Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ጊዜው ትንሽ ራቅ ቢልም የእንግሊዝ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ሚኒስትር ከአንድ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ዩኒቨርሲቲዎች ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ መብት ዋስትና እንዲሰጡ መታዘዛቸውን መናገራቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ድርጊቶች እንዲያበቃላቸው መታዘዙንና ይህንን ተግባራዊ የማያደርጉ ዩኒቨርሲቲዎች ፈቃዳቸው ይሰረዛል ብለው ነበር፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕግ እንደሚጠበቅ ያረጋገጡት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ወጣቶቻችንና ተማሪዎቻችን ጤናማና ብርቱ የሐሳብ ፍጭቶች የመኖራቸውን አስፈላጊነት እንዲቀበሉ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተቃራኒ ሐሳቦች የሚስተናገዱበት መሆኑን እንዲረዱ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ተግባራዊ ሲሆን ነው የተለያዩ ሐሳቦች የሚፈተኑት፣ ሚዛናዊነት የጎደላቸው ድርጊቶች የሚጋለጡትና ማኅበረሰቡም የተሻለ ግስጋሴ የሚኖረው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በምንም ዓይነት ሁኔታ የንግግርም ሆነ የጽሑፍ ነፃነት ማፈኛ መሆን የለባቸውም፤›› ማለታቸውንም አልረሳውም፡፡ ይህ እንግዲህ ታላቋ እንግሊዝ ውስጥ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ‹ማን ከማን ያንሳል?› ለምን አንልም? ዘራፍ ለመቼ ነው ታዲያ?

ከላይ እንደ መነሻ የተጠቀምኩበትን ዘ ታይምስ የተባለው ሚዲያ ያቀረበውን ጽሑፍ ሳነብ ውስጤ በተደባለቁ ሐሳቦች ተወጥሮ ነበር፡፡ አንደኛው እንግሊዝን የምታህል ዓለምን በአንድ ወቅት አስገብራ ‹በእንግሊዝ ግዛት ፀሐይ አትጠልቅም› ያሰኘች አገር የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ነበረባቸው ወይ የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እኛ እንደ ቀደምቶቹ የዘመነ ጋርዮሽ ሰዎች ገና ከዛፍ ዛፍ እየተንጠላጠልን የዱር ፍሬ የምንለቅም መምሰላችን ነው፡፡ ሦስተኛውና ዋናው ነጥብ ከተራ ግለሰብ እስከ መንግሥት ድረስ ዴሞክራሲ የሚባለውን ጽንሰ ሐሳብ እያመነዠግን፣ የማይመቹንን ሐሳቦች ድባቅ የመምታት ወይም ባለሐሳቦቹን ድራሽ የማጥፋት አባዜያችን ድንቅ ብሎኝ ነው ይህንን የጻፍኩት፡፡ ከገጠመኞቼ ልነሳ፡፡

የመሥሪያ ቤታችን ዋና ኃላፊ በታይታና በማስመሰል የተካነ፣ ከእባብ የበለጠ ተናዳፊ፣ አንደበተ ርቱዕ ሆኖ በአፉ ጥሬ የሚያበስል፣ ከገዛ ጥቅሙ በላይ ለሥራ ባልደረቦቹም ሆነ በአጠቃላይ ለአገር ደንታ የሌለው መሰሪ ግለሰብ ነው፡፡ በሆነ አጋጣሚ በኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ከሥራ ጋር በተገናኘ ለቀረቡለት ጥያቄዎች በሰጠው ምላሽ ጠያቂዎቹን ብቻ ሳይሆን፣ በቀጥታ ሥርጭት ለአስተያየት በቀረቡ አድማጮች የፈጣሪ ያህል ውዳሴ እየቀረበለት ሲጨበጨብለት አስታውሳለሁ፡፡ የሬዲዮ ማብራሪያውን የሰሙ ሰዎች፣ ‹ምናለበት ይህንን የመሰለ ድንቅ ምሁር አገር ቢመራ…› እያሉ ሲደመሙም እንደነበር አልዘነጋም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ይህ ሰው በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ የራሱን ‹ሚሊሻዎች› አደራጅቶ ሰውን መሰለል የሚወድ፣ በነፃነት የመሰላቸውን የሚናገሩና አስተያየት የሚሰጡ ሠራተኞችን በሰበብ አስባብ ዕድገት የሚነፍግ፣ አበሳጭቶ በገዛ ፈቃዳቸው ከሥራ እንዲለቁ የሚያደርግ፣ የእሱ ጎራ ውስጥ ተቀላቅሎ ከበሮ ለመደለቅ ፈቃደኛ ያልሆነን በሚሊሻዎቹ አማካይነት አደጋ የሚያደርስ ሰይጣን ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ሁሉም ሠራተኛ ማለት ይቻላል ተፈጥሯዊ መብቱን ተገፎ እንደ እንስሳ መኖር ተስኖታል፡፡ የመረረው ጥሎ ይሄዳል፡፡ መሄጃ የሌለው ዕድሉን እየረገመ ዕድሜውን ይቆጥራል፡፡ ሁለት ዓመታት ሠርቼ ከዚያ መሥሪያ ቤት ስወጣ ጭንቀቴን የተገላገልኩት የምጥ ያህል ነበር፡፡ አሁን ይኼን ማን ያምናል? እኔ ግን እውነት ነው እላችኋለሁ፡፡

መንግሥት የሐሳብ ነፃነትን እንዳይገድብ በሕግ መከልከሉን ብዙዎቻችን እናውቃለን ብዬ እገምታለሁ፡፡ የሐሳብ ነፃነትን ማፈን የብዙዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት ባህርይ መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ አንድ የአፍሪካ አገር መሪ፣ ‹‹በአገራችን የሐሳብ ነፃነት የተከበረ ነው፣ ከንግግር በኋላ ግን ዋስትና አንሰጥም…›› በማለቱ ይቀለድበታል፡፡ የሕግ የበላይነት ሲጠፋ መጀመርያ የሚጎዳው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ በዚህ ጉዳይ በበርካታ ወገኖች የሰሉ ትችቶች ቢቀርቡለትም፣ ‹ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሉ ግን ጉዞውን ቀጥሏል› እያለ መልካም አጋጣሚዎች ይባክናሉ፡፡ ልክ እንደ መንግሥት የዚህ ዓይነቱ በሽታ የተጋባባቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ አንዱ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲ መምህሬ ነበሩ፡፡ እሳቸው መንግሥትን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በመንቀፍና በመቃወም ይታወቃሉ፡፡ በፊት በፊት በጋዜጦች ይጽፉም ነበር፡፡ ለእኔ ግን በጣም ዕንቆቅልሽ ናቸው፡፡ እሳቸው የሚሉትን አለመቀበል ከቁጣና ከግልምጫ ባለፈ ‹ግሬድ› ያስቀጣል፡፡ አንድ ቀን ‹በፌዴራሊዝም ላይ የጻፉት ጥሩ ጎኖች ቢኖሩትም፣ ሚዛናዊነት ይጎድለዋል፤›› ስላቸው፣ ‹‹አንተ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው የመንግሥት ተላላኪ የሆንከው?›› ብለው ደሜን አፈሉት፡፡ ከቁጣዬ በረድ ብዬ በጽሑፉ አመክንዮ ላይ እንነጋገር ብላቸው፣ ‹‹መጀመርያ አቋምህን አስተካክል…›› ብለውኝ ተለያየን፡፡ የ‹‹ኤ›› ተማሪ የ‹‹ሲ›› ሰለባ ሆኜ ቀረሁ፡፡ ድንቄም ዩኒቨርሲቲ፣  ድንቄም መምህር፡፡

በአንድ ወቅት እኔም እንዳቅሚቲ አንዱን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ተቀላቅዬ እንዘጭ እንዘጭ ማለት ጀምሬ ነበር፡፡ አይ መፈክር? አይ ቅስቀሳ? ዘው ብዬ በገባሁበት ጊዜ አፍላ ወጣቶችና ጎልማሶች ለፓርቲው ተልዕኮ መሳካት ላይ ታች ሲሉ ወኔያቸው አስገራሚ ነበር፡፡ በአገር ፍቅር ስሜትና ለለውጥ ካለ ፍላጎት የተነሳ ቀንና ሌሊት እንደዚያ ሲራወጡ ያስቀኑ ነበር፡፡ እኔ ጊዜው ባይኖረኝም በገንዘብ፣ በሐሳብና አንዳንዴም ጽሑፎችን በማቅረብ በተቻለኝ መጠን እሳተፍ ጀመር፡፡ እየዋለ እያደር ግን አንድ ነገር ግልጽ ሆነልኝ፡፡ በዚያ ሁሉ የተጋጋለ ጥረት ውስጥ ጥላውን የጣለ ነገር አለ፡፡ የፓርቲው ውስጠ ዴሞክራሲ ጤነኛ አይደለም፡፡ የአባላትና የደጋፊዎች ትኩረት ውጫዊ እንዲሆን ተደርጎ፣ የውስጡ ጉዳይ በጥቂቶች ታግቷል፡፡ ከውጭ የሚመጣ ገንዘብ መጠኑና የመምጫው አቅጣጫ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህንን ጉዳይ የሚያነሱ ‹ሰርጎ ገብ› ተብለው በፍጥነት ይፈረጁና ይወገዳሉ፡፡ ደፈር ብለው በቅንነት ጥያቄ የሚያነሱ ወይ በመረቡ ይጠመዳሉ፣ አሊያም ‹ሰርጎ ገብ› ተብለው ተነጥለው ይወገዳሉ፡፡ እንኳንስ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ የፊት እንቅስቃሴ ሳይቀር ይገመገማል፡፡ አዲዮስ ዴሞክራሲ፡፡ ይህንን እያዩ እዚያ ቦታ መቆየት መርህ ላለው ሰው ስለማይጠቅም ሸሸሁ፡፡ ያለ ዛሬ ይህንን ጉድ ለመናገር ድፍረት አጥቼ ኖሬያለሁ፡፡ አይ ኢትዮጵያ አገሬ፡፡

እኔ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚባለው ጉድ ውስጥ ስላለው እንቶ ፈንቶ ለመነጋገር አልፈልግም፡፡ በተለይ ፌስቡክና ዩቱዩብ መሰል ነገሮች የነባራዊው ዓለም ተቃራኒ ማነፃፀሪያ በመሆናቸው ለምሳሌዬ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ ነገር ግን በየዕለቱ የፌስቡክና የዩቱዩብ ዓለም ተዋንያንን ከሚያደርጉት ንግግር ስረዳ ተቃራኒ ሐሳብ ከመስማት፣ ሳይወለዱ ቢቀሩ የሚሻላቸው ብዙ ናቸው፡፡ አንዱን በቅርብ የማውቀው በፒኤችዲ ደረጃ ያለ ግለሰብ፣ ‹‹ብዙ ጊዜ አስተያየቶችህን አያቸዋለሁ፡፡ አንተ የምትፈልገው ድጋፍ የሚሰጡህንና የሚያንቆለጳጵሱህን ብቻ ነው፡፡ የአንተን ሐሳብ የማይቀበሉት ግን ስድብ አዘል ምላሽ ትሰጣለህ፡፡ ይህንን ምን ይሉታል?›› ብዬ ወቀሳ ሳቀርብለት፣ ‹‹አንተም ከእነሱ የማትሻል ነህ፡፡ እኔ የማንንም ዝንባዝንኬ የመስማትም ሆነ የማንበብ ትዕግሥት የለኝም…›› እያለ ሲንጣጣብኝ ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ መንግሥት መብቴን አፈነብኝ የሚል ሌላውን ለማፈን የሚታገል ከሆነ መድረሻችን የት ነው? ጎበዝ በዚህ ሁኔታ እኮ የአደባባይ ሰዎቻችንን እያጣን የዱር አውሬ መሆናችን ነው፡፡ በዚህ ላይ ገንዘብን ብቻ ዒላማ አድርገው ዩቱዩብ ውስጥ የመሸጉ ጉዶች ደግሞ፣ ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን በመጣስ የሚሠሩትን ለሚያይ ምሬቱ ምን ያህል እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ተሸክመን ነው እንግዲህ ትዕግሥቱ ይኑረን የምንለው፡፡

(ሰለሞን ተሻገር፣ ከሲኤምሲ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...