Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ የግብፅን ብቻ ሳይሆን ከዚያ ባሻገር ያሉ አገሮችን ጫና የምትቋቋመው የማይቋረጥ የኃይል መሠረተ ልማት ሲኖራት ነው›› ሳሙኤል ተፈራ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ምርምር ማዕከል ተመራማሪ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፣ በጃፓን ኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በአፍሪካና በእስያ ጥናት ትምህርት ክፍል አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ የጂኦ ፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ በቀይ ባህር ፖለቲካ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ እንዲሁም በአፍሪካ አኅጉር አጠቃላይ የፖለቲካ ምኅዳር ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ መድረኮች በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎቸን በማቅረብ የሚታወቁት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የወቅቱን የፖለቲካ ግለት አስመልክቶ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡ በኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት በፊት ለውጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ለውጥ በፊትና ለውጥ ተደረገ ከተባለበት ጊዜ ወዲህ ያለውን የኢትዮጵያና የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሒደት እንዴት ይገልጹታል?

/ ሳሙኤል፡ አገሮች ከተለያዩ አገሮች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት በእያንዳንዱ አገር ብሔራዊ ጥቅም ምክንያት በአዎንታዊ ወይም በአሉታዊ ተፅዕኖ ውስጥ ይወድቃል፡፡ የጂኦ ፖለቲካዊ ዕሳቤ ከጂኦ ኢኮኖሚያዊ ጽንሰ ሐሳብ የሚቀዳ ነው፡፡ ይህ ማለት የሆነ ቀጣና ውስጥ የሚነሳ ፍላጎት በዚያ አካባቢ ከሚገኙ አገሮች፣ የሕዝባቸውንና የሀብታቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ ምን ጥቅም አገኛለሁ ብለው የሚገቡበት ነው፡፡ ለምሳሌ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ኢራንንና ቱርክ የመሳሰሉት አገሮች በእኛ ቀጣና ላይ ያላቸውን እንቅስቃሴ ሲታይ ቀጣናው ብዙ የካፒታል ኢንቨስትመንት ያለበት ሲሆን፣ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ወሳኝ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህም በደኅንነት፣ በወታደራዊ፣ በኢንቨስትመንትም ሆነ በሌላም በብዙ መልኩ ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡ ያ ማለት ዝም ብሎ የሚደረግ ነገር አይደለም፡፡ አገሮች ብሔራዊ የኢኮኖሚና የደኅንነት ፍላጎታቸውን ሊያሳካ ይችላል የሚሉት አጋጣሚና ሥርዓት ሲገኝ ነው ኢንቨስትመንቱ ላይ የሚያደሉት፡፡ አንዳንድ አገሮች በሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማቸው ሶሻሊዝም ይሁን ካፒታሊዝም በዚያ አካባቢ ያለው ፍላጎት ማጠንጠኛ መሠረቱ ምንድነው? ወደ ቀጣናው መግቢያ የሚሆነን የመንግሥት አወቃቀሩ ነው? ባህል ነው? በታሪክ ያለን ግንኙነት ነው? ወይስ ደግሞ እየታዩ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ምንድናቸው የሚሉ ጉዳዮችን በማጤን ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁነኛ መሠረት ይጥላሉ፡፡ እንደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙና እንደምትመሠርተው የኢንቨስትመንት ግንኙነት መጠን ደግሞ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ ማለት የነበረውን ሙሉ ለሙሉ የሚያጠፋና የሚሸረሽር፣ ወይም ያለውን አጠንክሮ የሚሄድ ሊሆን ይችላል፡፡

ለምሳሌ በኢትዮጵያ ለውጥ መጣ ከተባለበት ጊዜ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህና በቀደመው ጊዜ ያለውን ሁኔታ ስትመለከት፣ ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ በቀጣናው ከፍተኛ የሆነ የፀረ ሽብር ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የትግሉ ደጋፊ አገር ተደርጋ በምዕራቡ ዓለም ትታይ ነበረ፡፡ በተለይ ደግሞ ሽብርተኝነት የዓለም ሥጋት ስለነበረና ብዙዎቹ የምዕራባውያን አገሮች የዚህ ተጠቂ ስለነበሩ፣ በዚያ ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ የሚባል ነበር፡፡ ብዙ ድጋፍም ተገኝቶበት ነበር፡፡ በዚያ የፀረ ሽብር ትግል ከምዕራባውያን ጋር በተፈጠረ ግንኙነት ኢትዮጵያ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነ ሚና ነበራት፡፡ የሰላም ማስከበርን ሚና ጨምሮ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ታሪክ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ በተለይም ንጉሡ በነበራቸው የጋራ ደኅንነት (Collective Security) አቋም ላይ የማያወላውል አቋምና መርህ ላይ የተመረኮዘ ነበር፡፡ በዓለም ሰላም እንዲሰፍን የምናደርገው ጥረት ከዚያ ዘመን ጀምሮ የቆየ ነው፡፡ በዚያ ምክንያት በአካባቢው ያሉ በተለይ ደግሞ አንዳንድ ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ የሚባሉ መንግሥታትን ተፅዕኖ ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግሥትን እንደ አጋር አድርጎ ይዞ መሄድ አዋጭ ስለነበር፣ በወቅቱ ምሥራቁንም ጨምሮ በተለይ በኢንዶኔዥያ ከተደረገው የባንዱንግ ኮንፈረንስ በኋላ ጣልቃ ገብነት የሌለበት መርህን ተጠቅመዋል፡፡ በውስጥ የፖለቲካ መስመር ሳይገቡ ነገር ግን የኢኮኖሚ ዕርዳታ በመስጠት፣ እነሱም ይጠቅመናል ብለው ባሰቡት ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ በዚያኛው ጎን ደግሞ ኢትዮጵያ የምሥራቁንም ኃይል በመያዝ የሁለቱንም ወገን አቻችላ የምትሄድ አገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ያ ማለት ግን ፍፁም የሆነ ፍቅር ስለነበረ አይደለም፡፡ በአገሮች መካከል ባለ ግንኙነት ውስጥ ምንጊዜም የፖለቲካ ጥቅም ይቀድማል፡፡

ስለዚህ ቢያንስ ሁለቱንም አጣጥሞ የመሄድ ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ ችግርና መሰናክል ሳይኖር፣ ቀርቶ ሳይሆን የሁለቱንም ፍላጎት አጣጥሞ ከመሄድና የነጮቹን ፍላጎት ከማስጠበቅ አንፃር ኢትዮጵያ ያላት ሚና ትልቅ ነው ብሎ በማሰብ ስለነበር፣ በዘመኑ ኢትዮጵያንም በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ሳይጎዳ ብድርም ሌሎች ድጋፎችን እያገኘች በተቻለ መጠን በአንፃራዊነት የሰላም ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ሁኔታ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የዓለም ሁኔታ በጣም ተቀይሯል፡፡ በተለይ ደግሞ የአሁኑ መንግሥት ከመጣ በኋላ በኢትዮጵያ ያለው የውስጥ ፖለቲካ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ የትልቁ የፖለቲካ ፓርቲ ወሳኝ አጋር ይባሉ የነበሩት ፓርቲዎች ወደ ዋናው ፓርቲ እንደ አዲስ ተዋቅረውና ገብተው በፓርቲው ውስጥ እኩል የመምረጥና የመመረጥ ዕድል እንዲኖራቸው ሁኔታው ፈጥሯል፡፡ በእርግጥ ጉዳዩ በአንዴ የተፈጠረና የመጣ አይደለም፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ እንዲህ ዓይነት የመወሀድ ውይይቶች ተደርገው ነበር፡፡ በይደር ተቀምጠው የቆዩ ቢሆንም፣ ነገር ግን አሁን የመጣው ሥርዓት ኢሕአዴግን አፈራርሶ ብልፅግና ብሎ በአዲስ ስያሜና አደረጃጀት ከመጣ በኋላ በተፈጠረ ስምምነት አለመኖር ልዩነቱ ልዩነቱ እያደገ ሄዶ ግጭት መፍጠሩ ይታወሳል፡፡ የትግራይ ክልል ከፌደራል መንግሥቱ ተነጥሎ የራሱን ምርጫ እስከማድረግ አድርሶታል፡፡

ይህም ግጭት እንዲፈጠርና ውስጣዊ አለመረጋጋትና ዘር ተኮር ጥቃት እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በተለይም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሳሰሉ ቀጣናዊ ቅርፅ ያላቸውና የቀጣናውን የኃይል ሚዛን ሊለውጡ በሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ኢትዮጵያ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለማጨናገፍ ለሚሠሩ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረስ የሚከነክናቸው የውጭ ኃይሎች በጊዜ ሒደት የጨዋታ ቀያሪ ሆኖ እያደገ የመጣውን ፕሮጀክት በተፋሰሱ አገሮች ውስጥ ሊፈጥር የሚችላቸውን ዕድሎች እንደ ሥጋት የሚያዩና የኢትዮጵያን ፍላጎት የማይደግፉ ኃይሎች፣ መሣሪያ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ኃይሎችን በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት በማድረግ የልማት ውጥናችን እንዲጨናገፍ ዕገዛ እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗል፡፡

ስለዚህ ይህ ከግጭቱ ባለፈ የፈጠረው ጫና ከሱዳን ጋር በምንዋሰነው ድንበር ሳይቀር አለመረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ፣ መንግሥት ተረጋግቶ የዕለት ተዕለት ሥራውን መሥራት እንዳይችል ብዙ ጫናዎችን ፈጥሯል፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፡፡ በጠላትነት ሲፈረጁ የነበሩ እንደ ሶማሊያና ኤርትራ የመሰሳሉ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን ወደ ሰላም ጎዳና መምጣታቸውና የትብብር ጥምረት መፍጠራቸው ጥሩ ነው ተብሎ እየተነገረ ባለበት ወቅት፣ የተስፋው ጭላንጭል ብዙም ርቀት ሳይጓዝ በአገሮቹ መካከል ግንኙነቶች የመቀዛቀዝና ከዚያም ባለፈ መቃቃር መፈጠር ቀጣናውን መልሶ ወደ አለመረጋጋት ሥጋት ውስጥ አስገብቶታል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በቅርቡ ሶማሊያ ውስጥ በተደረገው ምርጫ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ (ፎርማጆ) መንግሥት መንበረ ሥልጣኑ በሀሰን ሼክ መንግሥት በመተካቱ ምክንያት ነው፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ቀድሞ ኢትዮጵያን ያስተዳድር ከነበረውና በሕወሓት ከሚመራው የኢሕአዴግ ሥርዓት ጋር በፀረ ሽብር ትግሉ ውስጥ ቁልፍ አጋር የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ የእሳቸው መምጣት የሦስቱን አገሮች ጥምረት የሚያኮላሹ አካሄዶችን ይዞ መጥቷል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ከሰውየው ጋር ያለውን ጥብቅ ግንኙነት ለተገነዘበ፣ አሜሪካና የምዕራቡን ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ተፅዕኖ ከፍተኛነት ለተረዳ፣ በሰሜኑ ጦርነት ውስጥ ኢትዮጵያ ከሰብዓዊ ዕርዳታና መሰል ጉዳዮች በመነጨ ስታራምድ የነበረውን አቋም ላስታወሰ፣ ከሰሞኑ አጋሮቿ ሚዛናዊ ያልሆነ ለግብፅና ለሱዳን ያደላ አቋም ማንፀባረቅ ተደምሮበት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለመጉዳት ሊሄዱ የሚችሉትን ርቀት መተንበይ አይክብድም፡፡

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውንና መሪዎቻቸው የሚሰጧቸውን አስተያየቶች ስንመለከት፣ እነሱና በአካባቢያችን ያሉ አጋሮቻቸው በተለይም ግብፅ ከጎረቤቶቻችን ጋር እያደረገችው ያለችው የወታደራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የደኅንነት ትብብሮች ስንተነትንና በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ አልሸባብ ያደረግውን ጥቃት ጨምሮ አለመረጋጋት የበለጠ በቀጣናችን እንዲሰፍንና የፀጥታ ሥጋቶች እንዳያገረሹ መሆኑን እንረዳለን፡፡ የአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሥልጣን መቆናጠጥም ትርፉ ለኢትዮጵያ ምን ሊሆን እንደሚችል በግልጽ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ይህ ደግሞ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ የጉብኝታቸው አለመሳካትና ግብፅ ሄደው ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር በዓባይ ጉዳይ ላይ ያደረጓቸውን ንግግሮችና በግድቡ ላይ አሳሪ ስምምነት መደረግ አለበት የሚል መግለጫ እስከ ማውጣት ጭምር የደረሱበትን ፍጥነትና ድፍረት ስናይ፣ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዙሪያዋ ካሉ አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት ቀላል የማይባል ጥልፍልፍ ውስጥ እንዳስገባት እንረዳለን፡፡

ሪፖርተር ኢትዮጵያ ከቀጣናው አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት እየተበላሸ ነው ማለት ይቻላል?

/ ሳሙኤል፡ እሱ ብቻ አይደለም፡፡ የግብፅን እንቅስቃሴ ካየህ በቅርቡ ወደ ኬንያ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር የደኅንነትና የወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ኬንያ በአንፃራዊነት ለኢትዮጵያ ሥጋት የምትላት አገር አይደለችም፡፡ ኬንያ በዓባይ ጉዳይ ላይ የተከፋፈለ ዓይነት ዕሳቤ ያላት አገር ናት፡፡ ነገር ግን ኬንያ ከዓባይ ግድብ ኃይል ማግኘት የምትሻ አገር ነች፡፡ ያንን የሚፈልግ የመንግሥት አካል አለ፡፡ በሌላ በኩል ከኦሞ ወንዝና ከቱርካና ሐይቅ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በጊቤና በኦሞ ወንዞች ላይ በምትሠራቸው ግድቦች ሳቢያ ውኃ እያጠረ የቱርካና ሐይቅ አካባቢ ነዋሪዎች፣ የኦሞ ተፋሰስ ማኅበረሰብ ሕይወት አደጋ ላይ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በአብዛኛው በሌሎች የውጭ ኃይሎች ድጋፍ ተቆርቋሪ ነን ከሚሉት አካላት የሚመጣን ግፊት ስታይ፣ በኬንያ መንግሥት በኩል ራሱ በዓባይ ግድብ ላይ የተከፋፈለ ዕይታ እንዲኖር ሳያደርግ አልቀረም ለማለት ያስገድዳል፡፡ ኬንያ የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፉን የፈረመች አገር ብትሆንም፣ ፓርላማው ስምምነቱን የአገሪቱ ሕግ አካል አድርጎ ማፅደቅ ግን ላይ በጠቀስኳቸው ጎታች የሆኑ ምክንያት እስካሁን ሳይችል ቀርቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ ጠላት እያፈራባት ነው ማለት ይቻላል?

/ ሳሙኤል፡- ግድቡ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ሊያጎላ የሚችል ፕሮጀክት ካለ፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረው ጫና እየጨመረ ነው የሚሄደው ማለት እንችላለን፡፡ በግድቡ ላይ ያሳየነው መረባረብና ከትብብር የመነጨ ኢትዮጵያዊ መንፈሰ ጠንካራነት፣ የኢትዮጵያን መልማት በማይፈልጉ ኃይሎች ዘንድ መሰባሰብን በመፍጠር ጠላትነትቸውን አጉልቶ አሳይቶናል፡፡ ለምሳሌ ያህል የዓረብ ሊግ አቋም ከድሮውም ግልጽ ነው፡፡ እነሱ ያላቸው አቋም ከአስዋን ግድብ መገንባት በኋላ ኢትዮጵያውያን በተለይም አፄ ኃይለ ሥላሴ ስለአፍሪካ መዋሀድና ስለፓን አፍሪካዊነት በሚናገሩ ጊዜ የግብፅ መሪዎች እነ ጋማ አብዱልናስር ዓባይን ፓን ዓረባዊ ገጽታ በማላበስ የዓረብ የውኃ ደኅንነት ጉዳይ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ አሁን በስፋት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ግብፅ በቀጣናው ኃያልነቷን ለማስቀጠል ከአስዋን መገንባትና በኋላ በኢኮኖሚና በወታደራዊ ዘርፎች ልማት ረጅም ርቀት ሄዳለች፡፡ የዓባይ ግድብ መገደብና ኃይል ማመንጨት ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ግሪድ በማስተሳሰር ለኢትዮጵያና በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ለሚኖሩ አገሮች የሚያመጣውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅም ስለሚረዱት፣ ይህ ዕውን እንዳይሆን የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም፡፡ ስለዚህ ይህን ግድብ ስትገነባ በተዘዋዋሪ ወደውም ሆነ በአስገዳጅነት የኃይል ፍላጎታቸውን ለማሟላት በኢትዮጵያ ላይ የሚንጠለጠሉ አገሮች ስለሚኖሩ፣ በምታዛቸውና በምታሰምርላቸው መስመር ነው የሚሄዱት፡፡ ይህ ማለት በጎ ጥገኝነት የሚፈጥር ጉዳይ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ግብፅ ይህ እንዲሆንና የኢትዮጵያ ትንሳዔ እንዲሳካ አትፈልግም፡፡ ነገ የዓባይ ግድብን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና ልማቷን ሊለውጥ የሚችል ፕሮጀክት ከመጣ በእርግጠኝነት ይህን መደገፍ አትፈልግም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የውኃ ጥያቄ አይደለም፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ዓባይን አትገድብም የሚለው ጥያቄ የግብፅን ኃያልነት የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡

እንግዲህ እንደ ቀጣና ስታየው በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች ግብፅን ጨምሮ በዙሪያችን ነው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያን ለማጥቃት ለሚፈልጉ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ የደኅንነት ሥጋቶች/ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ መውጣትን ማንሳት ትችላለህ፡፡ የመከላከያ ኃይል በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከድንበር አካባቢዎች እንዲንቀሳቀስ ሲደረግ የተፈጠሩትን ክፍተቶች በማየት፣ እንደ ሱዳን የድንበር ወረራና አልሸባብን ዓይነት ድርጅቶች ትልቅ የጥፋት ሴራ እንዲያሴሩ ዕድል ፈጥሯል፡፡ የዚህ እንቅስቃሴያቸው ማሳያ ደግሞ በቅርቡ የተመለከትነው የአልሸባብ ድንበር ጥሶ መግባት ነው፡፡ አልሸባብ ደፍሮት በማያውቅ ሁኔታ ለምን ገባ የሚለውን መጠየቅ አለብን፡፡ ዳር ድንበራችንን የመጠበቅ ጉዳይ የውስጥ ሰላም ከማጣታችን የሚያያዝ ሊሆን ይችላል፡፡ በየቦታው ያለው ውስጣዊ ችግር አገሪቱን ለሌላ ውጪያዊ የፀጥታ ችግር ተጋላጭነት ዳርጓታል ወይ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡፡

አልሸባብ በሙከራው አልተሳካለትም የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ ኢትዮጵያዊያን ይህንን መሰል ኃይሎችን የሚቀበልና የሚተባበር ማኅበራዊ ዕሳቤ እንደሌላቸው ግን ያሳየናል፡፡ ይህ አገርን ያስቀደመ ጠንካራ ሽብርተኝነትን የሚፀየፍ ማኅበራዊ እሴት ባይኖረን ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ አለብን፡፡ ቢሳካለት ኖሮ በቀላሉ የሽብር ማዘዣ ጣቢያና ታጣቂ የሚመለምልበትን ምቹ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈጥርበት ነበር፡፡ በእርግጥ አልሸባብና ሶማሊያ ውስጥ ያለው የአይኤስአይኤስ ቡድን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ጥሩ ግንኙነት የላቸውም ብሎ የሚያስባቸውን ኃይሎች በማሳተፍ፣ በመመልመልና የሚመለምለው ሰው ደግሞ ወታደራዊ ኃላፊነቶችን በመስጠት ተከታዮችን የማፍራት ሥራ ይሠራል፡፡ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ አማካይነት በሃይማኖት፣ እንዲሁም ንግድን በመሳሰሉ ሽፋኖች በመጠቀም አገር በቀል አሸባሪዎችን የመመልመል እንቅስቃሴዎች እያደረጉ እንደሆነ የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው የአልሸባብ የወታደር አባላት ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ፣ በተለይ ደግሞ አሁን አገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰላም መደፍረስ በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዳይፈጠር የሚያደርጉ አካላትን ባህሪ የተላበሱ ሰዎችን የኃላፊነት ቦታ በመስጠት ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ አልሸባብ እንደሚታወቀው አገር ለመምራት ወይም ለሌላ በጎ ተግባር አይደለም የሚንቀሳቀሰው፡፡ ፍላጎቱ ይልቁንም በሕገወጥ መንገድ ቢዝነስ ለመሥራትና ለዚህ የሚመች ጽንፈኛ የሆነ አስተሳሰብ በመፍጠር፣ ኢትዮጵያን የማተራመስ እኩይ ዓላማ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተርየኢትዮጵያ መንግሥት ምን ዓይነት መንገድ መከተል አለበት?

/ ሳሙኤል፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ጉዳዩ በመንግሥት ብቻ የሚፈታ ነው ብዬ አላስብም፡፡ በጣም ብዙ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ይህ ሲባል የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያሉ ጎረቤት አገሮችን በማሳተፍ መፍትሔ ለማምጣት ረዥም ርቀት መሄድ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ አንደኛው አሁን የሚታዩት ጥሩ ጅማሮዎች በተለይም ከምዕራባውያን ጋር የነበረውንና በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የታየው ጽንፍ የያዘ ግንኙነት ጋብ እንዲል የማድረግ ጥረቶችን ማጠናከርና ማፅናት ነው፡፡ በተለይ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የነበረውን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ የተሻሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በውጭ ጉዳይ በኩል ተነድፈው እየተሠሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያና አሜሪካ ረዥም ጊዜ ወዳጅ የነበሩ አገሮች ናቸው፡፡ በእርግጥ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ሆነ በኢሕአዴግ ወቅት መልካም የሚባል ግንኙነት ነው የነበረው፡፡

ስለዚህ ያንን ወደ ነበረበት የመመለስና የማስተካከል ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ይህ መልካም የሚባል ጅማሮ አሁን የተወሰኑ ማሳያዎች አሉት፡፡ ነገር ግን በዚያው ልክ ደግሞ ችግሮቻችን በጣም ጨምረዋል፡፡ ሶማሊያ ውስጥ አሁን ያለውን ችግር ማየት ትችላለህ፡፡ በእርግጥ ሥር የሰደደና ጭራሹኑ የለየለት የሚባል አይደለም፣ ሊስተካከል ይችላል፡፡ ነገር ግን በጊዜ ካልተጠገነ በጣም ትልልቅ ተግዳሮቶችን ሊያስከትሉ ይችላል፡፡ አልሸባብን ለመቆጣጠር ኢትዮጵያ ዋጋ ከፍላለች፡፡ ነገር ግን ሶማሊያም ሆነች ኢትዮጵያ የማይረጋጉ ከሆነ፣ አልሸባብ በቀላሉ መንቀሳቀስ የሚችልበት በር ይከፈትለታል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተርየቻይና፣ሩሲያና የአሜሪካ ሹማምንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት፣ እንዲሁም በቅርቡ የአልሸባብ ወታደሮችና ከፍተኛ ኃላፊዎቻቸው ጭምር በኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸው ለኢትዮጵያን ምን ዓይነት ፋይዳ ሊያመጣላት ይችላል?

/ ሳሙኤል፡ በአዎንታዊም በአሉታዊም ጎን ልታየው ትችላለህ፡፡ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ መምጣታቸው አሜሪካንና ምዕራባውያንን አያስደስትም፡፡ ሩሲያ ከአፄ ምንሊክ አስተዳደር ዘመን ጀምሮ ለኢትዮጵያ ጥሩ የምትባል ወዳጅ አገር ናት፡፡ አሁን ደግሞ ከአሜሪካና ከሌሎች ምዕራባውያን አገሮች ጋር ካላት ግንኙነት አንፃር ሩሲያ መርጣ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ በብዙ መንገድ ሊመነዘር ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ግንኙነቷን የማደሻ ስትራቴጂ ቀርፃ ከአሜሪካ ጋር ችግሮቿን ለመፍታት፣ ተፈጥሮ የነበረውን መቃቃር ለማረም በምትሠራበት ጊዜ ነው ሰርጌ ላቭሮቭ የኢትዮጵያ ጉብኘት ያደረጉት፡፡ ይህ የሚያሳየው ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር በተለይ ደግሞ ከጎበኟቸው አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ጥንካሬ ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌ ሩሲያ የዓባይ ግድብን በተመለከተ ጠንካራ የኢትዮጵያ ደጋፊ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ በሰሜኑ ጦርነትም ሆነ በፀጥታው ምክር ቤት በነበሩ ተከታይ ስብሰባዎች፣ ኢትዮጵያ የራሷን ችግር መፍታት ትችላለች በማለት ጠንካራ አቋም በማሳየት ታማኝ አጋር መሆኗን አሳይታለች፡፡

በዚያኛው አቅጣጫ አሜሪካኖች የሄዱበት መንገድ ምናልባት ስላልጣማቸው ይሆናል ጉብኝቱ የተደረገው፡፡ አሁን ይህ የሁለቱ አካላት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን መሀል ውስጥ የሚከት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባት ወደ የምትታወቅበት መርህን መሠረት ያደረገ፣ በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ፖሊሲ ጣልቃ የማይገባ፣ መቻቻልና ዓለም ሰላም እንድትሆን የጋራ ደኅንነት መኖር አለበት ወደ ሚል አቋሟ መመለስ ነው፡፡ አንድም ኢትዮጵያ የምትታወቀው የሰላም አስከባሪ ኃይል በመላክ ዓለም ሰላም እንዲሆን በምታደርገው ፖሊሲ ነው፡፡ ስለዚህ ያንን አካሄድ ማየትና አሁንም ወደ ነበረበት መስመር እንዲገባ መከለስ አለበት፡፡ በተለይ የአገሪቱን ጥቅም ሳያስነካ ከምዕራቡም ከምሥራቁ ዓለም ሁለቱንም ሳይጎዳ የነበረውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አጠናክረን መሄድ አለብን፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩሩ ጉዳዮች ላይ መሥራት አለባት፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ውስጥ የኢትዮጵያ ተቀባይነት ፈተና ውስጥ ሲገባ አይተናል፡፡ ስለዚህ መርህን ያማከለ አካሄድ መቀጠል አለበት፡፡ ሩሲያን ይዘህ አሜሪካ ወይም አሜካን ይዘህ ሩሲያን ጥለህ የምትሄድበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ኢትዮጵያ ጠንክራ የተጀመሩ እንደ ዓባይ ዓይነት ፕሮጀክቶችን በቶሎ መጨረስ መቻል አለባት፡፡

የግብፅ ጥያቄ እንዳልኩህ የውኃ አይደለም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ በቀጣናው ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ሆና እንዳትወጣ የመፈለግ ጉዳይ እንጂ፡፡ ግብፅና ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ረዥም ዓመታት ያስቆጠረ ግንኙነት ነው ያላቸው፡፡ ግብፅ ዓረብ ሊግን መቆጣጠር ችላለች፡፡ ይህን ማድረግ እንደምትችል ለአሜሪካ ስላሳየችና ስላሳመነች፣ አሜሪካ ከኢትዮጵያ የበለጠ ግብፅን ስትደግፍ በተለያዩ አጋሚዎች ታዝበናል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያም በዚህኛው ቀጣና የበለጠ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ዕድል የሚፈጥሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በቶሎ መጨረስ አለባት፡፡ ግድቡን በመጨረስና አገሮች የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ጥገኛ እንዲሆኑ ማድረግ አለባት፡፡ አገሮችን በኤሌክትሪክ በማስተሳሰር የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉና የሚበጠብጡ ኃይሎች እንዳይኖሩ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር መሠራት አለበት፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ዳግም የባህር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰጡ የመቀበልና የመደጋገፍ ዓይነት ኢንቨስትመንት ላይ አተኩሮ መሥራት ሲቻል ነው፣ ኃያል አገር መሆንና ተፅዕኖ መፍጠር የሚቻለው፡፡

ስለዚህ ለኢትዮጵያ ይህን ሊያሳካላት የሚችለውና አሁናዊ መፍትሔ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጨረስ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የግድቡ ግንባታ እንዳያልቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አገሮች ይህ እንዳይፈጠር በመፍራት ነው፡፡ በህዳሴ ግድቡ ላይ ታሪካዊ የሆነውን የውኃ መብታችንን ኢትዮጵያ ማክበር አለባት የሚለው ዕሳቤ ለድርድር የሚመጥንና የሚቀርብ አይደለም፡፡ ይህ ማለት እዚህ ምግብና ውኃ አለ፣ እኔ ስበላ አንተ እየኝ፣ ፆምህን እደር ማለት ነው ምንም ሌላ ማስረጃ የለውም፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም የሚያነሱት ይህንን እናሸንፍበታለን ብለው የሚያስለቅሱበትን የተጎድቻለሁ የሐሰት ትርክት ነው፡፡

ሪፖርተርየግድቡ ሦስተኛ ዙር ሙሌት ተከናውኗል፡፡ ግብፆች ወደፊት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

/ ሳሙኤል፡- እስከሚችሉት ድረስ ይሄዳሉ፣ እስከ መጨረሻው የደም ጠብታ መሄዳቸውን ይቀጥላሉ፣ መቼም አይተኙም፡፡ በተለይ በኢኮኖሚ ረገድ እያደግን በመጣን ቁጥር የጂኦ ፖለቲካ ዕሳቤ ተገዳዳሪ ኃይል ስለማይፈልግ፣ ተግዳሮቱም በዚያው ልክ ያድጋል፡፡ አሜሪካ ማንም እንዲገዳደራት አትፈልግም፡፡ በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ ባለችበት ቀጣና፣ ቻይናም እንዲሁ ከሥር ያሉ አገሮች እንዲያድጉ አትፈልግም፣ አገር ሆነው እንዲቀጥሉ እንጂ፡፡ አንተ ልዕለ ኃያል ሆነህ እንድትወጣ አይፈልጉም፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ሁልጊዜ የአሜሪካም ሆነ የሌሎች ጉዳይ አስፈጻሚ ሆና ገንዘብና የዳቦ ፍርፋሪ እየተጣለላት እንድትከተል እንጂ፣ ኃያል እንድትሆን እንደማይፈለግ መታወቅ አለበት፡፡ በፖለቲካ በጥቅም ትገናኛለህ እንጂ ፍቅር የለም፡፡ ስለዚህ ይህ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጠንካራ ሆና የግብፅን ብቻ ሳይሆን ከዚያ ባሻገር ያሉ አገሮችን ጫና የምትቋቋመው የማይቋረጥ የኃይል መሠረተ ልማት ሲኖራት ነው፡፡

በ1950ዎቹ ከነበሩት የአፍሪካ መሪዎች የሴኔጋል መሪና የጋና ኩዋሜ ንክሩማህ ይህንን ነበር የሚናገሩት፡፡ በተለይ አፍሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር በነበረችበት ወቅት አፍሪካ ማደግ የምትችለው የመንገድ፣ የኃይልና የኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ሲኖራት ነው ይሉ ነበር፡፡ በተለይ የሴኔጋል መሪ ዲዮፕ የኮንጎ ወንዝን ገድበን አኅጉሩን ተጠቃሚ ማድረግ ካልቻልን አፍሪካዊያን ሊበለፅጉ አይችሉም ይሉ ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ሲዘጋጅ ከነበሩ 15 ዋና ዋናዎቹ ዋነኛ ፕሮጀክቶች አንዱ የኮንጎው ኢንጋ ግድብ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት 42 ሺሕ ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ ተደርጎ የታቀደ ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን ከፍፃሜ ሊደርስ አልቻለም፡፡ ዝም ብለህ ውስጡን ስታየው በአፍሪካ ኅብረት የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ዘርፉን የሚመሩት ግብፃዊ መሆናቸውን ትታዘባለህ፡፡ ይህ ማለት እንዲህ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዲኖሩ አይፈለጉም፡፡ ኮንጎ ይህን ብታለማ ይህ ሁሉ ረብሻ ቀርቶ ከራሷ አልፋ ለዓለም ትተርፍ ነበር፡፡ ነገር ግን አይፈለግም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ይህን አልፋ የአፍሪካ ኅብረት ከያዛቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ ማስፈጸም ያቃተውን በራሷ አቅም የዓባይን ግድብ ስትሠራ፣ አፍሪካ ኅብረት ቆሞ ማመሥገን ነበረበት፣ አላደረገም፡፡ ኅብረቱ ካስቀመጣቸው ዕቅዶች መካከል ማስፈጸም ያልተቻለውን የኢንጋ ግድብ ፕሮጀክት ባያሳካም፣ ኢትዮጵያ ይህን ያህል ርቀት ሄዳ ይህን ግድብ ገንብታለች ብሎ ማመሥገን ነበረበት፡፡ ኅብረቱ ስለቀጣናዊ ትስስር የሚናገርና የሚያስብ ከሆነ የሆነ ያልሆነውን ከማውራት በተግባር የሠሩትን መደገፍ መቻል አለበት፣ ግብፅን መኮነንም ነበረበት በግልጽ፡፡

ሪፖርተርከጎረቤት አገሮች የሚመጣን ጫና ኢትዮጵያ መግታት ትችላለች?

/ ሳሙኤል፡- ጠንካራ ሆኖ ከመቆም ውጪ ምንም የለም፡፡ ዓባይን ገድቦ መጨረስና ኃይል ማመንጨት መጀመር የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ሰፋፊ የእርሻ መሬት ያላት አገር ነች፣ በጣም አምራች የሆነ ሕዝብ አላት፡፡ ለአውሮፓ በጣም ቅርብ ነች፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓይነት ትልቅ ተቋም ያለባት አገር ነች፡፡ በታሪኳ ለአፍሪካ መልካም ነገር ስትሠራ እንጂ መጥፎ ነገር ስትመኝ ያልነበረች ነች፡፡ አሁን ሰዎች መጥተው ኢንቨስት እንዳያደርጉ የኢነርጂ ችግር አለብን፡፡ በተለይ ትልልቅ የእርሻ ልማቶች ላይም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት የኃይል አቅርቦት አለመኖር ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ከዓባይ ኃይል ማመንጨት መቻል ራሷን የቻለች ከማድረጉም በላይ፣ ኢንቨስትመንት የሚስብ ትልቅ አማራጭ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክም ከአውሮፓም ሆነ እስያ ጋር ያለን ቅርበት ኢኮኖሚያዊ ትርፉ ትልቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከግብፅ ጋር ስታነፃፅራት በኃይል ራሷን ስትችል የኢንቨስትመንት ፍልሰቱ ወደ ኢትዮጵያ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ በግብፅ ወይም በሌሎች የዓረብ አገሮች ያሉ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ማየት ሲጀምሩና ኢንቨስት ሲያደርጉ የኃይል አሠላለፍ ይቀይራል ማለት ነው፡፡ የግብፅ ፍራቻም ይኼው ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ኃይል ካለ ምቹ ሁኔታዎች በመኖራቸው፣ በግብፅና በዙሪያዋ ያሉ ኢንቨስተሮች ሊሸሹ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለ፡፡ ያ ማለት ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ ከሌለህ አንደኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ አትሆንም፡፡ የዚህ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ኢትዮጵያን ተፅዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ በታሪክ የነበራትን ስምና ዝና የበለጠ እንዲያብብ ያደርገዋል፡፡ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ችግር ይፈታል፣ ድህነት ይቀረፋል፡፡ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ደሃ ሕዝብ ነው የሚጣላው፣ አገሪቱም ለውጭ ተፅዕኖ ተጋላጭ የምትሆነው፡፡

ስለዚህ በኢኮኖሚ ጠንካራ መሆን ከተቻለ፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከጨመረ፣ ብዙ ሰዎች የትምህርት ዕድል ካገኙና በዕውቀት ከበቁ ተፅዕኖ ፈጣሪነትና ታላቅነት ይከተላል፡፡ ይህንን ደግሞ ግብፆች አይፈልጉትም፡፡ ሰብዓዊ መብትም ሆነ ዴሞክራሲ፣ ትምህርትም ሆነ ሌላ ልማት የኃይል መሠረተ ልማት ያስፈልገዋል፡፡ ኃይል ከሌለህ ሆስፒታሎች በቂ ኃይል አግኝተው የሰውን ጤና መንከባከብ አይችሉም፡፡ በቂ ኃይል ከሌለ ትምህርት ቤቶች አይኖሩም፡፡ ስለዚህ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ካልሠራህ ጤናማና መልካም የሚያስብ ትውልድ መፍጠር አትችልም፡፡ ስለዚህ በትምህርት የበቃ ዜጋ ከሌለና ሁሉም ሲከፋው መሣሪያ ይዞ የሚሮጥ ከሆነ፣ በመነጋገር የማያምን ከሆነ አገርን ፈቀቅ ማድረግ አትችልም፡፡ ብዙ ሰው ስለማይመስለው መጀመርያ ምግብ እንብላ ይላል፡፡ ይህን ደግሞ ዕርዳታ እየተቀበልክ ጥገኛ ሆነህ እንድትኖርና ዕርዳታ ሲቀርብ ዕርዳታ ለሚሰጥህ አካል ታጎነብሳለህ፡፡ ምንዳ ሲወረውርልህ ሕዝብን የምትፈጅ አሸባሪ የምትሆነው ጥገኛ ስትሆን ነው፡፡ ይህ የሥራ ባህልህ እንዲጠፋ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ይህ የምንፈልገው ኃይል ካለ ሁሉንም መሠረተ ልማት ታሟላለህ፡፡ ለሕዝብም ትክክለኛ የሆነ የመንግሥትና የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት ሕዝቡ ዴሞክራቲክ እየሆነ የተሻለ አገር መፍጠር ትችላለህ፡፡ የዴሞክራሲን መሠረታዊ ሐሳብ የተረዳና ስለመብቱ የሚያወራ ማኅበረሰብ ከገነባህ፣ መልካም አስተሳሰብ ያለው ማኅበረሰብ ማምጣት ትችላለህ፡፡ ለሆዳቸው ያላደሩ፣ ስግብግብ ያልሆኑ፣ ለሕዝብና ለአገር የሚኖሩ፣ ሥልጣንን የሕዝብ ማስተዳደሪያ እንጂ የሕይወት ዘመን ርስት የማያደርጉ መሪዎችን ትፈጥራለህ፡፡

ሪፖርተር፡ኢትዮጵያ በእርግጥ እንደሚባለው በሕዝብም በቆዳ ስፋትም ትልቅ አገር ነች፡፡ ነገር ግን በድህነት ውስጥ የምትኖር አገርም ነች፡፡ አሜሪካ መራሹ ምዕራባውያን፣ ቻይናናሩሲያኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ትኩረት ከምን የመነጨ ነው ማለት ይቻላል?

/ ሳሙኤል፡ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት አገር ነች፡፡ ለምሳሌ በዓለም ላይ ካሉ ዘጠኝ በጂኦ ፖለቲካው በጣም ወሳኝ የሚባሉ ቁልፍ አካባቢዎች ውስጥ ሁለት ወይም ሦስቱ ለምሳሌ የባቤል መንደብ፣ የሆርሙዝ ሰርጥና የስዊዝ ቦይ ወሽመጦች ናቸው፡፡ እነዚህ የዓለም የንግድ የደም ስሮች ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በቂ አቅም ካለህ ማንንም ኃይል ማስገበር የምትችል አገር መሆን ትችላለህ፡፡ ለምሳሌ ኢራን እንድትጠነክር የማይፈለገው ሆርሙዝን ለመቆጣጠርና አሜሪካ ወደ ምሥራቅ እስያ አገሮች ቻይና፣ ጃፓንና በቀጣናው ያሉ ወዳጅ አገሮችን ለማገዝና ለመቆጣጠር እንድትችል ነው፡፡ ስለዚህ አሜሪካ ከኢራን ጋር በምታደርገው ግብግብ ውስጥ ጉሮሮዋ ተይዟል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያም ግብፅም ለአሜሪካ ካላቸው ግንኙነት በታሪክ ሲታይ እኩል የሚባል ነው፡፡ ነገር ግን የስዊዝ ካናልና የአስዋን ግድብ ከተገነቡ በኋላ ግብፅ ኃይልና አቅም በመጨመሯ ጠንካራ ስትሆን ኃያላን አገሮችም ጂኦ ስትራጄካዊ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ተሽቀዳደሙ ማለት ነው፡፡ አሜሪካ ግብፅን የምትፈልጋት በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ቁልፍ አጋር ስለሆነች ነው፡፡ በተመሳሳይ አሜሪካ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን ተጨንቃ ሳይሆን አልሸባብን ማጥፋት የምትፈልግው በእርግጥ ወዳጅ አገሯ ሰላም ብትሆን፣ የሆነ የፖለቲካ ፋይዳ ሊኖረው ይችላል ከሚል ዕሳቤ ነው፡፡

ነገር ግን ዋናው ዓላማ የንግድ መርከቦች በደንብ መንቀሳቀስ እንዲችሉና ሰላማዊ አካባቢ ለመፍጠር ዕርዳታ ለማግኝት ነው፡፡ ከአጋሮቿ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳለጥ ሰላማዊ የሆነ አካባቢ መፍጠር ትሻለች፡፡ ስለዚህ ያንን ለማሳካት የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብር መፍጠር የግድ ስለሚል ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነ የኃይል አቅርቦት ላይ መሥራትና ሕዝቦቿ እንዲማሩ ማድረግ ቀዳሚ የሆነ ሥራ ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ ጠንካራ ወታደር፣ አገሩን የሚወድ ታታሪ ዜጋ መፍጠር የሚቻለው በቂ የሆነ የኃይል አቅርቦት ሲኖር ነው፡፡ ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚታየው ግብግብ የውኃ ማጣት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ኃይል አመንጭታ የተሻለ የኢንቨስትመንት አማራጭ ትፈጥራለች ከሚል ሥጋት ነው፡፡ አቅሟ እያደገ ሲሄድ ዓባይን ከዓባይ ሸለቆ አውጥታ በማልማት ጡንቻዋን ታፈረጥማለች በማለትም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም አገሮች ያደጉት እንደዚያ ነው፡፡ አሜሪካ፣ ግብፅ፣ ሴኔጋል፣ ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ፓኪስታንና ህንድ ይህን አልፈውበታል፡፡ ወንዝን በቦይ እያሻገሩ፣ እየጠለፉና እያለሙ ተለውጠውበታል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ለምን ትከለከላለች? ጣልቃ እየገቡ ያሉት እኮ ኢትዮጵያ ለራሷ መቆም ስላልቻለችና ደሃ ስለሆነች ነው፡፡ ምክንያቱም አቅም ቢኖራትማ ማንም አይፈነጭባትም ነበር፡፡ ለምሳሌ ቱርክ፣ ህንድ፡ ፓኪስታን፣ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ ውስጣዊ ችግር ቢኖርባቸውም እንኳ ራሳቸውን አስከብረው ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ አቅም መፍጠር ከታሰበ ማንም እንደፈለገ የማይፈነጭበት የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር ከስንዴ ልመና መውጣት አለብህ፡፡ ይህን የምታስቀረው በቂ የሆነ ኃይል ስታመርትና ወጣቱን ሥራ ላይ ስታሰማራው ነው፡፡ ነገር ግን ስንዴ እየለመንክ ፖለቲካዬ ለምን ተነካብኝ ብለህ ቡራ ከረዩ ብትል መሳቂያ ነው የምትሆነው፡፡

ሪፖርተርየፌደራል መንግሥቱ ከሕወሓት ጋር የጀመረው የሰላም ድርድር ለቀጣናው ምን ፋይዳ ያመጣል?

/ ሳሙኤል፡ አሁን በቀጣናው ውስጥ የሚታየው አለመረጋጋትና ውጥረት መርገብ ካልቻለ በድርቅና በኑሮ ውድነት የሚከሰት ኢኮኖሚያዊ ቀውስና መሰል ተዛማጅ ችግሮች ጋር ተዳምሮ የሚያስከትለው ሰብዓዊ ዕልቂትና ቁሳዊ አደጋ ቀላል አይሆንም፡፡ የሱዳን መበጥበጥ ለኢትዮጵያ ላይ እያደረሳባት ያለውን ወይም የኢትዮጵያ መበጥበጥ በሌሎች አገሮች ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና መመልከት ትችላለህ፡፡ በቀላሉ ስደተኝነትን ማንሳት ትችላለህ፡፡ ደቡብ ሱዳን ወይም ሱዳን ሲበጠበጥ ሕዝቡ ፈልሶ ወደዚህ ይመጣል፡፡ የኢትዮጵያም መረበሽ በተመሳሳይ መሰል የደኅንነት ሥጋቶችን ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት አስገድደውም ሆነ አሳምነው ወጣቶችን መሣሪያ በማስታጠቅ በማያባራ ጦርነትና ግጭት ውስጥ ሊማግዷችው ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰላም መሆን በራሱ ብቻ በዙሪያዋ ያሉ አገሮች አለመረጋጋት እስካለ ድረስ ሰላማችንን ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ ሁልጊዜም አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ማለት የኢጋድ አባል አገሮች ተምሳሌት ናት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ ሁሉም የጎረቤት አገሮች ውስጥ አለ፡፡ ስለዚህ ችግሩ እዚህ ብቻ አይቀርም ማለት ነው፡፡ የተዋለደና የተጋመደ ሕዝብ ነው በሁሉም አቅጣጫ ስታየው፡፡ ይህ ማለት የአንዱ መነካት ሁሉንም ይነካል፡፡ ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ የሆነ የአገራዊ ምክክር ከተካሄደና ሁሉን አቀፍ የሰላም ውይይት ተደርጎ ሰላም መጣ ማለት ትርፉ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለጎረቤት አገሮች ሁሉ ጭምር ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ አርብቶ አደሩ፣ ገበሬው፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ ልሂቁ፣ የንግዱና የሲቪክ ማኅበረሰብ አካላትና ሁላችንም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ያመጣሉ በምንላቸውን ጉዳዮች ላይ ከብሔርና ከሙያ ውክልናችን በዘለለ ችግሮቻችንን መነጋገር አለብን፡፡ በጥበብና በሠለጠነ መንገድ ችግሮቹን ለመፍታት እንድንችል ለአገራችን ይበጃሉ፣ በጋራ ሊያሻግሩን ይችላሉ የሚሉ አጀንዳዎችን በመቅረፅና በመወያያት ብሔራዊ መግባባት ላይ እንድንደርስ ፈጣሪ ይርዳን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች