Monday, December 4, 2023

በደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ 11 ሰዎች ተገደሉ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ አራት ሴቶችን ጨምሮ 11 ሰዎች ተገደሉ፡፡ በወረዳው የሚገኘው ጊዶሌ ሆስፒታል አራት ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸው ለሕክምና ከመጡ በኋላ ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ ሰባት ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የአካባቢው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ ንፁኃን ነዋሪዎችን መግደላቸውን ሲናገሩ፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ፣ ‹‹ዕርምጃ የወሰድኩት በታጣቂዎች ላይ ነው፤›› ብሏል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. እና በማግሥቱ ማክሰኞ ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በልዩ ወረዳው በሚገኙት አተያና ሆልቴ ቀበሌዎች ነው፡፡ የአካባቢ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ሰኞ ዕለት ከእኩለ ሌሊት በኋላ ወደ ቀበሌዎች በመግባት፣ በነዋሪዎች ቤት ላይ ፍተሻ ካደረጉ በኋላ በወሰዱት ዕርምጃ የነዋሪዎች ሕይወት አልፏል፡፡

አቶ አልታዬ በላቸው የተባሉ ነዋሪ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በዕለቱ ሌሊት ከሰባት ሰዓት በኋላ በተፈጸመው ድርጊት እናቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን  ተገድለዋል፡፡ ‹‹እርሻ ላይ ውሎ የነበረው ገበሬ ቤት ሁሉ በሌሊት በክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ተዘርፏል፤›› ሲሉም ድርጊቱን አስረድተዋል፡፡

አቶ እንግዳ ኪታንቦ የተባሉ ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በልዩ ወረዳው አተያ ቀበሌ ከተገደሉት ስምንት ሰዎች መካከል ወ/ሮ ኩንፋዴ ኩዮ የተባለች ነፍሰ ጡር ሴት መገደሏን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በነጋታው በሆልቴ ቀበሌ መልካሙ ሩቃ የተባለ አርሶ አደርን ገድለዋል፡፡ ስንቁን ይዞ ወደ እርሻ እየሄደ ነው የገደሉት፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ፍሬው ተስፋዬ የተባሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የደራሼ ሕዝብ ተወካይና የሰው ሀብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ አባል፣ በተመሳሳይ ከአሥር በላይ የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤት አባሉ በዚህ ግድያ ነፍሰ ጡር እናትና ሕፃናት ጭምር ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል፡፡

‹‹ከአጎራባች መዋቅሮች ጋር የሚፈጠሩ የብሔር ግጭቶችንና ችግሮችን በቅርበት ለመፍታት ጥረት አለመደረጉ ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው፤›› ሲሉም፣ የድርጊቱ መነሻ በአካባቢው ከሚነሳው የዞን መዋቅርነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የደራሼ ልዩ ወረዳ ማዕከል በሆነችው ጊዶሌ ከተማ በሚገኘው ጊዶሌ ሆስፒታል የሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታደመ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ሆስፒታሉ ጥቃት የደረሰባቸው ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ በአጠቃላይ አራት ሰዎችን ለሕክምና ተቀብሏል፡፡ ረዕቡ ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ደግሞ አንዲት የ26 ዓመት ሴትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕይወቷ አልፎ የመጣችውን የ26 ዓመት ሴት ነፍሰ ጡር ነበረች የመባሉን ጉዳይ በተመለከተ፣ ‹‹ባለሙያዎች ባደረጉላት ምርመራ ነፍሰ ጡር መሆኗን እርግጠኛ መሆን አልቻሉም፤›› ብለዋል፡፡

ግለሰቦቹ ሕይወታቸው ያለፈበትን አኳኋን በተመለከተም ዝርዝር መረጃዎች መስጠት እንደማይችሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር፣ ክላስተር አስተባባሪና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዲ በሳምንቱ መጀመሪያ በልዩ ወረዳው ስለተፈጸመው ድርጊት ሲናገሩ፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በሕግ ማስከበር ኦፕሬሽ ላይ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹የቀድሞ የልዩ ወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ አመራሮችን የገደሉ ግለሰቦች በሕዝቡ ውስጥ ተሸሽገዋል፤›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹እነዚህን ለመያዝ ሲሞከር በሠራዊታችን ላይ ጥቃት ለማድረስ በሞከሩ የተወሰኑ አካላት ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፤›› ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ለይተን አላጣራንም፤›› ብለው፣ በምን ያህል ሰዎች ላይ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

እንደ አቶ ዓለማየሁ ገለጻ፣ በአካባቢው የሚገኙ ታጣቂዎች በሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የልዩ ወረዳውን ዋና አስተዳዳሪ ጨምሮ 72 የፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ግድያ ፈጸመዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ጊዜ በልዩ ወረዳው የሚገኙ ሦስት ቀበሌዎች መንግሥት አልባ ሆነው መቀጠላቸውን አክለዋል፡፡

ታጣቂዎቹ የቀበሌ አመራሮች ለሥራ ሲንቀሳቀሱና ተቋማትም አገልግሎት እንዳይሰጡ ሠራተኞችን ያግታሉ ካሉ በኋላ፣ የክልሉ ፀጥታ ኃይል ይህንን ሁኔታ ለመቀየርና ወንጀለኞችን ለመያዝ ኦፕሬሽን መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ሰኞና ማክሰኞ በተደረገው ኦፕሬሽንም ታጣቂዎቹ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ሲዋጉበት የነበረ የቡድን መሣሪያን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ አምስት መሣሪያዎች መያዛቸውን አቶ ዓለማየሁ አስታውቀዋል፡፡ 21 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -