Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዛይ ራይድና ወዝ ከመንግሥት ፈቃድ ባያገኙም የኮድ-2 መኪናዎችን እየመዘገቡ መሆናቸውን አስታወቁ

ዛይ ራይድና ወዝ ከመንግሥት ፈቃድ ባያገኙም የኮድ-2 መኪናዎችን እየመዘገቡ መሆናቸውን አስታወቁ

ቀን:

ዛይ ራይድና ወዝ የተሰኙት የኤሌክትሮኒክ ታክሲ ስምሪት (ኢታስ) ድርጅቶች፣ ኮድ-2 የመኪና ሰሌዳ ያላቸውን የግል መኪናዎች ወደ ‹‹ራይድ›› ሥራ ለማስገባት ከሐምሌ ወር መጀመሪያ አንስቶ በምዝገባ ላይ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡ ይሁንና በመንግሥት በኩል እስካሁን ድረስ ኮድ-2 የመኪና ሰሌዳ ያላቸው ተሽከርካሪዎች የኤሌክትሮኒክ ታክሲ ሥራ ላይ እንዲሠሩ የሚያስችል አሠራር አልተዘረጋም፡፡

አሁን ባለው አሠራር የኤክትሮኒክ ታክሲ ሥራን ለመሥራት የተፈቀደላቸው ኮድ-3 ሰሌዳ ኖሯቸው የንግድ ፈቃድ ያወጡና ኮድ-1 ሆነው የታክሲ ቀለም የተቀቡ መኪናዎች ናቸው፡፡

ሁለቱ ድርጅቶች ኮድ-2 መኪናዎች ይኼንን ሥራ እንዲሠሩ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ያስችላል ያሏቸውን አማራጮች ለአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ታክሲ ስምሪት (ኢታስ) አገልግሎት አሰጣጥ መመርያን በማሻሻል ላይ ያለው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ፣ የኮድ-2 መኪናዎች ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኘው መመርያው ሲወጣ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ብዙ መኪናዎች እየተሳተፉበት ያሉት የኤሌክትሮኒክ ታክሲ አገልግሎት፣ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪና በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ምክንያት አደጋ እየተጋረጠበት መሆኑን ዛይራይድና ወዝ ዓርብ ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ድርጅቶቹ መግለጫውን የሰጡት በጋራ ሆነው እየመሠረቱት ያሉትን ‹‹የኢትዮጵያ ራይድ ሄሊንግ ኅብረት››ን ወክለው ነው፡፡

‹‹ነዳጅ ሲጨምር፣ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትም ሲያጋጥም የነዋሪው ገቢ ግን እየጨመረ አይደለም›› ያሉት የዛይራይድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ታደሰ፣ በዚህም ምክንያት ባለፉት ወራት የኤክትሮኒክ ታክሲ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ የነዳጅ ጭማሪን ተከትሎ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ የመነሻ ዋጋ ላይ እስከ 30 ብር ጭማሪ ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡

ሁለቱ ድርጅቶች ይኼንን ችግር ለመቅረፍ አማራጭ አድርገው ያቀረቡት፣ በከተማ ውስጥ የሚገኙ ኮድ-2 መኪናዎችን በብዛት በማሳተፍ በቅናሽ ዋጋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግን ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኮድ-2 መኪናዎች እንደሚገኙ በኅብረቱ መግለጫ ላይ ለጋዜጠኞች ያስረዱት ድርጅቶቹ፣ ከእነዚህ መኪኖች ግማሽ ያህሉ እንኳን በመንገዳቸው ተሳፋሪዎችን በመጫን ከፍተኛ የሰው ቁጥር ማዘዋወር እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

‹‹መንግሥትም ከኤሌክትሮኒክ ታክሲዎች የሚሰበስበውን ግብር በዓመት ከሦስት ቢሊዮን ወደ ስድስት ቢሊዮን ማሳደግ ይችላል›› ሲሉ መንግሥትም ተጠቃሚ ነው የሚል ሐሳባቸውን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በኮድ-2 የሚሠሩ መኪናዎች ለሚሠሩት ሥራ በዓመት መክፈል የሚጠበቅባቸውን ግብር በምን መንገድ ይከፍላሉ የሚለው አሁንም ጥያቄ ሆኗል፡፡

ኮድ-3 መኪና ይዘው የሚሠሩ ባለ መኪናዎች ሥራውን ለመጀመር ንግድ ፈቃድ የሚያወጡ ሲሆን፣ በየዓመቱ ንግድ ፈቃዳቸውን በመያዝ የተወሰነላቸውን ቁርጥ ግብር ይከፍላሉ፡፡ ኮድ-3 ሰሌዳ የሚሰጣቸው የንግድ መኪናዎች ናቸው፡፡

ኮድ-2 መኪናዎች በአንጻሩ የሚቆጠሩት እንደ መንቀሳቀሻ የግል መኪና በመሆኑ፣ በተለመደው አሠራር መሠረት ሥራውን ለመሥራት ሰሌዳቸውን ወደ ኮድ-3 ቀይረው የንግድ ፈቃድ ማውጣት አለባቸው፡፡

ሁለቱ የኤክትሮኒክስ ታክሲ ድርጅቶች የኮድ-2 ሾፌሮች የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ንግድ ፈቃድ ማውጣት ግዴታ መሆኑ አላስፈላጊ ነው የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

‹‹እኛ አገር ብቻ ነው ሾፌር ንግድ ፈቃድ የሚያወጣው›› ያሉት የወዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ናርዶስ አዲስ፣ ጎረቤት አገር ኬንያን በምሳሌነት በማንሳት ይኼ ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

የመኪና ሰሌዳ ኮድ ልዩነት ሳይሆን አሽከርካሪዎች በሚያወጡት ‹‹ቲን ነምበር›› አማካይነት ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ አግልገሎቱን የሚያሰጡት ድርጅቶችም ባለ መኪናው በዓመት ውስጥ ምን ያህል እንደሠራ ለመንግሥት በማቅረብ የግብሩ ትመና በአግባቡ እንዲሠራ በማድረግ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል አማራጭ አቅርበዋል፡፡

ዛይራይድ በበኩሉ መፍትሔ ይሆናል ያለውን ሌላ መንገድ ጠቁሟል፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ሀብታሙ ገለጻ ድርጅቶቹ ከእያንዳንዱ ጉዞ ላይ ከሚቆርጡት ኮሚሽን ባሻገር የዓመታዊ ቁርጥ ግብሩን መሸፈን የሚያስችል ተጨማሪ ገንዘብ በመቁረጥ ሰብስቦ ለመንግሥት መክፈል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ይኼም ድርጅቶቹ በረቂቅ ላይ ባለው የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) አዋጅ መሠረት፣ ከስምንት መቀመጫ በታች ያላቸው መኪናዎች ላይ የሚጣልን ቫት ሰብስበው ለመንግሥት ከሚከፍሉበት አሠራር ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን አክለዋል፡፡

ከእነዚህ አሠራሮች አንዱ ተግባራዊ ሆኖ ኮድ-2 መኪናዎች የኤሌክትሮኒክ ታክሲ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ በሚል ዕሳቤ፣ ሁለቱም ድርጅቶች ተሽርካሪዎች በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡ ገበያው ላይ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ የገለጹት ድርጅቶቹ፣ በቀናት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሸርካሪዎችን መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የቢሯቸው አቋም ምን እንደሆነ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት የሺጥላ፣ ‹‹እኛ ፈቃድ አልሰጠንም እነሱ እየመዘገቡ ነው፤›› በማለት ቢሮው አሠራሩን እንዳልዘረጋ ተናግረዋል፡፡

ይሁንና ይኼ አሠራር የመፈቀድና አለመፈቀዱ ጉዳይ የሚታወቀው እየተሻሻለ ባለው የኤሌክትሮኒክ ታክሲ ሥምሪት (ኢታስ) አገልግሎት አሰጣጥ መመርያ ላይ ይኼ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቢሮው መመርያውን ሲያወጣ የመጨረሻ ውሳኔን አብሮ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...