ኮስሞ ትሬዲንግን ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ በተጣለው ዕግድ ላይ ክርክር ይደረጋል
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ከአዋሽ ባንክ በተበደሩት 61 ሚሊዮን ብር ላይ እምነት በማጉደል፣ የባንክ ሥራ ተክተው በመሥራትና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀሎች ተጠርጥረውና ተከሰው በነበሩ ግለሰቦች ላይ ያቀረበውን ክስ አሻሽሎ አቀረበ፡፡
ዓቃቤ ሕግ ይህንኑ ክስ ቀደም ብሎ መሥርቶት የነበረ ሲሆን፣ ከተጠቀሱት የወንጀል ድርጊቶች በተጨማሪ አራጣ የማበደር ወንጀልን አካቶ የነበረ ቢሆንም፣ ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጉምሩክ ወንጀል ችሎት፣ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ጠይቆ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. አሻሽሎ አቅርቧል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ተከሳሾች ወ/ሮ አዜብ ምሕረትአብ፣ አቶ ተመስገን ይልማ፣ አቶ አደፍርስ ሀብቴ፣ ጄጄ ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ቲቲኤች ትሬዲንግ ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ቦስተን ሪል ስቴትና አቶ መስፍን አስማማው ይባላሉ፡፡
ግለሰቦቹና ድርጅቶቹ የተከሰሱት፣ ኮስሞ ትሬዲንግ ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን ወ/ሮ አዜብና አቶ ተስገንን በምክትል ሥራ አስኪያጅነት እንደሚያስተዳድሩ ባለ አክሲዮኖች በቃለ ጉባዔ መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ሾመዋቸዋል፡፡ ግለሰቦቹ የተሰጣቸውን ሹመት በመጠቀም ከአዋሽ ባንክ አራዳ ቅርንጫፍ 61 ሚሊዮን ብር የረዥም ጊዜ ብድር መውሰዳቸውን በተሻሻለው ክስ ተጠቅሷል፡፡
ከተበደሩት ገንዘብ 21 ሚሊዮን ብር ኮስሞ ትሬዲንግ ከኅብረት ባንክ ለወሰደው ብድር መክፈላቸውንም አክሏል፡፡ 40 ሚሊዮን ብር ደግሞ ወደ ድርጅቱ የሒሳብ ቋት ካስገቡ በኋላ፣ አሥር ሚሊዮን ብር በኦቨር ድራፍት ለዋና ሥራ አስኪያጅ ለአጭር ጊዜ ብድር እንዲፈቀድላቸው ባንኩን በመጠየቅ፣ ወ/ሮ አዜብ ምሕረትአብና አቶ ተመስገን ይልማ በጋራ ለሚያስተዳድሩት ጄጄ ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት 32,500,000 ማስተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ከዚሁ ገንዘብ ላይ ወ/ሮ አዜብ በግል ላቋቋሙትና ምንም ዓይነት የሥራ ግንኙነት ለሌለው በሥራ አስኪያጅነት ለሚመሩት ቦስተን ሪል ስቴት 11,014,000 ብር እንዲሁም አቶ ተመስገን በግል ላቋቋሙት፣ ቲቲኤች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 5000 ብር ለባንክ ብድር ክፍያ ማዋላቸውንም አብራርቷል፡፡
ኮስሞ ትሬዲንግ ለዋንሃው ሆቴል ያከራየውን ሕንፃ 14,400,000 ብር ገቢና ከአንድ ግሬደር ሽያጭ የተገኘን 1,410,000 ብር ገቢ አቶ ተመስግን ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ኮስሞ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን እንዲያስተዳድሩና እንዲመሩ የተሰጣቸውን እምነት ማጉደላቸውንም በክሱ ገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ የተጠቀሰውን ወንጀል ድርጊት የፈጸሙት፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ፣ ለ) እና አንቀጽ 676 (ሀ) ድንጋጌን በመተላለፍ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡
ወ/ሮ አዜብ፣ አቶ ተመስገን፣ አቶ አደፍርስና ቲቲኤች ትሬዲንግ፣ ምንም ዓይነት የባንክ ሥራና ገንዘብ የማስተላለፍ የሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው የባንክ ሥራን በመተካት፣ ወ/ሮ አዜብ በአሜሪካና በአውሮፓ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች፣ በኢትዮጵያ ባንኮች በሕጋዊ መንገድ መላክ የነበረባቸውን የውጭ ምንዛሪ በግል በመሰብሰብና በኢትዮጵያ ገንዘብ (ብር) በመመንዘር፣ ኢትዮጵያ ላሉ ግለሰቦች ማስተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ገንዘቡን የሚያስተላልፉት ለዚሁ ሥራ በተመሠረተው ቦስተን ሪል ስቴት የሒሳብ ቋት መሆኑን፣ ለተለያዩ ግለሰቦች መላኩንና ሁሉም ተከሳሾች ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው በባንክ ሥራ ላይ ተሰማርተው ወንጀል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር አብራርቷል፡፡ ተከሳሾቹ ንብረቱ ወይም ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ ሕጋዊ በማስመሰል ሲያቀርቡ እንደነበርም ዓቃቤ ሕግ ባሻሻለው ክሱ አብራርቷል፡፡ ክሱን በችሎት ለማንበብም ለጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በኮስሞ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው የዕግድ ትዕዛዝ እንዲነሳ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ኃይለየሱስ መንግሥቱ ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ነገ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ክርክር ይደረጋል፡፡