Tuesday, October 3, 2023

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ግምገማ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከተቋቋመ ስድስት ወራት ያስቆጠረው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በእነዚህ ወራት አዘጋጀሁት ያለውን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ቅዳሜ ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ለተለያዩ አካላት ይፋ አድርጓል፡፡ ለሚዲያ፣ ለፖለቲካ ሰዎች፣ ለሲቪክ ማኅበራትና በአገራዊ ምክክር ውስጥ ጉልህ ድርሻ አላቸው ለሚባሉ የማኅበረሰብ ተወካዮች የቀረበው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ነበር፡፡

ባለፉት አምስት ወራት የውይይት ጽንሰ ሐሳብን የበለጠ ለመረዳት በሚያስችሉ፣ በአደረጃጀትና በስትራቴጂካዊ ሰነድ ዝግጅት ሥራዎች ኮሚሽኑ ማሳለፉን የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ ለሥራው የሚረዳውን ወሳኝ የስትራቴጂካዊ ዕቅድ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

‹‹ኮሚሽናችን ሦስት ወሳኝ ሥራዎች አሉት፡፡ አጀንዳ ቀረፃ፣ ውይይትና ከውይይት የሚገኙ ምክረ ሐሳቦች እንዲተገበሩ ክትትል ማድረግ ነው፤›› በማለት የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ለዚህ መሳካት ወሳኝ የሆነ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡ ዕቅዱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቀርቦ ግብዓት መወሰዱን ገልጸው፣ ለሚዲያዎች፣ ለፖለቲከኞችና ለሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች መድረኩ መመቻቸቱን በማመልከት ነበር ውይይቱን ያስጀመሩት፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ በዚህ መድረክ የታደሙ ከተለያዩ ዘርፎች የመጡ አካላት ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ጎድሎታል ያሉትን ግብዓት ሲሰጡ ውለዋል፡፡ የስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ምንነትና አስፈላጊነት፣ መልካም አጋጣሚና ሥጋቶች (ውጫዊና ውስጣዊ ተፅዕኖዎች)፣ አስቻይና ፈታኝ ሁኔታዎች፣ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ፍላጎት ተብሎ በአራት ዋና ዋና ንዑስ ክፍሎች የቀረበው የስትራቴጂካዊ ጭማቂ ዕቅድ በዕለቱ ከፍተኛ ውይይትና ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ነበር፡፡የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ግምገማ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ለውይይቱ በሚያመችና በማይመጥን አዳራሽ ዝግጅቱ መሰናዳቱ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ በሌላም በኩል የስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ሰነድ አስቀድሞ ለተወያዮች አለመላኩ ብቻ ሳይሆን፣ በባለሙያዎቹ በስላይድ ገጾች ከቀረበው ውጪ ሰነድ ለተወያዮቹ አለመቅረቡ ሌላው ቅሬታ ያስነሳ ነበር፡፡

በውይይቱ መካከል ደግሞ ለውይይት ታዳሚያን ኮሚሽኑ መርጦ አድሏዊ የተሳትፎ ግብዣ አድርጓል የሚል ጥያቄ መቅረቡም ሌላው የተወያዮችን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነበር፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ ስትራቴጂካዊ ዕቅድን በተመለከተ የሁኔታ ትንተና፣ እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን በተመለከተ ጥልቅ ትንተና በመሥራት መቅረቡ በብዙዎች ዘንድ በበጎ ተወስቷል፡፡ ይሁን እንጂ ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ይጎድለዋል ተብለው የተሰጡ ሐሳቦችም ነበሩ፡፡

ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ በአገራዊ ምክክር ዝግጅት፣ ሒደትና ትግበራ ምዕራፍ ወቅት የኮሚሽኑና የቁልፍ ባለድርሻ አካላትን ሚና በግልጽ አላመለከተም ከሚል ሐሳብ ጀምሮ ቢካተቱ የተባሉ በርካታ ነጥቦች በውይይቱ ወቅት ተነስተዋል፡፡

የተነሱ ነጥቦች

ስትራቴጂካዊ ዕቅዱን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በማንሳት ቀዳሚ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራሮች ነበሩ፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ራሔል ባፌ (ዶ/ር)፣ ‹‹መንግሥት ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት ሊያሟላቸው የሚገቡ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በግልጽ በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ አልሠፈሩም፤›› በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከመንግሥት ምን እንደሚጠበቅ በግልጽ ማስቀመጡ ተገቢ እንደሆነም አሳስበዋል፡፡

ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ መብራቱ ዓለሙ በበኩላቸው፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ውስጥ በቁልፍ ባለድርሻ አካልነት ሊካተት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር አያይዘው፣ ‹‹የቁልፍ ባለድርሻ አካላት ሚና በዝርዝር አልተቀመጠም፤›› የሚል አስተያየት የሰጡት አቶ መብራቱ፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር ፖለቲካ ፓርቲዎች የጀመሩት ምክክር እንደነበር በማስታወስ፣ ይህ ጅምር ሒደት በምክክር ኮሚሽኑ እንዲታቀፍ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ከምርጫ ቦርድ ጋር ያስቀመጥናቸው የመግባቢያ ነጥቦች እንዳይታለፉ፤›› በማለት ነው አስተያየታቸውን ያጠቃለሉት፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽንን በመወከል የተሳተፉት አቶ ጌቱ ሙላቱ በበኩላቸው፣ ‹‹አካል ጉዳተኞች አካታችና አሳታፊ ብሔራዊ ምክክር እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አካል ጉዳተኞች የሚወከሉት ዘርፈ ብዙ በሆነ መንገድ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ጌቱ፣ ‹‹እኔ የዓይን አካል ጉዳተኞች የሚወከሉበትን ማኅበር ነው የወከልኩት፤›› ሲሉ፣ አካል ጉዳተኞች በጉዳትም በአደረጃጀትም የተለየዩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ አቶ ጌቱ በአስተያየታቸው ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ሁሉንም አካል ጉዳተኞች የመሳተፍ ዕድል እንዳይነፍግ ነው ሐሳብ ያቀረቡት፡፡

የሚዲያ ባለሙያዎች ማኅበርን በመወከል የተገኙት አቶ ጥበቡ በለጠ፣ ሚዲያው በምክክር ሒደቱ ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡ በየክልሉና በተለያዩ አካባቢዎች አንድ ክልል ከሌላው ማኅበረሰብ ተመካከሩ ወይም የጋራ ኮሚቴ ፈጠሩ የሚሉ የውይይት ጅማሮዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ጥበቡ፣ እነዚህ የውይይት ሒደቶች በአገራዊ ምክክሩ ቢታቀፉ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ ታዬ መስፍን በበኩላቸው፣ ‹‹ከኮሚሽኑ ኮርፖሬት ፕላን ባለፈ አጠቃላይ የአገራዊ ምክክሩን ሒደት የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ መቼ ነው የሚቀርብልን፤›› በማለት ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡

አቶ ታዬ ከዚህ ባለፈም፣ ‹‹በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ውስጥ ዳያስፖራው ተዘሏል፤›› ሲሉ ያልተካተተ ባለድርሻ አካል ያሉትን ጠቁመዋል፡፡ ዳያስፖራው ትልቅ የፖሊሲ ተፅዕኖ ፈጣሪ ክፍል ሆኖ ሳለ አለመካተቱ ችግር ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ፖለቲከኛው አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በበኩላቸው፣ የምክክሩ ተሳታፊ ቁጥር እንዴት እንደሚወሰንና የኮሚሽኑ የኃላፊነት ወሰን እንዴት እንደሚሆን ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ‹‹ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ያስፈለገው በመደበኛ ተቋማት የማይፈቱ ችግሮች ስላሉብን ነው፤›› ሲሉ የጠቀሱት አቶ ኤፍሬም፣ ምክክሩ በማን ተፅዕኖ ሥር ይወድቃል የሚለው ሥጋትም ምላሽ እንደሚጠብቅ አሳስበዋል፡፡ ኮሚሽኑ እነዚህን ሁሉ ሥጋቶች ለብቻው ማርገብ ይችላል የሚለው ግምትም አሥጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከአገር ሽማግሌዎች ጉባዔ መጣሁ ያሉት አቶ ተስፋጽዮን ደለለው በአሁኑ ወቅት ብዝኃነት ለኢትዮጵያ መርገምት እየሆነ መምጣቱን በመጠቆም፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ይህንን ችግር ለመፍታት ከባድ ሸክም መሸከሙን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህንን ለመሸከም ኮሚሽኑ ጊዜና ጉልበቱ አለው ወይ?›› ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ከወጣቶች ፌዴሬሽን በኩል በአገራዊ ምክክሩ የወጣቶች ጉዳይ በሌሎች ሳይሆን በራሳቸው በወጣቶች እንዲወከል የሚጠይቅ አስተያየት ነበር የቀረበው፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው፣ ‹‹ጭቁኖቹ የኢትዮጵያ ሠራተኞች እየተገለሉ ነው፤›› የሚል አስተያየት አቅርበው ነበር፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ የምክክር ሒደቱን አሳንሶ ማየት አገሪቱን ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ከሌሎች ነገሮች ቅድሚያ ሰጥተው በዚህ የስትራቴጂካዊ ዕቅድ ስብሰባ የተካፈሉት፣ ምክክሩ ከእሳቸው ባለፈ ለልጆቻቸው ጭምር በጎ ተስፋ ይዞ ይመጣል ብሎ በማመን መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የመላው ኢትዮጵያውያን ተስፋ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተስፋ በዚህ የምክክር ሒደት ላይ አርፏል፤›› ያሉት ፍፁም (ዶ/ር)፣ ይህንን ተስፋ የሚያደናቅፍ ሁኔታ እንዲፈጠር ኮሚሽኑ መፍቀድ እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡ ‹‹እንደ መንግሥት የሥራ ኃላፊነቴ ብቻ ሳይሆን፣ እዚህ የመጣሁት ለራሴና ለልጆቼ ስል ሐሳብ ማበርከት አለብኝ ብዬ ነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሦስት ዓመታት የሥራ ጊዜው ባይገደብ የሚል አስተያየትም በዚሁ የውይይት መድረክ ለኮሚሽኑ ቀርቧል፡፡ የኮንሰርቲየም ፎር ሪሊፍ ዴቨሎፕመንት አሶሴሼን (CCRDA) ዳይሬክተር ንጉሡ ለገሠ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ አስቻይ ተብለው የተቀመጡ የሕግ ማዕቀፎች በተጨባጭ በተግባር መተርጎማቸው ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ሕግ ሳይሆን ማስፈጸም መቻል ነው ትልቁ ችግር፤›› ሲሉ የጠቀሱት ንጉሡ (ዶ/ር)፣ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ ለኮሚሽኑ ሰፊና አመቺ ተብለው የተቀመጡ የሕግ ማዕቀፎች በተግባር መተርጎማቸውን እንደሚጠራጠሩ ገልጸዋል፡፡

በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ውስጥ ክልሎች በባለድርሻ አካልነት አለመካተታቸው በጥያቄ ተነስቶ ነበር፡፡ በሌላም በኩል ሕግ አውጪው ፓርላማና ሕግ አስፈጻሚው መንግሥት በባለድርሻ አካልነት ስማቸው ቢቀመጥም፣ ነገር ግን ሦስተኛውና ቁልፍ መዋቅር የሚባለው ሕግ ተርጓሚ ከባለድርሻ አካላት ዝርዝር ውስጥ ስሙ ተዘሏል የሚል ሐሳብም ለኮሚሽኑ ቀርቧል፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የውጭ አገሮች ልምዶችን መፈተሽና ተሞክሮዎችን ቀምሮ ማቅረቡ በበጎነት ተወስቷል፡፡ ይሁን እንጂ በውጭ አገር በተመሳሳይ ዘርፍ የሠሩና ተጨባጭ የተግባር ልምድ ያላቸው ሰዎች ተፈልገው ቢሳተፉበት የሚል ሐሳብም ቀርቦ  ነበር፡፡

የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በተለይ በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ተቋማት፣ በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ በባለድርሻ አካልነት መወከል እንዳለባቸው ለኮሚሽኑ ሐሳብ ቀርቦም ነበር፡፡ ኮሚሽኑ በአገራዊ ምክክር ሒደት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ዕውቅና ሰጥቶ ይመክራል ወይ የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ለተፈተጸመባቸውና ተበዳዮች ካሳ የሚያገኙበት ዕድል ያመቻቻል ወይ የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከቤትና ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ከ5.1 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች ውክልና፣ እንዲሁም ተሰሚነት ባለው መንገድ በአገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ የሚጠይቅ ሐሳብም በዚህ መድረክ ተስተጋብቷል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት (የልማት አጋሮች) እንደ አንድ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ቢቀመጡም፣ ነገር ግን ደግሞ ጣልቃ እንዳይገቡና አስፈላጊ ጫና እንዳያሳድሩ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ለኮሚሽኑ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ይህንን ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ሒደት ኮሚሽኑ ምን ያህል አሳታፊና አካታች መንገዶችን ተከትተሏል ከሚለው ጀምሮ፣ የስትራቴጂካዊ ዕቅዱን ዝርዝር ጉዳይ በግልጽና በሰነድ ለውይይት ለምን አታቀርቡም የሚሉ ጥያቄዎችም ከተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፣ ከኮሚሽኑ ጎን የወከሉት ተቋም የሚኖረውን ሚና አጉልተው ለማሳየት ሞክረዋል፡፡፡

‹‹የምክክር ኮሚሽኑ ብቻውን ለብሔራዊ መግባባትም ሆነ ለአገር መንግሥት ምሥረታ በቂ አስተጽኦ ያበረክታል የሚል እምነት የለም፡፡ የምክክር ኮሚሽኑ የዓምዶቹን መሠረት ካስቀመጠ ሌሎች ኮንክሪቱን እየሞሉ ይሄዳሉ፡፡ ኮሚሽኑ ሞልዱን ከሠራ የእኛ የሰላም ሚኒስቴር በዚያ ላይ አርማታውን እየሞላ ይሄዳል፤›› በማለት ነበር አቶ ታዬ ሐሳብ የሰጡት፡፡ ይሁን እንጂ መጠላለፍና ሴረኝነት የሞላበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኮሚሽኑን እንዳያደናቅፈው አሳስበዋል፡፡

‹‹ያላግባብ ከጠፋችው ዶሮዬ ይልቅ በአግባቡ የጠፋው በሬዬ አያሳዝነኝም፤›› ሲሉ በምሳሌ የተናገሩት አቶ ታዬ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹ እሴቶች እንዲታቀፉ ጠይቀዋል፡፡ ለእውነት መቆም፣ ቅድሚያ ለአገር መስጠት፣ መከባበርና ሌሎች እሴቶች ትኩረት ካሉ በኋላ፣ ከምክክር ውጪ ትልቅ አጀንዳ አገሪቱ እንደሌላት ጠቁመዋል፡፡

እነዚህና ሌሎችም እጅግ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሲሰበስቡ ያረፈዱት የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮችና የስትራቴጂካዊ ዕቅዱ አዘጋጅ ባለሙያዎች፣ ውይይቱን ገንቢ ሆኖ እንዳገኙት በማጠቃለያቸው ገልጸዋል፡፡

የግብዓት መሰብሰብ ሒደቱ ከተገባደደና ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ከተሻሻለ በኋላ በዝርዝር ለውይይት እንደሚቀርብ የተናገሩት ሦስቱ የዕቅዱ ዝግጅት ኤክስፐርቶች፣ ያልታዩና ያልተካተቱ ጉዳዮች እንደሚገቡ በማጠቃለያቸው ቃል ገብተዋል፡፡

ትግራይና ወለጋን ጨምሮ በግጭት ውስጥ ያሉ ቀጣናዎች ሁኔታ በስትራቴጂካዊ ዕቅድ ዝግጅቱ በትኩረት መታየታቸውንም የኮሚሽኑ ዕቅድ አቅራቢዎች ተናግረዋል፡፡ ግጭትና ጦርነት በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ፈተና ተብለው መቀመጣቸውንና ብዙ ጥያቄዎች ግን በአሠራር ሒደት በሰነዶች እንደሚመለሱ ቃል ገብተው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -