Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ የገንዘብ መጠኑን ከ1.1 ትሪሊዮን ብር በላይ ለማድረስና በሌሎች አገልግሎቶቹም ከ20 በመቶ በላይ ዕድገት ለማስመዝገብ እንደሚሠራ ተገለጸ፡፡

ባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ካስታወቀ በኋላ የባንኩ አመራሮች ባደረጉት የሁለት ቀናት ግምገማና የቀጣይ ዓመት የሥራ ዕቅድ አስመልክቶ የደረሱበት ስምምነት በዋና ዋና የባንኩ የሥራ ክንውኖች ውስጥ በትንሹ የባንኩን አገልግሎት ከ20 በመቶ በላይ ዕድገት እንዲመዘገብበት ማስቻል ነው፡፡ 

ባንኩ ይህንን አፈጻጸም ለማስመዝገብ የሚሠራው 70 በመቶ የሚሆነውን ተግባሩን መደበኛውን የባንክ አገልግሎት በመሥራት ሲሆን፣ 30 በመቶ ሥራው ደግሞ የባንኩን ትራንስፎርሜሽን በሚመለከቱ ሥራዎች ላይ በማተኮር ነው፡፡ ባንኩ ከ2014 የሒሳብ ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ባስጠናው ጥናት መሠረት ነባሩን አሠራር በአዲስ የመተካት ሥራው የተጀመረ ሲሆን፣ በተለይ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ነባሩን አሠራር በአዲስ የመለወጥ ተግባር ሥራ እንዲሚተገበር ታውቋል፡፡ 

ሠራተኛውም ይህንን በማወቅ ከመደበኛው የባንክ አገልግሎቱ ጎን ጎን የትራንስፎርሜሽኑን ሥራውን በተቀመጠለት አቅጣጫና ዝርዝር ዕቅድ መሠረት እንዲተገብር ይደረጋል ተብሏል። ለዚህም ሲባል ሁሉም አመራር ለመደበኛው ሥራና የትራንስፎርሜሽን ሥራውን ለመተግበር ምን ያህል ጊዜ እንደተመደበለት የሚያሳይ ዝርዝር ማስተግበሪም መዘጋጀቱንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡  

ባንኩ በየደረጃው ያሉ ሠራተኞችና አመራሮች ተቆጥሮ የሚሰጣቸውን የትራንስፎርሜሽን ሥራ ከማስፈጸም ጎን ለጎን በቀጣዩ ዓመት ባንኩ መድረስ አለበት ተብሎ የተቀመጠውን ዕቅድ ማስፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በ2015 የሒሳብ ዓመት ባንኩ እደርስበታለሁ ብሎ ካስቀመጣቸው ዕቅዶች ውስጥ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ25 በመቶ በላይ በማሳደግ በ2015 መጨረሻ ላይ ከ1.1 ትሪሊዮን ብር በላይ ማድረስ አንዱ ነው፡፡ በ2014 የሒሳብ ዓመት ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ21 በመቶ በማሳደግ 891.1 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ደግሞ በ25 በመቶ በማሳደግ የባንኩን የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ትሪሊዮን በላይ ለማሳደግ ግብ መጣሉን መረጃው ያመለክታል።  

ይህ ዕቅድ በተሟላ መልኩ ከተተገበረ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመጀመርያ ጊዜ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ በማድረስ የቻለ የአገር ውስጥ ባንክ ያደርገዋል። በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የሁሉም ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1.7 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከጠቅላላው የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ብልጫ ያለውን ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ ከባንኩ ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ዕድገት ባሻገር በሒሳብ ዓመቱ 2015 ዓ.ም ሊሰጠው ያሰበውን ብድርና የሀብት መጠኑንም በተመሳሳይ በአነስተኛ ምጣኔ ከ20 በመቶ በላይ የማድረስ ውጥን ይዟል፡፡ አሁን ያለው የባንኩ ጠቅላላ የሀብት መጠን 1.2 ትሪሊዮን ብር ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት 1.44 ትሪሊዮን ብር ለማድረስ ታስቦ እየተሠራ መሆኑን የባንኩ የ2015 የሒሳብ ዓመት ዕቅድ መረጃ ያመለክታል፡፡  

በ2014 የሒሳብ ዓመት ባንኩ የሰጠውን አዲስ ብድር ከ20 በመቶ በላይ የማሳደግ ዕቅድ ያወጣ ሲሆን፣ በ2014 ዓ.ም. የሰጠው አዲስ ብድር 179.2 ቢሊዮን ብር መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከቅርንጫፍ ማስፋፋት ጋር በተያያዘም በ2015 የሒሳብ ዓመት ተጨማሪ 150 አዳዲስ ቅርንጫፎች ለመክፈት አቅዷል፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ባንኩ የከፈታቸው አዳዲስ የቅርንጫፎች ብዛት 124 ነው፡፡ በ2015 የሒሳብ ዓመት የታቀዱት 150 አዳዲስ ቅርንጫፎች እንደታቀደው የሚከፍቱ ከሆነ በሐሳብ ዓመቹ መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላ አገሪቱ የሚኖሩት ቅርንጫፎች ብዛት 1,974 ይሆናል።

በዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት አንፃርም ባንኩ 20 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ግብ የተጣለ ሲሆን፣ አማራጭ የዲጂታል ባንኪንግ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማስፋትም ተመሳሳይ ዕቅድ መያዙ ተጠቁሟል፡፡ ባንኩ አማራጭ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎትን በተመለከተ ይፋ እንዳደረገው፣ ከጠቅላላ የባንኩ ደንበኞች ከ35 በመቶ በላይ የሚሆኑ የዲጂታል ባንኪንግ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ነው፡፡ እነዚህ ደንበኞች በ2014 ዓ.ም. ብቻ በአማራጭ የባንኪንግ አገልግሎት ከ1.2 ትሪሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ ይህ መልካም ጅምር በ2015 የሒሳብ ዓመት በተመሳሳይ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ የሚያደርግ እንደሚሆንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በዓመታዊ የባንኩ ቦርድና ማኔጅመንት፣ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ያሉ አመራሮች በተሳተፉበት ግምገማና ዕቅድ ውይይት ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት በአነስተኛ መጠን ከ20 በመቶ በላይ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ታቅዶ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ዋናው ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ 30 በመቶ የሚሆነው የባንኩ ሥራ ግን ባንኩ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲያካሂድ ማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም ባንኩ ለ2015 የሒሳብ ዓመት በተቀመጠለት የድርጊት መርሐ ግብር መሠረት በተጠናቀቀው የ2014 ሒሳብ ዓመት ባንኩ ካስመዘገበው ውጤት በ20 በመቶ ብልጫ ያለው ዕድገት እንዲመዘገብ ማስቻል ነው፡፡ 

ለትራንስፎርሜሽኑ ሥራ እያንዳንዱ ሠራተኛና የሥራ መሪ የየራሱ የሥራ ድርሻ እንደሚኖረው ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከቦርዱ ጀምሮ ታች ያለው አመራር ድረስ እንደ ኃላፊነቱ በሚወስደው ሥራ ዕቅዱን ማስፈጸም ይኖርበታል፡፡  

እንደ አቶ ተክለወልድ ገለጻ፣ የባንኩን ትራንስፎርሜሽን ዕውን የማድረጉ ሥራ እንዴትና ምን ያህል እየተፈጸመ ስለመሆኑ፣ እንዲሁም አጠቃላይ ሒደቱን በመከታተሉ ረገድ ከቦርዱ ጀምሮ ክትትል የሚደረግበት ይሆናል።

ትራንስፎርሜሽኑን ለማስፈጸም ከወጡት ዕቅዶች መካከል የባንኩ ቦርድ  በየወሩ፣ የቦርዱ ንዑስ ኮሚቴ ደግሞ በየ15 ቀናት የሚከታተለው ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ ምክትል ፕሬዚዳንት 60 በመቶ ሥራው ትራንስፎርሜሽኑን ከማስፈጸም ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ መደበኛውን ሥራ በ40 በመቶ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡ 80 በመቶ የሚሆነውም የቦርዱ ሥራ ይሄው ትራንስፎርሜሽን ጋር የተያያዘ ሥራ ነው፡፡ በተመሳሳይ የባንኩ ፕሬዚዳንትም 80 በመቶ ክንውኑ ይህንኑ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ከማሳካት ጋር ይሆናል፡፡ 

ባንኩ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ውጭ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲወጣ፣ እንዲሁም በሁሉም ረገድ አገልግሎቱን ለማዘመን ይረዳል ተብሎ በውጭ ኩባንያ የተከናወነው ጥናት ምክረ ሐሳብ በሒደት ለመተግበር ይቻል ዘንድ በወራትና በዓመታት በተከፋፈለ የድርጊት መርሐ ግብር መሠረት እየተፈጸመ ይሄዳል ተብሏል፡፡ 

በጥናቱ መሠረት ባንኩ የሚተገብራቸውና የሚጠበቁ ውጤቶች 1,600 የሚደርሱ ሲሆን፣ እነዚህን ውጤቶች በአምስት የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚተገበሩ ይሆናል፡፡ 

በትራንስፎርሜሽን ውጥኑ መሠረት አምስተኛ ዓመቱ ድረስ ወደ 1,600 ውጤቶች የሚተገበሩ መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ይህም በየዓመቱ ተከፋፍሎ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ እነዚህ ውጤቶች አሠራሮችን በአዲስ በመለወጥ የሚከናወኑ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል፡፡ 

ለዚህም በየእያንዳንዱ ግሩፕ ውስጥ ትራንስፎርሜሽኑን የሚከታተል አካል ሁሉ ተዋቅሯል፡፡ በዚህ ውጥን መሠረት ባንኩ ለመለወጥ የሚሠሩ አሠራሮችን በአዲስ በመተካት እስከ አምስተኛው ዓመት መጨረሻ ድረስ በመሄድ በዕቅዱ መሠረት ባንኩን በአዲስ መልክ በመቀየር እንዲሠራ ይደረጋልም ተብሏል፡፡

የዚህ የትራንስፎርሜሽን አካል የሆነው ሌላው መሠረታዊ ተብሎ የተወጠነ ነው፡፡ የሰው ኃይልን ማብቃት፣ አወቃቀሩን ማስተካከልና ሁሉን አካታች የሆነ አደረጃጀት ማበጀት ነው፡፡ ለዚህም ሠራተኞችን ለአዲሱ አሠራር በሚሆን ደረጃ የሚያበቃ ሥልጠና መስጠት ነው፡፡ ትራንስፎርሜሽኑን በተቀመጠለት ዕቅድ ለመተግበር ለሠራተኞች የአገር ውስጥና የውጭ ሥልጠናዎች እንደሚሰጣቸው አቶ ተክለወልድ ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው ተተኪዎችን ለማፍረት ጭምር ያለመ ሲሆን፣ አጠቃላይ አሠራሩ ከቀድሞ የተለየ በመሆኑ አምስተኛው ዓመታት ላይ ብቁ የሆኑ 400 ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ እንዲሁም 100 ፕሬዚዳንቶች ማፍራት የሚያስችል ዕቅድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ይህም ዕቅድ የትራንስፎርሜሽኑ አካል ነው ተብሏል፡፡ በዚሁ ሥልጠና የሚበቁ ሠራተኞች በየደረጃው ከታች እስከ ላይ ከሥር ከሥር እየተተኩ የሚሄዱበት አሠራር ይኖራል ተብሏል፡፡ 

የሥልጠናው ሌላው ግብ ኳሊቲው ኮምፕሮማይዝ ሳይደረግ ብሔር ብሔረሰቦችን ያካተተ አወቃቀር መዘርጋት ሲሆን፣ ይህም የትራንስፎርሜሸኑን ዕቅድ ተደርጎ የሚሠራበት መሆኑን  ከቦርድ ሊቀመንበሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በባንኩ ያለውን የፆታ ስብጥር በተመለከተም አዲስ አሠራር የሚዘረጋ ሲሆን፣ በየዓመቱ እስከ አምስተኛ ዓመቱ መጨረሻም ከዚያም በኋላ ባንኩን የሚመሩ ሴቶች እንዲኖሩ የሚያስችል ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ በአምስት ዓመት መጨረሻ ላይም የባንኩ ሠራተኞች ቁጥር ከ100 ሺሕ በላይ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ በመሆኑ፣ ከእነዚህ ሠራተኞች ባንኩን የሚመሩ 20 እና 30 ሴቶችን የማፍራት ሥራ ይሠራል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የሚሰጠው ሥልጠናም የብሔርና የፆታ ብዝኃነት እንዲኖር ለማድረግና ባንኩ የሁሉም መሆኑን የሚያረጋግጥ ጠንካራ መሠረት ለመጣልም እንደሆነ የቦርድ ሊቀመንበሩ አክለዋል፡፡ በባንክ ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተዋጽኦ ኖሮት ፕሮፌሽናል አሠራር እንዲኖር በሁሉም ረገድ ዝግጅት ስለመደረጉ ተገልጿል፡፡ አሁን 30 በመቶ የሚሆነውን የሥራ ክንውን ትራንስፎርሜሽኑ ላይ የተደረገውም እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ደረጃ በደረጃ ለመተግበር ነው፡፡ 

ስለዚህ ‹‹ከእከሌ አካባቢ ሰው የለም›› የሚል ነገር አይኖርም የሚሉት የቦርድ ሊቀመንሩ፣ በአምስተኛ ዓመት መጨረሻ ላይ ባንኩ ሙሉ በሙሉ የለውጥ ሒደቱን የሚያስተናግድበት ሙሉ ቁመና ይዞ፣ ከኢትዮጵያ ውጭም ጥሩ ተወዳዳሪ ሆኖ ይቀርባል፡፡ በተለይ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ እንደ ዋና ሥራ የሚታዩ ቁጠባ ማሰባሰብ፣ ብድር መስጠትና የመሳሰሉ ሥራዎች ከ20 በመቶ ያድጋል ሲባል፣ ይህ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የትራንስፎርሜሽን ሥራው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ መሆኑንም አቶ ተክለወልድ ገልጸዋል፡፡ በዚህ የትራንስፎርሜሽን ሒደት ውስጥ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ መንግሥትም በየዓመቱ 25 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ማሳደጊያ ያደርጋል ተብሎም ታቅዷል፡፡      

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች እየጠበቁ ያሉት የደመወዝ ጭማሪ በቀጣይ ሳምንታት ውሳኔ የሚሰጥበት እንደሚሆን ታውቋል፡፡ ከባንኩ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመውም፣ ቦርዱ የቀረበለትን ደመወዝ ጭማሪ አይቶ ውሳኔ እንደሚሰጥ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የደመወዝ ጭማሪው እንደ ግል ባንኮች የሰጡትን ያህል ባይሆን እንኳን የደመወዝ ጭማሪ የሚደረግ መሆኑን የሚጠቁመው ይኼው መረጃ፣ ቦርዱ ውሳኔውን የሚያሳርፈው ማኔጅመንቱ አስጠንቶ በሚቀርበው መረጃ መሠረት ነው ተብሏል፡፡

የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለመተግበርም ደመወዝ ጭማሪ የታመነበት ሲሆን፣ በቀጣይ ሳምንታት የግል የፋይናንስ ተቋማት በተለይ አብዛኞቹ የግል ባንኮች ለሠራተኞቻች እስከ አምስት እርከን የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ ያደረጉ ሲሆን፣ እስከ ስድስት ወራት የሚደርስ ቦነስም መስጠታቸው ይታወቃል፡፡     

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች