የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ልዩ ነፃ የንግድ ቀጣና ለማሻገር የተደረገው ዝግጅት በመጠናቀቁ፣ ነፃ የንግድ ቀጣናው አገልግሎት ሊጀምር መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከአንድ ወር በፊት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ ከሚገኘው የጥናት ቡድን ጋር የግምገማ መድረክ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ጽሕፈት ቤት አስተባባሪና የጥናት ቡድኑ መሪ አቶ እውነቱ ታየ እንዳስታወቁት፣ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያልተያዙ 90 በመቶ ለመጋዘንነትና ለኤክስፖርት ማቀነባበሪያነት የሚያገለግሉ ሼዶች ዝግጁ ሆነዋል፡፡ በቀጣናው ውስጥ የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወኑን የመሠረተ ልማትና ተያያዥ አገልግሎቶች እየተሟሉ መሆናቸውን መገለጹም አይዘነጋም፡፡
ድሬዳዋ የባቡርና የመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ በኢንዱስትሪ ፓርክና በደረቅ ወደብ አማካይነት ነፃ የንግድ ቀጣናውን ዕውን ለማድረግ አመቺ ሆና መገኘቷ ተገልጿል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የስትራቴጂ አማካሪ አቶ ኪያ ተካልኝ፣ የነፃ ቀጣናው የዝግጅት ሥራዎች በሚመለከታቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና አካላት በኩል ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ወራት በነፃ ቀጣናው የሚተገበሩ የሕግ ማዕቀፎችን ጨምሮ ምሥረታውን ለመጀመር የሚያስችል የመሠረተ ልማት ዝግጅት፣ በኮርፖሬሽኑ በኩል ተጠናቆ አገልግሎት መጀመር የሚቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ትኩረት የተደረገባቸው ዘርፎች አጠቃላይ ንግድ፣ ሁሉን አቀፍ የሎጂስቲክስ አገልግሎትና የአምራች ዘርፉ ማለትም የኤክስፖርት ማቀነባበሪያና ወደ ውጭ መላክ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የስትራቴጂ አማካሪው እንዳስታወቁት፣ ነፃ የንግድ ቀጣና በዋነኛነት በሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራበት ነው፡፡ የመጀመሪያው የአምራች ዘርፉን የተመለከተ ሲሆን፣ ሁለተኛው የአስመጪና ላኪ ድርጅቶችን (ጥሬ ዕቃና አላቂ ዕቃ አስመጪዎች) ሲይዝ፣ ይህም ከተለያዩ አገሮች በማስመጣት በቀጣናው ውስጥ የሚከማችበት፣ የሚቀናበርበት፣ እንዲሁም ተመልሶ ወደ ውጭ የመላክ ሥራዎች የሚከናወኑበት አገልግሎት ነው፡፡ እንዲሁም ሒደቱን ለማቀላጠፍ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚሰጥበት ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በቀጣናው የሚሰጠውን አገልግሎቶች የሚያቀላጥፉ የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ የደረቅ ጭነትና የምክር አገልግሎቶች በቅንጅት የሚሰጥበት ነው፡፡
በዓለም ላይ ከአምስት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች (ነፃ የንግድ ቀጣናዎች) መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ ኪያ፣ በተለያዩ አደጉ በተባሉት አገሮች ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና የተጫወተው የንግድ ቀጣና በኢትዮጵያ መመሥረቱ የወጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን ለማሳደግ፣ የዕውቀት ሽግግርን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡
በነፃ ቀጣናው የአገሪቱ የጉምሩክ ሥርዓትና አጠቃላይ ሕጎች ልማቱን ለማሳለጥ በሚያስችል ሁኔታ ላልተው የሚተገበሩበት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በመሆኑም በቀጣናው ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን የሚያገኙ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይህ የነፃ ንግድ ቀጣና አገልግሎት በአፍሪካ በጂቡቲና በኬንያ ውስጥ ውጤታማነቱ በተሞክሮነት የተወሰደ መሆኑን ያስረዱት የስትራቴጂ አማካሪው፣ ከዚያም አልፎ ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች ውስጥ የቱርክ አገር ተሞክሮ የተወሰደበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በቀናት ውስጥ በይፋ አገልግሎት መስጠት የሚጀምረው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና አልሚዎች ዕቃዎች የሚያራግፉበት፣ የሚስተናገዱበት፣ የሚመረቱበትና የሚገጣጠሙበት፣ እንዲሁም ወደ ውጭ እንደገና የሚላኩበት፣ ለኢንዱስትሪ ፓርክ በግብዓትነት እንዲቀርቡ የሚደረግበት እንደ ነፃ የንግድ ፓርክና የኤክስፖርት ማቀነባበሪያ ዞን ተብሎ የሚገለጽ ነው ተብሏል፡፡
በተያያዘም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ገልፍ ኢንጎት ኤፍ ዜድ ሲ የተሰኘው አምራች ኩባንያ በሳምንቱ ማጠናቀቂያ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የውል ስምምነት ከኮርፖሬሽኑ ጋር የፈጸመውና መቀመጫውን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ያደረገው ገልፍ ኢንጎት የተባለው ድርጅት ለተለያዩ የመጠጥ፣ እንዲሁም የውኃ ማሸጊያነት የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ማሸጊያዎችን ለማምረት የሚያገለግል ጥሬ ዕቃ ለማምረት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ኩባንያው በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ 11,000 ሜትር ካሬ የማምረቻ ሼድ በመከራየት 5.26 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ የሚያደርግ ሲሆን፣ ከ139 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሆነ የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ ተኪ ምርት በማምረት የውጭ ምንዛሪ መተካት፣ 80 ከመቶ በላይ የሚሆነውን ምርቱን ወደ ጎረቤት አገሮች መላክ፣ እንዲሁም የወጪ ንግድ ማሳደግና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን፣ በተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የቆየው የኢንቨስትመንት ፍሰት ወደ ነበረበት እየተመለሰ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ኮርፖሬሽናቸው አገር በቀል አምራች ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ማምረት እንዲጀምሩ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት እንዳደረገ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምርት ለመጀመር ውል የተፈራረመው ኩባንያ ተኪ ምርት በማምረትና የውጭ ምንዛሪን በማዳን በኩል ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለው፣ ኩባንያውም በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲገባ በማሳሰብ በኮርፖሬሽናቸው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ያለማማረጥ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡
የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ለመጀመር ስምምነት የፈረመው ገልፍ ኢንጎት ኤፍ ዜድ ሲ ኩባንያ ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ እዮስያስ ኤልያስ በበኩላቸው፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ለማምረት ባገኙት ዕድል ደስተኛ መሆናቸውን፣ በአፋጣኝ ወደ ሥራ ለመግባትና ምርቶቻቸውን ለአገር ውስጥ ገበያ፣ እንዲሁም ለኬንያና ለታንዛኒያ ኤክስፖርት ለማድረግ አንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡
የውል ስምምነት ከኮርፖሬሽኑ ጋር የፈጸመውና መቀመጫውን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ያደረገው “Gulf Ingot FZC” የተባለ ድርጅት ለተለያዩ የመጠጥ፣ እንዲሁም የውኃ ማሸጊያነት የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ማሸጊያዎችን ለማምረት የሚያገለግሉ (PET performs) የተባለ ጥሬ ዕቃ ለማምረት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ኩባንያው በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ 11,000 ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ በመከራየት 5.26 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ የሚያደርግ መሆኑን፣ ከ139 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሆነ የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ ተኪ ምርት በማምረት የውጪ ምንዛሪ እንደሚተካ፣ 80 በመቶ በላይ የሚሆነውን ምርቱን ወደ ጎረቤት አገሮች እንደሚላክ፣ እንዲሁም የወጪ ንግድ እንደሚያሳድግና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡