Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ላለፉት ሰባት ዓመታት ላልተጠናቀቀው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ተጨማሪ 4.8 ቢሊዮን ብር ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከስድስት ዓመት በፊት የኢትዮ ቴሌኮምን ዋና መሥሪያ ቤትን በ4.5 ቢሊዮን ብር በሦስት ዓመት ገንብቶ ለማጠናቀቅ ውል የገባው የቻይናው ሲጂኦሲ ኮንትራክተር፣ ሕንፃውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 4.8 ቢሊዮን ብር መጠየቁ ተሰማ፡፡

በቦሌ አይሲቲ ፓርክ ውስጥ በ37 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ግንባታው እየተከናወነ ያለውን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና መሥሪያ ቤት፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል የገባው የቻይናው ኩባንያ፣ ሕንፃውን ጨርሶ ለማስረከብ የመጀመርያ ውል ያሰረው እ.ኤ.አ. በ2016 ነበር ፡፡

ይሁን እንጂ በተያዘለት የማጠናቀቂያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ2019 ሕንፃውን ጨርሶ ማስረከብ ያልቻለው ኮንትራክተሩ፣ ይህንን ፕሮጀክት ፋይናንስ ሊያደርግ አስቦ የነበረው ከሌሎች አገሮች ከሚያገኘው የፕሮጀክት ገንዘብ የነበረ ቢሆንም፣ ኩባንያው የጠበቀውን ገንዘብ ማግኘት ባለመቻሉ፣ ከዓመታት በፊት የዋጋ ማስተካከያና የጊዜ ማራዘሚያ ጥየቄ እንዲደረግለትና የውጭ ምዛሪ እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ችፍ ፋሲሊቲስና ፍሊት ኦፊሰር አቶ ዓይናለም አልበኔ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የኮንትራክተሩን ጥያቄ ተቀብሎ ምክንያታዊ ነው ያለውን የስድስት ወራት ተጨማሪ ጊዜ እንደተሰጠው፣ ቆይቶም ኮቪድ-19 በመከሰቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዩ አስቸጋሪ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በመረዳት በልዩ ሁኔታ ተጨማሪ 18 ወራት ተፈቅዶለት፣ በታኅሳስ 2014 ዓ.ም. እንዲያጠናቅቅ ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር አክለው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኮንትራክተሩ አሁንም በመጀመሪያው ውል የተስማማበት ገንዘብ አያሠራኝም በማለቱና ተጨማሪ ገንዘብ በመጠየቁ፣ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ በተደጋጋሚ በማቅረቡ  ምክንያት፣ ሕንፃው ሊጠናቀቅ እንዳልቻለ አቶ ዓይናለም አስረድተዋል፡፡

80 በመቶ የሚሆነው ግንባታ መከናወኑን የገለጹት አቶ ዓይናለም፣ ባለ አሥር ፎቅ ሕንፃው ሲጠናቀቅ ከ5,000 በላይ ሠራተኞችን እንደሚችል፣ 1,500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የስበሰባ አዳራሽ እንደሚኖረው፣ ሦስት ቤዝመንቶች፣ 22 አሳንሳሰሮችና ሁለት ስካሌተሮች እንደሚገጠሙለት ተናግረዋል፡፡

የቻይናው ኮንትራክተር ሕንፃው ሙሉ አገልግሎት በሚሰጥበት ደረጃ አጠናቆ ለማስረከብ፣ በመጀመሪያ በተፈራረመው የፋይናንስና የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የተስማማ ቢሆንም፣ ሕንፃውን ለማጠናቀቅ የሚጠቀማቸው ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በመጀመሪያው ስምምነት መሠረት ምንም ዓይነት የዋጋ ማስተካከያ እንደማይደረግ፣ ኩባንያው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በመጠየቁ ኢትዮ ቴሌኮም ስለ ሕንፃው ግንባታ አፈጻጸም ዘርዘር ያለ ጥናት ካካሄደ በኋላ፣ ከኩባንያው ጋር ሦስት ጊዜ ውይይት ማድረጉን አቶ ዓይናለም አስተድተዋል፡፡ ‹‹የተደረገውን የውይይት ውጤት  ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ ለማቅረብ እየተዘጋጀንበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በተከታታይ የሕንፃውን ሁኔታ በመገምገም ከኮንትራክተሩና ከኩባንያው የምሥራቅ አፍሪካ ኃላፈዎች ጋር ውይይት በማድረግ፣ አሁን በተደረገው ድርድር መሠረት የተደረሰበት ስምምነት፣ በቀጣይ ለቦርዱ ቀርቦ ፕሮጅክቱ የሚጠናቀቅበት ሁኔታ ይመቻቻል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያው ስምምነት ከነበረው 4.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ 2.8  ቢሊዮን ብር የሚሆነው  ለኮንትራክተሩ  መከፈሉን፣ ኮንትራክተሩ ከቀረው 1.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ  20 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነውን በውጭ ምንዛሪ  እንደተሰጠው፣ ነገር ግን የተጠየቀው 20 ሚሊዮን ዶላር በመጀመርያው ስምምነት ያልተገለጸ መሆኑን አቶ ዓይናለም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የሕንፃውን የግንባታ ደረጃና ኮንትራክተሩ ያቀረበውን ተጨማሪ ገንዘብና ጊዜ፣ እንዲሁም በኩባንያው የተገኘውን የጥቅምና የጉዳት ዳሰሳ ጥናት በነሐሴ ወር ውስጥ በሚደረገው የኢትዮ ቴሌኮም የቦርድ ስብሰባ ሊቀርብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮ ቴሌኮም ኮንትራክተሩ የጠየቀውን ገንዘብ ለመክፈል የማይገደድ በመሆኑ፣ በቀጣይ የሚደረጉ የመንግሥትና የቦርድ ውሳኔዎች ታይተው ኩባንያውን በመቅጣትና ውሉን በማቋረጥ ሕንፃውን በሌላ ኮንትራክተር የማስጨረስ ወይም በአገር አቀፍ ደረጃ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የተፈጠረውን ከባድ ችግር በመረዳት፣ የሚያስፈልገውን ገንዘብ መድቦ በዚሁ ኮንትራክተር እንዲጠናቀቅ ሊደረግ ይችላል ብለዋል፡፡

ለኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት እንዲያገልግል ተብሎ እየተገነባ ያለው ሕንፃ ከቦታው ርቀት አንፃር ዋና መሥሪያ ቤቱን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዚህ ቦታ ለማሸጋገር የተወሰነ ሥጋት እንዳለ የገለጹት አቶ ዓይናለም፣ ሕንፃው  በጣም ግዙፍ በመሆኑ በአጭር ጊዜ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆነንም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እየሰጠ ያለው በጣም በተጣበቡ ቢሮዎች በመሆኑና በዋና መሥሪያ ቤት ደረጃ ብዙ ኪራይ እየከፈለ ስለሆነ፣ ሕንፃው እንደተጠናቀቀ ቢያንስ ለጥናትና ልማት፣ ለሥልጠና ማዕከልነት፣ እንዲሁም የምሥራቅ አካባቢ የቴሌኮም ዞን ወደ አዲሱ ሕንፃ በማስገባት አሁን እየተከፈለ ያለውን ኪራይ ማስቀረት ይቻላል ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 ሕንፃውን ለማስገንባት ስምምነቱ በቀድሞው የኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ እንዲሁም በቀድሞው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሰሽን ሚንስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌና የቻይናው ኮንትራክተር ሲጂኦሲ በተገኙበት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የግልና የመንግሥት የግንባታ ፕሮጅክቶችን እያከናወኑ የሚገኙት የቻይና ኮንትራክተሮች ለሚያካሂዷቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች በተመሳሳይ የዋጋ ማስተካከያ እየጠየቁ ነው፡፡

ለአብነት በቻይና ኮንስትራክሽንና ዲዛይን ኮርፖሬሽን በ2.47 ቢሊዮን ብር የሚገነባው የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታን ለማከናወን በዓለም አቀፍ ገበያ የግንባታ ዕቃዎች በመጨመሩ፣ ኮንትራክተሩ ከሁለት እስከ ሦስት እጥፍ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲከፈለው መጠየቁን ከጥቂት ሳምንታት በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች