Friday, September 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም አንዳችም አጀንዳ እንደማይኖር በደማቸውና በአጥንታቸው በከፈሉት መስዋዕትነት ነው፡፡ የተለያዩ ገዥዎች ቢፈራረቁም ኢትዮጵያ በተስፋፊዎችና በኮሎኒያሊስቶች የተደረጉባት ወረራዎች የከሸፉት፣ በአገራቸው ከመጡባቸው ለማንም የማይመለሱ ጀግኖች በየዘመኑ ከፊት ረድፍ ሆነው በአርበኝነት ስሜት በመዋደቃቸው ነው፡፡ ለዚህም ታላቁን የዓድዋ ጦርነት ድል ማንሳት በቂ ይሆናል፡፡ የዚህ ዘመንም ትውልድም የተለያዩ ፍላጎቶችና ምልከታዎች ቢኖሩትም፣ ሁሉንም ነገር በአገሩ ሰማይ ሥር በእኩልነትና በመተሳሰብ ስሜት መልክ ለማስያዝ መተባበር ይጠበቅበታል፡፡ ከፓርቲ ፖለቲካ ዓላማ ወይም ከቡድን ፍላጎት በፊት አገር መቅደም አለባት፡፡ አሁን በዓለምም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ከሚስተዋሉ ነባራዊ ሁኔታዎች በመነሳት፣ ኢትዮጵያ የበለጠ ጠንክራና ጎምርታ እንድትወጣ ይህ ትውልድ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በአገሩ ጉዳይ ተቀምጦ በእኩልነትና በሰጥቶ መቀበል መርህ መነጋገር ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ አንዱ ባለቤት እየሆነ ሌላው ባይተዋር መሆን የለበትም፡፡

በኢትዮጵያ ዙሪያ ባሉ ጎረቤት አገሮች እየተካሄዱ ያሉ ጉዳዮችን በጥንቃቄ ለማየትና ዝግጁ ለመሆን፣ በውስጥ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ያለን የጋራ ግንዛቤና መግባባት ይወስነዋል፡፡ ሱዳን በሕዝባዊ ተቃውሞ ቁም ስቅሏን እያየች ቢሆንም ወታደራዊው አስተዳደር የኢትዮጵያን ድንበር ወርሮ ከመያዙ በተጨማሪ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አታካች ሙግት የግብፅ ተቀጥላ ሆኖ የሚፈጽመው አሻጥር ይታወቃል፡፡ ደቡብ ሱዳን አሁንም ውስጣዊ የፖለቲካ ችግሯን በአግባቡ ለመፍታት ባለመቻሏ ምክንያት፣ በፍልሰትና በተለያዩ ሰበቦች ከምትፈጥረው ጫና ባሻገር ይህ ነው የሚባል ተስፋ የሚጣልባት አይደለችም፡፡ የተረጋጋችው ኬንያ እያካሄደችው ያለችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በሰላም ይጠናቀቅ ይሆን፣ ወይስ እንደ ተለመደው ደም መፋሰስ ያስከትል ይሆን የሚል ሥጋት ታቅፋ የአንፃራዊ ሰላሟ ጉዳይ ያሳስባል፡፡ ሶማሊያ አዲሱን ፕሬዚዳንት በምርጫ ካገኘች ወዲህ የሚስተዋልባት ሁኔታ ደስ አይልም፡፡ በአካባቢው አገሮች ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዚዳንቷ ኢትዮጵያ ድርሽ አለማለታቸውና ከግብፅ ጋር መሞዳሞዳቸው ብቻ ሳይሆን፣ ሰሞኑን ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ ቀንደኛውን የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን አመራር የነበረውን ሙክታር ሮቦን ሚኒስትር አድርገው መሾማቸው በዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ነቃ እንበል፡፡

ምንም እንኳ ከጂቡቲና ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ለጊዜው ደህና ቢመስልም፣ በሶማሊያ እየተከናወኑ ያሉ ያልተጠበቁ እንቅስቃሴዎች ትልቅ ትኩረት የሚሹ ናቸው፡፡ አልሸባብ በቅርቡ ከአንዴም ሁለቴ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ በመግባት ጥቃት ለመክፈት ሞክሮ መመታቱ፣ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከኢትዮጵያ ጋርም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ የሚከተሉት ፖሊሲ በውል አለመታወቅ፣ እሳቸው ሥልጣን በያዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ አልሸባብ ኢትዮጵያን ለማጥቃት መነሳቱ፣ በአንድ ወቅት በሞቃዲሾ ዩኒቨርሲቲ በመራው የሽብር ጥቃት ሦስት ሚኒስትሮችንና 19 ተመራቂዎችን ያስገደለና ብዙዎችን ለአካል ጉዳት የዳረገ አሸባሪ ለሃይማኖትና ለፀረ ሽብር ጉዳዮች ሚኒስትርነት መሾማቸውና ሌሎች ድርጊቶቻቸው ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው፡፡ ሰላም ውሎ ማደር የሚቻለው ጎረቤት ሰላም እንደ መሆኑ መጠን፣ ኢትዮጵያውያንም ጎረቤት አገሮች ውስጣቸው ሲታወክ ወይም የሴራ መጎንጎኛ ሲሆኑ፣ ነቃ ብሎ በአንድነት የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ ለመግባባት የሚረዱ ጉዳዮች ላይ  ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ ለውስጣዊ ችግሮች መፍትሔ በጋራ በመፈለግ የአገርን ጥቅም ማስከበር ይገባል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሰላም፣ ነፃነትና ፍትሕ አግኝተው መኖር የሚችሉትና አገራቸውን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች በጋራ መጠበቅ የሚችሉት በብሔራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመነጋገር ሲችሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ካስቸገሩ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው፣ ልዩነትን ይዞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር አለመቻል ነው፡፡ ሥልጣን በአጋጣሚ እጁ የገባ ኃይል ሌሎችን በጠላትነት እየፈረጀ ሲያስር፣ ሲያሰቃይ፣ ሲያሳድድና ሲገድል በኖረባት ኢትዮጵያ በአገር ጉዳይ መመካከር አልተቻለም፡፡ ሕገ መንግሥትን በሚያህል ትልቅ አገራዊ ዋስትና ላይ መግባባት ላለመኖሩ ምክንያት፣ በጋራ መምከርና የሚበጀውን መወሰን ባለመቻሉ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና በሁሉም አገራዊ ሀብቶችና ፀጋዎች ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር ማድረግ የሚቻለው፣ በእኩልነት መመካከርና መወሰን ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ጠንካራ ተቋማት የሚፈጠሩትና ብቃትና ሙያ ባላቸው ሰዎች የሚመሩት፣ ሕጋዊ ዋስትና ያለው ሥርዓት መፍጠር የሚያስችል ምክክር በማድረግ በሚደረስ የጋራ ውሳኔ ነው፡፡ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ የሚሆንበት ኢፍትሐዊ ግንኙነት ተወግዶ፣ በኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ላይ በጋራ ለመወሰን ቁጭ ብሎ መነጋገር ወሳኝ እንደሆነ ይታወቅ፡፡

በአሁኑ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አልገጣጠም ያሉ ነገሮች የበዙ ይመስላሉ፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ እንደሚገመት ከሚነገርለት ሕዝባችን ውስጥ 70 በመቶ ኃይሉ ታዳጊና ወጣት ነው፡፡ ይህንን የሚያህል አምራች ኃይል፣ የበርካታ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ባህሮችና የከርሰ ምድር ውኃ፣ በርካታ ሚሊዮን ሔክታሮች ለምና ጠፍ መሬት እያሉ የምግብ ነገር ይጨንቃል፡፡ ዳቦ፣ ዓሳ፣ ዕንቁላል፣ ሥጋ፣ ዶሮ፣ ወተት፣ ቅቤ፣ ዓይብና የመሳሰሉት የምግብ ዓይነቶችን ማግኘት የኤቨረስት ተራራን የመውጣት ያህል ከባድ ነው፡፡ ለኑሮ ተስማሚ የሆኑ መኖሪያ ቤቶች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ የዜጎች ደመወዝ ወይም ገቢ በፍፁም ሊጨምር ባለመቻሉ ድህነት በአስከፊ ሁኔታ ተንሰራፍቷል፡፡ እንኳንስ ከበሽታ ለመፈወስ ሕክምና ማግኘት ቀርቶ፣ በሕልፈት ጊዜም ለመቃብር ቦታ የሚከፈለው ገንዘብ አለመኖር ያሳስባል፡፡ በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት የሚችል ዕውቀት፣ ልምድና ቴክኖሎጂ አገር ውስጥ ባሉም ሆነ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን በነፃነት በአገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ መነጋገር ብንችል ኖሮ፣ ድህነት ላያችን ላይ ቤቱን ሠርቶ መጫወቻ አያደርገንም ነበር፡፡

ለምሳሌ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በተመለከተ የተለያዩ ተቃርኖዎች ይሰማሉ፡፡ ለዓመታት መንግሥት የኢኮኖሚው ዕድገት በድርብ አኃዝ እያደገ እንደነበረ ሲናገር፣ ሕዝቡ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ መንግሥት ከሚናገረው በላይ በእጥፍ ቁልቁል መቀመቅ እየከተተው እንደነበረ በግልጽ ይናገር ነበር፡፡ መንግሥት የዋጋ ንረቱን በነጠላ አኃዝ አውርዶ በየወሩ መግለጫ ሲያወጣ፣ የሕዝቡ ኑሮ የሚናገረው ከመንግሥት በተቃራኒ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እሰጥ አገባ ዛሬም እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ነገር ግን ጠንካራ ተቋማትና ብርቱ ባለሙያዎች ባሉበት የኢኮኖሚውም፣ የፖለቲካውም፣ የማኅበራዊውም፣ የዲፕሎማሲያዊውም፣ የወታደራዊውም፣ የሕጋዊውም ሆነ የሌላው ነገር ሁሉ በነሲብ እየቀረበ ንትርክ አይፈጠርም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ በመንግሥታዊ ተቋማት የሚቀርቡ መረጃዎችም ሆኑ ሪፖርቶች የጥራት ጉደለት የሚታይባቸው በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ ስለማይመሩ ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ጥቂቶች እንዳሻቸው እንዲፈጩ ዕድሉን የሚያገኙት፣ ብዙኃኑ ከተሳፊነት እንዲገለሉ ስለሚገፉ ወይም ራሳቸውን ስለሚያሸሹ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጠቀመው በሕገወጥ መንገድ ሥልጣን ለሚቆናጠጡና ለዘረፋ ለሚሰማሩ ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...