርበት መኖሪያ ወደ በረንዳ ሲወጣ መሆኑን ነው፡፡

ከሃያ ዓመታት በላይ ታድኖ፣ ለወራት ከቆየ ዕቅድና ክትትል በኋላ አልዘዋህሪ ቢገደልም፣ በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ባይደን ተናግረዋል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው፣ አሜሪካ አፍጋኒታንን ለቃ ከወጣች ወዲህ ይህ የመጀመርያ የድሮን ጥቃቷ ነው፡፡ ጥቃቱ ደግሞ በታሊባን ዘንድ ውግዘት ገጥሞታል፡፡ ታሊባን ‹‹አሜሪካ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ጥሳለች›› ሲልም የአሜሪካን ድርጊት ነቅፏል፡፡

የአፍጋኒስታን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ፣ በከተማዋ አንድ ቤት በሮኬት መመታቱን፣ ሆኖም ቤቱ ውስጥ ማንም ስላልነበር ምንም ክስተት እንዳልታየ ገልጸዋል፡፡ በቤቱ አካባቢ የደኅንነት አካላት ቢላኩም ለጋዜጠኞች ክፍት ባለመሆኑ ደግሞ በሥፍራው ስለተከሰተው ግልጽ የወጣ ነገር የለም፡፡ ሆኖም አሜሪካ ሰውየውን ስለመግዷል አስረግጣ ተናግራለች፡፡

 የአልቃይዳ ቡድን ቁልፍ አል ዘዋህሪ፣ በዓለም ባለው ኔትወርክና አሜሪካን በማጥቃት የታወቀ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. በ1998 በኬንያና በታንዛኒያ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ ለደረሰው የቦንብ ጥቃት፣ ሦስት ሺሕ ያህል ሰዎች ለሞቱበት በዋሽንግተንና በኒውዮርክ ለደረሰው የ9/11 ጥቃት አቀናባሪ ነው፡፡

የአልቃይዳ መሥራች ቢንላደን ከተገደለ በኋላ የቡድኑ መሪ የሆነው አል ዘዋህሪ፣ ለውስጥ አርበኝነትን የታደለ ነበር፡፡ ከታዋቂ የሳዑዲ ዓረቢያ ቤተሰብ የተገኘው  ቢንላደን ለአልቃይዳ ሞገስና ገንዘብ ይዞ ሲመጣ፣ ግብፃዊው የዓይን ዶክተር አልዘዋህሪ ደግሞ ለአልቃይዳ ጥበብ፣ ዘዴና ድርጅታዊ መዋቅር ዘርግቶ የሚያንቀሳቅስ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. በ2001 አሜሪካ ከአፍጋኒስታን አልቃይዳን አጠፋለሁ ብላ ወታደራዊ ዘመቻ ስትጀምርና የቡድኑን አባላት ስታድን አልዘዋህሪ ለቡድኑ መኖር ትልቁን ሚና የተጫወተ የአልቃይዳ አዕምሮ ነበር፡፡

በወቅቱ በርካታ የቡድኑ መሪዎችና አባሎች ተይዘው ጓንታናሞ እስር ቤት ሲወረወሩ፣ በአፍጋኒታንና ፓኪስታን ድንበር አካባቢዎች አመራሩን መልሶ በመገንባት ለአልቃይዳ ሕይወት ዘርቶበታል፡፡ ድርጅቱን መልሶ በማቋቋምና የድርጅት መልክ በማስያዝ በማዕከላዊነት የሚመራ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓና አፍሪካ የደረሰ የጥቃት ዕቅድ በመዘርጋትም ይታወቃል፡፡

ዛሬ ይህ ሰው በአሜሪካ የድሮን ጥቃት ተገድሏል ቢባልም፣ የሚድል ኢስት ኢንስቲትዩትን ጠቅሶ ኤንዲቲቪ በድረገጹ እንዳሰፈረው፣ የግብፅ የቀድሞ ወታደርና የአልቃይዳ መሥራች አባልና የቡድኑ ሦስተኛ ሰው ሰይፍ አል አዲል ቀጣዩ የአልቃይዳ መሪ ይሆናል፡፡

ሰይፉ አል አዲል በአሜሪካ በሽብር ከሚፈለጉ ሰዎች አንዱ ሲሆን፣ የአልቃይዳ መሪ ሆኖ ከመጣ ከአል ዘዋህሪ የበለጠ ታዋቂና የተግባር ሰው እንደሚሆን አትላንቲክ ካውንስል አስፍሯል፡፡

ይህ ሰው የኦሳማ ቢን ላደን የደኅንነት መሪ የነበረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ1993 ጀምሮ በአሜሪካ መከላከያ ሲታደን ነበር፡፡ አዲል በዚህ ወቅት ዕድሜው 30 የነበረ ሲሆን፣ 18 አሜሪካውያን የሞቱበትን የአሜሪካ ሄሊኮፍተር በሞቃዲሾ ሶማሊያ የጣለ አሜሪካ በጠላትነት የፈረጀችው ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...