Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ180ዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በ‹‹መዝገበ አዕምሮ››

180ዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በ‹‹መዝገበ አዕምሮ››

ቀን:

በእስክንድር መርሐጽድቅ

ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተቋቋመው ከ15 ዓመታት በፊት ሲሆን፣ በርካታ የህትመት ውጤቶችን አሳትሟል፡፡ ከዚህ ተግባሩ ባሻገር ግን የተነሳው የአገር ባለውለታዎችን ታሪክ በመተንተንና በማቅረብ የራሱን ድርሻ መወጣት የጀመረው፣ ‹‹ታሪክን በሲዲ›› በሚል በሙያቸው አርዓያ የሆኑትን ዶክመንተሪ ፊልም አዘጋጅቶ ነው፡፡

ከባለታሪኮቹ መካከል ጸሐፌ-ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ አቶ አካለወርቅ ሀብተ ወልድ፣ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክና ሌሎች ከ40 በላይ የአገር ዋርካዎች ታሪክ በሲዲ ወጥቶ በልዩ ሥነ ሥርዓት ከተመረቀ በኋላ ለባለታሪኩ ወይም ለባለታሪኩ ወራሽ ቤተሰቦች እንዲሁም ለሚመለከታቸው ተሠራጭቷል፡፡

ከ‹‹ታሪክን በሲዲ›› ቀጥሎ፣ ‹‹ታሪክን በድረ ገጽ ከዘመኑ ሰዎች ጋር›› የሚለው ሐሳብ ተነድፎ የበርካታ ሰዎች ታሪክ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሠርቷል፡፡ ለዚህ ሲባል ታሪካቸው የተሰበሰበው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ፣ በሌሎች ባለሙያዎችና ባለታሪኮቹ ራሳቸው ጽፈው እንዲያቀርቡ ታዘው ነው፡፡ እንዲሁም ከድረ ገጽ፣ ከህትመቶችና ከሌሎችም መንገዶች ሲሆን መረጃዎቹ በሌላ መንገድ የማጣራት ሥራም ተካሂዶባቸው ነው በየተራ የወጡት (ፖስት የተደረጉት)፡፡ ለፌስቡክ የተመረጡት ሰዎች ታሪካቸው ሲወጣ አንዳንዶቹ፣ ‹‹እንዴት የእከሌን ታሪክ ትሠራላችሁ? የእርሱ ታሪክ ካለ የእኔን አልሰጣችሁም!›› ብለው ነበር፡፡ ታሪካቸው ቀድሞ የተሠራላቸው ደግሞ፣ ‹‹እኔ ባለሁበት የእርሱ ወይም የእርሷ ታሪክ መኖር የለበትም›› ብለው ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ ራሳቸውን ምንም እንዳልሠራ በመውሰድ፣ ‹‹እኔ ምን ታሪክ አለኝና ነው? እስኪ መጀመሪያ ብዙ የሠሩትን አዳርሱ››ም ብለው ታሪካቸውን የነፈጉ አሉ፡፡

እንዲህ እያለ የተጓዘው የባለታሪኮችን ታሪክ የመሰነድ ተግባር ወደ መጽሐፍ ሐሳብ አድጎ ከዚህ ቀደም በፌስቡክ ታሪካቸው የወጣ ሰዎች የፌስቡኩ ታሪክ እንዳለ ሳይሆን ሰፊ የአርትኦት ሥራ ተሠርቶበት፣ ‹‹መዝገበ አዕምሮ›› በመሰኘት በ600 ገጾች የታተመው መጽሐፍ የ180 የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ታሪክ ይዞ በመታተም ለፊታችን ሐምሌ 30 ለምረቃ ተዘጋጅቷል፡፡

አንድን መጽሐፍ በጠንካራ ሽፋን ማቅረብ ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛ፣ መጽሐፉ በሥርዓቱ የተጠረዘ በመሆኑ ረዥም ዓመታት የመቆየት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ መጽሐፉ ላይ ታሪካቸው የሚወጣ ሰዎች ቤታቸው የሚያስቀምጡትና ለትውልዳቸው የሚያስተላልፉት ጥሩ ማስታወሻ ያገኛሉ። ከዚህ በተጓዳኝ፣ በጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎችና ለተመራማሪዎች የጥናት መነሻ የሚሆን እውነት ያዘለ መጽሐፍ በመሆኑ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ እንግዲህ በዚህ መልኩ በመዘጋጀቱ እስከዛሬ ከታተሙት የበርካታ ሰዎችን ታሪክ የያዘ መሆንን ጨምሮ ለየት ያደርገዋል፡፡

ስያሜው በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹ኢንሳይክሎፒዲያ›› በመባል ቢታወቅም በአገርኛ ይዘት የተዘጋጀ በመሆኑ ይህንኑ በሚገባ አብራርቶ የሚገልጽ ስያሜ አስፈልጎታል፡፡ በዚህ ላይ የቋንቋ ምሑሩ የዶክተር ታከለ ታደለና የባህልና የቅርስ ባለሙያው የአቶ መንክር ቢተው ሐሳብ ተጠይቆ ስያሜውም በአገር በቀል ቋንቋ ሊገለጽ እንደሚገባው ታመነበት፡፡ በዚህም መሠረት የስያሜ ርዕሶች ሲታጩ፣ ‹‹የእውቀት ክምችት››፣ ‹‹ክምችተ-እውቀት››፣ ‹‹ክምችተ-አዕምሮ››፣ ‹‹ግብረ-ሰብ››፣ ‹‹መዝገበ-ጥበብ›› እና ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› ተጠቁመው በመጨረሻ፣ ‹‹መዝገበ-አዕምሮ›› ጸደቀ፡፡ ስያሜው ከግእዝ የተወሰደ ሲሆን ‹‹መዘገብ›› ማለት ስብስብ፤ ‹‹አዕምሮ›› ደግሞ እውቀትንና የሥራ ሁሉ መነሻን ጠቅሎ የያዘ ቃል ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹መዝገበ-አዕምሮ››፣ መረጃና እውቀትን፣ ጥበብና ሐሳብንና የራስ ተሞክሮን የሚያመለክት ስያሜ ስለሆነ ሁሉም ተስማማበት፡፡

በዚህ መጽሐፍ ከ1950ዎቹ እስከ 200ዎቹ ባሉት 54 ዓመታት ሠርተው ካለፉትና አሁንም በሥራ ላይ ከሚገኙት 180ዎቹ ተካተዋል፡፡ ባለሙያዎቹ ወደ ሚዲያ የመጡበትን ዓመት የያዘው መጽሐፉ ባለታሪኮቹን በዘመን ከፋፍሎ ‹‹የ1950ዎቹ››፣ ‹‹የ1960ዎቹ››፣ ‹‹የ1970ዎቹ››፣ ‹‹የ1980ዎቹ››፣ ‹‹1990ዎቹ›› እና ‹‹የ2000ዎቹ›› በሚል ነው ያስቀመጠው፡፡ የአቀማመጥ ቅደም ተከተሉ በዘመን ከ1950 ተነስቶ 2000ው ላይ ቢደመድምም ባለታሪኮቹን ግን በአማርኛ ፊደል ተራ (ከ‹‹ሀ›› ተነስቶ ‹‹ፐ›› ላይ በማጠቃለል) ነው ያሰፈራቸው፡፡

በዚህ መጽሐፍ ላይ የቀረቡት ሰዎች አብዛኛዎቹ ጋዜጠኛ ሆነው አገራቸውን ያገለገሉ፣ ጥቂቶቹ መገናኛ ብዙኃንን መሥርተው አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ መነሻ ሥራቸው መገናኛ ብዙኃን ሆኖ በየመሥሪያ ቤቶች ጥሩ የተግባቦት ወይም የኮሙዩኒኬሸን ባለሙያ ሆነው የሠሩ ወይም እየሠሩ የሚገኙ  ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ በግራፊክስና በቴክኒክ ዘርፍ የተካተቱ ናቸው፡፡

‹‹በመዝገበ-አዕምሮ›› መጽሐፍ ላይ ከተካተቱት 180 ሰዎች ከእነዚህ ውስጥ 34ቱ በሕይወት የሌሉ ሲሆኑ 52ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ ባለታሪኮቹ የተመረጡበት መሥፈርት በመጽሐፉ የመማክርት ቡድን ጊዜ ተወስዶ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በዚህም መሠረት በራሳቸው ዘመን የኖሩ፣ የራሳቸውን መለያ ቀለም ያበጁና በሙያቸው የተመሰከረላቸው መሆናቸው አንዱ መሥፈርት ነው፡፡ ሌላው በዘመናቸው ካሉ እኩያ አቻዎቻቸው የተሻሉ ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡

የመዝገበ-አዕምሮ 180 ባለታሪኮች በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ፣ በአፋርኛ፣ በአዊ፣ በሶማሊኛና በዓረብኛ ጋዜጠኝነትን ያራመዱ ናቸው፡፡ ሁሉም ታሪካቸው የተነጻጸረው ከኖሩበትና ከሠሩበት ጊዜ እንዲሁም በጊዜው ከሠሩት ሥራ አኳያ እንጂ የቀደሙትን ከአሁኖቹ ጋር በማነጻጸር አይደለም፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነው ይህ መጽሐፍ አንዱ የቀደሙትን ጋዜጠኞች እግር እየተከተለ መሄዱን ከማሳየት አልፎ የእነዚህን ባለሙያዎች አርዓያነት ለመከተል የልምድ ገበያነቱን እንደ መርካቶ ገበያ ከፍቶ የሰጠ በመሆኑ በተለይ ለተመራማሪዎች፣ ለጋዜጠኞችና ለሌሎችም ጽሑፍ አዘጋጆች ጥሩ የመረጃ ምንጭ ነው፡፡

የዚህ መጽሐፍ ሌላው ጠቀሜታ፣ በሌሎች የሙያ መስክ ያሉ ባለታሪኮችን በአንድ ሰብስቦ ለመጻፍ መነሻ መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ የተለያዩም ይሁን የአንድ ሙያ ባለቤቶችን ታሪክ ተርጉሞም ሆነ ወጥ አድርጎ መጻፍ በዚህ መጽሐፍ የተጀመረ ባይሆንም እንዲህ በዝተውና መነሻ ጽሑፉ በራሳቸው ተዘጋጅቶ መቅረቡ እንዲሁም በገጽ ብዛቱና በጥረዛ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡

ይህን መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ያደረጉት አባላት እንደየድርሻቸው በመረጃ ስብሰባ፣ በአርትኦት፣ በፊደል እርማት፣ በጥናትና በፊቸር ጽሑፍ እንዲሁም በሌይ አውት ንድፍ እና በማማከር አዳብረውታል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ርብርብ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ከአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የአዕምሯዊ ንብረት መብት (ፓተንት ራይት) የተገኘበት ስለሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃም የመስፋፋበት እንዳለው ከአዘጋጁ ተረድተናል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነው ይህ መጽሐፍ አንዱ የቀደሙትን ጋዜጠኞች እግር እየተከተለ መሄዱን ከማሳየት አልፎ የእነዚህን ባለሙያዎች አርዓያነት ለመከተል የልምድ ገበያነቱን እንደ መርካቶ ገበያ ከፍቶ የሰጠ በመሆኑ በተለይ ለተመራማሪዎች፣ ለጋዜጠኞችና ለሌሎችም ጽሑፍ አዘጋጆች ጥሩ የመረጃ ምንጭ ነው፡፡

የዚህ መጽሐፍ ሌላው ጠቀሜታ፣ በሌሎች የሙያ መስክ ያሉ ባለታሪኮችን በአንድ ሰብስቦ ለመጻፍ መነሻ መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ፣ የተለያዩም ይሁን የአንድ ሙያ ባለቤቶችን ታሪክ ተርጉሞም ሆነ ወጥ አድርጎ መጻፍ በዚህ መጽሐፍ የተጀመረ ባይሆንም እንዲህ በዝተውና መነሻ ጽሑፉ በራሳቸው ተዘጋጅቶ መቅረቡ እንዲሁም በገጽ ብዛቱና በጥረዛ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...