Thursday, May 23, 2024

በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች ጉብኝት ያደርጋሉ መባሉ ብዙ ግምቶች እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሰውየው ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ ያቀናሉ ተብሏል፡፡ የብሊንከን ጉዞ የሩዋንዳና ዴሞክራቲክ ኮንጎን የድንበር ፍጥጫ ለማርገብ የታለመ ነው ቢባልም፣ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግን የብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝት ሩሲያና ቻይናን ለመፎካከር የታለመ ነው እያሉ ነው፡፡ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የብሊንከን ጉዞ አሜሪካ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮች አዲስ ዕቅድ የምታቀርብበት ነው ቢሉም፣ ከዚህ ባለፈ አሜሪካ አገሪቱ በአፍሪካ ጉዳይ ከሩሲያና ከቻይና ጋር ጂኦ ፖለቲካዊ ግብግብ ውስጥ መግባቷን በበቂ ሁኔታ ማስተባበል አልቻሉም እየተባለ ነው፡፡

ቻይና እ.ኤ.አ. 2022ን የተቀበለችው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዋንግ ዪን ወደ ኤርትራ፣ ኬንያና ኮሞሮስ ለአራት ቀናት ጉብኝት እንዲያደርጉ በመላክ ነበር፡፡ ቻይና ላለፉት 32 ዓመታት እንዳደረገችው ሁሉ ትልቅ ባለሥልጣኗ አፍሪካን በመርገጥ ዓመቱን የመጀመር ባህሏን ዘንድሮም አስጠብቃለች፡፡ ቻይና ዘንድሮ ከዚያም ያለፈ ዕቅድ ነበራት፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ በማድረግ በፓፓዋ ኒው ጊኒ አምባሳደር የነበሩትን ዡ ቢንግን ሰይማለች፡፡ በሰኔ አጋማሽ ደግሞ የቻይና አፍሪካ የሰላም ጉባዔ በአዲስ አበባ የመስተናገዱ ዜና የመላው ዓለም መገናኛ አውታሮች የዜና ርዕስ ሆነ፡፡

ባለፈው ሳምንት ደግሞ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግብፅ፣ በኡጋንዳና በኮንጎ ብራዛቪል ጉብኝት ማካሄዳቸው ሌላ የዓለምን ትኩረት የሳበ ዜና ነበር፡፡ ላቭሮቭ በተለይ በአዲስ አበባ ጉብኝታቸው በሰጡት መግለጫ፣ የዩክሬን ጦርነት ከመነሳቱ በፊት ምዕራባውያኑን የዓለም እህል ገበያን በማናጋት መክሰሳቸው የተለየ ትኩረትን የሳበ ነበር፡፡ ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ የአፍሪካ አገሮች የእህል ምርት እያጠራቸው ነው ለሚለው የምዕራባዊያኑ ትችት ምላሽ የሰጡት ላቭሮቭ፣ ከጦርነቱ በፊትም የዓለምን የእህል ገበያ ያናጉት ምዕራባዊያኑ ነበሩ ማለታቸው የብዙ ዜና አውታሮች ዋና ርዕስ ነበር፡፡

የቻይናና የሩሲያ ወደ አፍሪካ አገሮች የበለጠ መቅረብ ምዕራባዊያኑን አሥግቷል በሚባልበት በዚህ ወቅት፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ አፍሪካ መምጣት ምዕራቡ ዓለም አፍሪካን ወዳጅ ለማድረግ ወደ ፉክክር እየገባ ነው የሚል መላምት ማስነሳቱ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ከሁሉም በተለይ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ የስበት ማዕከል በምትባለዋ ኢትዮጵያ ዙሪያ የኃያላኑ የጂኦ ፖለቲካ ፉክክር አየል ብሎ እንደሚታይ የገመቱ ደግሞ በርካቶች ናቸው፡፡ በቅርብ ዓመታት በተለይ የትግራይ ክልል ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከምራባዊያኑ ጋር ግንኙነቷ ሻክሮ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ አሁን በዓለም ጂኦ ፖለቲካ ገበያ ዳግም ተፈላጊ እየሆነች መጥታለች የሚለውን ግምገማ የሚጋሩ በርካቶች ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ሳሙኤል ተፈራ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ‹‹አሜሪካኖቹ የኢትዮጵያን ጠቃሚነት ይገነዘባሉ፡፡ የተበላሸውን ግንኙነት ለማደስም ጥረት ለማድረግ እየመጡ ነው፤›› ይላሉ፡፡  

በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑትና ሀቀኛ መረጃዎችን ለአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች በማቅረብ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥቅሞች የሚታገለው የጌት ፋክት ማኅበር አባል የሆኑት ብርሃኑ ቡልቻ (ዶ/ር)፣ በአሜሪካ የአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ፖሊሲ ከባቢ አየር ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉልህ ለውጥ እንደመጣ በቅርበት መከታተላቸውን ይናገራሉ፡፡  

‹‹አፍሪካ ምን ትፈልጋለች ብለው 54 የአፍሪካ አገሮችን መሪዎች እዚህ ጠርተው ለማናገር ዕቅድ ይዘዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው በቻይናና በሩሲያ እየገጠማቸው ያለውን መቀደም ለማስመለስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳደረባቸው ነው፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ ነገሮች በበጎ መልኩ ይለወጣሉ ብዬ አላስብም ነበር፡፡ ከእኛ ጋር አንድ ደቂቃ ተቀምጦ ማውራት የማይፈልጉ ፖለቲከኞች ዛሬ በደንብ ለማዳመጥ ዝግጁ ሲሆኑ እያየን ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶች የኢትዮጵያ መንግሥትን ማስጨነቅ እንዳላዋጣ የተረዳ ቡድን አለ፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ መንገድ መግፋትና በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር የሚፈልግም አለ፤›› ሲሉ የሚናገሩት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በአሜሪካ የአፍሪካ ወይም የኢትዮጵያ ፖሊሲ ላይ ሁለት ዓይነት ገጽታዎች እንደሚንፀባረቁ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የአሜሪካ አጋር በሆኑ የአውሮፓ አገሮች ዘንድም ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነትን የማሻሻል ስሜት እየተስተጋባ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹እንደ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስና ዩናይትድ ኪንግደም የመሳሰሉ አገሮች ይህን ኢትዮጵያን ማስጨነቅ የሚል ጂኦ ፖለቲካዊ አካሄድ አላዋጣም የሚል ድምፅ እየተስተጋባባቸው ነው፤›› በማለት፣ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት ዳያስፖራ ትዝብታቸውን አጋርተዋል፡፡

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በአፍሪካ ፖሊሲያቸው ከሩሲያና ከቻይና ለገጠማቸው ፉክክር በሚል ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እየጣሩ ነው የሚለውን ግምት ብዙም አይቀበሉትም፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፣ ቻይናና ሩሲያን ለመፎካከር ነው አሜሪካ ብሊንከንን ወደ አኅጉሩ የምትልከው የሚለውን ጥያቄ ከሰሞኑ አጣጥለውታል፡፡ ‹‹ቁጥሮችን የምናይ ከሆነ ከአፍሪካ ጋር በመነገድ ቻይና በርቀት ትበልጠናለች፤›› ያሉት ዲፕሎማቷ፣ ‹‹ነገር ግን በሁለንተናዊ ግንኙነት ካየን አሜሪካ ሁሌም ከአፍሪካ አገሮች ጋር ግንኙነቷ የጠበቀ ነው፤›› በማለት ለአገራቸው ተከራክረዋል፡፡

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህን ቢሉም በአፍሪካ አኅጉር ጂኦ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚፈልጉና ከአፍሪካ አገሮች ጋር ለመወዳጀት የሚከጅሉ ኃያል የዓለም አገሮች መብዛታቸውን መካድ ፈፅሞ አይቻልም፡፡ ቻይናና ሩሲያ ወይም የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ ወደ ጎን ቢባሉ እንኳን የዓረብ አገሮችና እስራኤልን ጨምሮ፣ እንደ ቱርክ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ብራዚልና የመሳሰሉ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ እየጠነከሩ የመጡ አገሮች የአፍሪካን ሽርክና አንፍንፈው ወደ አኅጉሩ መግባታቸው የሚቀር አይመስልም፡፡ አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ ለአፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ የዓለም ጂኦ ፖለቲካው ገበያ መስፋቱን መካድ እንደማይቻል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡    

‹‹ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ፣ ለፖለቲካ፣ ለሃይማኖት፣ ለርዕዮተ ዓለም፣ ለደኅንነትና ለሌላም ፍላጎታቸው አመቺ ሆና እስከተገኘች ድረስ አሜሪካንን ጨምሮ ለመወዳጀት የማይመጣ ማንም አገር የለም፤›› ሲሉ የሚሉት ሳሙኤል (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ስለወቅቱ የዓለም ጂኦፖለቲካ ቅኝት ሲያስረዱ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በቀደመው የኢሕአዴግ አስተዳደር ወቅት የዓለም ፀረ ሽብር ዘመቻ አጋር አገር ተብላ ከምዕራባዊያኑ በኩል እጅግ በርካታ የገንዘብ፣ የደኅንነትና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ስታገኝ ቆይታለች፡፡ የዓብይ አስተዳደር ሲመጣ በተለይ የትግራይ ጦርነት ሲከሰት ግን በአንዴ ይህ ተለወጠ፤›› በማለት የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ የጂኦ ፖለቲካ ገበያውን ቅኝት እንደሚመራ አስረድተዋል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ የምዕራባዊያኑ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የከረረ ግንኙነት ለማለዘብ መለሳለስ መጀመራቸውን የሚያስረዱት ሳሙኤል (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስኬታማ ሥራ መሥራቱን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገሮች ጋር ግንኙነትን ለማሻሻል በውጭ ጉዳይ በኩል ትኩረት ተሰጥቶት በስትራቴጂካዊ ዕቅድ ተቀርፆ ወደ ሥራ መገባቱ ውጤታማ እንደነበር እያየን ነው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

በዓመቱ አጋማሽ ግድም በፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ‹‹ሲከር የማለዘብን›› አካሄድ የሚከተል ነው ማለታቸው፣ አስተዳደራቸው በትግራይ ጦርነት የተነሳ ጥርስ ከነከሱበት የምዕራባዊያን አገሮች ጋር ግንኙነትን ለማደስ ብዙ ርቀት እንደሚሄድ ጠቋሚ ነጥብ ተደርጎ ነበር የተወሰደው፡፡ መከላከያና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ከአማራና ከአፋር ክልሎች ጠራርገው ያስወጡትን የሕወሓት ኃይል መቀሌ ድረስ አሳደው ይደመስሱታል ተብሎ ሲጠበቅ፣ የትግራይ ክልልን ወሰን ሳይዘልቁ እንዲቆሙ መደረጋቸው ለምዕራባውያን የሰላም ስምምነት ውትወታ እንደ አንድ የይሁንታ ምላሽ ነበር የተቆጠረው፡፡ ቁርሾን በማርገብ ዕርቅን ለማስፈን በሚል ለገና በዓል የታሰሩ የሕወሓት አመራሮችን በመፍታት ጭምር መንግሥት ለሰላም ዝግጁ ነኝ የሚል መልዕክት ለዓለም ለማስተላለፍ መሞከሩ አይዘነጋም፡፡ ከትግራይ ኃይሎች ጋር መንግሥት በድብቅ ድርድር መጀመሩ ሲነገር ከመክረሙ ጋር ተዳምሮ፣ ይህ ሁሉ ከኢትዮጵያዊያን በኩል ብዙ ድጋፍ ያሳጣው ቢሆንም ከምዕራባውያኑ ጋር ዳግም ለመቀራረብ በር ከፋች አጋጣሚ ነበር ይባላል፡፡ 

በቅርቡ በሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) አማካይነት መንግሥት ያለ ቅድመ ሁኔታ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመደራደር ያለውን ዝግጁነት ይፋ ማድረጉ ደግሞ፣ ሌላ ከምዕራባውያን ጋር የሚያቀራርብ አጋጣሚ ነበር የሆነለት፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የሶማሊያው አሸባሪ አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ጥቃት ለመክፈት መሞከሩና በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በከባዱ መደምሰሱ፣ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ጉልበት ከፍ የሚያደርግ ክስተት መሆኑ ይነገራል፡፡

ኢትዮጵያ በጦርነት ደቃለች፣ በፖለቲካ፣ በጎሳና በሃይማኖት ተከፋፍላ ለመፈራረስ አንድ ሐሙስ የቀራት አገር ሆናለች ተብሎ በዓለም መገናኛ ብዙኃን ሟርት በሚነገርበት በዚህ ወቅት፣ እንደ አልሸባብ ላሉ ቀጣናዊ የፀጥታ ሥጋት ለሆኑ የሽብር ቡድኖች ዛሬም ጉልበት እንዳላነሳት ማሳየቷ የምዕራባውያን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በመፈራረስ አፋፍ ላይ ሆናለች ቢባልም በዓለም አቀፍ ፀጥታና ደኅንነት ጂኦ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ያላት አገር መሆኗን፣ ድንበር ጥሶ የገባውን የአልሸባብ ኃይል ከእነ አመራሮቹ በመደምሰስ ማሳየት መቻሏን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡

ይህን ሐሳብ የሚጋሩት በአሜሪካ ያለውን ፖለቲካዊ አተያይ በቅርበት የሚከታተሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ትጠቅመናለች የሚለው ዕሳቤ እንዳለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያን ለተጨማሪ ሥጋት የሚዳርግ አመለካከት መፈጠሩንም አብረው ያነሳሉ፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነትን ማስተካከልና የኢትዮጵያን አንድነት ማጠናከር የሚደግፍ ወገን ተፈጥሯል፡፡ ቢሆንም ግን ኢትዮጵያን በመከፋፈል ለራሳቸውና ለአሜሪካ ጥቅም ለማዋል የሚጥሩ ኃይሎችም ተፈጥረዋል፤›› በማለት፣ በአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ያለውን ባለሁለት ገጽታ አተያይ ያክላሉ፡፡

ሲቀጥሉም እነዚህ ከፋፋይ ኃይሎች ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የቆመውን ወገን ወደ ጎን ብለው፣ በብሔር የተደራጁ ኃይሎችን መወዳጀት ይዘዋል ይላሉ፡፡  

‹‹አሁን የትግራይ ኮሙዩኒቲ፣ የኦሮሞና የአማራ ኮሙዩኒቲ እያሉ ኢትዮጵያዊያንን በብሔር ከፋፍለው በተናጠል እያነጋገሩ ነው የሚገኙት፡፡ ከአንድነት ኃይሎች ይልቅ ፌዴራላዊ ኃይሎች ነን የሚሉ የብሔር ፖለቲከኞችን ነው ቀርበው የሚያማክሩት፡፡ የኢትዮጵያን ጂኦ ፖለቲካል ጠቀሜታ ተገንዝቦ የአሜሪካ አካሄድ እንዲስተካከል የሚጥር የአሜሪካ ሕግ አውጪ ክፍል ቢኖርም፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን የበለጠ በመከፋፈል በምርጫ ወቅት ከኢትዮጵያዊያን ለራሱ ብዙ ድምፅ ለመግዛት ብቻ ሳይሆን፣ የአሜሪካን ጥቅም በዚያ መንገድ አስጠብቃለሁ ብሎ የሚያስብ አለ፡፡ በብሔር ቁርሾ ውስጥ ገብተው የኢትዮጵያ ችግር የተናጥል ነውና የኦሮሞ፣ የትግሬ፣ የአማራ፣ ወዘተ ችግር በተናጠል ካልተፈታ ማለት የጀመሩ አደገኛ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ተፈጥረዋል፤›› ሲሉ የተናገሩት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በአሜሪካ ፖለቲከኞች ዘንድ የተፈጠረውን በጎ ስሜት ከእነ አደጋው አብራርተዋል፡፡

 ይህን ሥጋት ለመቅረፍ በዳያስፖራው ማኅበረሰብ መደረግ አለበት የሚሉትን ሲያስረዱም፣ ‹‹እዚህ አሜሪካ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ሁን ሌላ አፍሪካዊ ቢሳካልህም ሆነ ብትወድቅ፣ ጥቁር አሜሪካዊ ተብለህ ነው በጅምላ የምትጠራው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህን ኖረንበት እያየን ነገር ግን የአገራችንን አንድነት አሳልፈን ሰጥተናል፡፡ በብሔር እየተቧደንን ለአሜሪካዊያኑ ራሳችንን አሳልፈን መስጠታችን አደገኛ ጣልቃ ገብነት ነው የሚጋብዝብን፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ወደ ጎን ብሎ በብሔር ገብቶ የሚፈተፍት ፖለቲከኛ ከጀርባው አደገኛ ነገር መያዙን መገመት አለብን፡፡ ኢትዮጵያን የበለጠ በመነቅነቅ ለማፈራረስ የሚሠራ ፖለቲከኛ እዚህ አሜሪካ ተፈጥሯል፡፡ ይህ መንገድ ውድቀት እንደሚያመጣ ኢትዮጵያውያን ነቅተን መከታተል አለብን፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ኢትዮጵያዊ መቆም አለብን፡፡ ሊቢያን፣ ሶሪያን፣ ኮትዲቯርን፣ ማሊን፣ እነ ሄይቲን እንደ ምሳሌ ማየት እንችላለን፡፡ ማንኛውም ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነትና መፍትሔ ለኢትዮጵያ አይሠራም፤›› ብለዋል፡፡

ሳሙኤል (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ግንኙነቷ እንዳያድግም ሆና ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን እንዳትችል የሚሠሩ የውጭ ኃይሎች በዙሪያዋ መሠለፋቸውን ያክሉበታል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ጥቅም እንዲጠበቅ የማይፈልጉ ኃይሎች በተቀናጀ ሁኔታ እየተረባረቡባት እንደሆነ ያመለከቱት ምሁሩ ችግሩን ለመቅረፍ አገሪቱ ከምታደርጋቸው የግል ጥረቶች በተጨማሪ፣ በዙሪያዋ ያሉ አገሮችን ባማከለ መንገድ ጭምር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ‹‹በእኛ በኢትዮጵያዊያን ጥረት ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ያሉ በጎ አገሮችን በመጠቀም ከምዕራባዊያኑ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማስተካከል ይቻላል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ ጀመረችው ከሚባለው ዲፕሎማሲ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ፣ አኅጉራዊና ቀጣናዊ ትስስሮችን የሚያጠናክሩ ታላላቅ ተቋማትን በመመሥረት ጭምር በዓለም ዲፕሎማሲ መድረክ ጉልህ ሚና ስትጫወት የቆየች አገሮች መሆኗ በታሪክ ይነገራል፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ አፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ ድረስ የዲፕሎማሲ አሻራዋን ያሳረፈችባቸው ተቋማት በርካታ ናቸው፡፡ ለዓለምና ቀጣናዊ ሰላም መስፈን ጦር ማሰማራትን ከማንም ቀድማ የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ እንደ ጎረቤት ሶማሊያ ያሉ አገሮች በእግራቸው እንዲቆሙ ለማስቻል ብዙ መስዋዕት እንደከፈለች ይነገራል፡፡

ከሰሞኑ ከሶማሊያ የተነሳው የአልሸባብ ኃይል ድንበር ተሻግሮ ጥቃት ሲከፍት፣ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ቀጣናዊ የፀጥታ ሥጋት የሆነውን የሽብር ቡድን ለመደምሰስ ከባድ መስዋዕትነት መክፈላቸው ተነግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች አልሸባብን በመደምሰስ በቀጣናው ያለውን የፀጥታ ችግር ለማስወገድ በሚለፉበት በዚህ ወቅት ግን፣ የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት የቀድሞ የአልሸባብ ሰዎችን ሥልጣን ለመስጠት ሽር ጉድ ሲሉ መታየታቸው አስገራሚ መሆኑን ብዙዎቹ በትዝብት ዘግበውታል፡፡

ከዚህ በመነሳት ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት በመርህ በማይመራበት በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ፣ ኢትዮጵያ ጎረቤቶቿን አስተባብራ ጥቅሞቿን ማስጠበቅ ትችላለች የሚለው መላምት የዋህነት የበዛበት መሆኑን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲበረታባት ካደረጉት አንዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን በተመለከተ ከገጠማት ፈተና ብዙ መማር እንደምትችል የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

መቀመጫውን በሩሲያ ያደረገው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ አንድሪው ኮሪብኮ በታላቁ ህዳሴ ግድብ መዘዝ ግብፆቹ በኢትዮጵያ ላይ የሚዶልቱትን ሴራና ጫና ከሰሞኑ፣ ‹‹Nile dam is just a false pretext for Egypt to pressure Ethiopia›› በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፉ በደንብ ተመልክቶታል፡፡ ግብፆች የዓረብ ሊግን ብቻም ሳይሆን እንደ ሱዳን ያሉ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮችን ጭምር ለሴራቸው እንደሚጠቀሙ ያመለከተው ጋዜጠኛው፣ ሕወሓት የከፈተው ጦርነትም ሆነ የምዕራባውያኑ የሴራ ድጋፍ በሙሉ ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ ጫና የማድቀቅ ግዙፍ ሴራ አካል ነው በማለት ነበር ብዙዎች የማይደፍሩትን ዓይነት መልዕክት ለዓለም ለማስተላለፍ የሞከረው፡፡

‹‹ምዕራባዊያኑ ሁሌም ፍላጎቴን ፈጽምልኝ ይሉሃል፡፡ ነገር ግን ለእኔ የሚጠቅመኝን ለአንተ የሚያኖርህን ምረጥ ነው የሚሉህ እንጂ፣ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ደሃ የአፍሪካ አገሮች ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ለመፍጠር አይፈልጉም፤›› ሲሉ ብርሃኑ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

‹‹አንዳንዴ በጂኦ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ተፈላጊ አገር ልትሆን ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ደግሞ የምዕራባውያን ጥገኛ እስከሆንክ ነፃነትህ አይረጋገጥም፡፡ ግብፅን ብትመለከት ለምዕራባውያኑ በጂኦ ፖለቲካው ጠቃሚ ብትሆንም፣ ነገር ግን በዓመት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የእነሱን ድጎማ ትጠብቃለች፡፡ ቦታዋ እንጂ ራሷን ችላ አትቆምም፡፡ አሜሪካ ሌላ አማራጭ ካገኘች ግብፅ አደጋ ውስጥ ናት ማለት ነው፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት በሕዝብ የተመረጠ መሪን ከሥልጣን አውርዶ በጄኔራል የመተካቱ የፖለቲካ ሴራ ለግብፆች የተሸረበው በአሜሪካኖች ነው፡፡ በጂኦ ፖለቲካው ጠቃሚ ነኝ ብቻ ማለት በቂ እንዳልሆነ ከእነሱ መማር አለብን፡፡ የራስህን ዕድልና ዕጣ ፈንታ በራስህ መወሰን የምትችልበት ቦታ ላይ ካልተገኘህ በስተቀር በጂኦ ፖለቲካው ጠቃሚ ነኝ ማለት ብቻ አይበቃም፤›› በማለት ብርሃኑ (ዶ/ር) ስለምዕራባውያኑ ፖለቲካ የታዘቡትን ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ የአልሸባብ ኃይልን በመደምሰስ ለቀጣናው ፀጥታ መጠበቅ ያላትን ጠቀሜታ ብታረጋግጥም፣ ነገር ግን ያረፈባት ዲፕሎማሲያዊ ጫና ገና ሙሉ ለሙሉ ጥላው አልተገፈፈም ይባላል፡፡ እንደ ቻይናና ሩሲያ ያሉ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አማራጮችን ብትጠቀምም ነገር ግን ከምዕራባዊያኑ በኩል የሚመጣው ጫና ይህ ብቻውን እንደማያቀለው ይነገራል፡፡ በስትራቴጂካዊ ዕቅድ በተደገፈ የውጭ ግንኙነት ከምዕራባዊያኑ ጋር መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር ብትጥርም፣ ይህ ግንኙነቱን ከተወጠረበት አለዝቦት ቢሆን እንጂ ገና ሙሉ ለሙሉ እንዳልቀየረው እየታየ ነው፡፡

ከሰሞኑ የአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑኮች ወደ መቀሌ አቅንተው መመለሳቸው ልዩ ሽፋን የተሰጠው ጉዳይ ነበር፡፡ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ማይክ ሀመርና የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ አኔተ ዌበር በጋራ ካካሄዱት ጉብኝት በኋላ የሰጡት መግለጫ ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡ በትግራይ የመሠረተ ልማት አገልግሎት ዳግም እንዲቀጥል የጠየቁት ሁለቱ ልዑካን፣ የትግራይ ኃይሎችም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ ልዑካኑ ሁለቱንም ወገኖች ፖለቲካዊ ቃላቶቻችሁን አለዝቡ ብለው ካስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሲቀርብ ነበር፡፡ 

ይህ ብቻም አይደለም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዑክም ወደ ኢትዮጵያ ከሰሞኑ መጥቶ ነበር፡፡ ያለ ገደብ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የሚያስችል ሜዳ ይፈጠር የሚል ቅድመ ሁኔታ ልዑኩ ለመንግሥት በማስቀመጥ መመለሱ ነው በተለያዩ የዜና አውታሮች የተዘገበው፡፡ እነዚህን ሁለት ሁነቶች ተከትሎ ምዕራባውያኑ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነታቸውን ለማለዘብ ቢያስቡም፣ ነገር ግን በአስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርተው መሆናቸው አመላካች እንደሆነ በብዙዎች እየተነገረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ምዕራባውያኑ ቅድሚያ የሰጡትን የትግራይ ጉዳይ በሚፈልጉት መንገድ ብትፈታ እንኳን፣ ከምዕራባውያኑ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንደማትላቀቅ የሚገምቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ከሰሞኑ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ውኃ ሙሌትን በተመለከተ የክስ ዶሴ ይዘው የሄዱት ግብፆች ለሌላ ዙር ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመዘጋጀት ላይ መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡

ግብፅ በቅርቡ ታስተናግደዋለች ተብሎ በሚጠበቀው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይም የግድቡ ጉዳይ ዋና አጀንዳ እንዲሆን ትልቅ ሥራ ከወዲሁ እየሠራች መሆኑ ታውቋል፡፡ ግብፆቹ የውኃ ደኅንነት ጉዳይን በአፍሪካ በማስጠናት፣ ኢትዮጵያ የውኃ ህልውናችንን አደጋ ላይ የሚጥል ግድብ ገነባች የሚል ከባድ የዲፕሎማሲ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጁ መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ከወዲሁ እየተናገሩ ነው፡፡

መለዘብና መለሳለስ ቢታይበትም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ያላትን ግንኑነት ለማሻሻል ከወዲሁ በቂ ሥራ እንድትሠራ የሚያሳስቡ ድምፆች እየበረከቱ ይገኛል፡፡ የምዕራባውያኑ ጫና የከፋ ቢሆንም ከጎረቤት አገሮች ጋርም ያልተፈቱ ጉዳዮቿን መፍታት እንደሚኖርባትም አንዳንዶች ከወዲሁ እየመከሩ ነው፡፡  

ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሁሉንም የሚያቻችል ግንኙነት ኢትዮጵያ መፍጠር አለባት የሚሉት ሳሙኤል (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ኢትዮጵያ በማንም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለ መግባትና ለዓለም አቀፋዊ ሰላምና ደኅንነት በጋራ የመቆም የጥንት የውጪ ግንኙነት ፖሊሲዋን አጠናክራ መቀጠል አለባት፤›› ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

ብርሃኑ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ረዥም ጊዜ መታወቂያዋ የሆነውን ሁሉንም ሚዛን በጠበቀ መንገድ የመወዳጀት ዲፕሎማሲዋን ከማስቀጠል ባለፈ ታድርግ የሚሉትን ጉዳይ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፡፡

‹‹የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለኢትዮጵያ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ስንዴ ላይ መረባረቡ ጠቃሚ ነው፡፡ ሌላው እንደ ህዳሴ ያሉ ግድቦችን መጨረስና በኃይል ራስን መቻልም ትልቁ ከውጭ ጣልቃ ገብነት ራስን ነፃ ማውጫ መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሰው ጥገኝነት ወጥተን በአንድነት መቆም አለብን፡፡ ኢትዮጵያ እንዴት ትዋቀር በሚለውም ሆነ በርዕዮተ ዓለም ላንስማማ እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ትኑር በሚለው ጉዳይ ግን መስማማት መቻል አለብን፡፡ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ መንግሥት ላንስማማበት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን ከቅኝ ተገዥነት ማላቀቅ የሚቻለው ራስን በራስ በመቻል ነው፡፡ መንግሥትም ይህ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ ስንዴ ለማልማት መነሳቱን መደገፍ አለብን፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -