Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትበውዝግብ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ

በውዝግብ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ

ቀን:

ፊፋ ከምርጫው በፊት የሥነ ምግባር ባለሙያ ሊልክ መሆኑ ተሰምቷል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በሚያከናውነው ጉባዔ፣ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ብሔራዊ ተቋሙን የሚያስተዳድሩ የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ያደርጋል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ሦስት ለፕሬዚዳንታዊና 26 ለሥራ አስፈጻሚ የቀረቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ዝርዝር ይፋ ቢያደርግም፣ ከጥቅም ግጭት ጋር በተገናኘ የገለልተኝነት ችግር አለበት በሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከሁለት ወራት በፊት በአዲስ አበባ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው የፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ ገለልተኛ ሆነው ምርጫውን ሊያስፈጽሙ እንደሚችሉ የታመነባቸው የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መሰየሙ ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

አስመራጭ ኮሚቴውም ሐምሌ 22 እና 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ ለምርጫ በዕጩነት የቀረቡ ተወዳዳሪዎችን ዝርዝር ተመልክቶ ተገቢነታቸውን በማረጋገጥ ሦስት ለፕሬዚዳንትና 26 ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን አሳውቋል፡፡

ይሁንና የሐረሪ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ዕጩ አድርጎ ያቀረባቸው አቶ ገዛሃኝ ወልዴ፣ ክልሉ ‹‹ውክልናዬን አንስቻለሁ›› ብሎ ባቀረበው አቤቱታ፣ እንዲሁም ከጋምቤላ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዕጩ ሆነው የቀረቡት አሌሮ ኦፒዮ ኡጁሉ (ኢንጂነር)፣ ኛጆክ ጆንክ ካንግና ኡጁሉ አደይ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 40 (ሐ)  ንዑስ አንቀጽ (1 ሀ) መሠረት፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ማስረጃቸው በአምስት አባላት ተደግፎ ያልቀረበ በመሆኑ ከውድድር ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉን አሳውቋል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው እንደ ጋምቤላ የቤንሻጉል ክልል በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ (33) ንዑስ አንቀጽ (5) መሠረት ዕጩ ሆኖ ለመቅረብ መሥፈርቱን ማሟላት ባለመቻሉ የተወዳዳሪዎችን ዝርዝር ይፋ አላደረገም፡፡

ኮሚቴው በተጨማሪም ከአፋር ክልል ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ዕጩ ሆነው ቢቀርቡም፣ ነገር ግን ሦስት የምርጫ ዘመን አገልግለዋል በሚል አቶ አሊሚራህ መሐመድ ዓሊ ከዕጩ ተወዳዳሪነት ዝርዝር እንዲወጡ ማድረጉን ጭምር አሳውቋል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው ባደረገው ማጣራት ሦስቱ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የቀረቡት፣ አቶ መላኩ ፈንታ ከአማራ ክልል፣ አቶ ኢሳያስ ጅራ ከኦሮሚያ ክልልና አቶ ቶክቻ ዓለማየሁ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስለመሆናቸው ይፋ አድርጓል፡፡

ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ እንደሚችሉ ማረጋገጫ ያገኙት ደግሞ፣ ከሐረሪ ክልል አብዱላሂ አህመድ፣ ሀናን ሁሴንና ሙራድ አብዲ ሆነዋል፡፡ ከአፋር ክልል ኢብራሂም ሙክታርና አሲያ አብዱርቃድር ናቸው፡፡

ከደቡብ ክልል ቀድሞ የእግር ኳስ ዳኛና ኮሚሽነር የነበሩት ሸረፋ ደለቾ፣ ረዳት ኮሚሽነር እንዳለ አብራና በሀብቷ አስቻለው ሆነዋል፡፡ ከአማራ ክልል ዳኛቸው ንግሩ፣ ያየህ አዲስና ብርቱካን ስሜነህ ሲሆኑ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሀቢባ ሲራጅ፣ አሥራት ኃይሌና ተስፋዬ ኦሜጋ ሆነዋል፡፡

ከሶማሌ ክልል አብዱራዛቅ ሐሰን፣ አብዱልፈታህ እስማኤልና ፈይዛ ረሽድ ሲሆኑ፣ ከሲዳማ ክልል መዓዛ ተስፋዬ፣ አዲሱ ቃሚሶና ማርቆስ ኤልያስ ናቸው፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ኩመራ በቀለ፣ ቀድሞ የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዳይሬክተር የነበሩት መኮንን ኩሩና አበራሽ ታደሰ ሲሆኑ፣ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ድግሞ ኤርሚያስ ኃይሉ፣ ብዙአየሁ ጀንበሩና ወገኔ ዋልተንጉስ (ዶ/ር) መሆናቸው አስመራጭ ኮሚቴ ይፋ አድርጓል፡፡

በሌላ በኩል ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደሚደረግ ለሚጠበቀው የፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ የምርጫውን ሒደት እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተጣለበት አስመራጭ ኮሚቴ ከጥቅም ግጭት ጋር በተገናኘ ክስ ቀርቦበታል፡፡

ለዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ክሱን ያቀረቡት ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቀደም ሲል ከሐረሪ ክልል ውክልና የወሰዱት አቶ ገዛሃኝ ወልዴ ሲሆኑ፣ የክሱ መሠረታዊ ጭብጥ ደግሞ አስመራጭ ኮሚቴውን በሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ ኃይሉ ሞላ የፌዴሬሽኑ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ሆነው ያገለገሉ መሆናቸው፣ እንዲሁም አቶ መንግሥቱ መሐሩ የፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩ ከመሆናቸው ባሻገር የኢትዮጵያ መድን እግር ኳስ ክለብ ቦርድ በመሆናቸው የጥቅም ግጭት ስላለው ምርጫውን ገለልተኛ ሆነው ሊያስፈጽሙ አይችሉም በሚል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ፊፋ ዙሪክ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ እ.ኤ.አ. ግንቦት 30 ቀን 2007 ባወጣው ሕግ መሠረት፣ ከምርጫ ጋር ተያይዞ አባል ማኅበራት መብትና ግዴታ በሚል ባፀደቀው መመርያ አንቀጽ 2 መሠረት፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ምርጫ በሚያደርጉበት ጊዜ አስመራጭ ሆነው የሚሰየሙ አባላት ምንም ዓይነት የጥቅም ግንኙነት የሌላቸውና ገለልተኛ መሆን እንዳባቸው ይገልጻል፡፡

በመሆኑም ነሐሴ 21 የሚደረገውን ምርጫ ለማስፈጸም የተሰየሙት አባላት ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ‹‹ከብሔራዊ ተቋሙ ጋር ቀጥተኛ የሆነ የጥቅም ግንኙነት ያላቸው ናቸው፤›› ይህን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ በፌዴሬሽኑ በተለይም ከምርጫው ጋር ተያይዞ ተፈጽሟል የሚባለው የሥነ ምግባር ጉድለት እንዲስተካል ከመጠየቅም አልፎ ጉዳዩን የሚከታተል ባለሙያ እንደሚልክ  ስለመግለጹ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የክሱን ዓይነትና ሁኔታ አስመልክቶ፣ ‹ዕጩ ተወዳዳሪዎች ማሟላት ያለባቸውን መሥፈርት አሟልተው እንዲመዘገቡ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ መሠረት ማለትም ሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ማስረጃየን ለአስመራጭ ኮሚቴው አስገብቻለሁ፡፡ ይሁንና አስመራጭ ኮሚቴው የዕጩዎችን ምዝገባ እስከ ሐምሌ 18 ነው ካለ በኋላ፣ በቂ ዕጩ ተወዳዳሪዎች አልቀረቡም በሚል አንድ ተጨማሪ ቀን በመፍቀድና በዚሁ ተጨማሪ ቀን ውክልና የሰጠህ ክልል ‹‹ውክልናዬን አስቻለሁ›› ብሏል በሚል ከዕጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ውጪ እንድሆን አድርጎኛል፤›› የሚሉት አቶ ገዛሃኝ፣ ‹‹እንዴት ነው በቂ ተወዳዳሪ አልቀረበም በሚል በተፈቀደ ተጨማሪ አንድ ቀን ውክልናህ ተነስቷል የሚባለው?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

የክሱን ጭብጥ በሚመለከት አቶ ገዛሃኝ ‹‹በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ክፍሎች ወሳኝ በሚባሉ የሥራ ክፍሎች ተመድበው አገልግት ሲሰጡ የቆዩ ሰዎች የአስመራጭ ኮሚቴ ውክልና ሊሰጣቸው እንደማይገባ የፌዴሬሽኑም ሆነ የፊፋ ሕግ በግልጽ ያሳያል፡፡ ከዚህ አንፃር መብቴን ለማስከበር ጉዳዩን ለፊፋ አሳውቄያለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ሞላ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ከዕጩ አቀራረብ ጋር የተያያዙ ክስና መሰል ጉዳዮች ያላለቁ ነገሮች ስላሉ ማብራሪያ ለመስጠት እቸገራለሁ፤›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...