Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ከ760 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ185 ጭነት ተሽከርካሪዎችን ሊገዛ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 185 የጭነት ተሽከርካሪዎችን በ14.5 ሚሊዮን ዶላር ወይም 760.5 ሚሊዮን ብር ግዥ ሊፈጽም ነው፡፡

ድርጅቱ ለሁለተኛ ጊዜ ባወጣው ጨረታ ተሽርካሪዎቹን ለማቅረብ በጋራ የጨረታ ሰነድ ያቀረቡ ሁለት ድርጅቶችን መርጧል፡፡ የተመረጡት አቅራቢዎች አገር በቀሉ የምካብ ጄኔራል ኢምፖርት ኤክስፖርት (YEMKAB General Import Export PLC) እና የቻይናው ሲኖ ትራክ ኢንተርናሽል (SINOTRUK INTERNATIONAL CO., LTD) ናቸው፡፡

ሁለቱ ድርጅቶች ከ350 እስከ 400 ኩንታል የመጫን አቅም ያለውን አንድ መኪና 78,755 ዶላር ለማቅረብ የተስማሙ ሲሆን፣ በአራት ወራት ውስጥ 185 የጭነት መኪናዎች ለድርጅቱ እንደሚያስረክቡ የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ወንድሙ ደንቡ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ መኪናዎቹን ለመግዛት የተስማማበት ዋጋ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ወደ 760.5 ሚሊዮን ብር ያስወጣዋል፡፡ ይሁንና ድርጅቱ እስካሁን ድረስ ለግዢው የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ሙሉ ለሙሉ እንዳላገኘና በማፈላለግ ላይ መሆኑን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በ2013 በጀት ዓመት 150 የጭነት መኪናዎችን በ11 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ገዝቶ ነበር፡፡ እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ፣ አሁን ሊገዙ የታቀዱት 185 መኪኖች ለተለያዩ ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡና ወደ ውጭ የሚላኩ ብትንና ኮንቴይነሮችን በመጫን አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ ከጅቡቲ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ወደ ተለያዩ መጋዘኖች ማጓጓዝ እንዲሁም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ከመጋዘኖች ወደ ጅቡቲ ማጓጓዝም ድርጅቱ የሚገዛቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ነው፡፡

ድርጅቱ እነዚህን ተሽከርካሪዎች ለመግዛት የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ያወጣው ጥር ወር 2014 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይሁንና የጨረታ ሰነዱን ከገዙት አቅራቢዎች ውስጥ ሰነድ የመለሰው አንድ ኩባንያ ብቻ በመሆኑ ጨረታውን ለመሰረዝ ተገዷል፡፡

የጨረታ ሰነዱ ላይ ማስተካከያ ተደርጎ በድጋሚ የካቲት መጨረሻ ላይ ጨረታው ከወጣ በኋላ 32 ተጫራቾች ሰነዱን ገዝተው ስድስቱ መመለሳቸውን አቶ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡ ስድስት ተጫራቾች ሰነድ መልሰው መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የተከፈተው ጨረታ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ለቅድመ ግምገማ ያለፉ ተጫራቾች ሁለቱ ናቸው፡፡

ቴክኒካልና ፋይናንሻል ጨረታውን ያለፉት የየምካብና የሲኖትራክ ጥምረት ናቸው፡፡ ሲኖ ትራክ ኢንተርናሽናል ብዛት ያላቸው የጭነት መኪናዎቹ በኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ የዋሉለት ኩባንያ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. የተመሠረተው የምካብ ኢምፖርት ደግሞ መሠረቱን በአዲስ አበባ ከተማ ያደረገና በተለይ ከቻይናና ስፔን የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሥራ ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች