Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሶማሊያና የኬንያ የጫት ንግድ ስምምነት በኢትዮጵያ ጫት ላኪዎች ላይ ሥጋት ፈጠረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ምንም ዓይነት የቀረበ ቅሬታ የለም››

ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

ከሁለት ዓመታት ዕገዳ በኋላ የሶማሊያና የኬንያ የጫት ንግድ ስምምነት እንደገና በመደረጉ፣ በኢትዮጵያውያን ጫት ላኪዎች ላይ ሥጋት ፈጠረ፡፡ ባለፈው ሳምንት ኬንያ ወደ ሶማሊያ ከፍተኛ መጠን ያለው ጫት ልካለች፡፡

ኬንያ ወደ ሶማሊያ የሚላከውን ጫት ከሁለት ዓመት ዕገዳ በኋላ ማንሳቷ ይታወሳል፡፡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከወራት በፊት ከሶማሊያ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ጋር በተገናኙበት ወቅት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ታግዶ የቆየውን የጫት ንግድ በድጋሚ ማስጀመራቸው አይዘነጋም፡፡

ዕገዳው ከተነሳ በኋላ ባለፈው ሳምንት ኬንያ ከፍተኛ የሆነ የጫት የወጪ ንግድ ያስመዘገበች ሲሆን፣ 81.4 ቶን ጫት ወደ ሶማሊያ በመላክ 2.2 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘቷ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ጫት ላኪዎች በቀን ከ20 ሺሕ ኪሎ እስከ 40 ሺሕ ኪሎ ወደ ሶማሊያ ይልኩ የነበረ ሲሆን፣ አሁን አብዛኞቹ ላኪዎች ከሶማሊያ ትዕዛዝ ማግኘት ባለመቻላቸው የሚልኩት የጫት መጠን በግማሽ እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ጫት ላኪዎች፣ የጫት ወጪ ንግድ በመቀነሱና የኬንያ የጫት ንግድ በመጨመሩ በቀጣይ የሚልኩት የጫት ምርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዞ እንዳይቋረጥ ሥጋት እንዳላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ፋሚ አብዱልመጂድ ቅሬታውን ለሪፖርተር ካቀረቡት የጫት ላኪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በግል የጫት የወጪ ንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማራው አቶ ፋሚ፣ ባለፉት ሳምንታት ከሶማሊያ ይቀበል የነበረው ትዕዛዝ በእጥፍ ቀንሷል፡፡ በዚህም በቀን እስከ 20 ሺሕ ኪሎ ጫት ይልክ የነበረው የአቶ ፋሚ ድርጅት፣ አሁን ከስድስት ሺሕ እስከ አሥር ሺሕ ብቻ እንደሚልክ ይናገራል፡፡

‹‹እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የጫት ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ወደ ውጭ የሚላከው መጠን መጨመር እንጂ መቀነስ አይገባውም ነበር፤›› ሲል አቶ ፋሚ ሁኔታውን አስረድቷል፡፡

በተጨማሪም የጫት ምርት ከተሰበሰበ በኋላ በወቅቱ ጥቅም ላይ ማዋል ካልተቻለ እንደሚበላሽ፣ ምርቱ በባህሪው ለክምችት የሚሆን ባለመሆኑ የውጭ ትዕዛዝ ተገኝቶ መላክ እንዳለበት ገልጿል፡፡

እንደ አቶ ፋሚ ገለጻ ከሆነ፣ አሁን ዝቅተኛ የሆነ የጫት ምርት እየተላከ በመሆኑ፣ ቀስ በቀስ ሙሉ ለሙሉ እንዳይቆም ሥጋት አለው፡፡

ሌላው በጫት የወጪ ንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማራው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ግለሰብ በተመሳሳይ ሥጋቱን ገልጿል፡፡

የኬንያና የሶማሊያ የንግድ ስምምነት በኢትዮጵያ የጫት ላኪዎች ላይ ሥጋት ፈጥሯል የሚለውን ሐሳብ፣ የንግድና የቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አልተቀበለውም፡፡

 የጫት ላኪዎች ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው ብቻ ሳይሆን፣ ችግር ከገጠማቸው ቅሬታቸውን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምንም ዓይነት የቀረበ ቅሬታ አለመኖሩን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ተናግረዋል፡፡

‹‹ላኪዎች የጎረቤት አገር የወጪ ንግድ ተጠናክሯል ብለው ከመሥጋት፣ የሚላከውን ምርት ጥራቱን በመጨመር ከዓለም አቀፍ ንግድ ጋር መወዳደር ይገባቸዋል፤›› ሲሉ አቶ ካሳሁን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ዘርፍ የጫት ንግድ ነው፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከጫት የወጪ ንግድ ያገኘቸው 392 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር 2.5 በመቶ ቀንሷል፡፡ ዓምና የተገኘው 402 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የጫት ምርት የሚገኝበት አካባቢ ኦሮሚያ ክልል ሲሆን፣ በዓመት 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ይመረታል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሕገወጥ ተግባራት እየተስፋፉ በመምጣታቸው፣ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እያጣች መሆኑን፣ ለዚህም የተጠናከረ ሥራ መሥራት እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ዘመናዊ፣ የተቀናጀና ተወዳዳሪ የወጪ ንግድ ሥርዓት በመፍጠር የአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ አቅዷል። ጫት ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡት ምርቶች መካከል አንዱ ነው። ሆኖም የአፈጻጸም ሪፖርቱ እንደሚያሳየው የጫት ኤክስፖርት አፈጻጸም የሚጠበቀውን ያህል አልነበረም።

ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ይልቅ ኬንያን የመረጠችው በኪሎ የሚሸጥበት ዋጋ የኬንያ ቅናሽ በመሆኑ ሊሆን እንደሚችል የጫት ላኪዎች ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከስድስት ወራት በፊት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባሻሻለው የመሸጫ ዋጋ መሠረት አንድ ኪሎ ጫት እስከ 10 ዶላር ድረስ ይሸጣል፡፡ የኬንያ የጫት ንግድ ደግሞ በኪሎ ከስድስት እስከ ስምንት ዶላር ድረስ ያወጣል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች