Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የስንዴ እንቆቅልሽ በኢትዮጵያ

በቶፊቅ ተማም

ግብርና ለዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛና ወሳኝ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡ ያለ ግብርና የሰው ልጅ ህልውና ቀጣይነት አይኖረውም፡፡ በዚህም ምክንያት አገሮች ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ምርትን በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ጥቂት የማይባሉ አገሮች ከራሳቸው ፍጆታ ተርፎ ምርታቸውን ለሌሎች በማቅረብ፣ የኢኮኖሚ አቅማቸውን በወጪ ንግድ ሲገነቡ ይስተዋላል፡፡

ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለስ ለምግብነት ከሚውሉ ሰብሎች መካከል ዋነኛውና የፖለቲካ ሰብል (Political Crop)  በመባል የሚታወቀው ስንዴ ሲሆን፣ በአገሪቱም ከአሥር ሚሊዮን በላይ የስንዴ ገበሬዎች ስንዴ ያመርታሉ፡፡ ይህም ከአጠቃላይ ገበሬዎች 25 በመቶ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስንዴ ልማት ላይ የተሻለ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ ይህንንም መነሻ በማድረግ መንግሥት በቀጣይ ዓመት ስንዴ ወደ ጎረቤት አገሮች ለመሸጥ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ለመላው ሕዝብ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ዕውን በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ ብቁ ናት የሚለውን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በማሰናሰል፣ ሌሎች የበኩላቸውን ይሉ ዘንድ የውይይት በር ለመክፈት የተዘጋጀ ነው፡፡ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ባልተናነሰ ለግብርና አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ቢሆንም፣ የምርት አቅሟ ግን ለአገር ውስጥ የሚበቃ ካለመሆኑም በላይ፣ በየዓመቱ የሚጨምረው የስንዴ ፍላጎትና የሚመረተው መጠን ሊጣጣም አልቻለም፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ በስንዴ ራስን ከመቻል አልፋ ወደ ውጭ የመላክ አቅም ቢኖራትም፣ እንዲሁም የሚታየው የስንዴ ምርት ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ወዲህ በመንግሥት በተከናወኑ አበረታች ሥራዎች ሳቢያ እየጨመረ ሲገኝ፣ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በበጋ የስንዴ ልማት የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥርና የክላስተር እርሻዎች በማስፋፋት የበጋ ስንዴ ምርቷን መጨመር ችላለች፡፡

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስንዴ ከፍተኛ የተባለ ምርታማነት ብታሳይም፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ 25 በመቶ ገደማ የሚሆነውን ስንዴ ከውጭ ታስገባለች፡፡ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች በስንዴ ምርት ቀዳሚ ናት፡፡ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች ስንዴን ለማምረት የሚበቃ የተሻለ በቂ መሬት፣ ውኃ፣ አምራች ኃይልና ሌሎች ለግብርና ልማት ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችና ተፈጥሯዊ ገፀ በረከቶች ቢኖሩም፣ በሚሊዮን ቶኖች የሚለካ ስንዴ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ወጪ በማድረግ ታስገባለች፡፡ ለአብነት ያህል ከ2009 እስከ 2013 ዓ.ም. 17.7 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ 15.5 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የገዛች ሲሆን፣ ይህም ያልተገባ ግዥ በመሆኑ በውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ፣ ለስንዴ ግዥ ይውል የነበረ ገንዘብ ለአገር ዕድገት ጠቀሜታ ለሚኖራቸው ለካፒታልና ለኢንቨስትመንት እንዳይውል አድርጓል፡፡

አገሪቱ ስንዴ ከውጭ እንዳታስገባ በተለይ በያዝነው ዓመት የአፍሪካ ልማት ባንክ ተግባራዊ ባደረገው ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ግብርና ትራንስፎርሜሽን (Technology for African Agriculture Transformation) መርሐ ግብር አማካይነት የተሻለ የስንዴ ዝርያ አቅርቦት፣ የአፈርና የውኃ አጠቃቀምና ሌሎች ድጋፎች በማድረግና መሰል ተቋማት በሚደረጉ ድጋፎች ስንዴ በተያዘው ዓመት ከውጭ ገበያ አለመገዛቱ በቡድን ሰባት አገሮች ስብሰባ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም አመርቂ የሆነውን የስንዴ ምርት በአዎንታዊ መንገድ ዘግበውታል፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው አገሪቱ በስንዴ ምርት ላይ የተሻለ ሥራ እየሠራች ቢሆንም፣ ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ ዕውን በአገሪቱ የተመረተው ስንዴ በአግባቡ ለኅብረተሰቡ ተሠራጭቷል ወይ አገሪቱ በስንዴ ምርት ራስዋን ችላለች (Wheat Self-Sufficient) ወይ የሚለው በአግባቡ መታየት ያለበት ይሆናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት ለሚቀጥለው ዓመት ወደ ውጭ ስንዴ ለመላክ ቢያቅድም፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በተለይ አገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተከሰቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ ብሎም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ጫናዎች ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ  ዜጎች ዕርዳታ ጠባቂ በሆኑበት በጦርነት ሳቢያ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ የተፈጠረው ክፍተት በአግባቡ ባልተካካሰበት ሁኔታ፣ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ፣ በሱማሌና ደቡብ ክልሎች በተወሰኑ አካባቢዎች የድርቅ አደጋ ባጋጠመበት ስንዴ ወደ ውጭ መላክ አግባብነት የሌለውና ጊዜውን ያልዋጀ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡

በሌላ በኩል የስንዴ ዋጋ በተለይ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ከ300 በመቶ በላይ በመጨመሩ ሳቢያ በተለይ በከተሞች በስንዴ ምርት ላይ የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የዋጋ ማረጋጋት ያሻዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተሞች ስንዴ አቅርቦት ላይ እየታየ ላለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት የተሻለ የድጎማ ሥርዓት በማበጀት  በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ሳቢያ የዕለት የዳቦ ፍላጎትን በቅጡ ማሟላት ባለመቻሉ፣  ሊሚሰቃየው የከተማ ነዋሪ ጥሩ እመርታ እያሳየ ያለው የስንዴ ምርት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መፍትሔ ሊሆነው ይገባል፡፡

አገሪቱ የስንዴ ፍላጎቷን በራስ አቅም ለማሟላት፣ ለፖለቲካ ማስፈጸሚያ የሚውለውንና የዕርዳታ ምንጭ የሆነውን ስንዴ ለመቀነስና ለማስቀረት ትችል ዘንድ አሁን መንግሥት እንደሚለው ስንዴን ወደ ውጭ ኤክስፖርት በማድረግ ከሌሎች ኤክስፖርት ከሚደረጉ የግብርና ምርቶች እንደ አረንጓዴው ወርቅ ቡና የተሻለ አፈጻጸም ያሳይ ይሆን ዘንድ፣ ሊተገበሩና ትኩረት ሊሰጣቸው የምላቸውን ሐሳቦች በጥቂቱ ላንሳ፡፡

ለአገሪቱ ዝቅተኛ የግብርና ምርታማነት ምክንያት ውስን የሆነ የግብርና ፋይናንስ አገልግሎት፣ የተሸሻለ የምርት ቴክኖሎጂ አለመኖር፣ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የቅንጅት አናሳነት፣ የግሉን ዘርፍ በአግባቡ አለማሳተፍ፣ ስንዴ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የሚታየው ዝቅተኛ የምርጥ ዘር መጠቀም ምጣኔ አለማደግ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን እጥረቶች መቅረፍም ያሻል፡፡ በሌላ በኩል በተለይ የስንዴን ምርት በአሁኑ ካለበት ተስፋ ሰጪ ሁኔታ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች የተሻለ የስንዴ ምርት እንደተገኘባቸው ሁሉ የምርት እጥረት ባለባቸው በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በሱማሌና በቤኒሻንጉል ክልሎች ስንዴ በስፋት እንዲመረት የተሻለ ሥራ መሥራት ይጠበቃል፡፡ በተለይ በቆላ የመስኖ ልማት የተሻለ  አፈጻጸም እያሳዩ ባሉ እንደ አፋር ባሉ ክልሎች የተጀመሩ አበረታች ሥራዎችን ወደ ሌሎች ሥፍራዎች ማስፋት ይጠይቃል፡፡

የግብርና የሰው ኃይልን በተመለከተ የኤክስቴንሽን ሠራተኞችን ድጋፍና ክትትል ማሳደግ፣ የድኅረ ምርት ብክነትን መቀነስ፣ የተሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት፣ ስንዴ ላይ እሴት የመጨመር ተግባራት አጠናክሮ መቀጠልና አዳዲስ የገበያ ስትራቴጂ መቅረፅ ያሻል፡፡

የአገሪቱን የስንዴ ምርት ለማሳደግ ዋነኛ ሞተርና አንቀሳቃሽ የሆነው ዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነውን ግብርናችንን ከዝናብ ጥበቃ ሊያላቅቀን የሚችለው የመስኖ ልማት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የከርሰ ምድር ውኃን ሳይጨምር 123 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ የውኃ ሀብትና ከ36 ሚሊዮን ሔክታር ባለይ ሊለማ የሚችል መሬት እንዳለ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች አገሪቱ የምትፈልገውን ሰብል በተለያዩ አካባቢዎች ለማምረት እንድትችል ዕድል የሚፈጥሩ ቢሆኑም፣ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሰብል የለማው የአገሪቱ መሬት 16 ሚሊዮን ሔክታር ገደማ ያህል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም በመስኖ ልማት የለማው መሬት 1.1 ሚሊዮን ሔክታር ያህሉ ነው፡፡

አነስተኛ መካከለኛ ትልልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች በመንግሥት በልማት አጋሮች፣ በግሉ ዘርፍ፣ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ትብብር መገንባትና የዝቅተኛ ሥፍራዎችን የመስኖ ልማት ምርምር ማጠናከር ትኩረት ይሻሉ፡፡ መስኖን በአግባቡ በመጠቀም በየጊዜው እየጨመረ ያለውን የሕዝብ ቁጥር በአግባቡ መመገብ ያስችላል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱትን ድርቅና ረሃብ ለመቅረፍ፣ በመሬት መሸርሸር ሳቢያ የሚቀንሰውን የምርት መጠን ለማካካስ፣ የገበሬውን ምርታማነት ለመጨመር፣ እንዲሁም በገጠር በቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

የአገሪቱ የመስኖ ልማት የአገሪቱን ዕድገት በማይሹ አካላትና በሌሎች ሥውር ደባዎች ሳቢያ፣ በአገሪቱ የተጀመሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች ከትርፍ ይልቅ ኪሳራቸው እንዳመዘነ በዚሁ ጋዜጣ ብዙ ጊዜ ተነግሯል፡፡ አሁንም ቢሆን በመስኖ ግድብ ግንባታ የሚታዩ የዲዛይንና የአስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የተጨቆኑ የመስኖ ፕሮጀክቶች የተባሉትን የጎዴ፣ የአልዌሮ፣ የጣና በለስ፣ የተንዳሆ፣ የወለንጪቲ ቦፋ፣ የመገጭ፣ የርብ፣ የጊዳቦና የአርጆ ዴዴሳ የመሳሰሉ ግድቦች ሁኔታ ትኩረት ይሰጠው፡፡ ለስንዴ ልማትም ይሁን ለሌላ ሰብሎች ልማት የሚውሉበት ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል፡፡ በአገሪቱ የስንዴ ምርት ላይ እመርታ ያመጣው ጉዳይ ቢኖር ባህላዊ ከሆነ የእርሻ ዘዴ ይልቅ ዘመናዊ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማስፋፋት ነው፡፡ ይህም ግብርናን ለማዘመንና የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህን የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራ ወደ ሁሉም ክልሎች በሰፊው ማስፋፋት አገሪቱ አሁን በስንዴ ምርት ላይ እያሳየችው ያለውን እመርታ ዘላቂ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የግብርና ዘርፍ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውም የቴክኖሎጂ ግብዓትና ማሽነሪዎች ከግብር ነፃ በማድረግና የሊዝ ፋይናንሲንግ ብድር ሥርዓት በመገንባት ግብርናን ለማዘመን በትኩረት መሥራት ለነገ አይባልም፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለይ የማዳበሪያ ዋጋ በተለይ ባለፉት ዓመታት ከ150 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ይህም በስንዴ ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው፡፡ ይህንን ተግዳሮት ለመቅረፍ የድጎማ ሥርዓት በአግባቡ መተግበር፣ ከዚህ ባለፈም እንደ ኮምፖስት ያሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግና የመሬት አጠቃቀምን በማሻሻል፣ የኬሚካል ማዳበሪያ ፍላጎትን መቀነስ ለስንዴ ልማቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

በስንዴ ልማቱ እየተሠራ ያለው ሥራ የበለጠ ፍሬ ያፈራ ዘንድ የፀረ አረም፣ የፀረ ፈንገስና የፀረ ተባይ ኬሚካሎችን የመጠቀም ምጣኔ በማሳደግ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንዲሁም የፖሊሲ ማዕቀፎችን ማሻሻል፣ ጥናቶችንና ምርምሮችን ማስቀጠል፣  የበጋ ስንዴ ልማት ላይ የሚታዩ አሉታዊ አስተሳሰቦችን በመለወጥ በልማቱ የሚሳተፉ አርሶ አደሮችን ቁጥር መጨመር ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ቢኖር በስንዴ ልማት የተሠሩ አበረታች ሥራዎችን በሚፈለገው መጠን ለማሳደግ የግሉን ዘርፍ በሚገባ ማሳተፍ የግድ ሲሆን፣ የግሉ ዘርፍም በተለያዩ የአግልግሎትና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በስፋት እንደሚሰማራ ሁሉ፣ ወደ ግብርናው በተለይም ወደ ስንዴ ልማት ላይ እንዲሳተፍ ሁኔታዎች በአግባቡ ሊመቻችላት ይገባል፡፡

ለግሉ ዘርፍ ላይ የሚታዩ አናሳ የሆኑ የተቋማትን ድጋፍ ማሻሻል፣ ብሎም የግሉ ዘርፍ የአቅም ግንባታ (Private Sector Capacity Building) ተግባራት በተለይ በግብርናው ዘርፍ በማሳደግ አገሪቱን በስንዴ ራሷን ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት ግቡን እንዲመታ ያስችለዋል፡፡

ለማጠቃለል ያህል በሚሊዮን ሔክታር የሚገመት ሰፋፊ ያልታረሰ ድንግል መሬት ያላት፣ እንዲሁም የአፍሪካ የውኃ ማማ ተብላ የምትታወቀውና ከሕዝቧ 80 በመቶ በግብርና በሚተዳደርባት ኢትዮጵያ እንዴት በስንዴ ራሷን አትችልም?  በተጨማሪም የምግብ ዋስትና ጥያቄ እንቆቅልሽ ለመፍታት እንደ አገርም፣ እንደ መንግሥትና እንደ ግለሰብ ቆም ብሎ በማሰብ ወደ ግብርናው በደንብ መጠጋት ያስፈልጋል፡፡ የመፍትሔ አካል ለመሆን ራስን ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በቅርብ ዓመታት እመርታ እያሳየ ያለውን የስንዴ ምርት ይበልጥ የሚሻሻልበት ሁኔታ ላይ መትጋት ያሻል፡፡ ዕውን አሁን ባለው አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ የመንግሥት ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ ሐሳብ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ የፈጠረው የስንዴ እንቆቅልሽ (Wheat paradox) አስመልክቶ፣ በተለይ የዘርፉ ባለሙያዎች የተሻለ ሐሳብ ያጋሩን ዘንድ በማሰብ ያዘጋጀሁትን አጠር ያለ ሐሳብ በዚህ ላብቃ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles