Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበደቡብ ክልል አዳዲስ የክልል መዋቅሮች መፈጠርና የሸዋ ክልል አካባቢያዊና አገራዊ አንድምታ

በደቡብ ክልል አዳዲስ የክልል መዋቅሮች መፈጠርና የሸዋ ክልል አካባቢያዊና አገራዊ አንድምታ

ቀን:

በከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከታዩ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች አንዱ በደቡብ ክልል በሚኖሩ አካባቢዎች በሚኖሩ ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄዎች መበራከት ነው። በወቅቱ ክልሉን ይመራ የነበረው ፓርቲ ደኢሕዴን ችግሩን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት  ሃያ ምሁራንን የያዘ የጥናት ቡድን አቋቁሞ ስምንት ወራት የወሰደ ጥናት ሲከናወን የቡድኑ ተሳታፊ ነበርኩ።

 በጥናቱ ግኝት መሠረት አራት ምክረ ሐሳቦችን ነበር ያቀረብነው

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 አንደኛው በክልሉ  ሕዝብ በወቅቱ  ይነሱ የነበሩ የእኩል ተጠቃሚነትና ኢፍትሐዊነት  ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ  ሕግና አሠራሮች ተዘርግተውና  ችግሮቹ ተፈትተው፣ እንዲሁም የክልሉን መቀመጫ ከአንድ በላይ ማዕከል ኖሮት  56 ብሔረሰቦችን አቅፎ አንድ ክልል ሆኖ መቀጠል፣ ሁለተኛው የሲዳማ ክልል ጥያቄ የቆየና ብዙ ርቀት የሄደ በመሆኑ ሲዳማዎች የሚገፉበት ከሆነ 55 ብሔረሰቦች አንድ ክልል መመሥረትና ማዕከሉን በርካታ ቦታዎች ማድረግ፣ ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ በአንደኛውና በሁለተኛው አማራጭ ላይ ስምምነት ከታጣ ለጠየቀ ሁሉ መፍቀድ ከጥቅሙ ይልቅ ለአገርም ጉዳቱ ስለሚያመዝን ተጨማሪ ጥናት ተደርጎና ማዕከላዊ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶት  መሥፈርት አውጥቶ፣ የደቡብ ክልልን ከሦስት እስከ አምስት ቦታ በክላስተር  ይክፈል የሚል ነበር። ይህ ካልሆነም አሁን  ሰከን ተብሎ ጥያቄውን ለጊዜው ማቆየት የሚል ነበር።

በወቅቱ የዚህ ጥናት ውጤት ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ካድሬ፣ እንዲሁም ሕዝቡ ተወያይቶበት ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳገኘና  ጥናቱ ድርጅቱን (ደኢሕዴን) እና ክልሉን በድንገት ከመፍረስ ታድጓል።  ክልሉ በዚህ ጥናት ውጤት ምክንያት በድንገት ሳይበታተን የሲዳማንና የደቡብ ምዕራብ ክልሎችን ጥያቄ ተረጋግቶ እንዲፈታና የቀሩት አካባቢዎችን ጥያቄ  ተረጋግቶ እንዲፈታ ረድቶታል የሚል እምነት አለኝ። 

አሁን እንደምንሰማው ደቡብ ክልል አራት ክልሎችን ወልዶ ራሱን ሊያከስም መቃረቡን የሚያበሰሩ ውሳኔዎች በየዞን ምክር ቤቶች ተወስኗል። መንግሥት ለዚህ ውሳኔ በግብዓትነት የተጠቀማቸው ሐሳቦችና ምክንያቶች አሉ። አንዱና ምናልባትም ዋናው ግብዓት ከላይ እንደጠቀስኩት  ሃያ ተመራማሪዎች ሆነን በክልሉ ውስጥ ጥናት አድርገን ያቀረብነው ምክረ ሐሳብ እንደሆነ እገምታለሁ። 

 በጊዜ ሒደት ሲታይ  አማራጭ አንድና አማራጭ ሁለት ስላልሠሩ መንግሥት አማራጭ ሦስትን የመረጠ ይመስላል።  ውሳኔው ሳይንሳዊ የምርምር ግኝትን መሠረት ያደረገ ነው ብሎ ማለት ይቻላል። የደቡብ ክልል መዋቅር ጉዳይ በዚህ ሁኔታ ሲቋጭ በውጤቱ ያልተደሰቱ ወይም በአካሄዱ ያላመኑ ወገኖች (ግለሰቦችና ቡድኖች) ሊኖሩ ይችላሉ። ወደፊት መልሶ የማየት ዕድል ምናልባት ሊኖር ስለሚችል፣ ሐሳባቸውን እንደ ሐሳብ በሰላማዊ መንገድ በነፃነት እያቀረቡ አሁን የተደረሰበትን ውሳኔ ማክበር ተገቢ ይሆናል። ምክንያቱም አደረጃጀቱን በተመለከተ ምንም ይሆን ምን ሕዝብ የሚፈልገው ልማትና ፍትሐዊ አሠራር ማምጣት ይችላል ወይ ብሎ ሰከን ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። አዲሱ አደረጃጀት ያልተመቻቸው ወገኖች አሉታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከገቡ በልማት የሚጎዳው የሚወዱት ሕዝብ ነው። ከትናንት መማርና አገራዊ ዓውዱንም መገንዘብ ተገቢ ነው።

አገራችን ዛሬ በአራቱም አቅጣጫ በማያባራ ፈተና ውስጥ ስለሆነች፣ በክልል መዋቅር ጥያቄ ምክንያት ሌላ ፈተናና ውድመትና የሰው ሕይወት ሊጠፋና ተጨማሪ ግጭት ሊመጣ አይገባም።  ሰዎች ለሕዝባቸው በቅንነት የተሻለ አደረጃጀት ነው ብለው ባመኑት መስመር አቋም ይዘው ሊታገሉ ይችላሉ። አንዳንድ ለሕዝብ ደንታ የሌላቸውና ከግጭት  የሚያተርፉ አካላት አጀንዳ ቀምተው በድብቅ በማኅበራዊ ሚዲያ የሐሳብ ተጋሪ ወይም ተቺ መስለው ጉዳዩን በማጦዝ፣ ሕዝቡን አላስፈላጊ ዋጋ እንዳያስክፍሉ ማስተዋልና መጠንቀቅ ተገቢ ነው። ሕዝቡም የሰማውን ሁሉ ሳያረጋግጥ ማመን የለበትም።

 የደቡብ ክልልን አንድነት አናግቶ ወደ መበታተን እየገፋ ያለው ምንድነው? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ የእኛ ጥናት አሥራ ሦስት ገፊ ምክንያቶችን ነቅሶ እንዳወጣና የመፍትሔ አቅጣጫም እንዳስቀመጥን አስታውሳለሁ። ይህንንም በአዲሶቹ ክልሎች እንዳይደገም በጥንቃቄ ማየት ተገቢ ነው። አሁን እንደሰማነው ከብዙ አገሮች ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ቀምረን ያቀረብነው የክላስተር ሐሳብ ተግባራዊ ሊሆን ተቃርቧል። በጥቅሉ አገራችን የሚያስፈልጓት የየሕዝባችን የተሰናሰለና እጅግ የተጋመደ አንድነትና የየሕዝቦቹን ማንነት ያከበረ ክልላዊ አደረጃጀት ነው። 

በዛሬው መልዕክቴ በእነዚህ ዝርዝር ውስጥ ባልገባም ለአዳዲሶቹ ኅብረብሔራዊ ክልሎች ያለኝ ምክር በማዕከል አመራረጥና  አደረጃጀት፣ በሀብት ክፍፍል፣ በፖለቲካ ተሳትፎና በመሠረተ ልማት ሥራ የቀድሞ የደቡብ ክልል የሠራውን ስህተት እንዳይደግሙ፣ ሕዝቡን ቀርበው እንዲያዳምጡና ፍትሐዊና አሳታፊ አሠራር እንዲያሰፍኑ ነው። ከራስ ስህተት መማር ብልህነት ነው። አሁን የሚደራጁት የክልል መዋቅሮች ሕዝቡን በአብሮነት አጋምደውና በልማት አበልፅገው ረዘም ያለ ዕድሜ እንዲኖራቸው ከስያሜ ጀምሮ የብዙዎችን ፍላጎት ያማከለና ማንንም የማያስከፋ መንገድ መከተል ይገባል።

ለምሳሌ አንዱ ክልል ሸዋ ተብሎ ይጠራል የሚል ወሬ ይሰማል። እንደ እኔ ይህ ሸዋ የሚለው ስያሜ ያካትታቸዋል ተብለው የቀረቡት ጉራጌ፣ ሀድያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ሀላባና የም ዞን ሕዝቦችን ነው። እነዚህ ሕዝቦች በጥንታዊ የሀድያ ሡልጣኔት በጋራ ለዘመናት የኖሩ ሸዋ የሚለውን ስያሜ አንዴ በሸዋ ክፍለ አገር በጋራ የሚጋሩ፣ አዲስ አበባን ጭምር ሸዋ ብለው የሚጠሩና ሸዋነት የማንነታቸው አንዱ ክፋይ የሆነ በዕምነት፣ ባህል፣ በሥራ ባህል፣ በደምና በአኗኗር ዘይቤ የሚገናኙ በገበያ፣ በክፉና በደግ የሚገናኙ በመሆኑ ለእኔ ለኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ሞዴልና ለበርካታ የመሀል አገር ሕዝቦች አስተሳሳሪ ድንቅ ክልል እንደሚመሠርቱ ይታየኛል።

አካባቢው እጅግ ሥራ ወዳድ፣ በበርካታ የአገራችንና የውጭ አገሮች ተሰማርተው በሚሠሩ፣ አገር የሚያለሙ ሕዝቦች መፍለቂያና ከአዲስ አበባ አርባ ምንጭ፣ ከአዲስ አበባ ጂማ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ አዳማ፣ ሐዋሳ ዋና ዋና የአገራችን የፈጣንና የአስፋልት መንገዶች በአማካይ መሀከል ይዞ የሚገኝ ምሥራቅና ምዕራብ ኦሮሚያን የሚያገናኝ እጅግ ተመራጭና ምቹ  ጂኦ ፖለቲካዊ ቦታን የያዘ በመሆኑ ለንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪና ለቱሪዝም ተመራጭ የመሆን ዕምቅ አቅም ያለው በመሆኑ በአጭር ጊዜ የመበልፀግ ዕድል እንዳለው እንዲሁ በዓይነ ህሊናዬ ይታየኛል።

 ውድ የዚህ አካባቢ ሕዝቦች ነገን ለልጆቻችን እንዲመች አድርጎ መገንባት (Construct) ማድረግ በእኛ እጅ ያለ ነው። ከዚህ በፊት በነበረው አገራዊም ሆነ ክልላዊ አደረጃጀት መሄድ አስቸጋሪ እንደሚሆን አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ፣ በሕዝቦቻችን መካከል ያለው መጠራጠር፣ ግድያና መፈናቀል ህያው ምስክር መሰለኝ። በመሆኑም ነገን አስቦ ረጋ ብሎ መወሰን  ተገቢ ነው። ከዚህ ቀደም የቀረቡና በይደር ቆይተው ወደ አዲሶቹ ክልሎች የተሻገሩ የዞንና የወረዳ መዋቅር፣ እንዲሁም ሎሎች የአደረጃጀትና የሕዝብ የልማት ጥያቄዎች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህን ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱና በወቅቱ ተፈጻሚ በነበሩ የደቡብ ክልል ሕጎች መሠረት ብቻ ተገቢውን ምላሽ ሰጥቶ መቋጨትና ወደፊት የሚቀርቡ መሰል የሕዝብ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ የሚረዳ የክልል ሕግ ማውጣት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ቢሆን ጥሩ ነው። ጊዜ ተወስዶ በማስተዋል የሚሠሩ ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ስላሉ የወደፊቱ ጉዞ የአመራሩን ብስለት፣ የሕዝቡን አጋርነት፣ ትዕግሥት፣ የማዕከላዊ መንግሥትን ክትትልና ድጋፍ ይጠይቃል። 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ረዳት ፕሮፌሰርና በትምህርት ክፍሉ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም አስተባባሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን::

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...