Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ሕንፃ ግንባታ ከስድስት ዓመታት በኋላም አለመጀመሩ ቅሬታ ፈጠረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዲስ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ለመገንባት በተረከበው ቦታ ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ ሳይጀምር ስድስት ዓመታት መቆጠራቸው በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ቅሬታን ፈጠረ።

ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቱ ለዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ ግንባታ የሚሆን 3,000 ካሬ ሜትር ቦታ በአነስተኛ የሊዝ ዋጋ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተረከበ ሲሆን፣ መሬቱን በተረከበበት ወቅት ግንባታውን በአንድ ዓመታት ውስጥ እንደሚጀምር አስታውቆ ነበር።

ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ እስካሁን ግንባታውን እንዳልጀመረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ለዋና መሥሪያ ቤቱ የሚሆን ሕንፃ ለመገንባት መገናኛ አካባቢ ከሚገኘው የቦሌ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት አጠገብ የሚገኘውን መሬት የተረከበው በወቅቱ በአካባቢው ከነበረው የሊዝ ዋጋ ባነሰ ክፍያ መሆኑን ሪፖርተር ያገኝው መረጃ ያመለክታል። ምክር ቤቱ፣ በካሬ ሜትር 4,140 ብር የሊዝ ዋጋ ቦታውን እንደተረከበ መረጃው ይጠቁማል። ለቦታው የተከፈለው ጠቅላላ የሊዝ ዋጋ 12.4 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የሊዝ ክፍያ ውስጥ 20 በመቶውን ቅድሚያ ክፍያ ፈጽሞ ቀሪውን ክፍያ በ30 ዓመታት ለማጠናቀቅ ውለታ ገብቶ ቦታውን እንደተረከበም መረጃው ያመለክታል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ዕቅድ አውጥቶ ሲንቀሳቀስ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ግንባታውን እስካሁን አለመጀመሩ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ያነጋገርናቸው አንዳንድ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ ግንባታውን ለመጀመር የሚያስችል ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሲደረግ አለማየታቸውን የሚገልጹት ያነጋገርናቸው የምክር ቤቱ አበላት፣ በልዩ ሁኔታ በአነስተኛ የሊዝ ዋጋ የተገኘውን መሬት የከተማ አስተዳደሩ መልሶ እንዳይወስደው ሥጋት አድሮባቸዋል፡፡ በተለይ ሕንፃው በሚገነባበት አካባቢ በተመሳሳይ መንገድ በሊዝ መሬት የተሰጣቸው ድርጅቶች ግንባታውን በገቡት ውል መሠረት ባለመፈጸማቸው የከተማ አስተዳደሩ የሰጣቸውን ቦታ እንደነጠቃቸው ያስታወሱት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ ንግድ ምክር ቤቱም ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይደርሰው ግንባታውን በፍጥነት ማስጀመር እንዳለበት ይመክራሉ።

ምክር ቤቱ የመገንቢያ ቦታውን ከማግኘቱ አስቀድሞ የሕንፃውን ዲዛይን አሠርቶ የነበረ ቢሆንም፣ ቦታውን ካገኘ በኋላ ዲዛይኑን በተወሰነ ደረጃ እንዲሻሻል ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በአካባቢው የሚፈቀደው የሕንፃ ቁመት ከ10 በላይ ወለሎችን የያዘ መሆን አለበት በመባሉ ቦታውን ከተረከበ በኋላ የሕንፃ ዲዛይኑን በማሻሻል ከመሬት በታች ያለውን ሳይጨምር 11 ወለል ያለው ሕንፃ ሕንፃ ዲዛይን አሠርቶ ነበር።

በዚህ ዲዛይን መሠረት ምክር ቤቱ ለዋና መሥሪያ ቤቱ ጽሕፈት ቤት መገልገያ ከሚያስፈልገው የሕንፃ ክፍል ውጪ የተቀሩት አብዛኛው የሕንፃው ክፍል ለተለያዩ የንግድ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ታሳቢ ተደርጓል። ይህ የሕንፃ ዲዛይን ማሻሻያም ለንግድ ምክር ቤቱ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ጭምር ታስቦ የተሠራ ነበር፡፡ 

በወቅቱ የሕንፃውን አጠቃላይ ይዘት በተመለከተ ምክር ቤቱ በሰጠው መረጃ መሠረት፣ ሕንፃው ሲጠናቀቅ አነስተኛ የኤግዚቢሽን ማሳያ አዳራሽን ጨምሮ የተለያየ መጠን ያላቸው የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ እንዲሁም ለባንክ፣ ለኢንሹራንስና ለሌሎች የንግድ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች ይኖሩታል ተብሎ ነበር።

ንግድ ምክር ቤቱ ቀድሞ ባቀደው ዕቅድ መሠረት ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስፈልውን ወጪ ለማግኘት አቅዶ የነበረው የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች በማዘጋጀት ከዚህ የሚገኘውን ገቢ በቀጥታ ለግንባታ ሥራው ለማዋል ነበር፡፡ ሌሎች የገቢ ምንጮችንም ታሳቢ በማድረግ ይገነባል የተባለው ይህ ፕሮጀክት በዕቅዱ መሠረት ሊሄድ ባለመቻሉ የሕንፃውን መሠረት እንኳን ለማውጣት ሳይችል ቀርቷል፡፡ 

ከዚህም ሌላ ለሕንፃው የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ አለመደረጉን፣ ለዚህ ግንባታ የሚሆን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አለመቋቋሙንና በአጠቃላይ ግንባታውን ለማስጀመር ከፍተኛ የአመራር ክፍተት መስተዋሉ ለሕንፃ ግንባታው መዘግየት ምክንያት እንደሆነ ያነጋገርናቸው የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ የሕንፃው ግንባታ እስካሁን ሊጀመር ያልቻለበት መሠረታዊ ምክንያት የፋይናንስ እጥረት እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ሆነው በቅርቡ የሰየሙት አቶ ሺበሺ ቤተ ማርያም እንደገለጹትም፣ ለሕንፃ ግንባታው አለመጀመር አንዱና ትልቁ ምክንያት የፋይናንስ እጥረት ነው፡፡ ሆኖም ሕንፃውን ለመገንባት ቀድሞ ታስቦ የነበረውን ዕቅድ በመከለስ በአዲስ መልክ ፋይናንስ የሚገኝበት ሁኔታ በማመቻቸት ወደ ሥራ ለመግባት መታቀዱን ጠቁመዋል።

አዲሱን ዕቅድ ከመስከረም 2015 ዓ.ም. በኋላ እንደሚተገበር የገለጹት ዋና ጸሐፊው፣ የግንባታው መዘግይት ከፋይናንስ እጥረቱ በተጨማሪ ለሕንፃ ግንባታው መዘግየት ሌሎች ምክንያቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል። የሕንፃ ግንባታው አለመጀመርን አስመልክቶ ቅሬታቸውን የገለጹት የምክር ቤት አባላት በአዲስ ዕቅድ ግንባታውን ይጀመር ቢባል እንኳን አሁን ላይ ሕንፃውን ለመገንባት የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ጊዜውን መዘግየት በተመለከተ አስተያየት ሰጪ አባላቱ እንደሚጠቁሙት ተጨማሪ ወጪ ሊያስከትል ይችላል የሚለውን አቶ ሺበሺም ይህንን ሥጋት ይጋሩታል፡፡  ሕንፃውን ለመግንባት ከ10 ዓመታት በፊት ተጠንቶ የቀረበው አጠቃላይ ወጪ 240 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ዲዛይኑ እንዲሻሻል ከተደረገ በኋላ ወደ 1.3 ቢሊዮን ብር ማደጉን ገልዋል። አሁን ደግሞ ከወቅታዊ የኮንትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ መወደድ አንፃር፣ የሕንፃ ግንባታው ከ1.7 እስከ 2 ቢሊዮን ብር ሊጠይቅ እንደሚችል መገመቱን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ግንባታውን ለማስጀመርና ለማጠናቀቅ አዲስ ስትራቴጂ የሚነድፍ ስለመሆኑ የሚያመለክቱት ዋና ጸሐፊው ሕንፃውን በተሻለ መንገድ ለመገንባትም ድጋሚ የዲዛይን ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በቅርቡ 80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ያከበረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የንግድ ምክር ቤቶች በተሻለ ጥንካሬ ላይ የሚገኝ በርካታ አባላትን በመያዝም ይታወቃል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የዘገየውን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ በመጪው መስከረም ለማካሄድ ማቀዱ ተሰምቷል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሳያካሂድ ከሦስት ዓመታት በላይ መቆየቱ ሕወገጥ ነው ተብሎ ሲተች መቆየቱ ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች