Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የግሉ ዘርፍ ሸቀጦችን መቸርቸር ተፀይፎ በአገር ወስጥ የሚያመርተው መቼ ይሆን?

በአንድ አገር አኮኖሚ ውስጥ የግሉ ዘርፍ ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ግስጋሴያቸው ስማቸውን ደጋግመን የምንጠቅሳቸው አገሮች ዛሬ ለደረሱበት ዕድገት ደረጃ የበቁት የግሉን ዘርፍ ደግፈው ይዘው በመጓዛቸው ነው፡፡ የግሉን ዘርፍ ሊያበረታቱ የሚችሉ ፖሊሲዎችን በመቅረፅና በማብቃት ውጤታማ ሆነውበታል፡፡ ምርቶቻቸው ድንበር ተሻግረው ገበያ እንዲያገኙ በማድረግ ጭምር ይደግፏቸዋል፡፡ ደከም ሲሉ ፋይናንስ በማቅረብ ዕድገታቸውን ያስቀጥላሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን አገሬው በራሱ ምርት የመጠቀም ባህሉን እንዲያዳብር አድርገዋል፡፡ የአገር ውስጥ ምርትን መሸመት የዜግነት ድርሻን እንደመወጣት ይቆጠራል፡፡ ይህ ደግሞ ለኩባንያዎቻቸውም፣ ለአገሩ የኢኮኖሚ ዕድገትም ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በኢትዮጵያም የግሉ ዘርፍ ሚና መተኪያ የሌለው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲዎች ውስጥ የግሉን ዘርፍ በሚመለከት የሠፈሩ ቃላትም ይህንኑ የሚገልጹ ናቸው፡፡ የግሉ ዘርፍ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ መሆኑንም ያትታሉ፡፡ ይሁንና በአገራዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውስጥ የተካተቱ ቃላትም ሆኑ በመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ የግሉን ዘርፍ አስፈላጊነትና መተኪያ የለሽነት የሚገልጹ አንደበቶች ለይስሙላ ካልሆነ በቀር በተግባር አይተረጎሙም፡፡ የግሉ ዘርፍ አስፈላጊነት በሚዘመርለት ልክ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶው እንዲታይ አልተደረገም፡፡ ለግሉ ዘርፍ ዕድገት የተመቻቸ ሁኔታ በበቂ ደረጃ እየቀረበ ያለመሆኑንም መሬት ላይ ያለው እውነት ይነግረናል፡፡  

ስለዚህ የኢትዮጵያን የግል ዘርፍ በሚፈለገው ልክ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን እጅግ አስፈላጊ ሚና መጫወት ካልቻለባቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ቁልፉ ነገር፣ መንግሥት ለዚህ ዘርፍ ዕድገት የሚፈለገውን ያህል አስተዋጽኦ አለማበርከቱና የግሉ ዘርፍም ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት ያለው ተነሳሽነት ማጣት ነው ሊባል ይችላል፡፡ በአጭሩ ከሁለቱም ወገን ችግሮች አሉ ማለቱ በተሻለ ይገልጸዋል፡፡

ለዚህም ነው ዛሬ ለአገር ኢኮኖሚዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ የንግድ ዘርፎች ውስጥ ያሉ አገር በቀል ኩባንያዎች በጣት የሚቆጠሩ ሆነው የቀሩት፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር እንኳን ተወዳድሮ ሊያሸንፉ የሚችሉ ኩባንያዎች ባለመኖራቸው ውድድርን መፍራት ዛሬም መገለጫቸው ሆኗል፡፡ 

የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ በአብዛኛው በትንንሽ ቢዝነሶችና ንግዶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያመጡ አምራች ኢንቨስተሮችንና ኩባንያዎችን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች እምብዛም አይታዩም፡፡ ሁሉም በተለመዱ ቢዝነሶች ላይ በማተኮሩ አገራዊ ኢኮኖሚውን እምብዛም እንዳይራመድ አድርጎታል፡፡ መንግሥትም ቢሆን የግሉ ዘርፍ ከተለመደው የቢዝነስ እንቅስቃሴና በዘልማድ ከሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲወጣ ጠንካራ ዕርምጃ ሲወሰድ አይታይም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ውስጥ በቀላሉ በአገር ውስጥ ምርት ሊተኩ የሚችሉትን በመለየት የግል ባለሀብቱ እንዲሰማራባቸው አልተደረገም፣ የግሉ ዘርፍም በዚህ ረገድ በራሱ ያደረገው ጥረት ኢምንት ነው።

የግሉ ዘርፍ አገርን ታሳቢ ያደረገ ኢንቨስትመንት ላይ ከመግባት ይልቅ፣ በአብዛኛው ፈጣን ትርፍ ሊያስገኙ በሚችሉ የአጭር ጊዜ ንግዶችና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በሌላቸው ዘርፎች ማለትም ሸቀጦችን ከውጭ አስገብቶ በመቸርቸር፣ አሊያም ሕንፃ ሠርቶ በማከራየት ላይ ተቸንክሮ የቀረ ነው፡፡ ወይም በአየር በአየር ንግድ ሥራ የተጠመደ ነው። በመሆኑም በአገር ደረጃ የሚጠራ ትልቅ ጠቃሚ ኢንቨስትመንት ውስጥ የገቡ አገር በቀል ኩባንያዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። እንዲህ ያለው የቆየ የልምድ ዜጎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ሸማች ሆነው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል፡፡ በአገራቸው ምርት ኮርተው፣ ‹‹የእኛ!›› ብለው በፍላጎት የሚሸምቷቸው ምርቶች የሉም ማለት ይቻላል። የቡና መቁያ ‹‹ማንከሽከሻ›› እና የቡና ጀበና ቻይና አገር ተመርቶ እየቀረበለት መሆኑን በማሳያነት መጠቅስ ይቻላል።

ሸማቹ ለዚህ የተዳረገበት ምክንያትም የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ የቢዝነስ ዕሳቤ ሸቀጣ ሸቀጦችን ከውጭ አስመጥቶ በመቸርቸር ላይ የተገነባና ከዚህ የቆየና የተቸከለ አስተሳሰብ መውጣት ባለመቻሉ ነው። ይህ ሥር የሰደደ ልማድም ሸማቾችን የውጭ ምርት ተገዥ አድርጓቸዋል፡፡ በአገር ውስጥ ምርቶችን በብዛትና በጥራት አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡ ኩባንያዎችን መፍጠር ስለተሳነ ነው። በመሆኑም ውጭ ምርት አምላኪነት በኢትዮጵያ ነግሷል ማለት ይቻላል። 

በየአካባቢያው በየትኛውም መደብር ውስጥ ቢገባ የአገር ውስጥ ምርቶችን ማግኘት እጅግ ከባድ ነው፡፡ በተለይ የታሸጉ ምርቶችና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች ሳይቀሩ ከውጭ የሚገቡ ናቸው፡፡ በገበያ ላይ ከምናገኛቸው ምግብ ነክና ጥሬ የግብርና ምርቶች ውጪ ያሉ ምርቶች በሙሉ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች የተሞሉ ናቸው፡፡

የሠፈር መደብር ውስጥ ሳይቀር በሼልፍ ላይ ከተደረደሩት ምርቶች መካከል በአገር ውስጥ የሚመረቱ ጥቂት ብቻ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የእኛ የምንለው ምርት ካለ ከሼልፍ ውጪ ያሉ በማዳበሪያ የተሞሉ እንደ ምስር፣ መኮሮኒ፣ ቂንጬ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ስኳር፣ ዱቄትና የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም ምርቶች ውስጥ እንደ ምስር፣ ዱቄትና መኮሮኒ ያሉ ምርቶችም ቢሆኑ ከውጭ መግባት ከጀመሩ ዓመታትን ዘልቀዋል። ይህም በውጭ ምርቶች ጥገኝነት የተተበተብን መሆኑን ያሳያል፡፡ ‹‹እኛው ልናመርተው እየቻልን?›› የሚል ቁጭት ያልፈጠረብን ከመምሰል ወደ መሆን እየተሸጋገርን ነው። በተለይ በተለይ በቀላሉ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ሊያመርት የሚችል የእኛ የምንለው ኩባያን ማጣታችን ለምን ብሎ የሚጠይቅና የሚሞግት በመጥፋቱ ችግሩ ገዝፎ እየታየ ነው፡፡ ባለሀብቱን ጠቃሚ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዲገባ ማበረታታት ካለባቸውና በቀጥታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት መካከል አንዱ የሆነው የንግድ ምክር ቤትም እንዲህ ያለው ጉዳይ የሚያሳስበው አይመስልም፡፡ አመራሮቹ ዓለምን እየዞሩ መቼ እንዲህ ያለው ነገር ይታያቸዋል? 

በአጠቃላይ ምንም ምክንያት ይሁን ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸው የጎላ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ኩባንያዎችን በበቂ ሁኔታ እያፈራን አይደለም፡፡ ለዘመናት ዕቃ በማስመጣትና በመቸርቸር ብቻ የተጠመደው የኢንቨስትመንትና የንግድ ሥርዓታችንን ወደ አምራችነትና ጠቃሚ ወደ ሆነ የኢንቨስትመንት እንዲገባ ባለመደረጉ የሸቀጣ ሸቀጦች ማራገፊያ ሆነናል፡፡

ኢትዮጵያን የሚያህል በተፈጥሮ የታደለች አገር ምስር ሳይቀር ከውጭ የምታስገባ ከሆነ፣ የእኛን ስንፍና አያሳይምን? በአራቱም አቅጣጫ ሽንኩርት በቀላሉ ሊያመርት የሚችል ምድር ባላት አገር ሽንኩርት አጥሯት ከሱዳን ስታስገባ እንዴት እንቆጭም? ኪሎ በ20 ብር ቢሸጥ እንኳን ውድ ሊሆን የሚገባውን ሽንኩርት ዛሬ 50 ብር የምንገዛበቱ ምክንያት እኮ ባለን መጠቀም ያለመቻላችንና እንዲህ ያሉ ትንንሽ ነገሮችን በመለየት የምር ይዞ የሚሠራ መጥፋቱ ነው፡፡ ቲማቲም እንደ ልብ የሚመረትበት፣ አንዳንዴም ገበያ ጠፍቶ በሚበሰብስበት አገር የቲማቲም ድልህና ካቻፕ ማስመጣትስ ምን ይሉታል? ትንሽ ኢንቨስት አድርጎ እዚሁ ማምረት እየተቻለ ከውጭ አስመጥቶ መሸጥ መጥፎ ሱስ አይሆንም? ረግረግ መሬት ይዞ የውጭ ሩዝ ካልገባ ማለታችንስ? በቀርከሃ ምርት ከዓለም አሥር ቀዳሚ አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከቀርከሃ የሚሠራ የጥርስ እንጨት (ስቴኪኒ) እና ሌሎች የቀርከሃ ምርቶችን ማስገባት በሽታ ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል? ለዚህ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ የሚያሳዝነው ማነው?  

ይህ ሁሉ የሚመለከተን የግሉን ዘርፍ ማበረታታትና እንዲህ ያሉ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዲገቡ በበቂ ሁኔታ አለመሠራቱ ነው፡፡ መንግሥት ማበረታታትና የግል ዘርፉ ሊሠራበት የሚገባቸውን የኢንቨስትመንት መስኮች ከማመላከት ባሻገር፣ ጠቃሚ የሚሆኑ ኢንቨስትመንቶች እንዳይበረታቱ የተወሳሰበው ቢሮክራሲና ሌብነትም አንድ እንቅፋት እንደሆነም መታወቅ አለበት፡፡ 

ከግል ዘርፉ አንፃርም አገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሰማራት ያለው ፍላጎት መድከምና ኢንቨስትመንቱን ከአገራዊ ዕድገት ጋር አስተሳስሮ ያለ ማየት ችግር አለ፡፡ በእርግጥ ጠቃሚ በምንላቸው ኢቨስትመንቶች ለመሰማራት የመገንቢያ ቦታ ችግር ይነሳል፡፡ ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬት ያለ ችግርና ያለ ጉቦ ማግኘት ከባድ መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡ ቦታው ተገኘ ከተባለም የሚጠየቀው የሊዝ ዋጋ ያስደነግጣል፣ ፋይናንሱም ችግር ነው፡፡ 

በሌላ አንፃር ግን በየክልሉ ያሉ እጅግ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የወጣባቸው ፓርኮች አብዛኞቹ አፋቸውን ከፍተው የኢንቨስተር ያለህ እያሉ ባሉበት ወቅት እነዚህን ፓርኮች መጠቀም ፍላጎት የታጣበት ምክንያት የንግድ ባህላችን ያልዳበረ መሆኑን አያሳይም? በእነዚህ ፓርኮች ውስጥ ቦታ ወስዶ ለማምረትና ለመሥራት ፍላጎት ያለው የግል ኩባንያ በመታጣቱ የግሉ ዘርፍ ሊኮነን ይገባል። ዜጎች የውጭ ምርቶች ሸማች ብቻ ሆነው እንዲቀሩ የግሉ ዘርፍም ተጠያቂ ነው የምንልበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ 

ለማንኛውም ቢንያስ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶችን የሚያመርቱ ኩባንያዎችን ለመፍጠር ሊወሰዱ ከሚገባቸው በርካታ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ ወደ እዚህ ኢንቨስትመንቶች የሚገቡ ባለሀብቶችን ከሌላው በተለየ መደገፍ መስጠት አንዱ ነው፡፡ 

ከዚህም ሌላ መንግሥት የግሉ ዘርፍ ከአስመጪና ቸርቻሪነት፣ እንዲሁም ከአየር በአየር ንግድ እንዲላቀቅ በቀላሉ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ማንኛውንም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን እንዳይገቡ መከልከል ነው፡፡

የክልከላው ዋና ዓላማም እነዚህ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ግድ ይላል፡፡ ፋይናንስ አቅርቦትን ማመቻቸትም ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ራሱን የቻለ የኢንቨስትመንት ባንክ ማቋቋም የመፍትሔው አካል ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዲኖር የግሉ ዘርፍ ሚናን ለማጎልበት ከተፈለገ በትክክል ሊተገበር የሚችል አስቻይ ፖሊሲና ዕርምጃ ያሻል፡፡ የግል ዘርፉም ከተለመደው የአየር በአየር ንግድ እንዲወጣ ማስገንዘብ፣ እንዲሁም ሸማችም በአገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህሉን እንዲያዳብር ማድረግ የዚሁ ዕርምጃ አካል ካልሆነ ትርጉም ያለው ኢኮኖሚዊ ዕድገት ሊመጣ አይችልም፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብት እንዲህ ባሉ ኢንስትመንቶች ማሰማራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፣ ዛሬ የገባንበትን የዋጋ ንረት ለመቀነስ ጭምር አንድ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድም ይገባል፡፡

   

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት