Friday, September 22, 2023

በሐረሪ ክልል ሁለት ከተሞችን ለማቋቋም ያግዛል የተባለ መዋቅራዊ ፕላን ፀደቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሐረሪ ክልል ውስጥ ብቸኛ ከሆነው ከሐረር ከተማ በሻገር፣ ሌሎች ሁለት አካባቢዎችን ወደ ከተማነት የሚያሳድግ የአሥር ዓመት የሐረር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ፀደቀ፡፡

ባለፈው ሳምንት በሐረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ የፀደቀው የሐረር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን፣ ከዚህ ቀደም የነበረው የከተማ ፕላን የአገልግሎት ጊዜው በማለቁና የከተማዋንና የክልሉን አሁናዊ ሁኔታ በዝርዝር ጥናት ላይ በመመርኮዝ እንዲያገለግል ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡  

በሐረሪ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አሚና አብዱልከሪም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም የነበረው የከተማ መዋቅራዊ ፕላን ላለፉት 16 ዓመታት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡  

የሐረሪ ክልል እስካሁን ድረስ ያላት ሐረር ከተማ ብቻ ሲሆን፣ እንደ አዲስ የተዘጋጀው መዋቅራዊ ፕላን ቢያንስ ሁለት ተጨማሪ ከተሞች እንዲኖሩ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የአሥር ዓመቱ የከተማ መዋቅራዊ ፕላን ሦስት ከተሞች በሐረሪ ክልል ውስጥ እንዲኖሩ የሚያደርግ መሆኑን ወ/ሮ አሚና አስረድተዋል፡፡

ፕላኑ ከሐረር ከተማ በተጨማሪ ሌሎች የወረዳ ከተሞችና የገጠር ወረዳ ማዕከላት እንዲፈጠሩ በማድረግ፣ ወጣቶች በሚኖሩበት አካባቢ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ከፍተኛ ዕገዛ እንደሚኖረው ይታመናል ተብሏል።

ከሌሎች ክልሎች ተሞክሮ በመነሳት ከተማ የሚለው መዋቅራዊ አደረጃጀት የተሰጠው ምንን መሠረት በማድረግ የሚለው ታይቷል የተባለ ሲሆን፣ ከተሞክሮ ለመረዳት የተቻለው ከተሞችን ለማቋቋም ታሳቢ ከሚደረጉ ጉዳዮች ውስጥ  የሕዝብ  ብዛት፣ ለማቋቋም የታሰቡት ከተሞች ከክልል ርዕሰ ከተማ ምን ያህል ርቀት ላይ ይገኛሉ የሚሉት ጉዳዮች ይገኙበታል የሚለው እንዳለበት ተገልጿል፡፡

የሕዝብ ብዛትን ከግምት ውስጥ በመክተት በአሥር ዓመቱ መዋቅራዊ ፕላን  ወደ ከተማነት ለማሳደግ ከታሰቡት ውስጥ ድሬ ጠየራና ኤረር የተባሉት አካባቢዎች ወደ ከተማነት ያድጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

በመዋቅራዊ ፕላኑ በተለይም በክልሉ የሚገኙ የአርሶ አደር መንደሮች ሳይፈርሱ በፕላኑ እንዲካተቱ በማድረግ፣ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላትና መሠረታዊ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።

አዲስ የተዘጋጀው መዋቅራዊ ፕላን የከተማና የገጠር፣ የከተማና የከተማ፣ እንዲሁም የገጠርና የገጠር አካባቢዎችን ትስስር ሊያጠናክር የሚችል መሆኑ ተመላክቷል፡፡ የሐረሪ ክልል የመንገድ ሽፋኑ ብዙ የማይባል መሆኑን ያስረዱት ወ/ሮ አሚና፣ ከመሀል ከተማም ሆነ ከምሥራቁ ክፍል ያለውን የአገሪቱ ክፍል በመንገድ ለማስተሳሰር የመዋቅራዊ ፕላኑ መዘጋጀት አንደኛው ጥቅም መሆኑን ጠቁመው፣ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ እየተለወጠ የመጣውን የሐረር አየር ንብረት ለመመለስ በአረንጓዴ ልማት ላይ የሚከናወኑ ጉዳዮችም በመዋቅራዊ ፕላኑ የሚዳሰሱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሕንፃዎችን በሚመለከትም የትና እንዴት ነው መሠራት ያለባቸው የሚለውንም ማካተቱን አክለዋል፡፡

በሐረሪ ክልል ውስን የሆነ የመሬት ሀብት ከመኖሩ አኳያ የመዋቅራዊ ፕላኑ መዘጋጀት ወሳኝነቱን የገለጹት ወ/ሮ አሚና፣ ነገር ግን አዋጁ ወጥቶ ፀደቀ ማለት ሥራው ተከናወነ ማለት ስላልሆነ በቀጣይ የሚመለከታቸው አካላት ወደ ተግባር በማውረድ ሒደት ላይ ድርሻ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ይህም የሚመለከታቸው አካላት አዋጁ የሚፈጸምበትን ደንብና መመርያ ወደ ተግባር ለማስገባት የሚደረገውን ርብርብር የሚመለከት መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -