Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የውጭ አገር ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን እንግልት ለመቀነስ

በኢትዮጵያ የሕክምና አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ይታመናል፡፡ በተለይም በሕክምና ስህተት ሕሙማን ለሞት ሲጋለጡ አልያም ደግሞ ለሌላ ስቃይ ሲዳረጉም ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሆነው ለከፍተኛ በሽታ የተጋለጡ ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት በአገር ውስጥ ለማግኘት ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታትና አሠራሩን ለመቀየር ጌትዌል የጤና ማማከር አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በጋሻው ባይለየኝ (ዶ/ር) የማኅበሩ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የማኅበሩን ሥራ አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጌትዌል የጤና ማማከር አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እንዴት ተመሠረተ?

በጋሻው (ዶ/ር)፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ ስምንት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ በሰው ኃይልም ሆነ ቴክኖሎጂ ነክ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ለውጥ በመምጣቱ የሕክምና ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ ከተመሠረተ ጀምሮ ሕሙማን ወደ ተለያዩ አገሮች ሄደው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን እያመቻቸን ይገኛል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ላይ የማይሰጡ ሕክምናዎች በሚኖሩ ጊዜ ታካሚዎች የት ሄደው መታከም እንዳለባቸው ጭምር ግራ ሲጋቡ ይታያል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እንዴት እንደሚታከሙ? የት ነው የሚታከሙት? ምን ያህል ብር ያስፈልጋቸዋል? ምን ያህል ጊዜ ይቆያሉ? ከሕክምና ባለሙያዎች ጋርስ ይገናኛሉ? የሚለውን ባለማወቅ ብቻ ብዙ ሕሙማን ሕይወታቸውን ሲያጡና ላልተፈለገ ወጪ ሲዳረጉ ይታያል፡፡ ይህንንም ለማቅለል ማኅበሩ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ማኅበሩም ከተቋቋመ በኋላ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሕሙማን ሕክምናቸውን በሚፈልጉት መንገድ ታክመው ወደ አገራቸው መጥተዋል፡፡ ማኅበሩ በአሁኑ ሰዓትም ከለንደን፣ ከቱርክ፣ ከጀርመን፣ ከዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስና ታይላንድ ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል፡፡ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ከሚገኙ የጤና ተቋሞች ጋር ትስስር በመፍጠርና ያሉትን ችግሮች በመነጋገር ማኅበሩ እየሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ደግሞ በቱርክ አገር ከሚገኘው የሥራ አጋራችን አቺባደም ሆስፒታል ጋር በተመተባበር የካንሰር ሕክምና ባለሙያ  ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በአገር ውስጥ ከሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር ልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ አቺባደም በኢስታንቡል ከተማ ብቻ ወደ አምስት ሆስፒታሎች ያሉት ሲሆን፣ በዓለም ላይ ደግሞ በጠቅላላ 22 የሚሆኑ ሆስፒታሎች አሉት፡፡ ተቋሙ ከማኅበራችን ጋር በመሆን በቅርበት እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ በዘርፉ ላይ ውጤት ያለው ሥራ መሥራት ችለናል፡፡ ማኅበሩ ለሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት እንዲሁም የተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲያውቁ ከተለያዩ አገር ከተወጣጡ ባለሙያዎች ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ማኅበሩም ሃያ የሚሆኑ ከፍተኛ ስፔሻሊስቶችን ወደ ተለያዩ አገሮች በመላክ ሥልጠና እንዲወስዱ ማድረግ ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሕክምና ትምህርት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ ይኼንንም አሠራር ለስድስተኛ ጊዜ ማካሄድ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደዚህ ዓይነት ፎረሞችን ስታካሂዱ ለስድስተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጻችኋል ምን ዓይነት ለውጥ አምጥታችኋል?

በጋሻው (ዶ/ር)፡- ፎረም በማካሄድ የሕክምና ዘርፉ ላይ ለውጥ ማምጣት ችለናል፡፡ በተለይም የሕክምና ባለሙያዎች ሌሎች አገር ላይ ከሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸው አንድ ለውጥ እንዲያመጡ መንገድ ከፍተናል ማለት ይቻላል፡፡ ይኼም የሕክምና ዘርፉን ወደፊት አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ ማኅበሩ ይህንን አሠራር ወደፊት በማሳደግ ቀጣይነት ያለው ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ የውጭ አገር ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ሕሙማን ጉዞ እያመቻቸ ይገኛል? ተደራሽነታችሁ ምን ይመስላል?

በጋሻው (ዶ/ር)፡- ማኅበራችን ወደ ውጭ አገር ሄደው ለሚታከሙ ሕሙማን ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በተለይም የፈለጉት አገር ሄደው አገልግሎት እንዲያገኙና ምንም ዓይነት እንግልት እንዳይፈጠርባቸው ለማድረግ ከሄዱበት ጊዜ ጀምሮ ሕክምናቸውን እስኪጨርሱ ድረስ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ እስከ ዛሬ ከመቶ በላይ ዜጎችን መርዳት ችለናል፡፡ በተለይም ታዋቂ የሆኑ ሆስፒታሎች ላይ ተገልጋዮች በቀላሉ  ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ በራሱ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ምን ዓይነት ችግር ገጥሟችኋል?

በጋሻው (ዶ/ር)፡- ሥራችን ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተ ጊዜ ከፍተኛ ችግር ገጥሞናል፡፡ አብዛኛው ሕሙማን ወይም ታካሚዎች ወደ ተለያዩ አገሮች ሄደው ለመታከም ቢፈልጉም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ አገልግሎቱን ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ ወረርሽኙ በተከሰተ ወቅት አብዛኛው አገሮች በራቸውን መዝጋታቸው ይታወቃል፡፡ ይኼም ሥራችን ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮብናል፡፡ በዚህም የተነሳ በማኅበሩ ሥር የነበሩ ሕሙማን ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ አንዳንዶቹም ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ይኼም ችግር ሆኖብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ ከሌሎች ተቋሞች ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ነግረውናል? ምን ዓይነት አሠራር ዘርግታችኋል?

በጋሻው (ዶ/ር)፡- ቅድም እንደነገርኩህ ከተለያዩ የውጭ አገር ተቋሞች ጋር በቅንጅት እየሠራን እንገኛለን፡፡ በተለይም ሌሎች አገሮች ላይ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎችን እኛ አገር ካሉት ባለሙያዎች ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ ማድረግ በራሱ አንዱ የለውጥ ምልክት ነው፡፡ እዚህ አገር ከሚገኙ የሕክምና ተቋሞች ጋር በቀጥታ አብረናቸው እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ ሕሙማን ወይም ታካሚዎች በቀጥታ ወደ ውጭ ከመውጣታቸው በፊት እዚህ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮችን እንዲያገኙ የምናደርግ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሆነው ወደ ውጭ አገር ሄደው መታከም ለሚፈልጉ ሕሙማኖች ምን ዓይነት ድጋፍ ታደርጋላችሁ?

በጋሻው (ዶ/ር)፡- እኛ ትልቅ ተቋም አይደለንም፡፡ ትልቅ ሥራ ግን እንሠራለን፡፡ ይሄን ያልኩበት ምክንያት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሆነው ወደ ውጭ አገር ሄደው መታከም ለሚፈልጉ ሕሙማን ሙሉ ለሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ ማሳከም በጣም ይከብዳል፡፡ የእኛ ሥራ በዋናነት ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ውጭ አገር ሄደው የት መታከም እንደሚችሉ መጠቆም አልያም ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ አቅጣጫ መስጠት ነው፡፡ ውጭ አገር ሄደው የሚታከሙ ሕሙማን የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በምንም ዓይነት አሠራር ስንመለከት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች መርዳት ትንሽ ከባድ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሎች ላይ ምን ዓይነት አገልግሎት ትሰጣላችሁ?

በጋሻው (ዶ/ር)፡- ክልሎች ላይ ያሉን የሕክምና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እነዚህም የሕክምና ባለሙያዎች እዚህ አገር መታከም የማይችሉ ሕሙማን ወደ ማኅበራችን የመላክ ሥራ የሚሠሩ ናቸው፡፡ የሕክምና ባለሙያዎችም ለተለያዩ ባለሙያዎች መረጃዎችን በመስጠት እየሠሩ ይገኛል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በክልሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት የደረሰባቸው ሕሙማን የት አገር ሄደው መታከም እንዳለባቸው በቂ ዕውቀት የላቸውም ማለት ይቻላል፡፡ ይኼንንም ለመግታት ማኅበራችን ከተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

በጋሻው (ዶ/ር)፡- የተለያዩ የሕክምና አገልግሎቶች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ለምሳሌ አቺባደም ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ሆስፒታል መገንባት ይፈልጋል፡፡ ሆስፒታል ቢገነባ ወደ ተለያዩ አገር ሄደው የሚታከሙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቁጥር መቀነስ ይቻላል፡፡ በተለይም የአፍሪካ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲታከሙ ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች በቀላሉ ሕክምና እንዲያገኙ መንገድ ይከፍታል፡፡ ወደ ኢትዮጵያም እነዚህ ዓይነት ነገሮችን በማምጣት የሕክምና ዘርፉን ምኅዳር መቀየር ያስፈልጋል፡፡ የጤናው ዘርፍ ያልተነካ ነው፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...

‹‹የዋጋ ግሽበቱ እንደ አቅማችን እንዳናበድርና ተበዳሪዎችም እንዳይከፍሉ እያደረገ ነው›› አቶ ፍጹም አብረሃ፣ የአሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

አሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ በተቋም ደረጃ ለመመሥረቱ መነሻው ጓደኛሞች በየወሩ በቁጠባ መልክ የሚቆርጡት ተቀማጭ ገንዘብ ነው፡፡ በ20 ሺሕ ብር ካፒታል በ20 ጓደኛሞች...