በበቀለ ሹሜ
በሕወሓት አምልኮና ውስወሳ ውስጥ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ የትግራይ ወጣቶች ሕወሓት ምናችሁ ነው?
ከእነ መለስ ተክሌ ታናናሾች አንዱ ሆኜ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩንቨርሲቲ ውስጥ የነበርኩ፣ እነ መለስ ተክሌ ካለፉ በኋላ በረሃ ባልገባም ከተሃሕት/ሕወሓት ሰዎች ጋር አብሬ የኖርኩ፣ የትግል ድምፃቸውን እስከ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ድረስ የተከታተልኩ፣ ከዚያ ወዲያም በነበረው ገዥነታቸው ውስጥ ተቀንብሬ በዓይን ምስክርነት ዛሬ ድረስ የቆየሁ ሸበቶ ነኝና እኔ ልንገራችሁ፡፡
1) ሕወሓት የአያቶቻችሁንና የወላጆቻችሁን የትግል መዋጮ (የሕይወት መስዋዕትነታቸውን፣ ጉርሳቸውን፣ ፍቅራቸውን፣ ተስፋቸውን፣ ብሶታቸውን፣ አመኔታቸውንና አይዞህ ባይነታቸውን) እየተመገበ ያደገና ለ1983 ዓ.ም. ድል የበቃ፣ ግን ያን ሁሉ ተጋድሎ ረግጦ፣ የትግራይንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች ጉጉት አፈር ድሜ አብልቶ፣ በአዲስ ሥርዓት ስም ተጋዳላዮችን የሌላ የአፈና ሥርዓት መሣሪያ አድርጎ በኢትዮጵያ ላይ የዘረጋ፣ በዚህም አድራጎቱ የትግራይ ልጅነት ከእሱ ቅሬታ አፍላቂ ገዥነት ጋር ተዛምዶ እንዲታይ (የትግራይ ሕዝብ ከቡድኑ ጋር አብሮ የተጠቀመ ያስመሰለ ሥዕል እንዲፈጠር) ያደረገና ክፍልፋይ አስተሳሰብንና ወገናዊነትን ባባዛ አመለካከቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን መተሳሰብ የጎዳ አደራ በላ ነው፡፡
2) በ1990ዎች መጀመርያ ላይ፣ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ወታደራዊ ግጭት ውስጥ በገባበት ጊዜና ከዚያ ቀውስ ጋር ተያይዞ ሕወሓት ድርጅታዊ መሰንጠቅ በደረሰበት ጊዜ፣ በ1997 ዓ.ም. ብሩህ የምርጫ ዓመትም እንዲሁ፣ ከአፈና አዙሪት በወጣ የዕርቅና የለውጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር የመግባባት ዕድሎችን ታሪክ ደቅኖለት ነበር፡፡ እነሱንም አልተጠቀመባቸውም፡፡ የ2010 ዓ.ም. መጋቢት ለውጥ ከራሱ ከኢሕአዴግ ውስጥ ብቅ ባለ ጊዜም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ይቅርታ አክብሮ በአዲስ የለውጥ ስሜት የትግራይንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች የመካስ ዕድል ተደቅኖለት ነበር፡፡ ለፀፀት አልበገር ብሎ ያንንም ዕድል የረገጠ ቡድን ነው፡፡
3) ከዚያስ? የፀፀት፣ የይቅርታና ሕዝብን የመካስ አንጀት የሌላቸው የቡድኑ መሪዎች ትግራይን መሰባሰቢያ ማዕከል አድርገው ምን አደረጉ? ትግራይን የሌላ ጦርነት ማደራጃ ምሽግ፣ የትግራይን ሕዝብ ጉርስ የሌላ ጦርነት መዘጋጃ ስንቅ፣ የትግራይን ወጣት የሌላ ጦርነት ጥይታቸው የማድረግ ሥራ ውስጥ ገቡ፡፡ መታረምን በሸሸ በዚህ የጥፋት ጉዟቸውም፣ የወታደራዊና የደኅንነት አቅም ያልነበረውን የዓብይ መንግሥት በሕወሓትና በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥላቻና ጥቃት የከፈተ አስመስለው እያጭበረበሩ፣ የራያና የወልቃይት ሕዝብ ልብ መሸፈትም ከሕወሓታዊ የድፍጠጣ አገዛዝ የመጣ መሆኑን ደብቀው፣ የራሳቸውን ጥፋት በአማራ ሕዝብ ላይ እየላከኩ፣ ‹‹በትግራይ ሕዝብ ላይ ማግለልና ከበባ እየተካሄደ ነው›› በሚል ውስወሳ የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ተነጥሎ የበቀል ጓዳቸው እንዲሆን ሠሩ፡፡
3) በዚህ ውስወሳቸው አማካይነትም እነ መለስ ተክሌ፣ እነ ግደይ ገብረ ዋህድና ከበረሃ ትግል አንስቶ እስከ ድል ድረስ እንደ ገብረ መስቀል ኃይሉ ያሉ ተጋዳላዮች ጠባብ ጥቅም ሳይሰነክላቸውና ሳይደላቸው የተዋደቁላትን ኢትዮጵያን ለመበጫጨቅ ተነሱ፡፡ በዚህም የክህደት ተቀዳሚ ዕርምጃቸው፣ በትግራይ ውስጥ ቤት ንብረት እስከ መመሥረት የዘለቀ ትስስር የነበረውንና ቤተሰቡን ለመጦር እንደደረሰ ልጅ የትግራይን ሕዝብ በታማኝነት ሲያገለገል የቆየውን የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ከውስጥ ባስከዷቸው ደመኞቻቸው አማካይነትና በውስውሳ ካቴና ህሊናቸውን በሰለቧቸው ልዩ ኃይሎች አማካይነት ከመሣሪያ ነጥሎ የመፍጀትና ከሥራ ውጪ አድርጎ የመበተን ግፍ ፈጸሙ፡፡
4) ከፍጀትና ከክህደት ወጥመድ እየተታኮሰ ያመለጠው የሰሜን ዕዝ ተራፊዎች፣ ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በደረሱ ኃይሎችና በኤርትራ ታግዘው፣ ለደረሰባቸው ጅምላ ጥቃት ጅምላ በቀል በመውሰድ ነውር ሳያብዱ፣ በ15 ቀናት ውስጥ በድል መቀሌ በገቡ ጊዜም የሕወሓት ጦረኞች የትግራይ ሕዝብ ኧረ አሁንስ ከመከራ ይተንፍስ አላሉም፡፡ ብዙ ሺሕ ደረቅ ወንጀለኞችን ከወህኒ ለቀውና ከሞላ ጎደል የራሳቸው ካድሬዎች የተቆጣጠሩትን የጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር ማሻጠሪያ በማድረግ፣ (የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደራዊ የደንብ ልብስን የለበሱ ሸሮች በመሥራት ጭምር) በሰላም ሠርቶ መግባት እስኪያቅት ድረስ የትግራይን ሕዝብ ጉስቁልናና ብሶት እያበራከቱና የሕዝብ ቁጣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ እንዲፈላ እያደረጉ (የትግራይን ሕዝብ መከራ እየቸረቸሩ) ቀጣፊ የፖለቲላ ትርፍ ነገዱ፡፡ ይህም ንግዳቸው፣ የትግራይን ሕዝብ በእልህ አንቃቅቶ ለሌላ ጦርነት በማገዶነት የማሠለፍ ሌላ ግፍ ነበር፡፡
5) እንደፈለጉትም የበቀል ቁጣን በሸር አፍልተው የመከላከያ ሠራዊትን አስበተበቱ፣ የመከላከያ ሠራዊትም እየተበተበተና ሕዝብን ከመፍጀት እየሸሸ ከትግራይ ወጣ፡፡ ከወጣም በኋላ የትግራይ ሕዝብ ይህችን ክረምት አርሶ ይጉረስ እንኳ አላሉም፡፡ ታደጊዎችን ጭምር ባልተሟላ መሣሪያና ሥልጠና እያንጋፈፉና የትግራይን የሙያ ሰዎች የማሽኖች ነቀላና የዘረፋ ኃይል አድርገው ወደ አማራና ወደ አፋር ‹‹ክልሎች›› አዘመቱ፡፡ በዚህም ዘመቻ ተደራራቢ ወንጀል ፈጸሙ፣ አስፈጸሙ፡፡
ለጦርነታቸው ማገዶ ያደረጉት የትግራይ ሰውና ታዳጊ በንፁኃን የአፋርና የአማራ ሲቪሎችና ሲቪል ተቋማት ላይ በነውረኛ ስድብ የቀለመ፣ ኢሰብዓዊና ጨካኝ ጥቃት እንዲፈጽምና ቤተ እምነቶች እንዲደፍር አደረጉ፡፡
አዲስ አበባ ድረስ ገብተው በቀል ለመወጣት (ከተመቸ ኢትዮጵያን ወደ ትንንሽ አገር ቆራርሰው በኮንፌዴራላዊ ሥልት ከኢትዮጵያ ሊያገኙ የሚችሉትን ለመጋጥ ካልሆነም ኢትዮጵያን እንዳትገጣጠም አድርጎ ለማባላት) ሲሉ፣ ከትግራይ ሕዝብ በገፍ ያፈሷቸውን የተዋጊ ማገዶዎች (ወደ ምዕራብም፣ ወደ ምሥራቅም፣ ወደ ደቡብና ሰሜን ሸዋ ዘልቆ አዲስ አበባን እስከ ማማተር ድረስ) በሰፊና በረዥም ርቀት ረጭተው በአፀፋ መልሶ ማጥቃት ከባድ ዕልቂት እንዲደርስባቸው አደረጉ፡፡
እየዘረፉ፣ እያወደሙና እየረገፉ በመሸሽ ሒደትም ውስጥ፣ ከበፊቱ በተጨማሪ ሌላ የርሸና ወንጀል እንዲፈጸም በማድረግም የአፋርና የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ቁጭት በቁጭት ነደው ወደ ትግራይ በመግባት የትየለሌ የግፍ ብቀላ እንዲፈጽሙ (ሕዝብ ከሕዝብ እስከ መጨረሻው እንዲቆራረጥላቸው) አባበሉ፡፡ የትግራይ ጦረኞች የተረፈው ተርፎ ወደ ትግራይ ወሰን የገባውን ትራፊ ኃይል ዕረፍት እንኳ አልሰጡትም፡፡ እንደገና እየተወረወሩ አፋርና አማራ ላይ አስከፊ ጥፋት በመፈጸም ጅምላ ጥቃትና ጭፍጭፋ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲመጣ መለማመኛ አደረጉት፡፡
ለምን? ስለምንስ ከጅምር እስካሁን ድረስ ‹‹በትግራይ ሕዝብ ላይ ዘር የማጥፋት ግፍ ተፈጸመ›› የሚል ውንጀላንና ዋይታን ሙጭጭ ብለው ያዙ? የትግራይ ሕዝብና ወጣት ልብ ብለህ አጢን፡፡
በተመድና ተያያዥነት ባላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት አካባቢ፣ እንዲሁም የዓለም አገሮች ጉዳዮች ‹‹ፍትሐዊ›› መስተንግዶ እንዲያገኙ ማድረግ ኃላፊነታችን ነው በሚሉ ምዕራባዊ ኃያላን አገሮች አካባቢ፣ ቅኝ ተገዛሁ ያለና አዎ ተገዝቷል ያሉት ሕዝብ ከቅኝ ገዥው የመለየት መብት የታወቀ ነገር ሆኗል፡፡ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የተካሄደበት ሕዝብም ከጭፍጨፋ አደጋ መገላገልን ከመነጠል ጋር አያይዞ ሲንቀሳቀስ፣ ጥያቄውን ተገቢ አድርጎ የመደገፍና በሕግ አግባብ የማስተናገድ ዝንባሌ አለ፡፡ አንድ አገር እየተቆራረሰች ደም መፋሰስ ውስጥ ከገባች ወዲያም፣ የሆነ ጉማጅ ላይ በርዝራዥነት የተረፈ መንግሥት ቁርስራሾችን ገጣጥሜ የአገር አንድነት እመልሳለሁ ቢልም ቀላል አይሆንለትም፡፡ ተነጥሎ ለመቆየት በሕዝብ ድምፅ የወሰኑ ቁራሾች ዕውቅና የማግኘት ተስፋ አላቸው (ለተመድ አመልክተውም ሆነ ደጋፊዬ ያሉትን የሌላ አገር ጦር በመከታነት አሥፍረው)፡፡ የዛሬዎቹ የሕወሓት ጦረኞች ይህንን ያውቃሉ፡፡ በዚህም በዚያ ብለው የትግራይን ሕዝብ በማኅበረሰብ ጥላቻና በበቀል አውረው የእርስ በርስ ፍጅት ውስጥ እንዲገባ፣ ደመኛ የተባለ ሕዝብን በግፍ አንጨርጭረው ግዙፍ የጅምላ ጭፍጨፋ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲያወርድ ግብዣ ሲያደርጉ የነበሩት፣ የኢትዮጵያ ቀሪ ሕዝብና የትግራይ ሕዝብ ዳግም አብሮ እንዳይኗኗር ለማድረግ በጨካኝ ሸሮች ሸለቆ የመፍጠር ሥራ የሠሩት፣ ከዚህ ሁሉ ጋር በየትኛውም ዘግናኝ መጨራረስ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ለመበታተን ሲለፉ የቆዩት፣ በትግራይ ሕዝብ እንዲፈጸም የፈለጉት ጅምላ ጭፍጨፋ አልሳካ ቢላቸውም ‹‹ዘር የማጥፋት ግፍ በትግራይነት ላይ ተፈጸመ›› የሚል በሐሳዊ መረጃ የተቀናበረ ልቦ ወለድ የሙጥኝ ይዘው የሚጮሁት ለአንድ የበቀል ዓላማ ነበር፡፡ ቢሆን ትግራይን ቆርጦ ለመንገሥ፣ ይህ ቢቀር እንኳ ኢትዮጵያን አፍርሰው ገሃነም ካደረጉ ለእነሱ አንጀታቸው ቅቤ ይጠጣል፡፡
አንድ ቁራሽ አገር፣ ራሱንና ሰላሙን አስከብሮ ለመልማት ምን ያህል አቅም ይኖረዋል? ብሎ ማሰብ ለእነሱ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ቁርስራሽ አገርነት በአፍሪካ፣ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ዓውድ ውስጥ የትልልቅ ጎረቤቶችና የኃያላን ጥቅምና ጦር መሯሯጫ ከመሆን በቀር፣ እንደ እነ ስዊዘርላንድ የልማት ሙሽራ የመሆን ዕድል የለም፡፡ ለምናልባቱ እንኳ የትግራይ ሕዝብ እንዲሞክር በሰላም የመተው ዕድል እንኳ በሕወሓት ጦረኝነት ዘንድ የለም፡፡ በእነሱ ጦረኝነት ዘንድ አገር ከመቁረስ በመለስ የሆነ ሰላም ላይ በድርድር የመድረስም ዓላማ የለም፡፡ ሳይወዱ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ቢቆዩም በትግራይ ሕዝብ ደም እየዋኙ ከኢትዮጵያም ከኤርትራም ጋር መሬት አለኝ የሚል ጦርነት ለማካሄድ የቆረጡ ናቸው፡፡ ይህ ሳይሟላ ኢትዮጵያ በተበተነችበትም ሆነ ባልተበተነችበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ ቢለዩም የመሬት ቅርምት ውጊያቸውን ከብዙ አቅጣጫ ከመቀጠል አይመለሱም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከእነሱ ጋር ያለው ዕጣ የእነሱ ጦረኝነት ስንቅና ማገዶ መሆን ነው፡፡ ከሕወሓት ውጪ ያሉና ተቃዋሚ የሚመስሉት ‹‹ባይቶና፣ ሳልሳዊ…›› ወዘተ የሚባሉት (መሬት ላፍ አድርጎ ቁራሽ አገር ለመሆን የሚሮጡት ቡድኖች ሁሉ) ያው ጦረኝነትን ያዘሉ ናቸው፡፡ የመሬት ቅርምቱ በአንዱ መንገድ ባይሳካ በሌላው መንገድ ለማሳካት የተፈጠሩ፣ በሕወሓት የጦረኝነትና የበቀል ፖለቲካ ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው፡፡ በሕወሓትም በእነሱም በኩል ከጦርነት እሳት ዕፎይ ብሎ የመልማት ዕድል የለም፡፡
በነፃነት ከመተንፈስ ጋር ልማትና የተሻሻለ ኑሮ ያለው በኢትዮጵያ ሰፊ አገር ውስጥ በመዋኘት ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የተያዘው አዝማሚያ የሚያሳየውም ይህንን ብርሃን ነው፡፡ ከሕወሓት በፊት በነበሩ አስተዳደሮች ውስጥ የጠቅላይ ግዛቶች/የክፍለ አገሮች ካርታዎች ተነካክተው ነበር፡፡ በሕወሓቶች ጊዜም የኢትዮጵያ ካርታ ተነካክቷል፡፡ በነገዋ ኢትዮጵያም ውስጥ የመላ ሕዝቦችን ዕርቅ፣ መተሳሰብና መግባባትን መሠረት ያደረገ የካርታ መነካካት የማይቻል አይደለም፣ ይቻላል፡፡ ጥላቻና በቀልን፣ ድህነትንም ሆነ የየትኛውን ሕዝብ ጉዳት ታቅፎ መኖር የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥቅምም ዓላማም አይደለም፡፡ የየትኞቹም ሕዝቦች ጥቅም ሳይጎሳቆል የሚፋፋው ዝምድናን አውቆ ከማክበርና ከመተሳሰብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሥር የሰደደ ዝምድናን ለመረዳት መጽሐፍ ማፈላለግ አያሻንም፡፡ ከአክሱም ዘመን እስካሁን ድረስ ሕዝቦች በሥጋና በባህል ምን ከምን እየሆኑ ሲወጠወጡ እንደኖሩ ማስተዋል ብቻ በቂ ነው፡፡
እናም የትግራይ ወጣቶች የሕወሓታዊያን ደም አቃቢ ፖለቲካ ምርኮኛ ከመሆን ነፃ ውጡ! ሕይወታችሁን ለጦርነት መገበርን በቃን በሉ! የትግራይ ወጣት ልሂቃን ለታዳጊዎቹ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ድምፅ ሁኑ!! የትግራይ እናቶችና አባቶች የጉማሬ ቆዳ የመሰለ የፊት ቆዳ፣ አመድ የነዛበት ክሳታቸው፣ የታጠፈ አንጀታቸው፣ የታፈነ አንደበታቸው የሚጮኸው ‹‹የሰላም ያለህ! ከመከራና ከስደት የገላገለ የክብረኛ ኑሮ ያለህ!›› እያለ ነው፡፡ ይህንን የሰቆቃ ድምፁን አስተጋቡ! እያስተጋባችሁም ከአባቶች ከእናቶች ጋር በኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ጉባዔ ውስጥ ትግራይን ለመፈየድ ተንቀሳቃሱ!!!
ጦረኞችን ድል የመታ የልማት፣ የፍትሕና የነፃነት ሕይወት ለሁላችን!!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡