Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበዩኒቨርሲቲዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ለሚያገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የዕድሜ ጣሪያ ተቀመጠ

በዩኒቨርሲቲዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ለሚያገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የዕድሜ ጣሪያ ተቀመጠ

ቀን:

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኝ ነፃ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) የሚልኳቸው ሠራተኞች ላይ የዕድሜ ጣሪያ ተቀመጠ፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ገደብ ያስቀመጠው፣ ከዚህ ቀደም ወጥ የሆነ አሠራር ላልነበረው የከፍተኛ ትምህርት ስኮላርሺፕ አሰጣጥና ተግባራዊነት ባወጣው የማስፈጸሚያ መመርያ ነው፡፡

አዲሱ የሚኒስቴሩ መመርያ ለመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአገር ውስጥና ለውጭ ስኮላርሽፕ ለውድድር የሚያበቁ መመዘኛዎችን ለይቶ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዕድሜ አንዱ መሥፈርት ነው፡፡

በመሥፈርቱ መሠረት መንግሥት ለሚያመቻቸው የሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) የትምህርት ዕድል የዕድሜው ጣሪያ 35 ዓመት ሆኗል፡፡ የትምህርት ዕድሉ ሦስተኛ ድግሪ (ፒኤችዲ) ለመማር ከሆነ ደግሞ፣ የሠራተኛው ዕድሜ ከ45 ዓመት መብለጥ እንደሌለበት ሚኒስቴሩ ወስኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ስኮላርሽፕን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ወጥ የሆነ አገር አቀፍ አሠራር ባለመኖሩ ምክንያት፣ መሥሪያ ቤቶች በየራሳቸው አሠራር ሲመራ እንደነበር የሚኒስቴሩ የአካዴሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ነፃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የሚላኩ ሠራተኞች የዕድሜ ጉዳይ ‹‹ከዚህ በፊት ችግር ነበረት›› በማለት ኤባ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

‹‹በ50 እና በ60 ዓመት ለስኮላርሽፕ የሚልክ ተቋም አለ፤›› ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ አንዳንድ ተቋማት ደግሞ በ40 እና በ45 ዓመት ያሉ ሠራተኞቻቸውን ለመላክ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የስኮላርሺፕን ጉዳይ ‹‹በአግባቡ፣ በብቃትና በጥራት›› ለመምራት ማሰቡን የሚናገሩት ሥራ አስፈጻሚው፣ የዕድሜ ጉዳይ በመመርያ ውስጥ የተካተተው አሰራሩን ‹‹መስመር›› ማስያዝ በማስፈለጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ሰው እንዳይማር አይደለም፡፡ ሰው በጊዜ ዕድሜውን ተጠቅሞ ተምሮ እንዲጨርስ ነው የተፈለገው፤›› በማለት የሚኒስቴሩን ሐሳብ አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች በግላቸው የሚያገኙትና በግል ሙሉ ወጪ የሚሸፈን የትምህርት ዕድል ግን የዕድሜ ጣሪያ እንደማይኖረው መመርያው ተቀምጧል፡፡

በግል የሚገኝ የትምህርት ዕድልን በተመለከተ መመርያው የደነገገው ሌላው ጉዳይ፣ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግበትን ሁኔታ ነው፡፡ በመመርያው መሠረት አንድ ሠራተኛ በግሉ ከአንድ ወር በታች የሆነ የአጭር ጊዜ የውጭ አገር ስኮላርሺፕ አግኝቶ የትራንስፖርት ወጪው ስፖንሰርሺፕ በሰጠው አካል የማይሸፈን ከሆነ፣ የደርሶ መልስ ትራንስፖርትና የቪዛ ማስፈጸሚያ ገንዘብ የማግኘት መብት አለው፡፡

ይሁንና አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በግል የተገኘ የትምህርት ዕድል ከደብዳቤ ጀምሮ ከመንግሥት የድጋፍ የሚጠይቅ ከሆነ፣ አሠሪው ተቋም ውስጥ ተመልሶ ለማገልገል የውል ስምምነት መፈጸም እንደሚጠበቅበት መመርያው ያዛል፡፡

በመንግሥት በሚገኝ ዕድል ስኮላርሺፕ አግኝተው የሚማሩ ሠራተኞችም እንዲሁ ከትምህርታቸው መጠናቀቅ በኋላ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ የፈጀውን ጊዜ እጥፍ የማገልገል ግዴታ አለባቸው፡፡ ግለሰቦቹ ማገልገል የማይፈልጉ ከሆነ ደመወዝን ጨምሮ የወጣውን ወጪ ከእነ ቅጣቱ የመክፈል፣ በውሉ መሠረት ያልሠሩበት ጊዜ ተሰልቶ ክፍያ እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡

እንደ ኤባ (ዶ/ር) ገለጻ፣ መመርያው ከዚህ በኋላ በሚኖሩ አሠራሮች ላይ ብዥታ እንዳይፈጠርበት ያደረገው አንዱ ጉዳይ ስኮላርሺፕ የሚያገኙ ሠራተኞች ለምርምር የሚያወጡት ወጪ ነው፡፡

ከዚህ ቀደምም ባለው አሠራር ሠራተኛውን ለስኮላርሺፕ የሚልክ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሠራተኛውን ደመወዝና ሌሎች ክፍያዎች የሚፈጽም ቢሆንም፣ ለጥናትና ለምርምር የሚወጣ ወጪን በተመለከተ ‹‹ብዥታዎች›› ነበሩ፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም ደብዳቤ ተጽፎ ስኮላርሺፕ ይሰጠው ይባልና የሪሰርች ወጪውም እንዲሸፈን ይጠየቃል፤›› ያሉት ኤባ (ዶ/ር)፣ ሚኒስቴሩ የሚመደብለት በጀት ይህንን ሁሉ ማከናወን እንደማያስችል አስረድተዋል፡፡

ሠራተኛው ቢማር ለመሥሪያ ቤቱ ይጠቅማል ተብሎ ከተላከ፣ የዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊነት መሆን ያለበት ነፃ የትምህርት ዕድል መስጠት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

መመርያው ሠልጣኞች በአገር ውስጥ የሚማሩ ከሆነ ሙሉ ደመወዝ የማግኘት፣ በውጭ የሚማሩ ከሆነ ድግሞ የደመዛቸውን ግማሽ ማግኘት እንደሚችሉ አስቀምጧል፡፡

የትምህርት ዕድሉን አግኝተው ነገር ግን በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ትምህርቱን ሳያጠናቅቁ ያለ በቂ ምክንያት ባቋረጡ ሠራተኞች ላይ መመርያው ቅጣት ይጥላል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ትምህርቱን ያቋረጡ ሠራተኞች ለአንድ ዓመት በሌሎች ዕድሎች እንዳይሳተፉ ይከለከላሉ፡፡ በሥልጠና ወቅት ያባከኑት ወጪም ተሰልቶ እንደሚከፍሉ፣ ወይም ከመሥሪያ ቤታቸው ጋር ተጨማሪ ውል እንዲገቡ እንደሚደረግ መመርያው ደንግጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...